Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ የከተማ አስተዳደሩ ሕገ መንግሥታዊና የማይጣስ መብቴን ጥሶብኛል በማለት የሁከት ይወገድልኝ ክስ...

ኢዜማ የከተማ አስተዳደሩ ሕገ መንግሥታዊና የማይጣስ መብቴን ጥሶብኛል በማለት የሁከት ይወገድልኝ ክስ ከፈተ

ቀን:

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕገ መንግሥቱ ያከበረለትንና የማይጣስ የመሰብሰብ መብት እንደጣሰበት ገልጾ፣ ሁከት እንዲወገድለት ‹‹ግልጽ ውሳኔ ይሰጠኝ›› ሲል በፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ክስ ከፈተ፡፡

የፓርቲው የብሔራዊ ምክር ቤት አባልና የሕግ ባለሙያ አቶ ኢዮብ መሳፍንት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተደንግጎ የሚገኘውና የማይጣሰው የመሰብሰብ መብት ተጥሷል፡፡ የፓርቲውም ዋና ሥራ የሆነው ስብሰባ የማዘጋጀት፣ ባለድርሻ አካላትን የማወያየትና የማደራጀት መብትም ተጥሷል ብለዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የፓርቲን መብት ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌንም የጣሰ አካሄድ በመሆኑ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 12ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሁከት እንዲያስወግድላቸውና ግልጽ ውሳኔ እንዲሰጥላቸው የክስ አቤቱታቸውን ለሬጅስትራር በማቅረብ፣ ችሎቶች ሥራቸውን ስለጀመሩ ቀርበው ለማስረዳት እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወደ ክስ ያስኬዳቸው ዋና ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተፈጸመውን የመሬት ወረራ አስመልክቶ፣ ፓርቲው ባደረገው ጥናትና ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት ላይ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሊያደርገው የነበረ ውይይት በተደጋጋሚ በከተማ አስተዳደሩ መከልከሉ መሆኑን አቶ ኢዮብ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በተለይ በመሬት ወረራው ቀጥተኛ ተጎጂ የሆኑት አርሶ አደሮች፣ ምትክ ቦታም ሆነ የጋራ መኖሪያ ቤት ያልደረሳቸው በርካቶች በመሆናቸውና በተለያዩ ቦታዎች አቤቱታ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው በማጣታቸው፣ ከእነሱና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ሊያደርግ ፓርቲው ያዘጋጀውን ፕሮግራም፣ ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መከልከሉን አስረድተዋል፡፡

ፓርቲው የመጀመርያውን ውይይት መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማድረግ በማሰብ ከተማ አስተዳደሩ እንዲያውቀው ሲያደርግ፣ በመስቀል በዓል ዝግጅት ሳቢያ የፀጥታ አካሉ በሥራ በመጠመዱ ለሌላ ጊዜ እንዲያሳልፍና ስብሰባውን እንዲያደርግ ለፓርቲው ስለተገለጸለት፣ የኢሬቻ በዓልንም በማሳለፍ ለመስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ውይይት ማዘጋጀቱን አቶ ኢዮብ ተናግረዋል፡፡

በከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ በአቶ ኤፍሬም ግዛው ፊርማ ወጪ በተደረገ ደብዳቤ ለኢዜማ የደረሰው ማሳሰቢያ እንደሚያስረዳው፣ ፓርቲው ከመሬት ወረራና ከጋራ መኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ ከምክትል ከንቲባዋ ጋር ውይይት ማድረጉን በመጠቆም፣ መረጃውን ወስዶ የከተማ አስተዳደሩ እያጣራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም አስተዳደሩ የጀመራቸውን ሥራዎች መጨረስ ስለሚገባውና ኃላፊነቱም የመንግሥት መሆኑን በመጥቀስ፣ የኢዜማ አካሄድ ወደ ግጭት የሚወስድ በመሆኑ ለመስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም.  የጠራው ውይይትን እንዲሰርዝ አሳስቦታል፡፡

እንደ አቶ ኢዮብ ገለጻ ደብዳቤው ተገቢነት የሌለውና በተለይም ፓርቲውን ለማስፈራራት ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ሌሎችም የፀጥታ ኃይሎች ግልባጭ የተደረገበት ሒደት ሁከት በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ሁኔታውን በጥልቀት መርምሮ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥላቸው የክስ አቤቱታ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...