Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየቀጣይ ኦሊምፒክ ተስፋና ሥጋት በኃይሌ ገብረሥላሴ ዕይታ

የቀጣይ ኦሊምፒክ ተስፋና ሥጋት በኃይሌ ገብረሥላሴ ዕይታ

ቀን:

መሰንበቻውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከወትሮው ለየት ባለ የተነቃቃበት፣ አትሌቶቹ ድል ማድረግ ብቻ ሳይሆን የዓለም ክብረ ወሰንን ለመስበር የታደሉበት ነበር፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ውጤት ጠፍቶበት የነበረው የረዥም ርቀት ውድድር በተለይ የትራክ (መም) ዳግም ብርሃን እንዲታይ ካደረጉት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው የ5,000 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን በቅርቡ የሰበረችው ለተሰንበት ግደይ ናት፡፡

ለአሥራ ሁለት ዓመታት በጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረውና ክብረ ወሰንን በእጇ ማስገባቷ ብቻ ሳይሆን ያላትን ብቃትና አቋም ዘንድሮ ለሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ለድል እንደምታበቃ ታምኖበታል፡፡

ለበርካታ ዓመታት የለንደን ማራቶንን ድል ከጨበጡት ኬንያውያን እጅ ምልዐተ ኃይሉን በመጠቀም የድል አክሊሉን የጨበጠው ሌላው ባለድል ሹራ ኪታጣ ለሁለት አሠርታት የራቀውን የኦሊምፒክ ማራቶን ወደ ቤቱ ያመጣል የሚል ተስፋን አሰንቋል፡፡

በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ-19 ምክንያት ከዓምና ወደ ዘንድሮ በተላለፈው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ውጤታማ የሚያደርጋትን ዝግጅት ለመጀመር መዘጋጀቷን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ሰሞኑን መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በኦሊምፒክ ኮሚቴ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ እንደተገለጸው፣ በጋዜጣው መግለጫው ላይ ከተገኙትና ሙያዊ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዝግጅት የቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ይገኝበታል፡፡

የሁለት ኦሊምፒክ (አትላንታና ሲድኒ) የ10,000 ሜትር ባለድሉ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በመድረኩ እንደተናገረው፣ ኢትዮጵያ ከኦሊምፒኩ የምትፈልገው ውጤት እንደመሆኑ ሁሉም አካል መጠላለፉን ትቶ ዝግጅት ላይ ማተኮር አለባት

የኮሮና ወረርሽኝ በፈጠረው ተፅዕኖ በተለይም 5,000 ሜትር 10,000 ሜትር የሚሮጡ አትሌቶች ሌላ ርቀት ለመሮጥ እየተገደዱ መሆኑን የጠቆመው ኃይሌ ኢትዮጵያ ድል በለመደችባቸው ርቀቶች የሚዘጋጅ አትሌት አለመኖሩ ሥጋት እንደፈጠረበት ያስረዳል፡፡

ከእነዚህ ችግሮች አትሌቶችን ለማላቀቅ የሚፈልጉትን ነገር ማሟላት እንዲሁም የዝግጅት ቦታን ጨምሮ ሌሎች ነገሮች ከወዲሁ መስተካከል እንዳለባቸው ምክረ ሐሳቡን ሰጥቷል፡፡ በውድድር ላይ የሚኖር የአየር ፀባይ በተለይም በማራቶን ውድድር ውጤት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንዳለው የሚናገረው ኃይሌ ይህንን መሠረት አድርጎ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አብራርቷል፡፡ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀያየረ አትሌቶች በቴክኖሎጂ እየታገዙ መምጣታቸውን የታዘበው ኃይሌ በዚህ ረገድ አስፈላጊ ዝግጅት እንደሚጠበቅም ጠቁሟል፡፡

ከኮሮና ወረርሽኝ ወዲህ በቅርቡ እየተካሄዱ በሚገኙ ውድድሮች የሌሎች አገሮች አትሌቶች የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ነባር ክብረወሰኖች ጭምር በመስበር ሲያሸንፉ ይታያል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በአንፃሩ ያልተጠበቁ ድሎችንና ክብረወሰኖችን አልፎ አልፎም ቢሆን ሲያስመዘግቡ ይስተዋላል፡፡ ይህም በቀጣዩ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ የሚኖራትን ውጤትጋትም ተስፋም እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ኃይሌ በዚህ ረገድ ‹‹ለሻምፒዮናነትና ለክብረወሰን የሚሮጡ አትሌቶች ይለያያሉ›› በማለት ሥጋቱንም ተስፋውንም ወደ ኋላ ትቶ ዝግጅት ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም አትሌቶች በሰዓታቸው መሠረት ሳይሆን ኦሊምፒኩ ላይ የማሸነፍ አቅማቸው ታይቶ የሚመለመሉበትን አሠራር እንዲመርጥ አስረድቷል፡፡ ሁሉም አካል ሽኩቻዎችን ትቶ ተግባብቶ መሥራት ከቻለም ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ተስፋውን ገልጿል፡፡ ማንም የማንም ደጋፊ ሳይሆን ውጤትን መሠረት አድርጎ መሥራት እንደሚኖርበት አሳስቧል።

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ከዓርብ ሐምሌ 16 ቀን እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በጃፓን ብሔራዊ ስታዲየም እንደሚካሄድ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስቀድሞ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ የማራቶን ውድድሩ ግን በኃይለኛ ሙቀት ምክንያት ከቶኪዮ ወደ ሳፖሮ እንዲዘዋወር ሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...