የማኅበረሰቦችን ሕይወት በማሻሻል ረገድ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረለት የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ በቅርቡ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እና ሽልማት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትብብር ቢሮ፣ ኮንኮርዲያ በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትና በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ውድድር ከአምስት ዕጩዎች መካከል የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ረገድ የተሻለ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ በመገኘቱ ለሽልማት መብቃቱ ተዘግቧል፡፡ ጤና ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮና ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ባደረጉት የሦስትዮሽ ስምምነት በ1995 ዓ.ም. ሰኔ መጨረሻ አካባቢ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ጥቂት የማይባሉ ብርሃናቸው እንዲመለስ ምክንያት ሆኗል፡፡ እስካሁን ባካሄዳቸው እንቅስቃሴዎች ለ2,400 ወገኖች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አድርጎ ሰዎቹ ካለማየት ወደ ማየት መጥተዋል፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ብቻ ይሰጥ የነበረውም የንቅለ ተከላ ሕክምና አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በአራት ክልሎች ተደራሽ እንደሆነ፣ በሚቀጥሉት ዓመታትም የብሌን ማሰባሰቢያ ጣቢያዎችን በመክፈት፣ እንዲሁም ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምና መስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ከመንግሥትና ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ “ብርሃናችሁን አትቅበሩ” የሚል መርህ የሚከተለው ባንኩ ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡ ሰዎች ኅልፈት በሚያጋጥምበት ቅፅበት የሟች ቤተሰቦች ወደ ዓይን ባንክ በመደወል የሟቹን ቃል መፈጸም እንዳለባቸው በየጊዜው ማሳሰቡ አልቀረም፡፡ በዕውቅናውና በሌሎች ተያያዥ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የባንኩን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ለምለም አየለን ታደሰ ገብረማርያም አጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የዓይን ባንኩ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እንዴት ሊያገኝ እንደቻለና የዕውቅናውን ዓይነት ቢያብራሩልን?
ወ/ሮ ለምለም፡- ባንኩ የተቀዳጀው ዕውቅና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፐብሊክ ፕራይቪየት ፓርትነርሺፕ ወይም ፒ-ስሪ ኢምፓክት ይባላል፡፡ ዕውቅናም ሊሰጠው የቻለው በመንግሥት፣ በግለሰቦችና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሦስትዮሽ ቅንብር ወይም ደግሞ በአንድነት ሥራ ኅብረተሰቡ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ወይም ለማስተካከል የሚያደርጋቸው የጥምረት እንቅስቃሴዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን በማግኘቱ፣ እስካሁን ያከናወነው የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምናም ፍሬ ማፍራቱንና ቅንጅቱም ለውጥ በማስገኘቱ ነው፡፡ የዕውቅናው መገኘት የባንኩን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ወደ ልህቀት ማዕከል ለመሻገር የሚያስችለውን አቅጣጫ የሚያመላክት ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ሪፖርተር፡- ለተጠቀሰው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያበቃው ሌላ ዕውነታ አለው?
ወ/ሮ ለምለም፡- በተለይ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምናው ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች ብቸኛ መሆኑን፣ በአጠቃላይ በአፍሪካ ደረጃም ፈር ቀዳጅና በምሳሌነትም መታየቱ፣ እንዲሁም በዓይን ሕክምና ዙሪያ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠሩ፣ በዚህም ግንኙነት የቀሰመውን ተሞክሮ በዕለት ተዕለት ሥራው ላይ እንደ ግብዓት መጠቀሙ ለዓለም አቀፍ ዕውቅና መገኘት ያበቃው ሌላው እውነታ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ዕውቅናውን ለማግኘት የነበረውን ውድድር እንዴት ይገልጹታል?
ወ/ሮ ለምለም፡- ዕውቅናው ከፍተኛ የሆነ ውድድር ታይቶበታል፡፡ በዚህም በጤናው ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች በመንግሥትና ግሉ ዘርፍ አጋርነት (ፐብሊክ ፕራይቪየት ፓርትነርሺፕ) በተሠማሩ የበርካታ አገሮች ተቋማት አማካይነት የተከናወኑ የኅብረተሰቡን ችግር የፈቱና አገልግሎቱንም ያጠናከሩ ብዙ የቅንጅት ሥራዎች በውድድሩ ላይ ቀርበው ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ውድድሩ እልህ አስጨራሽ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን ውድድር የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ በአሸናፊነት እንዴት ሊወጣ ቻለ?
ወ/ሮ ለምለም፡- ከቀረቡትም የቅንጅት ሥራዎች መካከል የአምስት አገሮች የቅንጅት ሥራ ዕጩ ተመራጭ ሆነው ቀረቡ፡፡ ከዕጩዎቹም ውስጥ የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ያከናወነው የቅንጅት ሥራ አንዱ ለመሆን በቃ፡፡ በስተመጨረሻም ከዕጩዎቹ ውስጥም የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኖ ወጣ፡፡ በዚህም ለተጠበቀው ውጤትና ዕውቅና በቃ፡፡
ሪፖርተር፡– ውድድሩን፣ መስፈርቶቹን አዘጋጅተው ሽልማቱንም የሰጡት ዓለም አቀፍ ተቋማትን ማወቅ ይቻላል?
ወ/ሮ ለምለም፡- እንዲህ ዓይነቱን ውድድርና ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን መሥፈርቶች በማዘጋጀት ዓለም አቀፉ ዕውቅና ለኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የሰጡት በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ኮንኮርዲያ፣ በዚሁ አገር ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቨርጂኒያ ዳርዶን ስኩል ኦፍ ቢዝነስ፣ እንዲሁም በዓይን ባንክና በዓይን ጤና ላይ የሚሠሩ ሳይት ፎር ላይፍና ሂማሊያን ካታራክት ፕሮጀክት የተባሉ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ተቋማት ባደረጉት የቅንጅት ሥራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን ዕውቅና ማግኘቱ ፋይዳው ምንድነው?
ወ/ሮ ለምለም፡- የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱ በርካታ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ከፋይዳዎቹም መካከል አንደኛው የልህቀት ማዕከል የመሆኑን ራዕይ ለማሳካት የሚያሰችል አቅም መፍጠሩ ይገኝበታል፡፡ በዚህም እንቅስቃሴ ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገው ያለምንም ውጣ ውረድና ችግር የማግኘት ዕድሉን ያደላድሉታል፡፡ የመንግሥትና የግል ዘርፍ በጥምረት ቢንቀሳቀሱ የኅብረተሰቡን ችግር ለመፍታትና አገልግሎቱንም ተደራሽ ለማድረግ የሚያሰናክላቸው አለመኖሩን ባንኩ የተቀዳጀው ዕውቅና ጥሩ ማሳያ ሆኗል፡፡
ሪፖርተር፡- የዓይን ባንኩን ዓላማና ተግባር አስመልክቶ ኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?
ወ/ሮ ለምለም፡- ባንኩ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ለዓለም አቀፍ ዕውቅና ብቁ ቢያደርገውም ባንኩን አስመልክቶ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ግን ወደ ተፈለገው ደረጃ ደርሷል ለማለት አይቻልም፡፡ ይህም ሆኖ ግንዛቤ ማስጨበጡ ሥራ ተስፋ በሚሰጥ መልኩ እየተከናወነ ነው፡፡ ከሌሎችም የዓለም ክፍሎች የሰው አካል ወይም የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምና ለውጥ ማምጣት የቻለው በኅብረተሰቡ መካከል ብዙ ጊዜ የፈጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ከተከናወነ በኋላ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን፣ ኢትዮጵያ ውስጥም ከኅልፈተ ሕይወት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለባንኩ ለመለገስ ቃል የሚገቡት የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ከሚሰበስቡት ብሌኖች ብዛት ለመረዳት መቻሉ ግልጽ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ባንኩ ሆስፒታል ቅፅር ግቢ መቋቋሙ ምክንያት ይኖረው ይሆን?
ወ/ሮ ለምለም፡- ማንኛውም ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ የዓይን ብሌኑን ለባንኩ በፈቃደኝነት የመለገስ እንቅስቃሴው እንደተጠበቀ ሆኖ ባንኩ የዓይን ብሌን ከሚሰበስብባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው ሆስፒታልን ማዕከል ያደረገ መርሐ ግብር በማውጣት ነው፡፡ ይህም ማለት ሆስፒታሉ ውስጥ የሰው ልጅ ሕይወት በሚያልፍበት ሰዓት በአቅራቢያው የሚገኙ የሟች ቤተሰቦችን ስለ ልገሳው በመጠየቅና በማስፈቀድ የሚከናወን ሲሆን፣ ይህም ሁኔታ ካለን የለቅሶ ባህል የተነሳ ለእኛ ከባድ ሒደት ነበር፡፡ አሁን ግን እንቅስቃሴያችን ማኅበረሰቡን ለመርዳትና የዓይን ብሌን ጠባሳን ለማዳን መሆኑን ግንዛቤ እያገኘ በመምጣቱ የተነሳ የቤተሰብ አባላት ልገሳውን እየቸሩን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እየተዳረሰ ነው?
ወ/ሮ ለምለም፡- ባንኩ እንደተቋቋመ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምናን ያካሄደው በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ ብቻ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በጎንደር፣ በመቐለ፣ በጅማና በሐዋሳ ከተሞች ላይ አገልግሎቱን ማስፋፋቱን፣ አቅምን ባገናዘበ መልኩም በሌሎች ከተሞችም የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- የተለገሰው የዓይን ብሌን አያያዝና ለታካሚው እንዴት እንደሚሰጥ፣ እንዲሁም ባንኩ ከተቋቋመ አንስቶ እስካሁን ምን ያህል ዓይን ብሌን ተከላ እንዳከናወኑ ቢገልጹልን?
ወ/ሮ ለምለም፡- በልገሳ የተገኘ አንድ ዓይን ብሌን ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ ላብራቶሪ ውስጥ የሚቆየው ለ14 ቀናት ብቻ ሲሆን፣ በእነዚህም ጊዜያት ውስጥ የብሌኑ ጤንነትና ንፅህና ሙሉ ለሙሉ ተረጋግጦ ለታካሚው እንዲደርስ ይረጋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሒደትም ባንኩ ከተቋቋመበት እስካሁን ድረስ ለ24,000 ሰዎች የብሌን ንቅለ ተከላ ተከናውኗል፡፡
ሪፖርተር፡- የዓይን ባንኩን የሚመራው ማን ነው?
ወ/ሮ ለምለም፡- የዓይን ባንኩ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ውስጥ በ1995 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፡፡ የሚመራውም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ባለሙያዎች የተወጣጡ ሙያተኞችን ባቀፈው ባለአደራ ቦርድ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የሥራ አስፈጻሚ ያለው ሲሆን የአገልግሎቱም አካሄድ በቡድን ሥራ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ሥራን በቡድን ማከናወን ውጤታማና ፍሬያማ ያደርጋል የሚል የፀና እምነት አለን፡፡