Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየ“ቀኝ” እና “ግራ” ፖለቲካ በኢትዮጵያ

የ“ቀኝ” እና “ግራ” ፖለቲካ በኢትዮጵያ

ቀን:

በአብዱ ሻሎ

በአገራችን የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ታሪክም ሆነ የፓርቲ ፖለቲካ ተጀምሮ ወደ ዘመናዊ የፖለቲካ ዓውድ ከተቀላቀልን ጊዜ ጀምሮ አንድን የፖለቲካ ኃይል፣ አደረጃጀት፣ ቡድን፣ ፓርቲ ወይም ጎራ ከኦፌሴላዊ ስሙ ባሻገር በሌሎች ስሞችና አጠራሮች ሲገለጽ መስማት አዲስ አይደለም። በተለይም ቀለም ቀመሱ፣ በአንድም ሆነ በሌላ ለዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሁኔታዎች ተጋላጭነት ያለውና በአገር ውስጥ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርገው የኅብረተሰብ ክፍል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የፖለቲካ ኩነቶች ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች፣ በሚታተሙ መጣጥፎች፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ አጫጭር ጽሑፎች አንዱ ወገን ሌላውን “ቀኝ ዘመም” እና “ግራ ዘመም” በማለት የሚፈራረጅበት ሁኔታ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ይስተዋላል። በእርግጥ ይህ የፖለቲካ አሠላለፍ ወይም አገላለጽ በአገራችን አልፎ አልፎ ጥቅም ላይ የሚውል የቅርብ ጊዜ ክስተት ይሁን እንጂ፣ በሌላው ዓለም (በተለይም በላቲን አሜሪካ በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ) በሰፊው ጥቅም ላይ ከመዋል አልፎ የአንዳንድ ፓርቲዎች መገለጫ እሰከ መሆን የደረሰ የሁለት መቶ ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ነው። በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የተለያዩ በዘርፉ የተሠሩትን ጥናቶች ዋቢ በማድረግ የአሠላለፉን ታሪካዊ ዳራ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ ስለሚገኝበት ሁኔታ እንዲሁም በአገራችን ነባራዊ የፖለቲካ ዓውድ ያለውን አረዳድና አጠቃቀም በመዳሰስ በጉዳዩ ላይ ገንቢ አስተያት ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎችን ትኩረት ለመሳብ፣ ለቀጣይ ውይይቶችና ሐሳቦች እንዲሁም ጠለቅ ለሚሉ ዕይታዎች በር ለመክፈት ብሎም ጉዳዩን ከማኅበራዊ ሚዲያ ሰፋ ወዳለ መድረክ (Main Stream) ለመሳብ ያለመ መሆኑን በቅድሚያ ለመግለጽ እወዳለሁ።

የቀኝና የግራ ፖለቲካ አፈጣጠርና ታሪካዊ ዳራ

- Advertisement -

የታሪክ ድርሳናት እንደሚነግሩን በ17ኛው እና 18ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ ውስጥ የአብርሆት (Enlightenment) ዕሳቤ ተቀጣጥሎ ጫፍ የደረሰበት ብሎም በኅብረተሰቡ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አኗኗር ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለበት ዘመን ነበር። ከዚህ ወርቃማ ዘመን ቀደም ሲል ከነበረው የህዳሴ (Renascence) ዘመን ማኅበራዊ መነቃቃቶችን እንደ ግብዓት በመጠቀም የፋፋው የአብርሆት ዕሳቤ ከእምነት ወይም ከሃይማኖት ይልቅ ምክንያታዊነትን፣ ከተለምዷዊ አኗኗርና ዘይቤ ይልቅ ሳይንስና ምርምርን አማራጭ በማድረግ የተቀጣጠለ ማኅበራዊ አብዮት ተደርጎ ይወሰዳል። በወቅቱ እ.ኤ.አ. በ1440 የተፈጠረውን የጉተንበርግ ማተሚያ ማሽን በማሻሻል የዘመኑን ሐሳብና ፍልስፍናዎች፣ ሳይንሳዊ የጥናት እንዲሁም የምርምር ውጤቶች  በመጽሐፍ ታትመው በአጭር ጊዜ ውስጥ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመካከለኛውና ታችኛው የማኅበረሰብ ክፍሎች መድረስ መቻሉን ተከትሎ፣ ቀደም ሲል በፖለቲካና ሥነ መንግሥት ጉዳዮች ላይ ቸልተኛ የነበረው የኅብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ብሎም ተሳትፎ ከፍ እንዲል አደረገው።                          

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካን አብዮት ደጋፊ፣ በሀብትና ተፅዕኖ ከዘመኑ የአውሮፓ አገሮች ከፊት ተሠላፊ በነበረችው ፈረንሣይ አንድ ሺሕ ዘመናትን ያስቆጠረ ንጉሣዊ ሥርዓት ኅብረተሰቡን በሦስት መደቦች (Estates) ማለትም ንጉሥ ሉዊ 16ኛ (ቤተሰቡና መዋዕሎቹን ጨምሮ) በመጀመርያ ወይም የላይኛው መደብ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትና መኳንንቱ በሁለተኛ መደብና የመካከለኛ መደብ ነጋዴዎችና የእጅ ባለሙያዎችን (Craftsmen) ጨምሮ ከሃያ ሚሊዮን የሚበልጡ ገበሬዎች በሦስተኛ መደብ ተከፍለው የታችኛው መደብ ክፉኛ ይበዘበዝ ነበር። አብርሆትን ተከትሎ መንቃት የጀመረው የኅብረተሰብ ክፍል “የሕዝቡ መብቶች ምንድናቸው?”፣ “መብቶቹስ ከየት የመነጩ ናቸው?”፣ “ማነው በሌሎች ላይ የሚወስነው?” “ወሳኙ አካልስ ከየት ባገኘው/ቸው ሥልጣን?” በሚሉ መሠረታዊ የፖለቲካና የመብት ጥያቄዎች ዙሪያ ያጠነጠነ የአብዮት አየር መንፈስ ጀመረ። በዚህም በአገሪቷ በሁሉን አቀፍ አብዮት ፈላጊዎች (ተራማጆች) እና ሥርዓቱ እንዳለ እንዲቀጥል የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይደረግ የነበረው ሽኩቻው እያየለ ሄዶ እ.ኤ.አ. በ1789 የአገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት በሁለት ተከፈሉ። ይህንን ተከትሎ በምክር ቤቱ ሃይማኖተኛ፣ ከሥርዓቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚና ሀብታም ባላባቶች የንጉሡ ደጋፊ በመሆን በቀኝ በኩል የሚቀመጡ ሲሆን በተቃራኒው ንጉሡንና ሥርዓቱን የሚቃወሙ፣ ሃይማኖትና መንግሥት እንዲለያይ አጥብቀው የሚሹ በአብዛኛው ከመካከለኛውና ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ተራማጅ ስብስቦች በግራ ይቀመጡ እንደነበር በወቅቱ የምክር ቤቱ አባል የነበረው ባርኖን ዲ ጉዋቪሊ እንደሚከተለው መግለጹን (Geoffrey M. Hodgson) ከትቧል። “We began to recognize each other: those who were loyal to religion and the king took up positions to the right of the chair so as to avoid the shouts, oaths, and indecencies that enjoyed free rein in the opposing camp”.

እንዲህ ባለ ሁኔታ የጀመረው የ “ቀኝ” እና “ግራ” ፖለቲካ አሠላለፍ ይዘቱን ሳይለቅ ወደ ሌሎች አውሮፓ አገሮች ለመዛመት ችሎ የነበረ ቢሆንም፣ በጊዜ ሒደትና የነባራዊ ሁኔታዎች መቀየርን ተከትሎ ራሱን እያሻሻለና ጥያቄውን (Re-define) በማድረግ እነሆ ለሁለት ክፍለ ዘመን ለመቀጠል ከመቻሉም በላይ መሠረታዊ ዕሳቤና መርሆቹን ሳይለቅ በሰባቱም ክፍለ ዓለማት ለመንሰራፈት ችሏል።

ለአብነት ያህል ከኢንዱስትሪ አብዮት መምጣት በኋላ የመሬት ባለቤት የነበሩ ከበርቴዎች በትምህርትና ቴክኖሎጂ የፈጠሩትን የበላይነት ይዘው የዝቅተኛ እንዲሁም መካከለኛ መደቡን የኅብረተሰብ ክፍል የሚበዘብዙበት ሁኔታ መፈጠሩን ተከትሎ በወቅቱ መደብ አልባ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር እንታገላለን የሚሉ፣ ለሠራተኛው መደብ የቆሙ የፖለቲካ ኃይሎች “ግራ ዘመም” ነገር ግን በተቃራኒው መሬትና ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ አብዛኛውን ሀብት በእጃቸው ያደረጉ የካፒታሊዝም አቀንቃኞች “ቀኝ ዘመም” ተብለው የነበረበት ሁኔታ ይታወሳል። ይሁን ችንጂ ዕውቁ ምሁር ሳሙኤል ሃንቲንግተን “The Clash of Civilizations and the Remaking of World Order” በሚለው ዕውቅ ሥራው እንደሚነግረን፣ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማብቃት ወዲህ የዓለም ጦርነቶችና ተቃርኖዎች ከርዕዮተ ዓለም ይልቅ በአብዛኛው “የማንነት” (Identity) (በነገራችን ማንነት ሃንቲንግተን ዓውድ የብሔር፣ ቋንቋ ወይም ሃይማኖትን ያተኮሩ ስለመሆናቸው ልብ ይሏል) ሊሆኑ እንደሚሉ ማሳያዎችን እየጠቀሰ ሞግቷል። እነሆ ይኸው አብዛኛው አገራዊ፣ ዓለም አቀፋዊና ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ማንነት ላይ ያጠነጠኑ ስለመሆናቸው ቡዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በዚሁ ዓመት እያስተዋልናቸው የሚገኙት በአዘርባጃንና በአርሜኒያ ጦርነት፣ የሆንግ ኮንግ ጥያቄ፣ የቱርክና ግሪክ እሰጥ አገባ (በሜዲትራኒያ የባህር ክፍል የነዳጅ ክምችት ጉዳይ ተደራቢ ነው)፣ የቻይናና አሜሪካ ሽኩቻ፣ የኢራንና ዓረብ ጎረቤቶቿ ትንቅንቅ፣ የህንድና ቻይና ፍጥጫ፣ የህንድና ፓኪስታን መቆራቆዝ፣ የየመን ትራጄዲ፣ የሮሂንጂያዎች ሰቆቃ፣ በአሜሪካ አሁን ድረስ የቀጠለው አለመረጋጋት፣ የእንግሊዝና አውሮፓ ኅብረት መቋጫ ያጣው ውዝግብ (Brexit)፣ የአፍጋኒስታን ውድመት ብሎም የሶማሊያ ውጥንቅጥ ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንግድ ከማንነት ጋር የተያያዙ ስለመሆናቸው ለመረዳት ሃንቲንግተንን መሆን አያስፈልግም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የቀኝ እና ግራ የፖለቲካ ጎራ እንደ ከዚህ ቀደሙ በርዕዮተ ዓለም ዙሪያ ሳይሆን፣ በማንነት ዓውድ ላይ የሚሽከረከር ስለመሆኑ አጠር ባለ መልኩ ነባራዊ ሁኔታዎችን እያጣቀስኩ ለማሳየት እሞክራለሁ፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ ስለሚውልበት ሁኔታ (አውሮፓና አሜሪካ)

ቀኝ ዘመም

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስደተኞች ፍልሰትን ተከትሎ በአውሮፓ የማንነት ፖለቲካ እንደ አዲስ መቀንቀን የጀመረ ሲሆን፣  “አውሮፓ ነጭ የዘር ሐረግ ያለው አውሮፓዊ ብቻ ናት” “ዓለምን የቀየረው የነጭ ሥልጣኔ ሲሆን ሌላው ያልሠለጠነ ኢ ሰብዓዊ ነው” “በመጤና ስደተኞች ባህላችን እየተበረዘ ነው” የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ጎራ የሚመደቡ ሆነው ሲገለጹ ይስተዋላል። ይህ ዘርን መሠረት ያደረገ ዕይታ የናዚ ፍልስፍና ከሆነው “የአሪያን ዘር (Master Race)” ፍልስፍናና እሳቤ የሚቀዳ ሲሆን ናዚዎች ይህንን አስተሳሰብ ከአፈታሪክና ንግርትነቱ ባሻገር ሳይንሳዊ ለማድረግ ብዙ ርቀት ሄደዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አስተሳሰቡ በሳይንስ ካልተረጋገጡ ትርክቶች የሚነሳ ሲሆን፣ በዚህም “አርያኖች” ከሰማይ የተጣሉ መላዕክት ከሰው ልጅ ጋር ተዳቅለው የተገኙ ስለመሆናቸው ያትታል። ይህንን አፈ ታሪክ ሳይንሳዊ ቅብ ለመቀባት እ.ኤ.አ. በካውንት ጆሴፍ አርተር የተጻፈውን “The Inequality of Human Race” የተሰኘ መጽሐፍ የሚያጣቅሱ ሲሆን፣ የመጽሐፉ ዋና ማጠንጠኛ ነጭ ከሁሉም (ከጥቁር፣ ጠይምና በተለምዶ ቢጫ የሚባለው የእስያ ሰዎች ቀለም) የሰው ዘሮች የበላይ እንደሆነ  “አሪያኖች” ደግሞ (በሰሜን አውሮፓ የሚኖሩ፣ ሰማያዊ የዓይን ቀለምና ወርቃማ ፀጉር ያላቸው) ከነጮች ሁሉ የበላይ ዘር ስለመሆናቸው ከፊሎሎጂና ከአንትሮፖሎጂ “ጥናቶች” በመነሳት ያትታል። በአጠቃላይ እሳቤው የሰው ልጅ በሳይንስ፣ ሥነ ጥበብ፣ ሥነ ሕንፃና መሰል ሥልጣኔዎች ያስመዘገባቸው አዎንታዊ መሻሻልና ፈጠራዎች ከዚህ “ልዕለ ሰብ (Super-Man)” ከሆነ ዘር የተገኙ እንደሆነ በፅኑ የሚያምን ከመሆኑ በተጨማሪ በ1850ዎቹ ለኅትመት የበቃውን የዕውቁን ሶስዮሎጂስት ኸርበናት ስፔንሰር ‹‹Social Darwinism›› ዕሳቤ በማጣቀስ ጠንካራና የተሻለው ዘር (የእነርሱ ዘር) ሌላውን ሁሉ መምራትና ማሠልጠን እንዳለበት ያምናሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ እ.ኤ.አ. በ1899 ራዲያርድ ኪፕሊንግ በተባለ ነጭ ‹‹The White Man’s Burden›› በሚል ርዕስ የተጻፈውን አጭር ግጥም መመልከት እሳቤውን ይበልጥ ለመረዳት ይረዳል።

ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ይህ ጎራ አንደኛ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው የሚመስል ጠንካራ ትርክት ላይ በመመሥረት ራሱን የዓለም ሥልጣኔ ሁሉ ባለቤትና ፈር ቀዳጅ፣ ሌላው ዘር ከሱ ያነሰና ከፍ ሲል እርሱን ለማጥፋት የሚያሴር፣ እንዲሁም ራሱን የዓለም ማዕከል አድርጎ የሚመለከት ነው። በአሁኑ ወቅት በጀርመን (AFD)፣ ስዊድን (Nordic Resistance Army)፣ እንግሊዝ (British National Party)፣ ፖላንድ (National Revival of Poland)፣ ግሪክ (Golden Dawn)፣ ጣሊያን (The Right) እና የመሳሰሉት የግራ ዘመም ፖለቲካ ፓርቲዎች በአውሮፓ ተቀባይነታቸው እየጨመረ ነው። በተያያዘ በአሜሪካ የዶናልድ ትራምፕ ማኅበራዊ መሠረትና ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው እንደ (Ku Klux Klan, Aryan Nations, Aryan Republican Army, Atomwaffen Division, Identity Evropa) እና ሌሎች ከሃያ የሚበልጡ ቡድኖች በዚህ ውስጥ ይካተታሉ (በነገራችን ላይ ብዙዎቹ ‹‹Anti-Defamation League›› በተባለ የጥላቻና ዘረኝ ላይ በሚሠራው ዕውቅ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የተመዘገቡ ናቸው)፡፡

ግራ ዘመም

ቀደም ሲል ታሪካዊ ዳራው ላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በፈረንሣይ አብዮት ከንጉሡና ንጉሣዊ ሥርዓቱ በተፃራሪው በመሠለፍ አጠቃላይ አብዮት እንዲካሄድ ሲጠይቁ የነበሩ፣ ተራማጅ እነደሆኑ የሚነገርላቸው በተለይም ከመካከለኛ፣ እንዲሁም ታችኛው የማኅበረሰብ የተውጣጡ የፖለቲካ ኃይሎች በዚህ ጎራ ይመደቡ የነበረ ሲሆን ሃይማኖትና መንግሥት የተለያየበት ሪፐብሊክ እንዲመሠረት የሚታገሉ ነበሩ። ከኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳት በኋላ ወደ ሠራተኛው መደብ በማዘንበል ቡርዥዋና ካፒታሊስቱን ተቃውመው የኮሙዩኒዝም አቀንቃኝ ለመሆን ችለዋል። ከሶቭየት ኅብረት መፈራረስ እስካለንበት ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየገነነ በመጣው የማንነት ፖለቲካና ሉዓላዊነት (Globalization) ዘመን የነጭ የበላይነት የሚቃወም፣ ለስደተኞችና ህዳጣን (Minority) ቡድኖች የፖለቲካ ውክልና የሚታገል፣ ፀረ ቅኝ ግዛት ብሎም ጥቂቶችን ከሚያበለፅገው የኒዮ ሊበራሊዝም የፖለቲካ ርዕዮት መንግሥት በኢኮኖሚው ዘርፍ እንደ አስፈላጊነቱ ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቅድ (ሲለጠጥ የመንግሥት ቁጥጥር እንዲጨምር የሚሻ) ጎራ ስለመሆኑ ይገለጻል። ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካንን ጨምሮ በምዕራቡ ዓለም ለሁሉም ዜጎች የጤና መድህን ሽፋን (Universal Health Care)፣ በሒደት ድንበሮችን ልል በማድረግ ዓለም አቀፋዊነት (Internationalism)፣ ለሠራተኛው መደብ የሥራ ሰዓትና የዝቅተኛ ክፍያ ወለል (Minimum wedge)፣ ውርጃን ሕጋዊ ማድረግ (Pro-Abortion)፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን አደደጋ ለመከላከል የኃይል አማራጭን ከነዳጅና የድንጋይ ከሰል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ታዳሽ ኃይል የመቀየር (Energy Transformation) እና የመሳሰሉትን አጀንዳዎች ያነገበ ነው።

ጠቅለል ባለ ሁኔታ ይህ ጎራ ዘርን (Race) በተመለከተ በተቃራኒው ጎራ ከሚቀነቀነውና ሃይማኖታዊ ቅብ ካለው የዘር ምደባ በፅኑ የሚቃወም፣ ለአናሳና ሠራተኛው መደብ የሚወግን፣ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየትን በፅኑ የሚደግፍ ብሎም ከአገራዊነት (Nationalism/Patriotism) ይልቅ ዓለም አቀፋዊነትን የሚያቀነቅን ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ተቀባይነትን ያለው ገዥ ሐሳብ ከመሆን አልፎ በአሜሪካ እንደ የዴሞክራት ፓርቲ፣ እ.ኤ.አ. ከ1990-2000 ባሉት ዓመታት በተወለደው ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል (Millennials)፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም ኮርፖሬሽኖች ይደገፋል።                    

በአገራችን ያለው አጠቃቀምና አንድምታው

በአገራችን ለፓርቲ ፖለቲካ መወለድና ዘመናዊ የፖለቲካ ፈር ቀዳጅ የሆነው የተማሪዎች ንቅናቄ ከተጀመረበት 1960ዎቹ ዓ.ም. ወዲህ የአገሪቱን መሠረታዊ ተቃርኖ በመተንተን ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጡ ሒደት በጉልህ የሚታዩ ሦስት ዓይነት አሠላለፎ የነበሩ ሲሆን፣ ሦስቱም ጎራዎች ከሚከተሉት የሶሻሊዝም (የግራ ዘመም) ርዕዮት ባሻገር የማንነት ፖለቲካን በተመለከተ ጠንካራ ልዩነት እንደነበራቸው ይታወሳል። በዚህም ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ አንደኛ ‹‹የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር የቅኝ ግዛት ነው›› ብለው የሚያኑና ‹‹የራስን አገረ መንግሥት መሠረት›› እንደ መፍትሔ አስቀምጠው የሚታገሉ፣ ሁለተኛ የአገሪቱ ችግር “የብሔር ጭቆና” እንደሆነ በመተንተን ‹‹ለብሔሮችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ብሎም ራስን በራስ በማስተዳደር እንደሚፈታ በሚያምኑ››፣ ሦስተኛ የአገሪቱ ችግር “የመደብ ጭቆና” መሆኑን በመቀበል ‹‹ጨቋኝ የሆነውን የፊውዳል ገዥ መደብ በማስወገድ መደብ አልባ ሶሻሊስት አገር መመሥረት›› የሚሉ ኃይሎች በወቅቱ አንብሮ (Thesis) የነበረውን የንጉሡን ፊውዳላዊ ሥርዓት መጋፈጣቸው ይታወሳል። እነዚህን የፖለቲካ ኃይሎች (ንጉሣዊውን የፊውዳል ሥርዓት ጨምሮ) “ግራ” እና “ቀኝ” በሚል በሁለት ጎራ ከፍሎ ከመተንተን አንፃር ይህ ነው ሚባል የተደራጀ ጥናት ወይም ጽሑፍ ለጊዜው ማግኘት ያልቻልኩ ሲሆን፣ በፍቃዱ ኃይሉ ከኢኮኖሚ ርዕዮት አንፃር የቃኘበትን ጽሑፍ በፌስቡክ ግድግዳው ላይ አጋርቶን ተመልክቻለሁ። ይሁን እንጂ አሁን ባለው ወቅታዊ የዓለም አቀፍ ሁኔታ ብሎም አገራዊ ተቃርኖ የሁለቱ ጎራዎች ልዩነት (“የግራ” እና “ቀኝ” ዘመም አሠላለፎች) ከማንነት ፖለቲካ (Identity Politics) ጋር የተዋሀደበት ሁኔታ በጉልህ የሚስተዋል መሆኑን ተከትሎ አሠላለፉን ከኢኮኖሚክስ ርዕዮት ብቻ  መተንተን፣ አጠቃላይ ምሥሉን ከመረዳት አንፃር ውስንነት እንደሚኖርበት አምናለሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ጋሽ ሀብታሙ አለባቸው “ታላቁ ተቃርኖ” በሚል ርዕስ በ2009 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፋቸው (ገጽ 31) አሠላለፉን ከማንነት ፖለቲካ ጋር አያይዘው በጨረፍታም ቢሆን እንደሚከተለው ይገልጹታል ‹‹. . .የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ችግር ለመለየት በተደረጉ ያመረሩ ክርክሮችና ትንቅንቆች ውስጥ በተለይም በተማሪው ንቅናቄ ወቅት በጉልህ የታየ ፍንጭ ነው። ከፊሎቹ ‘ዋናው የኢትዮጵያ ማነቆ የመደብ ጭቆና ነው’ የሚሉ ናቸው (አሰፋ እንዳሻው፣ 2003) ግራ ዘመም ዝንባሌ ያላቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ደግሞ ‘የብሔር ጥያቄን’ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጠው ነው ሲሉ ይከራከራሉ። እናም የመደብ ጭቆና ሲወገድ አብሮ የሚወገድ ‘ጥገኛ ችግር’ መሆኑን ያስረዳሉ” ካሉ በኋላ በዚያው ገጽ ላይ ወረድ ብለው ‹‹ወደ ቀኝ የሚያዘነብሉት በበኩላቸው ‘የብሔር ጥያቄ’ ብሎ ነገር አይዋጥላቸውም። ጥያቄው በኢትዮጵያ ችግር ምርመራ ሒደት ምንም ዓይነት ቦታ የሌለው ያደርጉታል። ለእነዚህ ወገኖች ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህ አስተሳሰብ ያላቸው ልሂቃን ‘የብሔር ጥያቄ’ የሚለውን ስያሜ ራሱ ከመጠቀም እስከ መቆጠብ ይሄዳሉ። እንዲያውም በማጣጣል ድምፀት ‘ጎሰኝነት፣ ቀበሌያዊነት፣ ጎጠኝነት. . .’ ብለው ይጠሩታል። (መስፍን ወልደ ማርያም 2005)” በማለት በትንሹም ቢሆን አንስተውት ያልፋሉ። ምንም እንኳ ጋሽ ሀብታሙ ከላይ እንደተገለጸው አሠላለፉን በአጭሩ ቢያስቀምጡም፣ በጣም ግልጽና ለተያዘው ፍሬ ነገር አጋዥ በመሆኑ የእርሳቸውን የትንታኔ መስመር ሳልለቅ ዳሰሳዬን እቀጥላለሁ።

በአገራችን የፖለቲካ ዓውድ የቀኝና ግራ ዘመም ርዕዮት ልዩነት በኢኮኖሚክስ ርዕዮት ዓይን ከታየ፣ ‹‹የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር በመርህ ደረጃ የመደብ ጭቆና ነው›› ብለው ሲታገሉ የነበሩት (በመጨረሻም ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ጁንታውን ጨምሮ) የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ወይም ኢሕአፓና የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ወይም መኢሶን በግራ ዘመምነት መመደባቸው አከራካሪ አይደለም። በአንፃሩ ንጉሡን ጨምሮ የፊውዳሉ ሥርዓት እንዲቀጥል የሚሹ (የእነ ራስ መንገሻ ኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ዩኒየን ወይም ኢዲዩ ጨምሮ) ብሎም የፊውዳል ሥርዓቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ አደረጃጀቶች ቀኝ ዘመም መሆናቸው ግልጽ ነው።

በሌላ በኩል የማንነት ጥያቄን ከግምት ውስጥ በማስገባት አሠላለፉን የቃኘን እንደሆነ ከላይ ከተጠቀሰው የተለየ ውጤት የሚሰጠን ይሆናል። በዚህም በመርህ ደረጃ ‹‹የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር የብሔር ጥያቄ የብሔሮች ጭቆና ነው›› በማለት ተደራጁ ጀብሃ ጀምሮ ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (EPLF)፣ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ወይም ሕወሓት፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወይም ኦነግ፣ የኦጋዴን ነፃነት ግንባር ወይም ኦብነግ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ወይም ሲአንና የመሳሰሉት የፖቲካ ድርጅቶች ግራ ዘመም በሚባለው ጎራ የመመደባቸው ሁኔታ አከራካሪ አይደለም። እነዚህ ግራና ቀኝ ዘመም ተብለው በጥቅል የተገለጹት ጎራዎች ተንትነው ላስቀመጡት ችግር መፍትሔ በመስጠቱ ሒደት ላይ የተለያየ የመፍትሔ ሐሳብና አቅጣጫን በመከተላቸው ሌላ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል። በመሆኑም ለብሔር ጥያቄ እምብዛም ወይም በጭራሽ ዕውቅና ማይሰጡት ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ደም አፋሳሽ ብሎም እስከ መጠፋፋት የደረሱ ግጭቶች የተነሱ ሲሆን፣ ዘውዳዊ ሥርዓቱ በአንድ በኩል ኢሕአፓ፣ መኢሶንና ደርግ ወይም ኢሠፓ በሌላ በኩል በመሆን ከዘውዳዊ ሥርዓቱ ጋር የገቡት ግጭት አንዱ ነው። በሌላ በኩል ከዘውዳዊ ሥርዓቱ መወገድ በኋላ በደርግና ኢሕአፓ፣ ኢሕአፓና መኢሶን፣ መኢሶንና ደርግ መካከል መጠፋፋቱ ሊቀጥል መቻሉ ይታወቃል። በተመሳሳይ የግራ ዘመሙ ኃይሎች ምንም እንኳ የብሔር ጥያቄን የስበታቸው ማዕከል በማድረግ ቢቋቋሙም ልክ እንደ ቀኝ ዘመም ኃይሎች ሁሉ እነርሱም እንደ መፍትሔ ባስቀመጡት አቅጣጫ ልዩነት (እንደ ኦብነግ፣ ኦነግና ሕግሓኤ ችግሩን የቅኝ ግዛት አድርጎ በመተንተን ለመገንጠል በሌላ በኩል ሕወሓት በአገር ውስጥ ራስን በራስ ለማስተዳደር) ብሎም ለአካባቢያዊ የበላይነት ለደም አፋሳሽ ግጭትና መጠፋፋት መዳረጋቸው ዕሙን ነው።

በአሁኑ ጊዜ  ቀደም ሲል የተገለጹት የፖለቲካ ኃይሎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ የወጡ (ሕግሓኤ)፣ የጠፉ (መኢሶን፣ ኢሕአፓና ኢሠፓ) እንዲሁም ጥቂቶቹ ትንታኔያቸውን ከልሰው መቀጠል የቻሉ ሲሆን (ሲአን፣ ኦነግ፣ ኦብነግና ሕወሓትን ልብ ይሏል) በአንፃሩ በሁለቱም ጎራ የሚመደቡ ለዘብተኛና አክራሪ አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች ተፈጥረዋል። ይህንን ተከትሎ አሠላለፉ መሠረታዊውን የሐሳብ ልዩነት ሳይለቅ፣ አክራሪነትና ለዘብተኝነት እንደ መለኪያ ተጨምረውበት፣ ብሎም ወቅታዊውን ሁኔታ ከግምት በሚያስገባ ሁኔታ እንደሚከተለው በአራት በመክፈል ከመሠረታዊ  ልዩነቶቻቸው ጋር በአጭሩ በማሳየት ጽሑፉን ልቋጭ፡፡

  • ቀኝ አክራሪ (Far Right) በአገሪቱ መሠረታዊ ችግርም ሆነ ተቃርኖ አፈታት ላይ ለብሔር ማንነት ጥያቄ ፈፅሞ ቦታ የማይሰጥ ብሎም ቢቻል ያለፈውን ዘውዳዊ ሥርዓት ለመመለስ የሚሻ፡፡
  • ለዘብተኛ ቀኝ (Center Right/Conservative) በተወሰነ ደረጃ ለብሔር ጥያቄ ዕውቅና ቢሰጥም፣ በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አደረጃጀትም ሆነ አከላለልን (ክልልን) የማይቀበል።
  •  አክራሪ ግራ (Far Left) መሠረታዊው የብሔር ማንነት ጉዳይ የቅኝ ግዛት እንደሆነ ተቀብለው መገንጠልን ወይም የራስ አገር መመሥረትን እንደመፍትሔ የሚያስቀምጡ።
  • ለዘብተኛ ግራ (Center Left/Liberal) ለብሔር ማንነትና ጥያቄ ዕውቅና በመስጠት ችግሩ ራስን በራስ ማስተዳደር በሚያስችል የፖለቲካ አደረጃጀትና ማንነትን ተመሥርቶ በሚፈጠር አከላለል (ክልልነት) እንደሚፈታ የሚያምን።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...