በገለታ ገብረ ወልድ
ከአንድ ወር በፊት “አዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ!” የሚል አንድ ጽሑፍ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ መልዕክቱ መልካም ከመሆኑ ባሻገር፣ ካለፉት የስህተት ምዕራፎች ተምሮ ማለፍ እንጂ በስህተት መመላለስ እንደማይገባ፣ ጥንካሬዎችንም እየለዩ ማስፋት እንደሚጠቅም የሚነሳሳ ሀተታ ነበር፡፡ አሁንም አዲስ ዓመት መባቻ ላይ እንደ መገኘታችን፣ እኔም አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት የግል ዕይታዬን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡
እነሆ አዲስ ብለን በአደይ አበባ ሞሽረን ቄጤማ ጎዝጉዘን፣ በአበባ አየሽ ወይ ዜማ ከሽነን፣ በሆያ ሆዬ ጭፈራ አድምቀን የተቀበልነው 2012 ዓ.ም. የአዲስነት ግርማውን ለባለተራው 2013 ዓ.ም. ያስረከበበት ቀን አሳልፈን አዲሱን ጉዞ ጀምረነዋል። ያሳለፍነው ዓመት በሕይወታችን፣ በኑሯችን፣ በሥራችን ብዙ ነገሮችን የተማርንበት፣ ከነበረን ነገር ላይ የዕድሜ ቁጥር ብቻ ሳይሆን መልካም ነገር የጨመርንበት፣ በተሠማራንበት የሥራ መስክ ለአገራችንና ለወገናችን የሚጠቅም በጎ ሥራ ያከናወንበት እንደሆነ እናስባለን።
የመኖር ሁሉ ዓላማው ሌሎችን የሚጠቅም አዲስ ነገርን መፍጠር፣ መጨመርና ለቀጣዩ ዘመን መሠረት የሚሆን ሥራ ሠርቶ ማለፍ እንደ መሆኑ በግል ደረጃም ሆነ፣ በአገር ላይ ፈተናና ችግር ሲገጥም ሁሉን ተቋቁሞ ማለፍም እንደ መልካም ነገር ይቆጠራል። በእርግጥ ያሳለፍነው ዓመት በአገራችን መልካም ፀጋዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ፈተናዎችም ደረብረብ ብለው የታዩበት ነበር፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መውጣትና ሊገጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችንም ለመሻገር መነሳሳት ያስፈልጋል በዚህ ዓመት፡፡
በዚህ ውጣ ውረደ ውስጥ ኢትዮጵያ ለዘመናት በድህነትና ኋላ ቀርነት ሲጠራ የነበረውን ስሟን በመቀየር፣ ሕዝቦቿ የቀደመ ታሪካቸውን የሚያስመልሱበት ጉዞ እየወደቀ እየተነሳ መቀጠሉ ይሰማናል፡፡ ምንም እንኳን የፖለቲካ መንገራገጩ፣ አልፎ አልፎ ሰላም መታጣቱና ግጭቱ መኖሩ ባይካድም መደማመጥ ከተቻለ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ወደ ደልዳላው ሜዳ ለመውጣት የራሱን አሻራ ማሳረፉም የሚቀር አይመስልም፡፡ ፈጣሪም ይህንኑ ያድርግልን፡፡
አዲስ ብለን በዜማ አድምቀን የተቀበልነው አዲስ ዓመት የባለፈው ዓመት ጅምሮች የሚቀጥሉበት፣ ነገ ልናየው ለምንናፍቀው የብልፅግና መንገድ ተጨማሪ መደላድሎች የሚሠሩበት እንደሚሆኑ መንግሥትም ደጋግሞ ቃል ገብቷል። በፖለቲካው ሥነ ምኅዳር የሰውም ሆነ የሥርዓት ለውጥ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ትግል ቢመጣ እንኳን፣ እንደ ለውጡ አካል ሁሉ ሁሉም ነገር ከተጀመረበት የሚቀጥል በመሆኑ ያለፉትን መልካም ሥራዎች አጠናክረን የምንቀጥልበት መሆንም አለበት።
አዲሱን ዓመት ስንቀበል የባለፈው ጥንካሬያችንን አጎልብተን ድክመቶቻችንን የምንፈትሽበት መሆን ስላለበት በአገር ደረጃ ቢስተካከሉ የምንላቸው፣ አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት ከችግር ለመውጣት መጠቋቆም ነው በዚህ ጽሑፍ የተፈለገው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሰሞኑን የሰማነው፣ የብር ኖት መቀየርና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት የሚያስችሉ ዕርምጃዎች ተጠናክረው ከተተገበሩ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ለሁሉም ወደ ነጥባችን እንመለስ!!
ከመርህ አልባ የፖለቲካ ትግል አገር ትውጣ
እርግጥ ነው ፖለቲካችን ገና ታዳጊ ነው፡፡ የአገረ መንግሥት ምሥረታ ታሪካችን ከእነ አወዛጋቢነቱ ከሩቅ ዘመን ቢነሳም፣ በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክም ቢሆን የሰላማዊና የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ባህል ግንባታ ነበረን ማለት አይቻልም፡፡ ለአብነት ያህል የተማሪዎች ትግል፣ ከሚባለውና የፊውዳሉን አሀዳዊ ሥርዓት ከገረሰሰው ንቅናቄ ጀምሮ የታለፈበትን መንገድ እንኳን ለፈተሸ በርካታ መጠፋፋቶች፣ ጥሎ ማለፎችና የሴራ ትንቅንቆች አገርና ሕዝብን ውድ ዋጋ አስከፍለዋል፡፡
አሁን ብቻ ሳይሆን በፊትም በነበረው የአገራችን የፖለቲካ ትግል ወኔ ያለው፣ አገራዊ ኃላፊነት የሚሰማውና ተጨባጭ የፖለቲካ እምነቱ ይኼ ነው የሚባል ፖለቲከኛ የበዛ መሆን ያልቻለውም ከዚህ መነሻ ነው፡፡ አሁን ከለውጡ ወዲህ የምናየው ነገር ደግሞ አጀብ የሚያስብልና የሰዎችን ተለዋዋጭ ፍላጎትና በሴራ የመነዳት ክፋት ጭምር የሚያሳይ ነው፡፡
እነዚህ አገርና ሕዝብን ሳይሆን ወንበርንና ጥቅምን የሚያስቀድሙ አካሄዶችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንኳን ባይቻል፣ በአዲሱ ዓመት ለመቀነስ መትጋት የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሚና ሊሆን ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ እስካሁን እንደታየው አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ትናንት የገረፋቸውንና አስሮ በግፍ ያሰቃያቸውን ሕወሓትን ቅዱስ ለማስመሰል ወራት እንኳን መታገስ አልቻሉም ነበር፡፡ የተጀመረውን የመደመርና የዕርቅ መንፈስ ለመቃወምና አገር ለዓመታት ስትላጋ በቆየችበት የዘር ፖለቲካ ተጨማሪ ኪሳራ እንዲደርስባት ለማድረግ፣ አክራሪ ብሔርተኞች ሲሰባሰቡ እንደ ማየት የሚያሳፍር ገጠመኝ የለም፡፡
ትናንት የሥርዓት ለውጥ ሽተው በየውጭ አገሩ አደባባዮችና ኤምባሲዎቻችን ላይ የጮሁ ሰዎች፣ ዛሬም መልሰው ይህንኑ ጩኸት የሚያንቧርቁት ለምንና እንዴት እንደሆነም ግልጽ አልመስል እያለኝ ነው፡፡ መቼ ነው ትዕግሥት በተሞላበት፣ ከግጭትና ከትርምስ ተላቀን የሥርዓት ለውጥ ሊያመጣ የሚችል፣ ሕግን የተከተለና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የምንጀምረው የሚለው ጥያቄም መልስ እያገኘ አይደለም፡፡
ከዚህ በላይ ግን ትናንት የአንድነት ኃይሎችና ብሔርተኞች ተባብለው እሳትና ጭድ ሆነው የኖሩ ፖለቲከኞች ሳይቀሩ፣ ፀረ ለውጥ በሆነ ሥሌት ጋብቻ ሲመሠርቱ ማየታችንም፣ ሌላው የአልቦ ቋሚ እምነት መገለጫ ነው፡፡ በግለሰቦች በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ትግልና የምቀኝነት አዙሪቱም ገና አለመቀየሩን ያሳያል፡፡ በሐሳብና ለሕዝብ በሚጠቅም እምነት መዋደድና መፋታት ግልጽ ሆኖ አለመታየቱም መታረም ያለበት ችግራችን ነው፡፡
ለአብነት ያህል በፖለቲካ አስተሳሰባቸው የተለያዩ ጽንፍ ላይ የሚገኙት ሁለት ታዋቂ ሰዎች (ልደቱና ጀዋር) በአንድ ምሽት ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ሲወያዩ ተመልካቹ ጠብቆ የነበረው ልደቱ የአንድነት ኃይሉን፣ ጃዋር ደግሞ ብሔርተኛውን ወክለው የሐሳብ ፍልሚያ ያካሂዳሉ ብሎ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡
ግን እንደተጠበቅው አልሆነም። እንዲያውም ጃዋርና ልደቱን ያገናኛቸው ጭብጥ፣ ሕጋዊ ሥልጣን ያለውን መንግሥት ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ቅቡል አይደለም ብሎ ውዥንብር መፍጠርና በሕወሓት ወይም በኦነግ ፕሮጀክት መሠረት በአቋራጭ ሥልጣን ላይ ለመንጠልጠል ያለመ ሥልት እንደነበር ከሰሞኑ መንግሥት ባወጣቸው የተለያዩ መረጃዎች ለማስረዳት እየሞከረ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ግን ሕገ መንግሥታዊ የሆኑትን ሁሉንም ምክር ቤቶች ውሳኔ የሚጥስ ሕገወጥ ድርጊት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር ሰላምን የማያመጣና በንፁኃን ደም ቁማር የሚጫወት መሆኑ የማይቀር ነበር፡፡
አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን የኢትዮጵያ ሕዝብን አንድ ጊዜ ሳይሆን ደጋግመው የሚበድሉትስ እስከ መቼ ነው ያስብላል፡፡ በፖለቲካ ትግል መድረክ ‹‹ልዩነቶቻችንን ለጊዜው ወደጎን ትተን በጋራ መሥራት አለብን. . .›› ሲሉ የነበሩት በአገር ላይ ትርምስና ያልተገባ ጫና ለመፍጠር እንደነበርም በተለያዩ መገለጫዎች ታይቷል፡፡
ለዚህም ነበር በሁለቱ ታዋቂ ፖለቲከኞች ምክክርና የቴሌቪዥን ፐሮግራም ወቅቱ ብዙ ታዛቢዎች ልዩነቶቹን በግልጽ አውጥቶ በመነጋገር መፍታት ካልተቻለ፣ የግንኙነቱ ፋይዳ ምንድነው? ጃዋርና ልደቱ በጋራ የሚያሳኳቸው ዘላቂ ግቦች (Strategic Goals) ይኖራሉ? ወይስ የዓብይን መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ለማስገባት የሚፈጠር የትግል አጋርነት (Tactical Alliance) ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያነሱ የነበሩት፡፡
በእርግጥም የፖለቲካ ጋብቻ መፍጠር የተፈለገውና ጊዜያዊ ትብብሩ የታየው፣ ከዘላቂ ጥቅም ይልቅ በኋላ ለተከሰተው የንፁኃን ዕልቂትና የሀብት ውድመት በር የከፈተ ሴራ ለመዶለት ነበር የሚለው የመንግሥት ክስ ሲመረመር፣ የአገራችን ፖለቲካ ገና በሐሳብ ብልጫ፣ በብሔራዊ ጥቅምና በሕዝብ ደኅንነት ላይ ተመሥርቶ ለማደግ የሚችልበትን ደልዳላ መንገድ እንዳልያዘ አመላካች ነው፡፡
ያለ ሕጋዊነትና ቋሚ የፖለቲካ እምነት ደጋፊን በስሜት በማንጋጋት የሚመራ ፖለቲከኛ ሕዝቡስ ቢሆን እንዴት አምኖ ሊቀበለው ይችላል? የሚለው ተጠየቅም መልስ አላገኘም፡፡ ስለዚህ በያዝነው ዓመት ቢያንስ ቆም ብሎ ይህንን ዓይነቱን፣ የዓመታት ምልልስ የሰባበረውን መንገድ መፈተሽና ለሁሉም የሚመች ማድረግ ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡
ለዘለቄታው የብሔራዊ መግባባት ውይይቶችን ማጠናከር
ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የአገራችን ሕዝቦች ዋነኛ መገለጫ በብሔር፣ በሃይማኖትና አለፍ ሲልም በመንደር መፈላለግና መሰባሰብ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ይህን እውነት በፖለቲካ አደረጃጀት፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ (አክሲዮን፣ የሥራና ቤት ማኅበር. . .) ወይም በማኅበራዊ ጉዳዮች (የሰንበቴ ማኅበርና ዕቁብ ሳይቀር) ውስጥ ወለል ብሎ አሁን ድረስ እናየዋለን፡፡ ዛሬም እየኖርነው ነው፡፡ መካረሩ እየበረታ ሲሄድም አብሮ ለመኖርም እንቅፋት መሆኑ ግን መታየቱ አልቀረም፡፡
እውነት ለመናገር ሕወሓት ወይም ኢሕአዴግ ለከፋፍለህ ግዛው ሥልቱ ተፈጸሚነት፣ ይህን መለያየትና መብላላት ሲፈልገው ስለነበር የሕዝቦችን ልዩነቶችና መቃቃርን ሲያባብሰው ቆይቷል ይባል እንጂ፡፡ በብዙዎቹ አካባቢዎች ክልሎች፣ ልዩ ዞኖችም ይሁኑ ወረዳዎች በብሔር መደራጀታቸውና፣ በታሪክ አጋጣሚ ተዋልዶና ተሰናስለው ቢኖሩም ነባር ብሔረሰብ ያልሆኑና ኅብረ ብሔራዊ ሕዝቦችን የዴሞክራሲ መብት የደፈቀ፣ ያገለለ አካሄድ መትከላችን፣ ለመገፋፋቱ አመቺ የሆነ ትውልድ ሳይፈጥር እንዳልቀረ ይታመናል፡፡
ለአብነት ያህል የቀድሞ አገዛዞችን አይሉት፣ የሥርዓቱ ቁንጮዎች የወጡበትን የአማራ ማኅበረሰብ፣ በየአካባቢው እየዞረ አገር እያቀናና እየጠበቀ ሠርቶ፣ በማግኘቱና ከሌሎች ጋር ተባብሮ በመኖሩ አንዱ ብሔር ሌላውን እንዳጠቃ በመስበክ፣ ከዘመናት በኋላ ዛሬ ለጥቃት እንዲጋለጥ እየተደረገ መሆኑ ቁልጭ ብሎ የሚታይበት ዘመን መጥቷል፡፡
ያለፈው ሥርዓት ሆን ብሎ በሚመስል ደረጃ የብሔር ፍረጃን (ትምክህትና ጠባብነት) እንደ መለያያ ቆጥሮም አተራምሶት ነበር፡፡ ጦሱ ዛሬም በቀላሉ ሊነቀል እንዳልቻለም የምንመለከተው ነው፡፡ ገና መነሻው በኢትዮጵያ አሁን ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በልዩነት ውስጥ ጠንካራ አንድነት እንደሚፈጥር ተስፋ ቢጣልበት ውድቀቱ የሚመዘዘው፣ ከዚህ አብሮነትና አገራዊ አንድነትን ከማጥፋት ችግሩ ነው፡፡
ዘውግ ተኮሩ መንገድ በቀየደው አከላለል ምክንያት እስካሁን አወዛጋቢ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ተድበስብሰው በይደር በመቆየታቸው፣ ለአሁኑ ትውልድም ጭቅጭቅ አውርሶታል፡፡ እነዚህና መሰል የውዝግብና የመገፋፋት መንስዔዎች ሊፈቱ የሚችሉት ግን በጉልበትና በአመፅ ሳይሆን በውይይት፣ በፖለቲከኞቻችን መተማመን፣ ብሎም በጠንካራ ብሔራዊ መግባባት እንደሆነ መዘንጋት አይገባም፡፡
ለዚህም ነው በመንግሥትም ሆነ በተገዳዳሪ ኃይሎች መካከል፣ ራሱን ለብሔራዊ መግባባትና በቅንነት ለመነጋገር የሚዘጋጅ ፖለቲከኛ ሁሉ ቅድሚያ ወጥመዶቹን መነቃቀል ይኖርበታል መባሉ፡፡ መደማመጥና በተጨባጭም ለትውልዱ ዕርቅና አብሮነትን ለማውረስም መዘጋጀት ከሁሉም ኃይሎች የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ ተወደደም ተጠላም፣ ታሪክ ያሰባሰባቸውና ያስተሳሰራቸው ሕዝቦችን በፖለቲካ አጥርና ጎራ ተደብቀው እንዲጠዛጠዙ ከመፍረድ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ወቅታዊና ትልቅ ተግባርም ሊኖር አይችልም፡፡
ለዚህም በያዝነው ዓመት ፖለቲከኞች ከግልና የቡድን ፍላጎታቸውም በላይ አገርና ሕዝብን ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የቆየን ቁስል በማከክና የተዛባ ትርክት በማነብነብ ትውልድን ከማወዛገብ፣ የዕርቅና የመተማመን መንፈስ ብሎም የእኩልነትና ፍትሐዊ ተቋሚነት ባህልን ማስረፅም ይገባል፡፡ ከግትርነትና “እኔ ብቻ ልደመጥ” ከማለት ወጥቶም፣ የአገራችን ሕዝቦች የሚቀራረቡበትና የሚግባቡትን መሠረት መደልደልም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደ ብሔራዊ መግባባት የሚወስዱ ውይይቶችና ግንባታዎችን ማጠናከር ጠቃሚ ነው፡፡
ሙስናን እንዋጋ
በአሮጌው ዓመት ማገባደጃ ገደማ ይፋ የሆነው የአዲስ አባባ ከተማ የመሬትና የኮንዶሚኒየም ቅርምትና የሙስና መባባስ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ሰነባብተን ደግሞ ባለፉት ሦስት አሠርት ዓመታትም ሕገወጥ ገንዘብ በማሠራጨት ወንጀል በሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ ባለሀብት ተብዬዎችና ባለሥልጣናት እንደነበሩ መነገሩም አስደንጋጭ እውነታ ሆኖብናል፡፡ ይህ መሠረታዊ ችግርና የአገር ነቀርሳ ወደ ቀጣዩ ዓመት እንዳይሻገር መትጋት ነው ግድ የሚለን፡፡
በእርግጥ ሰው ሲበዛ መሬት ይጠባል፡፡ መንግሥታዊ አገልግሎትና አቅርቦትም ያንሳል፡፡ በዚህ ላይ ስግብግብነትና አልጠግብ ባይነት ሲበረታ ንጥቂያና የሌላውን ድርሻ ማግበስበስ ይባባሳል፡፡ ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳን በሃይማኖቶቻችንና በባህሎቻችን ፈሪኃ ፈጣሪና ጠንካራ ሞራላዊ ማንነት ያለን ቢሆንም፣ እየተሸረሸረ እየመጣ እንዳይመስል መጠንቀቅም አለብን፡፡
በተለይ በከተሞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያቆጠቆጠ የመጣው በአቋራጭ የመክበርና ሕግና ሥርዓትን በገንዘብ የመጠምዘዝ ድርጊት ፈር እያሳተን እንዳይሆን ያሳስባል፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላን. . .›› ከማበረታታትም በላይ የሄደ መስሏልና፡፡ እንደ ተገልጋይስ ከትንሿ የአገልግሎት ሠልፍ አንስቶ፣ እስከ ትልልቅ የኩባንያና ድርጅቶች የታክስና የጉምሩክ ሥራዎች ድረስ በጉቦ ለማስፈጸም የማይቋምጥ እስኪ ማነው? በእርግጥ አንዳንዱ ባለሥልጣን (ባለሙያ) ዓይኑን እያስለመለመ የ‹‹ስጡኝ›› ጥያቄውን በእጅ አዙር ሊያቀርብ ይችላል፡፡ እኛ ግን ስንቶቻችን ነን ‹‹ይኼ መብቴ ስለሆነ በዚህ ጊዜና መጠን አገልግለን›› ብለን በድፍረት የምንታገል?
ለነገሩ በገቢዎችና በጉምሩክ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግዥ ወይም በሽያጭ ጨረታ፣ በኢንቨስትመንትና በማዕድን ሥራ፣ በፈቃድ ዕድሳትና ብቃት ማረጋገጫ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈል. . . ሕገወጥ አካሄድን የሚከተሉ ባለጉዳዮች ሁሉ ጉቦ ካልከፈሉ ሕጉን እንደማይጥሱት ያውቃሉ፡፡ ለዚህም ሲባል ለድርድርና በእጅ ለመሄድ በራቸውን ክፍት ከማድረግ ባሻገር ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› እና ደላላ እስከ መቅጠር የሚሄዱ ጥገኞች በዝተዋል፡፡ ካለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ጊዜ ‹‹የፓራሹት ቱጃር›› ስለሆኑ ሰዎች መናገር አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ጉዳዩን በአርምሞ የሚታዘብ አንድ ወዳጄ ያስቀመጠልኝ ትዝብት ግን፣ አሁን ኢዜማ የተባለው የፖለቲካ ድርጅት ካወጣው መረጃም በላይ የሚያስደምም ነው፡፡ ዛሬ አዲሷ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቴሌቪዥን የሚናገሩትን ስናዳምጥ ደግሞ ተስፋ እንዳንቆርጥ ሆነናል፡፡
በመሠረቱ በእኛ አገር ሁኔታ አንዳንዶች በሙስና የሚዘፈቁት መኪና የለንም ብለው ይሆናል፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ ግን የረባ ጫማ እንደሌለው ነጋሪ አያስፈልግም፡፡ ኑሮ ከበደኝ፣ በልቼ ማደርና ልጆቼን በወጉ ማሳደግ ተሳነኝ እያለ ከሚማረረው ደሃ ሕዝብ ጉሮሮ ላይ እየነጠቁ መሆኑን ለማወቅ አስታዋሽ ሊያስፈልግ አይገባም፡፡ ሁሉም ህሊናው ሊመራው ይገባል፡፡
ሁላችንም እንደ ሰው ህሊናችንን ካልተጠቀምንበት እንጠፋለን፡፡ በጢሞቲዎስ 1፡19 ላይ እንደተጻፈ ‹‹. . .በጎ ህሊና ይኑርህ አንዳንዶች ህሊናን ጥለው መርከብ አለመሪ እንደሚጠፋ ጠፍተዋልና›› ይላል፡፡ የገንዘብ ወይም የሥልጣንም ጥም እንዲህ በቀላሉ የሚቆርጥ አይደለም፡፡ በጠጡት ቁጥር አምጡ አምጡ ጨምሩ ጨምሩ ይላል፡፡ ይሉኝታንና ንፁህ ህሊናን ያሸጣል. . . የገንዘብ ባሪያ ያደርጋል. . . ለገንዘብ ለጣዖት እንድንሰግድ ያደርገናል. . . በታላቁ ሰብዓዊነታችን ላይ ያላግጥብናል. . . በዙሪያችን ያለውን ዓለም ረስተን በሕዝብና በፈጣሪ ፊት የተዋረድን እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ስለዚህ በፍፁም መገታት ያለበት የአገር ነቀርሳ ነው ሙስና፡፡
እርግጥ በአሁኑ ሁኔታ በግሌ አገሪቱ በሙስና ተወርራለች፣ ታንቃለች፣ ታፍናለች የሚል ተስፋ የቆረጠ አቋም የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ለሦስት አሠርት ዓመታት ሲንከባለል የመጣው የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር በቀላሉ የሚታይ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ላይ የፖለቲካ ኢፍትሐዊነት አዝማሚያና የአሻጥር ምልክቱ በፍጥነት ካልተገራ አገር ይዞ የሚጠፋ ነውና አሁኑኑ መቆም አለበት፣ የግድም ነው፡፡
እንግዲህ የዛሬውን ጽሑፍ ለማጠቃለል በአዲሱ ዓመት በርካታ የሕዝብና የመንግሥት ኃላፊነቶችና ግዴታዎች ቢኖሩብንም፣ ዋና ዋና ያልናቸውን ለውይይት መነሻ በሚሆን መንገድ ጠቃቅሰናል፡፡ ሌሎች አንባቢያንና የጋዜጣው ተሳታፊዎችም በየራሳቸው ዕይታ እንደሚያክሉበትም እምነቴ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡