በአሰፋ አደፍርስ
የቤተ መንግሥት ነባር ተሽከርካሪዎች ለሕዝብ ዕይታ ይፋ እንደሚደረጉ ሰማን፡፡ የሰማነውን ማወደስ መልካም ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በየቦታው ስለሚናፈሰው የወሬ ውዥንብር በመገረም፣ የማውቀውንና የማስታውሰውን ያህል ግራ ለተጋባው የወሬ አዝማች ለማካፈል አስቤ ነው። በመጀመርያ መኪኖቹ በገንዘብ ተገዝተው የመጡ ሳይሆኑ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታላቅነትና ግርማ ሞገስ የጎበኙዋቸው የወዳጅ አገሮች መሪዎች በስጦታና በዕርዳታ የሰጡዋቸው ናቸው፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የዕንግዳ መቀበያና መሸኛ፣ የንጉሠ ነገሥቱ መገልገያ ሆነው በክብር የተቀመጡ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ ደርግ በጨረታ የሸጣቸውም ነበሩ፡፡ አንድ የማስታውሰው አንድ ስቱድባከር፣ አንድ ኦልድስ ሞቢል፣ አንድ ቼቭሮሌት፣ አንድ ክራይስለር፣ እንዲሁም አንድ ዶጅ መኪኖች በጨረታ ደርግ ለአሜሪካን ኤጄንት እንደሸጠ አስታውሳለሁ። ሌሎችም ነበሩ፡፡ ያላየሁትን ልመሰክር ግን አልፈልግም።
ከላይ የጠቀስኳቸውን መኪኖች የገዛው አሜሪካዊ አንድ መኪና በአሜሪካ ሊገዛ በማይችልበት ዋጋ ሁሉንም መኪኖች ገዝቶ ወደ አሜሪካ በመውሰድ፣ ‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› የሚለው የዘውድ ምልክት እንኳ ሳይነሳ በሚሊዮኖች እንደ ሸጠና በአንድ ሌሊት ሚሊየነር እንደተባለ ጭምር አስታውሳለሁ። ወደ ቁምነገሩ ልመለስና መኪኖቹን እነማን በስጦታም በዕርዳታም እንደ ሰጡ ላስታውሳችሁ።
ከአሜሪካ
ንጉሠ ነገሥቱ የሚገለገሉባቸው ሁለት ካዲላክ ላሜዝን፣ ሁለት ስቱድባከር፣ አምስት ክራይስለር፣ ሰባት ኦልድስ ሞቢል፣ እንዲሁም 14 ሼቭሮሌት ፒክ አፕ ጭምር በነፃ የተሰጣቸው ነው።
ከእንግሊዝ
ሦስት ሮልስ ሮይስ፣ አምስት ጃጉዋር፣ 16 አውስቲን፣ ሁለት ቤድፎርድ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱን ሮልስ ለመጀመርያው የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሥ ሳዑድ ሰጡ፡፡ እንደ ዛሬ አገራቸው ባልበለፀገችበትና ታላቅ ቁምነገር ውስጥ ባልገባችበት ዘመን አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ‹‹ንጉሥ ነህና በተራ መኪና አትሂድ›› ብለው ሰጥተዋቸው ነበር። በዚህም መነሻነት ንጉሥ ሳዑድ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የተባረከችና የተባረከ መሪ ያላት፣ በተፈጥሮ የበለፀገች አረንጓዴና ሁላችንንም አጠቃልላ ልታስተዳድር የምትችል አገር ነች፣ አላህ እስከ ወዲያኛው ይባርካት›› ብለው ከተናገሩት በአጭሩ ነው ያስቀመጥኩት። የዛሬውን አያድርገውና ኢትዮጵያ በዓረብ አገሮች በሙሉ መንፈሳዊ አገር እንደሆነችም ትቆጠር ነበር። ዛሬ የኢትዮጵያ ልጆች መድረሻ አጥተው ወደ እነዚህ አገሮች እየተሰደዱ እንደ ሰው ሳይታዩ መቅረታቸው፣ እኛ የዛሬዎቹ ትውልድ በሠራነው የቁልቁለትና የቅሌት ጉዞ መሆኑን መረዳት ለሚሻ የተሻለ ምሳሌ ነው።
ከጀርመን
ሦስት መርሲዲስ ሊሞዚኖች ለንጉሡ መገልገያ ስድስት በር ያላቸው፣ 12 መርሰዲሶች ለእንግዳ መቀበያ፣ ሦስት መርሰዲስ ዩኒሞግ ለበረሃና ወጣ ገባ መንገዶች የሚያገለግሉ፣ እንዲያው አይታወቅም ብዬ ሳይሆን ለማስታወስ ያህል ነው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በእንግሊዝና በፈረንሣይ ላይ ጀርመን ያደረገችውን ደባ አታውቁም ብዬ አልገምትም፡፡ ነገር ግን ለማስታወስ ያህል በሠራችባቸው ተንኮል ምክንያት ከታላቅነት ወርዳ ከአውሮፓ አባልነትም ተሰርዛ ወደ ድህነት ማቅ ገብታ ሳለ፣ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከተቀያየመቻቸው ታላላቅ መንግሥትታት ጋር አስታርቀውና ለችግረኞች ጀርመኖች በኢትዮጵያ የተሠራ የብርድ ልብስና ገንዘብ መመፅወታቸውን ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ያውቁት ይሆን? መቼም የኢትዮጵያ ምሁራን ምንም አይሳናቸውምና ያውቃሉ ብዬ አምናለሁ።
እንዲያው ለማስታወስ ያህል ወጣቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩትን የጆን ኤፍ ኬኔዲ ምስክርነት እዚህ ላስፍርና ላስታውሳችሁ ብዬ ነው። ‹‹Emperor Hailesilassie was the first head of State to visit West Germany after the end of the World War 2nd the Emperor’s visit signaled the acceptance of West Germany, back in to the World as a peaceful nation. He donated Blankets manufactured in Ethiopia to the War Ravaged German People.›› ይህ እንግዲህ ቀንጨብ አድርጌ ያቀረብሁት እንጂ ሙሉውን ፕሬዚዳንትን ኬኔዲ የተናገሩት አይደለም። ጊዜ ለመቆጠብ ነው። ከፈረንሣይ
ፈረንሣይም ስጦታ አበርክታለች፡፡ ግን ቁጥሩንና የመኪኖቹን ዓይነት ስለማላውቅ ነው፡፡ ምናልባት ሲትሮይን መኪኖች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ለፖሊስና ለወታደር አገልግሎት በዕርዳታ መልክ የተሰጡትን ሳይጨምር ነው። እንደሚታወቀው በብዛት የፖሊስ መኪኖች ላንድሮቨር ከእንግሊዝ፣ ቮክስ ዋገን ከጀርመን፣ እንዲሁም ለአዛዦች መርሰዲሶች ከጀርመን በነፃ ነበር የሚሰጡት። ታላላቅ የወታደር ማመላለሻ ካሚዮችንም ከግንዛቤ ማስገባት ያሻል።
በዕርዳታ መልክ የተሰጡት በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደነበሩ የታወቀ ነው። ታዲያ ዛሬ ንጉሡ ከደሃው አፍ እየነጠቁ መኪና ሰበሰቡ የሚለው አሉባልታ ‹ሳያጠሩ ‹ወሬ ሳይገድሉ ጎፈሬ› እንዳይሆን መጠንቀቁ ይበጃል። ወሬ ለማስመር መሽቀዳደም በወገን መካከል ብዥታ ከመፍጠርና ያለ ምክንያት መቀያየምን እንዳያስከትል ‹ነገር ከሥሩ ውኃ ከጥሩ› የሚለውን የአባቶች ብሂል ብንከተል የተሻለ ይሆናል።
ለአውራ ጎዳና ባለሥልጣን በዕርዳታ መልክ በሺዎች የሚቆጠሩ የጠጠር ገልባጭና ፒክ አፕ የፎርማኖች ማመላለሻዎች፣ ጂኤምሲ የተባሉ ገልባጭ፣ ግሬደር፣ ቡል ዶዘር፣ ስካቫተርና ሌሎች ለመንገድ ሥራ የሚጠቅሙ መሣሪያዎች ከደሃው አፍ ተነጥቀው የመጡ ናቸው የሚል አለ? ካለ እስኪ ብቅ ይበል፡፡ ወይስ ኢትዮጵያ በዚያን ዘመን በነበራት የኢኮኖሚ አቅም ይህንን ሁሉ ችላ ገዛች ለማለት ይሆን? እንዲያው የኢትዮጵያን ጉዳይ ከመሠረቱ ካለማወቅ ነውን? ለማወቅ መጣሩ የተሻለ ስለሚሆን ስም ለማጠልሸትና ወሬ ለማሳመር ብቻ ባንከንፍ መልካም ኢትዮጵያዊ ያደርገናል። ዳሩ ምን ያደጋል በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በብሔር ስለሆነ ሁሉም ነገር መላቅጡ የጠፋበት ዘመን ላይ ነን፡፡ እግዚአብሔር ልብ ሰጥቶን ወደ ልቦናችን እስክንመለስ ድረስ ባለንበት ሆነን ለእውነት መቆም ይኖርብናል። ልቦናም ይስጠን፡፡ በወሬ ናዳ መሸበርና ማሸበር ‹ላሞች ባልዋሉበት ኩበት ለቀማ› መሆኑ ነው።
መቼስ ምን ይደረግ ባለፉት ከ80 በማይበልጡት ዓመታት ውስጥ ትምህርት ቤት ከፍተው፣ ደሃና ጌታ፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ወይም ከምባታ ሳይሉ ሁሉም እኩል እንዲማሩ አድርገው ዓይን በከፈቱ ውለታ ሲገባቸው አቃቂር ሆነ ካሳቸው። ይህ ከሆነ በየአገሩ የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝተው ተልከው የተማሩ ሰዎች ለምን ተበራከቱ ተብሎ ወቀሣ ሳይነሳ አይቀርም፡፡ በተራድኦ ንጉሠ ነገሥቱ ባገኙት ጥቅምና የአገር ልማት የሚወቀሱ ከሆነ፣ ባደረጉት መልካም ሥራ ሁሉ ይወቀሱና ከማዕዱ የተሳተፈ የዛሬ ወጣት ሁሉንም ጨምሮ ለመክፈል ወይም ለመወቀስ ይዘጋጅ ለማለት ነው።
ያለፈን ካልወቀስን መሥራት ወይም መሻሻል አንችል ይሆን? ለምን ከሠለጠኑ አገሮች ምሳሌ ክፉ ከፉውን ሳይሆን ደግ ደጉን አንቀላውጥም? ቋንቋቸውን በጥራዝ ነጠቅነት ተውሰን በቋንቋችን ላይ ተቀጥላ በማድረግ መናገር የአዋቂነት ምልክት የመሰለን፣ የእነሱን ሥርዓት ያጣ አለብባበስ እንደ ቁምነገር የወሰድን፣ ከእነሱ የፈረሰኞች አለባበስ ከጉልበት በታች አጥብበን የመልበስን ዘይቤ ለምን እንደሚያደርጉት እንኳ ሳናውቅ የምን ውርስ ይሆን? ተራው ሰው ብቻም ሳይሆን እስከ መሪዎች ድረስ የአለባብበስ ኮድ እንኳ የማናውቅ ትውልድ አንዴት ነው አገር የምንመራው? ሁሉ መሪ መሆን ፈለገ፣ ማነው ተመሪው? ፊደል የቆጠረ ሁሉ ሊቅ ተባለ፣ ታዲያ ማን ነው ሊቅ ያልሆነ ተመሪ?
ልብ በሉ አገር ጨዋታ አይደለም፣ አገር ክብር ነው፣ ሞገስ ነው፣ አለኝታ ነው፣ ተው ልብ እንግዛ። የጊዜውን መሪ አክብሩት፣ ግን መልዓክ አታድርጉት። ዘመኑን ጨርሶ ካልተመረጠ ለአገለገለበት ዘመን አመሥግኑት። በወረደ ቁጥር መውቀስን፣ በተሾመ ቁጥር ማሞገስን ልምዳችን አናድርገው። ወኔና ተመክሮ ይኑረን፣ ወጣቱን በጥሩ ሞራል እንዲራመድ እንምራው፣ ለክፋት ፈር አንቅደድለት።
ሰላም ለሁላችን! አሜን!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ የሕይወት ጉዞአቸውን የተረኩበት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡