ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ለመፍጠር እንደ አገር ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ የሚታየውን፣ በጥሬ ገንዘብ የሚደረግን ግብይት ለመግታት በመንግሥት ደረጃ እየተወሰዱ ካሉት ዕርምጃዎች ባሻገር፣ የፋይናንስ ተቋማት የዲጂታል የባንክ አገልግሎቶቻቸውን በማስፋት ከፍ ያለውን ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይታመናል፡፡
በኢትዮጵያ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት እጅግ አነስተኛ ሽፋን ያለው ቢሆንም፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት ባንኮች ወደዚህ ወሳኝ የሆነ አገልግሎት መግባት ግድ ይሆንባቸዋል፡፡
ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን ለመተግበር እየተንቀሳቀሱ ካሉት ባንኮች መካከል ዳሸን ባንክም አንዱ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከተገበራቸው የካርድ አገልግሎቶች የተለየ ያለውን የግብይት የስጦታ ካርድ ባለፈው ቅዳሜ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡ ይህንን አዲስ የግብይት ካርድ የተገበረው በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ከሚገኙት ኩዊንስ ሱፐር ማርኬትና ሆምዲፖት ጋር በመሆን ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሽያጭ ያከናውናሉ በሚባሉት ሁለት ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ ማንኛውም ግብይት ለማድረግ የሚያስችል ክፍያ መፈጸሚያ ካርድ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ይህ የግብይት ካርድ ጦር ኃይሎች አካባቢ በሚገኘው ኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ቅጥር ግቢ ውስጥ ይፋ በተደረገበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ እንደገለጹት፣ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት አማራጭ የሌለውና መጪው ጊዜ ከዚሁ ቴክኖሎጂ ጋር በመተሳሰሩ በመንግሥት ደረጃ የተቀረፀውም ስትራቴጂ ይኼው በመሆኑ ባንካቸው በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ የበለጠ መሥራቱን እንደሚገፋበት አስታውቀዋል፡፡
በካርዱ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ንገድና ኢንዱስትሪ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ ዩሱፍ እንዳመለከቱት፣ የንግድ እንቅስቃሴ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ሚና እንዲጫወት ከተፈለገ፣ በቴክኖሎጂ መደገፍ አማራጭ እንደሌለው በመግለጽ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን የሚያስቀሩ የክፍያ አማራጮች እንዲጎለብቱ የከተማው አስተዳደር ይተባበራል፡፡
ሌሎች ተቋማትና ድርጅቶች ይህንን ፈለግ ይከተሉ ዘንድም ኃላፊው አሳስበዋል፡፡ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው ኩባንያቸው ይህንን ዘመናዊ አሠራር ከመተግበር ባለፈ ሱፐር ማርኬቶችን ለማስፋፋት ትልቅ ውጥን ለማሳካት ጭምር የሚያግዝ በመሆኑ ነው፡፡
የዲጂታል ባንክ አስፈላጊነት ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አስፋው እንደ አገር በገበያ ሥርዓቱ ላይ ካሉ ተግዳሮቶች አንዱ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ በመሆኑ ባንካቸው ለዲጂታል የባንክ አገልግሎት ትልቁን ሥፍራ ሰጥቶ እንደሚሠራና በዕለቱ ይፋ የተደረገው የካርድ አገልግሎት መጀመር ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የወደፊት የባንክ ህልውና የሚመሠረተው፣ እንዲሁም የወደፊቱ የአገሪቱ የክፍያ ሥርዓት መሠረት የሚሆነው ዲጂታል ሥርዓት እንደሚሆን ባንካቸው ያጤነው ጉዳይ መሆኑን አመልተዋል፡፡ የፋይናንስ አካታችነትን ወደ መሬት ከማውረድ አኳያ በአገር ደረጃ በብሔራዊ ባንክ የወጣና በባንኮች ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ስትራቴጂ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ይህ መሠረታዊ ነው፡፡ ዋናው ፈተናችን ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የገንዘብ ንክኪን ከመቀነስ ካሽለስ ሦሳይቲን ከመፍጠር አንፃር ለደንበኛው ዓይነተኛ አማራጭ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
ከተገልጋዮች አንፃርም የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ግብይት መፈጸም ሊያስገኝ የሚችለውም ጥቅም እንደሚኖር ባለሙያዎች በሰፊው ተብራርቷል፡፡ እንደ ምሳሌም ከ30 እና 40 ሺሕ ብር በላይ የሆነን ዕቃ ለመግዛት ያን ያህል ገንዘብ ተሸክሞ መሄድ በራሱ ለተገልጋዩ አደጋ ያለው መሆኑ አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ይህንን አደጋ ከደንበኞች ላይ የሚያስወግዱ እንደሚሆኑም ተጠቅሷል፡፡
የዳሸን የግብይት ስጦታ ካርድ አንዴ በስጦታ ከተሰጠ በኋላ ስጦታ ተቀባዩ ወስዶ የሚጥለው ባለመሆኑና ካርዱን እንደገና አስሞልቶ መጠቀም የሚያስችል ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ማንኛውም ይህንን ካርድ ከአንድ ሺሕ ብር ጀምሮ በመግዛት መጠቀም የሚችል ሲሆን፣ አጠቃቀሙም ቀላል ስለመሆኑ የሚያመለክተው ባንኩ ተጨማሪ አገልግሎቶችን የሚሰጡና ከጥሬ ገንዘብ ለመላቀቅ የሚያግዙ የተለያዩ አገልግሎቶችን ወደ ገበያ ይዞ እንደሚመጣ ዳሸን ባንክ አስታውቋል፡፡ ይህ አዲስ ካርድ የብድር አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋልም ተብሏል፡፡ እንደ አገር በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ ግብይቱን ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ካርዱ ለመጠቀም ቴክኖሎጂውን ሥራ ላይ ለማዋል ሲባል ለሌሎች ኩባንያዎችም የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኩባንያዎች ከባንክ ጋር የሚሠራው የካርድ ግብይትን ሲተገብሩ ራሳቸውን የበለጠ ለመግለጽ የሚረዳና የሽያጭ መጠናቸውን የሚጨምር ነው ተብሏል፡፡
ከኩዊንስና ሆምዲፖት አንፃር ይህ ካርድ ሲዘጋጅ ሽያጫቸውን ከፍ እንደሚያደርግና አዳዲስ ደንበኞችን እንዲያፈሩ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ይህም እርግጥ ስለመሆኑ በምክንያት የሚጠቀሰው የካርዱ መገለጫ በስጦታ የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡ እንደ ስጦታ የሚሰጥን ካርድ ደግሞ በስጦታ የወሰደው ደንበኛ በዚህ የስጦታ ካርድ ለመሸመት ወደ ሱፐር ማርኬቶቹ የግድ የሚሄድ በመሆኑ ያለጥርጥር የኩባያዎቹን ገበያ ከፍ ያደርገዋል ብለው ኃላፊዎቹ ያምናሉ፡፡
ሜድሮክ ኢትዮጵያ አንፃር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህን ዘመናዊ ሱፐር ማርኬቶችን ለማስፋፋት የያዘው ዕቅድ ደግሞ የካርድ አገልግሎቱን ያሰፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሜድሮክ ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል እንደገለጹትም፣ ኩባንያቸው ይህንን ሥራ ዓለም አቀፍ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው በአሁኑ ወቅት ካሏቸው አራት የሽያጭ ማዕከሎች በተጨማሪ ሌላ አምስት ትልልቅ የሱፐር ማርኬት ማዕከሎችን በቀጣዩ ሦስት ወራት ተከፍተው ሥራ ይጀምራሉ ብለዋል፡፡ በቅርቡም ናኒ ሕንፃ ላይ አንድ ሱፐር ማርኬት የሚከፍት ሲሆን፣ ቃሊቲ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ውስጥ ሠፈረ ሰላም ላይ ይከፈታሉ፡፡ ብሥራተ ገብርኤል ጋር ያለው ማዕከልም በዘመናዊ መልክ ተቀይሮ የሚጀመር ሲሆን፣ እነዚህ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ለገበያ ክፍት ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት በተመሳሳይ 13 ለአገልግሎት የሚበቁ የግብይት ማዕከሎች በአዲስ አበባ ሥራ ይጀምራሉ፡፡ በ2014 ዓ.ም. ደግሞ በክልል ዋና ከተሞች ላይ እንዲህ ያሉ ፋሲሊቲዎች የሚያስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ገለጻ በእነዚህ ሱፐር ማርኬቶች እይቀረቡ ያሉ ምርቶች ከሌሎች ገበያዎች በቅናሽ እየተሸጡ መሆኑን የተመለከተ ሲሆን፣ በተለይ በኩዊንስ ሱፐር ማርኬት መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ዋጋ ተመጣጣኝ እንደሆነ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ የሚድሮክ የሥራ ኃላፊዎች ይህንን በማድረግ ገበያ በማረጋጋት ረገድ የድርሻቸውን ለመወጣት እየጣሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚድሮክ እንዲህ ያለውን ሥራ የሚሠራው በችርቻሮ ገበያ ያለውን የዕዝ ሰንሰለት አሳጥረው የሚሠሩ አገሮች የደረሱበት ለመድረስ ጭምር መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በዓለም ላይ እንደሚታወቁት እንደ ዎልማርት ቴስኮና የመሳሰሉ የዓለም ገበያን የተቆጣጠሩ ኩባንያዎች ሁሉ ሚድሮክም በኢትዮጵያ ገበያውን እንቆጣጠራለን ስንል ተወዳዳሪ ለማጥፋት ሳይሆን ለሸማቾቻችን ተደራሽ፣ ተወዳደሪና ተመራጭ ለመሆን የምናደርገው ጥረት አካል ነው በማለት ኩባንያው በዚህ የቢዝነስ ዘርፍ ያለውን ረዥም ዕቅድ አመክቷል፡፡ በእስካሁኑ ሒደት የማምረቻ ድርጅቶቻችንንም ይዞ የሚጓዝ በመሆኑ የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ እየተደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ በብርቱካን፣ ወተት፣ ሥጋና እንቁላል ግብይት ሸማቹን የማስደሰት ሥራ ስለመሠራቱን አስታውሰው በበጀት ዓመቱ በሜድሮክ ትልልቅ ይዞታዎች ላይ ለሚገነቡት በቀላሉና እየተገነቡ ያሉ ተመሳሳይ መደብሮች የግንባታ ሲታከል ብዙዎችን የመድረስ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ግንባታዎችን ጨርሶ በተለይ ለመግባት 350 ሚሊዮን ብር በጀት እንደፀደቁም ተገልጿል፡፡
የሚድሮክ የንግድና ሰርቪስ ሴክተር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በቀለ ቡላዳ (ዶ/ር) እንደገለጹትም፣ ሜድሮክ ለውጥ ካደረገ ወዲህ እየተገበራቸው ካሉት ወሳኝ ጉዳዮች አንዱ የእርሻም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶችን የመጨረሻ አጭር በሚባል የግብይት ሰንሰለት ለተጠቃሚው እንዲደርስ ማስቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም በማምረት ሒደት የተለፋበትን ምርት ከራሳችንና ከአጋሮች የእርሻ ማሳ በተመጣጣኝ ዋጋ ለደንበኞቻችን ማቅረብ እየተቻለ ስለመሆኑና በተለይም በአዲስ አበባ መሠረታዊ በሚባሉ ምርቶች ላይ የሠራውን ሥራ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
ገበያን ከማረጋጋት አኳያ በሰፊው በተሠራው ሥራ ውጤት እየተገኘ ስለመሆኑ አመላካች ነው ብለው የጠቀሱት ከሚድሮክ ከለውጡ በኋላ የተከተሉት ስትራቴጂ የካውንስልና የሆምስዲፓታ ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር መደረጉ ነው፡፡ ለንፅፅር ያስቀመጡትም ሱፐር ማርኬቶች በሰኔ 2012 ዓ.ም. እና በመስከረም 2013 ዓ.ም. ሱፐር ማርኬቱን የጎበኙ ደንበኞችን ቁጥር ነው፡፡ በሰኔ ወር የኪውንስ ሱፐር ማርኬቶችን የጐበኙ የደንበኞች ቁጥር 53,000 የነበረ ሲሆን፣ በመስከረም 30 (እ.ኤ.አ) ግን 270,000 መድረሱ ነው፡፡
ድግግሞሹ እንደተጠበቀ ሆኖ በመስከረም ወር በአዲስ አበባ ከሚኖረው ቤተሰብ 27 በመቶው የካውንስ ሱፐር ማርኬትን እንደጐበኘ የሚሳይ መሆኑንም ዶክተር በቀለ ገልጸዋል፡፡
ሚድሮክ ኢትዮጵያ በዚህ የቢዝነስ ዘርፍ ገበያውን ለማስፋት የያዘው ውጥን በአገር ውስጥ ብቻ የተወጠነ ባለመሆኑ ከዳሸን ባንክ ጋር በመሆን የጀመረው ሥራ ድንበር ተሻግሮ ለሚሠራው ሥራ አጋዥ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ሥራ ባሻገር ዛሬ የምንጀምረው የዲጂታል ፔይመንት ሥራ ደግሞ የዘመናዊነታችን መገለጫችን ይሆናል ያሉት በቀለ ዳሸን ባንክ ብዙ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ፋና ወጊ ሆኖ የቀጠለ ትልቁ ፓርትነራችን ሆኖ ይቀጥላል ተብሏል፡፡ በሚድሮክ ውጥን መሠረት በአፍሪካ ነፃ ገበያን ለመፍጠር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሚድሮክ ኢትዮጵያ በእነዚህ የሽያጭ ማዕከሎች በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ይሠራል ተብሏል፡፡