በነሲቡ ስብሐት (ሰሜን አሜሪካ፣ ቨርጂኒያ)
ክፍል አንድ
- የመጽሐፉ ርዕስ፡ “ዳኛው ማነው?” የብርሃነ መስቀል እና የታደለች ሕይወት
በኢሕአፓ የትግል ታሪክ
ደራሲ፡ ታደለች ኃይለ ሚካኤል
የኅትመት ዘመን፡ 2012 ዓ.ም.
ገጽ ብዛት፡ 442
- የብርሃነ መስቀል የእሥር ቤት ቃል ምርመራ
ሰኔ 1971 ዓ.ም.
ታሪክ ያለው ይጻፍለታል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል ታሪክ ኢሕአፓ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ስለኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ ስለየካቲት 1966 አብዮት፣ ስለመሬት ለአራሹ፣ ስለዲሞክራሲያዊ መብት፣ የብሔር ጥያቄ፣ የሕዝብ መንግሥት ሲነሳ፣ ሲጻፍ፣ ሲነገር ኢሕአፓ ባለ ሁለት ነጥብ ነው፡፡ ኢሕአፓ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጎኑ በተለያየ መልኩ ተጽፏል፣ ተነግሯል፡፡ ኢሕአፓ ሲባል ወጣቶች ውቅያኖሱ ናቸው፣ እናት አባቶች በልጆቻቸው ታሪክ ተቋድሰዋል፣ ታዳጊ ሕፃናት ወላፈኑ አግኝቷቸዋል፡፡ ስለኢሕአፓ ሲነገር ሕዝብ፣ ዓላማ፣ ፅናት፣ ትግል፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ኪነት የመሳሰሉት ስለሚነገሩ ተወርቶ አያልቅም፡፡ አፈሳው፣ እስሩ፣ ግርፊያው፣ ግድያው፣ ስደቱ፣ መቆዘሙ፣ ጀግንነቱ፣ መስዋዕትነቱ፣ ደፋርነቱ፣ አጅሃብ! እስኪያሰኝ ይደመጣል፣ ይነበባል፡፡ ፍርኃት፣ ቀላባጅ፣ አስመሳይ፣ ወሬኛ የራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፡፡
ኢሕአፓ በኢትዮጵያ የትግል ታሪክ አምባገነንነትን የተፋለመ፣ ተፋልሞ የተደበደበ፣ ተደብድቦ የተሰናከለ፣ ተሰናክሎ ታሪክ የሠራ ቀዳማይ ፓርቲ ነው፡፡ የኢሕአፓ ታሪክ ለትግል መሠረት ነውና ሁሉም ይጠቅሰዋል፡፡ ስለኢሕአፓም ሆነ ስለያ ትውልድ ዘመን ጸሐፊዎች፣ ተራኪዎች፣ ቲያትር ሠሪዎች ሁሉም በትክክል ዘገቡ ወይስ አዛቡ ብሎ መቃኘት በተለይ የዘመኑ አባላት ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ ዝም ከተባለ ቀጣይ ትውልድ የሚከራከርበት፣ የሚጠቅሰው ሞጋች ሐሳብ ያጣልና፡፡ የእኛ ሕይወት ዘለዓለማዊ እንዲሆን ከፈለግን ትውልድ ይመራመርበት፣ ኖ! ይህማ ልክ አይደለም ይልበት፣ ትምህርት ይቀስምበት ዘንድ አሻራችንን ታሪኩ ላይ ማዋል ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
መንግሥቱ ኃይለ ማርያም “ትንኝ ገድዬ አላውቅም” ሲል በመቶ ሺሕ የሚቆጠረውን የትውልድ ፍጅት በሁለት መጽሐፍና በዘጋቢ ጸሐፊው አማካይነት ካደ፣ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ሽምጥጥ አድርጎ በትውልዱ ተሳለቀ፣ ካደ፣ ፍሥሐ ደስታ በይቅርታ ስም ትውልዱን አንቋሾ ካደ፣ ሌሎችም ካዱ፣ ትረካቸው ለነፍሳቸው አደላ፡፡ መጽሐፈ ቀይ ሽብር ዘ መኢሶን ካደ፣ በምስክርና በሰነድ ወንጀለኝነታቸው የተረጋገጠባቸው እንደ ቀልቤሳ ነገዎ፣ ከፈለኝ ዓለሙ ዓይነቶች እንደካዱ ወደ እስር ቤት ተወረወሩ፡፡ ‹‹የዘንድሮ ጅብ የሚያውቁት አገርም ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላልና›› የትናንት ወንጀላቸውን ደብቀው ዛሬ ስለዲሞክራሲ መብትና ስለሕዝብ ብሶት መድረኩን ያጣበቡ የዕድሜ ባለፀጋ ባለ ነጭ ፀጉሮችና ፀጉር አልባዎች ምን ያህል ልባቸው ለጭካኔ ቢደነድን ነው ፀፀትን የዘነጉት ያሰኛል፡፡
“ዳኛው ማነው?” መጽሐፍን ከሥነ ጽሑፍ አንፃር ለመገምገም ሙያውም ችሎታውም የለኝም፡፡ የታሪኩ መጠነኛ ተቋዳሽ ብሆንም ሁሉንም አውቃለሁ ብዬ አልንቦራጨቅም፡፡ ማንበብ፣ ማድመጥ ማወቅ ነውና ነበርን ከሚሉት ያላነሰ ታሪክን የሚዘግቡ፣ ለትውልድ የሚያስተላልፉ መኖራቸውን ያህል በመጠኑም ካገላበጥኳቸው፣ ዕድሜ የሰጠኝን ግንዛቤ በመጠቀም የዛሬዋ አምባሳደር፣ የትናንቷ ጓዲት ታደለች ኃይለ ሚካኤል መጽሐፍ ኢሕአፓን በሰፊው ስለሚነካ የተሰማኝን፣ የገባኝን፣ የኮረኮረኝን፣ ያስተከዘኝን፣ ያስቆጨኝን፣ ወይ ኢትዮጵያ! ወይ አገሬ! አይ ኢሕአፓ! እና ሌላም ያሰኘኝን ላስነብባችሁ ወደድሁ፣ ፈለግሁ፡፡
“ዳኛው ማነው?” በቅርብ ቀን በገበያ እንደሚውል ማስታወቂያ ስመለከት ከርዕሱ የመጽሐፉን መልዕክት ጠረጠርሁ፡፡ ያም ሆነ አንድ መጽሐፍ ሳይነበብ፣ የአንድ ሰው ቃለ መጠይቅ ሳይደመጥ ትችት አይሰጥምና በጉጉት የተጠባበቅኩት መጽሐፍ እጄ ገብቶ ወረድኩበት፡፡ መጽሐፉን ገና ሳላነበው አምባሳደር ታደለች በትግል ያገኙትን የወጣትነት ፍቅረኛቸውን፣ በውጭ አገር፣ በአገር ቤትና በእስር ቤት ያወላለድ ታሪክ ያላቸውን የሦስት ልጆቻቸውን አባት ብርሃነ መስቀል ረዳን በኢሕአፓ በተሰጠው “የአንጃ መሪ” ተቀፅላ ሊከላከሉ እንደሚችሉ ገምቻለሁ፡፡ ግና በምን መልኩ? በአሳማኝ ነጥቦች በማስቀመጥ፣ ነገሮችን ግራ ቀኝ በመመልከት? ወይስ እንደ አንዳንድ ጸሐፊና ተናጋሪዎች በሆነው ባልሆነው ኢሕአፓን ጥላሸት በመቀባትና በማንቋሸሽ? በሌላ መልኩ ጥርጣሬም ቢኖራቸው የማያውቁት ላይ ድምዳሜ ከመስጠት ተቆጥበው የኢሕአፓውን መሥራች ብርሃነ መስቀል ረዳ ባህሪ፣ ችሎታና፣ አስተሳሰብ አስታከው በተሸፋፈነና ግልጽ ባልሆነ መልኩ የተደረሰበት የአንጃ ፍረጃን የሚያውቁትን አስቀምጠው “አንባቢ ሆይ! እናንት ፍረዱኝ” በሚል በሩን ከፍተው፣
‹‹ከስህተታችን እንድንማር ለጊዜያችን ዳኝነት ለመስጠት ሁሉም በየራሱ ቡድንና ድርጅት የተከሰተውን ችግር ነቅሶ በማውጣት ችግሮቹን እንዳሉ መቀበል፡፡ ተነቅሰው የወጡትን ችግሮች ልዩነታቸውንና ተመሳሳይነታቸውን በመገንዘብ ብሔራዊ ተግባቦት ለመፍጠር መትጋት ያስፈልጋል፡፡›› (ዳኛው ማነው? ገጽ 424) በሚል ያቺ ለሞት የታጨች የያ ትውልድ ወጣት እንደስሟ ታድላ ዛሬ ላይ ሆና አንቱ ልበልና አስነብበውናል፡፡
የመጽሐፉን የመጀመርያ ምዕራፍ አንድ የመጀመርያ ዓረፍተ ነገር አንብቤ ሦስት ገጽ እንደተጓዝሁ “ጥላሁን ግዛው የሞተ ጊዜ” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን የዓመተ ምሕረት መዛባት ገና ከጅምሩ ሳይ፣ ስህተቱ ከእኔ አነባበብ ነው ብዬ መልሼ መላልሼ ባየው ያየሁት መዛባት ያው ነው፡፡ ማንበቤን አቋርጬ ዘጋሁትና ይህ እውነተኛ ታሪክ መጽሐፍ፣ ለአሁኑና ለነገው ትውልድ ተቀማጭ፣ በመረጃ ተደግፎ ተጽፎ ለነገ በመረጃነት የሚያገለግል ገና ከጅምሩ በዓመተ ምሕረት ሲጣላ ገባ ሲባልማ መሣሪያ እንዳይማዘዝ ሠጋሁ፡፡ ከደራሲዋ በበለጠ በምሥጋና የተወደሱት አንባቢያን ላይ አዘንሁ፡፡ 12 አንባቢያን 24 ዓይኖች እንዴት ዘለሉት አልኩ? አንብበዋል እንጂ አላስተዋሉም አልኩ፡፡
ወጣት ታደለች ኅዳር 5 ቀን 1962 ዓ.ም. በ19 ዓመት የልደት ቀኗ ዕለት ወደ ስዊዘርላንድ ለትምህርት ተጓዘች (ገጽ 3) ከ3 ገጽ ጉዞ በኋላ ታኅሣሥ 19 ቀን 1962 ዓ.ም. ጥላሁን ግዛው የተገደለ ዕለት “እኔም ከጥቂት ጓደኞቼ ጋር እዚያው ታድሜያለሁ” ትለናለች፡፡ ስዊዘርላንድ በሄደች በወር ከ14 ቀን ማለት ነው፡፡ ጥላሁን ግዛው ያረፈበት ዕለትና ዓመት ትክክል በመሆኑ ለቀጣይ ዕትመት ወደ ስዊዘርላንድ የተጓዘችው ኅዳር 5 ቀን 1963 ዓ.ም. በሚል ቢስተካከል ሳልጠቁም አላልፍም፡፡ ቀላል ሎጂክ??? በጥቅሉ መጽሐፋቸውን በቃላት ለቀማ እጅግ የተዋጣለት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ቋንቋቸውና አጻጻፋቸውም ጭንቅላቴን ገና በገና “የአንጃ ሚስት” ብዬ በጥላቻ ሳይሆን፣ በምን መልኩ አቀረቡት? የሚለውንና ምን አገኝበታለሁ? በሚል ጉጉት ስለአነበብኩት ቋንቋቸውንና አገላለጻቸው ከዘመኑ ወጣቶች ቃላት ልዋስና ለእኔ ተመችቶኛል፡፡
በፖለቲካ ብስለትና ፍላጎት እምብዛም የሆነችው ታደለች በስዊዘርላንድ ሕይወቷ የኢሕአፓውን መሥራች ተስፋዬ ደበሳይን (ዶ/ር)፣ አክሊሉ ህሩይ በአጋጣሚ በአገር ልጅነት ተዋውቃ እንዴት ወደ ፖለቲካው ልትሳብ እንደቻለች ሒደቱን ስትተርከው የእነ ተስፋዬን ትዕግሥት፣ የአክሊሉን ብልጠት አስታኮ ምን ያህል ሴቶችን በትግሉ ለማሳተፍ የነበራቸውን ጥረት ያሳያል፡፡ እውነትም ተሳክቶላቸዋል፡፡ ኢሕአፓ ሴቶችን ከቤት እመቤትነት ወደ ትግል እመቤትነት ያወጣ ጠንካራ ፓርቲ ነበርና፡፡ “ተዋት! በእርግጠኝነት አንድ ቀን ትመጣለች” (ገጽ 21) ይል የነበረው ተስፋዬ ደበሳይ (ዶ/ር) “የማትመጪው ፈርተሽ ነው አይደል?” (ገጽ 17) በሚል በሞራሏ የሚጫወተው አክሊሉ ህሩይ በውይይት መድረካቸው “ፍቅር እስከ መቃብር”ን በማቅረብ አስጀምሮ ወደ ተማሪዎቹ ስብሰባ እየተጎተተች፣ እየተሳበች ሳታስበው ጥልቅ እንዳለች ስታስቀምጠው በወቅቱ የነበሩ ሴቶች ኢሕአፓውያን እንዴት ድርጅቱን እንደተቀላቀሉ መለስ ብለው የ46 ዓመት ካሴት ወደ ኋላ እንዲያጠነጥኑ ታደርጋለች፡፡ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የበቁትና የውጭ ዕድል አግኝተው በትምህርት መስክ ያሉት በኢሕአፓም ሆነ በመኢሶን በኩል የተሠለፉት ወጣት ሴቶች በወቅቱ በኑሮ ደረጃም ሻል ያሉ ነበሩ፡፡
ታደለች በውጭ ትምህርቷ ተከራይታ የምትኖርበትን ቤት ተስፋዬ ደበሳይ ለአንድ ቀን እንድትፈቅድለት በጠየቃት መሠረት ታዋቂው ብርሃነ መስቀል በእንግድነት መጥቶ ከወጣት ታደለች ለመተዋወቅና የትዳር ጓደኛ የመሆንን ሒደት በጥሩ መልኩ ገልጻዋለች፡፡ በነሐሴ ወር 1961 ዓ.ም. ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር የአውሮፕላን ጠለፋ ላይ ተሠማርቶ ወደ አልጄሪያ ካቀናው ቡድን ውስጥ ብርሃነ መስቀል ረዳ ከዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ጋር ለመገናኘት ወደ ሲዊዘርላንድ በመጣ ወቅት የጋራ ውይይታቸው በታደለች የትምህርት መኖሪያ ቤት ተካሂዷል፡፡ ሁለቱ ዝነኛ ታጋዮች በያዙት የአገር፣ የሕዝብ፣ የድርጅት፣ ሌላም ሌላ ጉዳይ ውይይት ሁኔታ ታደለች በዚህ መልኩ ትገልጸዋለች፣
‹‹. . . እኔ አዘገጃጅቼ እስክጨርስ ምንም አላቆሙም፣ በለሆሳስ አፍ ለአፍ ገጥመው ያወራሉ፡፡ አንደኛው ሲያቆም ሌላኛው ይቀጥላል፡፡ . . .” (ገጽ 39) “. . . እቤት ደርሼ ቁልፉን ስከፍት እንደዚያው ጥያቸው እንደሄድኩት ወሬያቸውን ጠምደዋል፡፡ ምግቡን በልተው አላነሱትም፡፡ ወይኑንም ጥቂት ቀምሰውታል እንጂ አልጠጡትም፡፡›› በሚል ለታላቅ የአገርና የሕዝብ ገድል ረዥሙን ጉዞ እንዴት እንደሚጀምሩት? ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚነጋገሩት ሁለቱ አንጋፋ የኢሕአፓ ምሰሶዎች አፍ ለአፍ የገጠሙት ማሳረጊያቸው ሆድና ጀርባ ሲሆን ያማል፣ ያቆስላል፡፡ ለሰው ልጅ ዛሬ በፍቅር፣ በእምነት፣ በፅናት የተሳሰርንበት ዓላማ ነገ በአንዲት ጠብታ ሤራ እሳትና ጭድ ሊኮን እንደሚችል ይመጣብናል፡፡ ሰዎች ያመኑት ሰዋቸው ሳያውቁት ነገ እሚሰምጥ ገደል ላይ (Sinkhole) አቁሟቸው ውስጡ ሲስቅ ይታያችኋል፤ “ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው” ቢያቃጭልባችሁም እንዴት ተደርጎ በኢሕአፓ ያለ እምነት? ያስብላችኋል፡፡ ሌላም ሌላ፡፡
ሰው የፈለገ ቢሆን ፍቅርን ይወዳል፣ የተቃራኒ ጾታ ፍቅር ደግሞ እጅጉን ይወደዳል፡፡ ከምስኪኑ ደሃ እስከ ባለፀጋው፣ ከመኃይሙ እስከ ምሁሩ ብቻ የሰው ዘር በሙሉ የተቃራኒ ጾታ ፍላጎት ገደብ የለውም፡፡ ከዚህ አኳያ በትግል ከተሠለፉ ሴቶች መጽሐፉ ውስጥ በሰፊው ከታወሱት ፍቅርተ ገብረ ማርያም፣ አበበች በቀለ፣ አዳነች ፍሥሐዬ ጀምሮ ማርታ መብርሃቱ፣ መዝገብነሽ አባዩ፣ ገነት ግርማ፣ ሰላማዊት ዳዊት መሰል ከፍተኛ የኢሕአፓ መሥራች ሴቶች በአብዛኞቹ የአመራር አካሉ ፍቅረኛ ወይም ባለቤቶች መሆናቸው ትግልና ፍቅር መጣመዳቸውን ያሳየናል፡፡
የዛሬዋ አምባሳደር ታደለች መጽሐፍን ካነበብሁ በኋላ በቀጥታ ጉዞ ወደ ብርሃነ መስቀል አደረግሁ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሁለት ጊዜ አንብቤውና ትዝብት ወርሼ፣ ሀዘኔን ቋጥሬ “ያ ትውልድ” ድረ ገጽ ላይ “ምን ብለው ነበር?” (http://yatewlid.com/images/PDF/MinBlewNeber/Berhanemeskel.pdf) በሚል ዓምድ ሥር ወደ ተቀመጠው 96 ገጽ የብርሃነ መስቀል ቃል ምርመራ ሰነድን “ዳኛው ማነው” ከሚለው መጽሐፍ ጋር እያዛመድሁ፣ እያገናዘብሁ ማንበብ ጀመርሁ፡፡ ጸሐፊዋ ይህንን ሰነድ አንድ ጊዜ (ገጽ 271) ብቻ ቢጠቅሱትም መጽሐፋቸውና የብርሃነ መስቀል የምርመራ ሰነድ አንድ ናቸው፡፡ በመሆኑም መጽሐፉን ከመገምገም ጋር ራሱ የተናገረውን፣ የሰጠውን ቃል ይበልጥ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት አምባሳደር ውድ ባለቤታቸውን፣ የሦስት ልጆቻቸውን አባት እንዴት ብለው ተሳስቷል ይላሉ? እንዴት ብለው ደርግ ፋሺስት ነው ይላሉ? ብዬ በኢሕአፓ ያለችኝን አንድ ጠብታ ውሎና ዕድሜ ከሰጠኝ ግንዛቤ በመነሳት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ልጽፍ ፈለግሁ፡
“ዳኛው ማነው?” የሚለውንም ሆነ ስለሌሎች መጻሕፍት ስለእያንዳንዱ የራስ ግምጋሜ መስጠት ቢቻልም እኔ ያተኮርኩት በብርሃነ መስቀልና የአንጃ ጉዳይ ጋር የተነሱት ነጥቦች ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መጽሐፉን አንብቦና አጣጥፎ መጽሐፍ መደርደሪያው ላይ በማስፈር መቋጨቱ በተለይ በኢሕአፓ ጉዳይ በተደጋጋሚ በመጽሐፍም ሆነ በቃለ ምልልስ የሚደናገረው የአሁኑ ትውልድም ሆነ መጪው ትውልድ ይህ ተጽፏል ብሎ ይወያይበት፣ ይከራከርበት ዘንድ ያለኝን ነጥብ ማካፈሉ ከዝምታ ይሻላል ብዬ ወርውሬአለሁ፡፡
ኢሕአፓ ፕሮግራሙን ለሕዝብ አሠራጭቶ ራሱን ይፋ በአደረገበት ነሐሴ 26 ቀን 1967 ዓ.ም. የደርግ አገዛዝ ዓመት ሊሞላው ከሁለት ሳምንት ያነሰ ቀናት ነበር የሚቀረው፡፡ በቀጣይ ዓመት 1968 ማለት ኢሕአፓ ሙሉ በሙሉ የጀመረውን መዋቅሩን በማጠናከርና በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ይዟቸው የተነሳውን ወቅታዊ መፈክሮች ማታገያ አደረጋቸው:: ደርግ የካቲት 25 ቀን በ1967 ዓ.ም. የመሬት አዋጅን ቢያውጅም የሚያካሂደው እመቃና አፈና ጎልቶ መውጣቱ የኢሕአፓ ማታገያ መፈክሮች የኃይል ሚዘኑ ወደ ሕዝብ እንዲያጋድል ሆኗል፡፡ “የዲሞክራሲ መብት ያለገደብ” መፈክር ተቀባይነት ማግኘት ከደርግ ይልቅ ኢሕአፓ ተደመጠ፣ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁንኑ” መፈክር ደርግ ወደ ጦር ሠፈሩ ይመለስ ዘንድ በወጣቱና በሕዝቡ ዘንድ እምቢታን አስከተለ፣ “የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል” ኢሕአፓ ቢቀበልም ቅስቀሳውና ትግሉ የመደብ ትግል ላይ ማተኮሩ በብሔር የተደራጁ ኃይሎችን ተደማጭነት አሳጣ፡፡ ይህ የአንድ ዓመት በተለይ የ1968 ዓ.ም. እንቅስቃሴ ኢሕአፓን እንደስሙ ሕዝባዊ አድርጎታል፡፡ የሕዝብን ስሜት ይዞ ስለተነሳ ተደማጭነት፣ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ከዚህ ሒደት በኋላ ኢሕአፓ የወጣቱ፣ የሴቶች እህቶቻችን፣ የላብ አደሩ፣ የአርሶ አደሩ፣ የጭቁን ወታደሩ፣ የመምህራን፣ የተማሪዎች፣ የሠራተኛው፣ የእናቶች፣ የአባቶች በጥቅሉ የሕዝብ ሆኗል፡፡ ይህ ነበር የዚያ ጊዜ ዘር ቆጠራው፡፡ ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ ለአንድ ዓላማ ያስተቃቀፈ ፓርቲ፡፡ በመዋቅርና በማደራጀት ደረጃ ኢሕአፓ ካስመዘገበው ከፍተኛ ድል በኋላ ኢሕአፓ የብርሃነ መስቀል፣ ኢሕአፓ የጌታቸው ማሩ በሌላ በኩል ኢሕአፓ እንደ መጽሐፉ አባባል “የክሊኩ” (የዶክተር ተስፋዬ ደበሳይ፣ የዘርዑ ክሸንና የክፍሉ ታደሰ) ሳይሆን የአገርና የሕዝብ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች መሥራች አመራር አካላት ድርጅቱን በጋራ መሥርተው ሕዝባዊ እንዳሉት በአጭር ጊዜ ሲሳካላቸው ከዚያ በኋላ ንብረትነቱ የሕዝብ ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ በውስጣቸው ሊከሰት በሚችል አለመግባባት በርካታ አባላቱና ደጋፊዎቻቸው የጥቃቱ ሰለባ ሊሆኑ ባልተገባ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ነው የብርሃነ መስቀል ስህተት፡፡
ብርሃነ መስቀል እንደሚለውና ባለቤቱ ታደለች እንዳስነበበችን “በክሊኩ” አንጃ ተብሎ ተፈረጀ፣ ከፖሊት ቢሮ አባልነቱ ተነሳ፣ ከፓርቲው ተገለለ፣ በቀጣይነት ሊገደል ተፈለገ፣ ሸሸ፡፡ ጥሩ ለምን ግን “በክሊኩ” እልህ የኢሕአፓ ልጆች እንዲጠቁ፣ ምንም ሳናውቅ እየታገልን ያለነው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ላይ ፈረደ? ዕውን ትልቅ አገራዊ አጀንዳ ይዞ ያን ያህል ለትግሉና ለኢሕአፓ ትልቅ ስም የያዘ ብርሃነ መስቀል መርሐ ቤቴ ገብቶ ከተራ ሽፍታ መንግሥቴ ደፋር ጋር ሲደራደር አያሳፍርም? ብርሃነ መስቀል “በክሊኩ” ንዴት የተነሳ ከሚያውቃቸው ተባባሪዎቹ ጋር (በመጽሐፉ እንደተነገረው ከእርማት ንቅናቄው ጋር) በመሆን የኢሕአፓ ድርጊት እንዳይሳካ ማሰናከልና ምስጢር አሳልፎ መስጠት ማንን እንደጎዳ ሲታሰብ አያሳዝንምን? ዕውን ብርሃነ መስቀል ያላግባብም ሆነ በአግባብ አንጃ ተብሎ እንደ ጌታቸው ማሩ በእጃቸው ላይ ስላልወደቀ ሁኔታዎች እንዳበቁለት ተገንዝቦ ከአገር ለመውጣት ሙከራ ቢያደርግ በተገባ ነበር፡፡ በደርግ ከተያዘም በኋላ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ለታሪክ ጥሎ ያለፈውን የምርመራ ቃል ከሚሰጥ በቆራጥ ዓላማው ተተልትሎ ቢሞት ስሙ እጅግ በተለወጠ፡፡
በዓይኑ ያየውን የሸሸበትን መርሐ ቤቴ ነዋሪ እህልና ጎጆ የሚያቃጥል፣ የሚያወድም ደርግ እንዴት እኔን ይምረኛል ብሎ ተስፋ አደረገ? ዕውን ከደርግ ጋር ተቀላቅሎ ገራፊና ገዳይ ካድሬ ከመሆን ሌላ ምን ያተርፍ ነበር? በየከፍተኛው፣ በየክፍለ አገሩ እየከዱ ለደርግ እጃቸውን የሰጡ አንዳንድ የኢሕአፓን ልጆች ለጥፋት በነፃ ዕርምጃ ከመሳተፍ ጀምሮ፣ ራሳቸውን ቀይረው ያሉ ኢሕአፓዎችን ከየተደበቁበት በማስያዝ፣ በመግረፍ፣ በማስገደል ድርጊታቸው ነው የሚታወቁት፡፡ በፖለቲካው ረገድ ትልቁን ተንኮልና ሤራ ያሠለጠኑትን መኢሶኖች የበላ መንግሥቱ፣ ከጎኑ የነበሩትን ኪሮስ ዓለማየሁን፣ ሻለቃ ሲሳይ ሀብቴን፣ ብርጋዴር ጄነራል ጌታቸው ናደውን፣ ሌተና ጄኔራል አማን አንዶምን፣ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ በንቲን፣ ሌተና ኮሎኔል አጥናፉ አባተንና በርካታ የደርግ አባላትን መግደሉን በተግባር ያየ የኢሕአፓው መሥራች ብርሃነ መስቀል ዕውን ከፋሺስት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር “ጓድ” ሊባባል ሲያስብ እንኳን ያኔ ዛሬ ያማል፡፡
የችግሩ መነሻ
ብርሃነ መስቀል ከፖሊት ቢሮው ለመውጣት ዋናው ምክንያት የሆነው ፓርቲው ከመታወጁ ነሐሴ 26 ቀን 1967 ዓ.ም. በፊት በተደረገው ክስ ወይም ውንጀላ እንደሆነ በሰጠው የምርመራ ቃል ገጽ 7 እንዲህ ይላል
‹‹. . . የስብሰባው ዋና ተግባር ለመለስተኛ ጉባዔው መዘጋጀት ሲሆን ሌላው ሰፊ ጊዜ የፈጀው ውይይት ከታጠቀው ቡድን ጠፍተው ስለወጡት ሰባት ሰዎች ነበር፡፡ በዚህም ውይይት ዋናው ዓላማው ሰዎቹ የጠፉት በፖለቲካ መስመር ልዩነት ሳይሆን በእኔ አስተዳደር ብልሹነት መሆኑን ለማሳመን ነበር። . . .›› ሰረዝ የተጨመረበት። በማስከተል
“ . . . ስህተቴን በመጠቆም ፈንታ እኔ ባልተገኘሁባቸው ስብሰባዎች ስለእኔ ሥራ ብዙ ክሶች ይቀርቡ ስለነበር. . . ከጉባዔው በፊት እውነተኛ ጓዳዊ መንፈስ እንዲሰፍን ሒስና ግለ ሒስ ይደረግ ብል አጣዳፊ ተግባሮች አሉና ከጉባዔው በኋላ ሒስና ግለ ሒስ እናካሂዳለን ተብሎ ነገሩ በዚህ ተደፋፈነ። . . .››
የብርሃነ መስቀል መነሻ ልዩነት ከታጠቀው ቡድን ጥለው የወጡት ሰባት ሰዎች ምክንያት መሆኑን ራሱ ይመሰክራል፡፡ ወደ አሲምባ የገባው የመጀመርያው የኢሕአሠ ቡድን ኤርትራ በረሃ እያለ የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም. ከታወጀው የመሬት ለአራሹ አዋጅ በኋላ እዚህ ምን እናደርጋለን? የምንታገልለት ጥያቄ ተመልሷል ዓይነት ጥያቄዎች በቡድኑ ውስጥ ሲነሱ በአግባቡ እንዳልተስተናገዱ ተዘግቧል፡፡ በኤርትራ ቆይታቸው ብርሃነ መስቀል ቡድኑን ትቶ ወደ አውሮፓ መጓዝና በሌላም በኩል ከሻዕቢያ ጋር በምን ጉዳይ ተስማምቶ ወደ አሲምባ ሊገቡ እንደተፈቀደላቸው ለሚነሱ ጥያቄዎችና ለተነሱ ቅሬታዎች አግባብ መልስ አለመሰጠቱ በአንድ ምሽት ወደ ግማሽ የሚሆኑት ለደርግ እጃቸውን ለመስጠት መሠወር የብርሃነ መስቀልን የአመራር ብቃት ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባውና ከሌሎች የፓርቲው አመራር አካላቱ ጋር የቅሬታና የልዩነት አዝማሚያ መነሻ ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡ ከዚህ ሒደት በኋላ ብርሃነ መስቀል ከነሐሴ ወር 1967 ዓ.ም. ቀደም ሲል በተካሄደው የኢሕአፓ እወጃ ኮንፈረንስ ላይ ይሳተፍ እንጂ የጸሐፊነቱን ቦታ ሁሉ ክብር ሳይሰጠው ጉባዔውን ሊከፍት አለመቻሉ የሚያሳድርበትን የሞራል ድቀት መረዳት አያዳግትም፡፡ ይህንንም ሲገልጸው፣
‹‹. . . መለስተኛ ጉባዔ ሲካሄድ ለሚቀርቡት ሪፖርቶች ስንነጋገር በየትኛውም ሌላ ማርክሲስት ሌኒንስት ፓርቲ ትራዲሽን የሌለ ፕሮሲጀር አቀረቡ፡፡ ይኸውም በሕጋዊ መንገድ ከኃላፊነቱ ያልተነሳ ዋና ጸሐፊ እያለ ሌላ ተራ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጉባዔውን እንዲከፍት የሚል ነበር፣ በእኔ በኩል ያኔ በእኔ ላይ ፐርሰናል ቅሬታ ስላላቸው እንጂ ከማዕከላዊ ኮሚቴ በስተጀርባ የተቋቋመው ክሊክ በመመሥረቻ ጉባዔ የተመረጡትን የፓርቲው መሪዎች ዘዴኛና ድብቅ በሆነ መንገድ ለማውረድ ማቀዳቸውን አልገመትኩም ነበር፡፡ . . .›› እያለ የሚነበበው የብርሃነ መስቀል የቃል ምርመራ ገጽ 12 መጨረሻና ገጽ 13 መጀመርያ እንዲህ ይለናል፣
‹‹. . . ከዚህ በኋላ ማዕከላዊ ኮሚቴው አዲስ ፖሊት ቢሮ ይምረጥ ተባለና ቀደም ብሎ ይተበተብ የነበረው በመመሥረቻው ጉባዔ ላይ የተመረጡትን መሪዎች የመለወጥ ሴራ ይፋ ወጥቶ ሕጋዊ መልክ ያዘ፡፡ በዚሁ ምርጫ መሠረት የሚከተሉት ሰዎች ለፖሊት ቢሮ አባልነት ተመረጡ፡፡ አንደኛ ተስፋዬ ደበሳይ (ዶ/ር) ሁለተኛ ክፍሉ ታደሰ (የኢሠማው) ሦስተኛ ዘሩ ኪሸን፣ አራተኛ ጌታቸው ማሩ፣ አምስተኛ አበራ ዋቅጅራ ነበሩ፡፡ . . .›› በማለት ከገለጸ በኋላ አበራ ዋቅጅራ በተደረገው ምርጫ ባለመደሰቱ በሕመም ምክንያት እኔ እንድተካው ቢጠይቅም በፖሊት ቢሮው መግባት እንደሌለበትና ገና ኢሕአፓ ሳይታወጅ የነበረውን ልዩነት እንዲህ ያስቀምጠዋል።
“. . . በእኔ በኩል ከተቀሩት አራት ሰዎች ጋር የፖለቲካ አስተሳሰብና የርዕዮተ ዓለም ልዩነት (በተለይም በኮሚኒስት ፓርቲ ሥነ ምግባር ረገድ) ስለአለኝ የፖሊት ቢሮ ሥራ በየጊዜው በሚነሳ ክርክርና ጭቅጭቅ እንዳይደናቀፍ መግባት የለብኝም፣ . . .›› ሠረዝ የተጨመረበት፡፡
ይህ የብርሃነ መስቀል ቃል ምርመራ የሚነግረን ብርሃነ መስቀል ከአመራሩ አካል ወሳኝ ሰዎች ጋር ቅራኔ/አለመግባባት የገባው ከነሐሴ 26 ቀን 1967 ዓ.ም. በፊት መሆኑን ነው፡፡ ይህ አለመግባባትም ከላይ በሠረዝ እንደተቀመጠው የፖለቲካ ልዩነት ነበር ይለናል፡፡ በመሆኑም ብርሃነ መስቀል በ1968 ዓ.ም. የኢሕአፓ ጣፋጭ የትግል ዓመት በምን ሁኔታ አሳለፈ? የሚለው ለቀጣይ አለመግባባቶች መሠረት ነበሩ ቢባል ያስኬዳል፡፡ የደርግ የግንባር ጥሪ የመጣው ከሰባት ወር በኋላ ሚያዝያ 12 ቀን 1968 ዓ.ም. ሲሆን፣ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ግድያ ጉዳይ በዓመቱ መስከረም 13 ቀን 1969 ዓ.ም. ሲሆን በዚህ ረገድ ብርሃነ መስቀል ካስመዘገበው ልዩነት በፊት ጉዞው ሁሉ የተነጠለ እንደነበር ያመላክታል፡፡
ብርሃነ መስቀል ከኢሕአሠ ለከዱት ለሰባቱ አባላት ተጠያቂ አድርጎ ጉዳዩን እጅግ ሞራል በሚነካ መንገድ ከማክረር ለምን በሒስና ግለሒስ መፍታት አልተቻለም? የብርሃነ መስቀል ኢሕአፓን በመመሥረት አኳያ ያስመዘገበው ጥረት ቀላል አይደለምና ለድርጅቱ አንድነት ሲባል እልህ ከመጋባት በምክርና በግሳፄ ቢታለፍ ምናለበት? የሚሉ ምኞቶች ይመጣሉ፡፡ እዚህ ጅምር ንትርክ ላይ ነው በአጠቃላይ የአመራሩ ድክመት፡፡ ከዚህ ሒደት በኋላ ብርሃነ መስቀል የሚናገረውም የማይጥማቸው፣ ተደማጭነቱም እየቀነሰ መምጣቱ ሰብዓዊ ባህሪውን እየተፈታተነ ቢመጣ ሊደንቀን አይገባም፡፡
ማታገያ መፈክሮች
ብርሃነ መስቀል ስለመስከረም 1968 ዓ.ም. ስለተጠራው የሠራተኛው የሥራ ማቆም ዓድማ፣ ስለሚጠየቁት ጥያቄዎች፣ ደርግ መስከረም 1968 ዓ.ም. ስለአወጀው “አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና” አስከትሎም በተለይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ላይ ስለአደረገው እስርና ፍጅት የሰጠው ቃል (ገጽ 15 እና 16 ዝርዝሩን ተመልከቱ) በእውነቱ አምኖበት ነው ወይስ ሰው ነውና ደርግ ይምረኛል በሚል ተስፋ ራሱን ለማዳን? ያሰኛል፡፡
የቀረቡት የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትና የዲሞክራሲያዊ መብት መፈክሮች በደርግ ተሳኩ አልተሳኩ ማታገያነታቸውን እንዴት ሊቀበላቸው አልቻለም፡፡ እንደውም ኢሕአፓን ከሕዝብ ያስተቃቀፉት እነዚህ ሁለት መሠረታዊ መፈክሮች ናቸው፡፡ እንኳን ያኔ ዛሬም ምላሽ ያላገኙ አታጋይነታቸው ህያው ነው፡፡
“. . . እኔ እንኳንስ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እስኪቋቋም የሥራ ማቆም ዓድማውን ቀጥሉ ልንል የሠራተኛው ማኅበራት መሪዎች ዲሞክራሲያዊ መብቶች ካልታወጁ የሥራ ማቆም ዓድማ እናደርጋለን ማለታቸው ስህተት ነው የሚል ነበር። . . .” እነዚህን አታጋይ መፈክሮች ለሕዝብና ለሠራተኛው ማስተዋወቂያ አንዱ የሰላማዊ ትግል ዘዴ የሥራ ማቆም ዓድማ መሆኑን መቃኘት የሚከብድ አይደለም፡፡ ደርግ ጥያቄውን ይመልሳል ብሎ ተስፋ ለማድረግ ሳይሆን፣ ትግሉ እንዲጎመራ ዘልቆ ኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ ሰላማዊ የማታገያ ዘዴ በመጠቀም ተግባራዊ ሲደረግ ባህሪው ነውና ደርግ ያስራል፣ ይደበድባል፣ ይገድላል፡፡ ታጋይ እስርና ሞት ከፈራ ትግል መጀመርም የለበትም፡፡ እስርና ግድያ ተፈርቶ ሰላማዊ ሠልፍ ካልተደረገ፣ የሥራ ማቆም ዓድማ ካልተጠራ፣ መፈክሮችና በራሪዎች በየግድግዳው ካልተለጠፉ፣ በሕዝባዊ መድረኮች ላይ ቅስቀሳ ካልተደረገ ትግል ምኑን ትግል ሆነ!
በኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. እጁን በደም ያጨማለቀው ደርግ ሙሉውን ዓመት “በፍየል ወጠጤ” ሲያስካካ መክረሙ በቀጣይ ዓመትም 1968 ዓ.ም. ገና በመጀመርያው ወር በአየር መንገድ ሠራተኞችና በሠራተኛው ማኅበራት ላይ ያደረገው እስርና ግድያ እየቀጠለ ሙሉው 1968 ዓ.ም. ኢሕአፓ አንድም መሣሪያ ሳያነሳ አልነበረምን ልጆቹንና አባላቱን ሲገብር የኖረው? ብርሃነ መስቀል ቀጠል አድርጎ ስለደርግ ተራማጅነት እንዲህ ሲል ቃሉን ይሰጣል (ገጽ 16)
‹‹. . . በዚሁ ወቅት በአየር መንገድ ሠራተኞች ላይ በፀጥታ ኃይሎች የተከፈተው ተኩስና ከዚያም ተከታትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግሥት በልዩ ልዩ ምክንያት በተለይም በተጋነነ መረጃ ተሳስቶ ያወጣው ቢመስለኝም ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ፀረ ዲሞክራሲያዊ እንዲያውም ፋሺስታዊ ዝንባሌ ባላቸው ኃይሎች ተፅዕኖ ሥር የወደቀ መስሎኝ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ እኔም እንደተቀሩት የፓርቲ መሪዎችና የፓርቲ አባላት በመንግሥቱ ተራማጅነት ተስፋ ማጣት አድሮብኝ እንደነበር ልሸሽግ አልችልም፡፡ ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በነበረበት ወቅት ይታየኝ የነበረው ዋናው አብዮታዊ የትግል ዘዴ የትጥቅ ትግል ነበር፡፡ ደግነቱ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በኋላ የወሰደው ተራማጅ ዕርምጃ ይህ ስሜት ተጨባጭ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን ከማቅረቤ በፊት ሊያስለውጡኝ ችሏል፡፡ . . .›› ይለናል የኢሕአፓው መሥራች ብርሃነ መስቀል ረዳ፡፡
ይህንን ቃል ብርሃነ መስቀል የሰጠው በሰኔ ወር 1971 ዓ.ም. ሲሆን እሱ በሸሸበት መርሐ ቤቴ ጨምሮ በመላው አገሪቷ ደርግ ያደረሰውን ዕልቂትና ሰቆቃ ሰምቷል፣ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ወቅት ደርግ ኢሕአፓን ብቻ ሳይሆን አጠገቡ የከበቡትንም መኢሶን፣ ወዝ ሊግ፣ ኢጭአት ሳይቀሩ የበላና አንድ አምባገነን ፈላጭ ቆራጭ ፋሺስታዊ አገዛዝ ይበልጥ የተንሰራፋበት ወቅት መሆኑን እያወቀ ምን ያህል ነፍሱን ለማዳን ደርግን መሸንገሉ እጅጉን አሳዛኝ ነበር፡፡ ክብርና ስሙን እንደያዘ ቢሰዋ ምናለ ያሰኛል፡፡
ዕውን የደርግ ተራማጅነትና አብዮት ደርግ ከሕግ በላይ ገዝፎ በአንድ ምሽት ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. 54 የቀድሞ የአፄ ኃይለ ሥላሴን ባለሥልጣናት፣ ከደርጉ ሊቀመንበር ጄኔራል አማን አንዶምና ሌሎች አምስት ተራማጅ ወገኖች ጋር ደባልቆ የረሸነ ዕለት ይበልጥ አክትሞለታል፡፡ ደርግ ማንነቱን ያሳየበት ዕለት ነበር፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በዋዜማው የሰጠው የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት ምን ያህል በደርጉ ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍን በበላይነት እንደያዘ አመላካች ነበር፡፡ ‹‹. . . እነዚህ ዕርምጃዎች ከዚያ በፊት ያልነበረኝን ያህል በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ተራማጅነት ከፍተኛ ተስፋ አደረብኝ፡፡ . . .›› (ገጽ 17) የሚለን ብርሃነ የእስረኞች መፈታትን እንደ አብነት ከሚጠቅሳቸው ውስጥ ናቸው፡፡ ደርግ ገና ከሥልጣን ጅምሩ ማሰር፣ መፍታት ዋናው ተግባሩ ነው፣ የቀረው ቢኖር “የእስርና ግድያ ሚኒስትር” አለማቋቋሙ ብቻ ነው፡፡ ዕድሜ ለመኢሶን ባንዳ ምሁሮች ደርግ የኢሕአፓን ሕዝባዊ ቅላፄ በግልባጩ በመለፈፍ ለፕሮፓጋንዳ የሚጠቀም ብሔርተኛ አይደለምን? ስለባንዲራና አገር እየለፈፈ አይደል እንዴ ትውልድ የቀበረው? እርጉዝ አስገድሎ ንፁኃን ሠራተኞችን በአደባባይ አስረሽኖ የሕዝብ ቁጣ ሲያይልና ለአጎቱ ሲል ግርማ ከበደን ቢረሽን “ደርግ ተራማጅ ሆነ” ልንል አግባብነት አለውን? ይህ ነው እንግዲህ አምባሳደር ታደለች መመልከት የሚገባቸው፡፡ በወጣትነት ዕድሜያቸው በአፍላ ትግሉ ወቅት ሲዊዘርላንድ ከዚያም መርሐ ቤቴ ቢሆኑም የአገራችን ዕልቂትና የደርግ ፍጅት በንፁኃን አርሶ አደሮች ላይ ሳይቀር ክምር እህልና ቤታቸውን ማጋየት እንደነበር በገጽ 330 ሲገልጹት እንዲህ ብለውናል፡፡
‹‹እጅግ አሳዛኝ የነበረው ጉዳይ በጎተራ የተሞላ እህል፣ ሲያሻቸው በእሳት አለዚያም ቁልቁል በገደሉ በማፍሰስ፣ ከብቶችን በማረድና በመግደል ካልሆነም በመንዳት፣ ሕዝቡ እንዲማረር መደረጉ ነው፡፡
‹‹ከአንድ ከባድ አሰሳ በኋላ ደህና የተደራጀ የገበሬ ቤት እየመረጡ ገብተው ያለውን በማደፋፋት ጎጆዎችን ያቃጥላሉ፡፡ የዚህ የጭካኔ ዓላማ ‹‹ገበሬው በንብረቱና በጎታው ከመጡበት የተሸሸጉትን አማፂዎች አሳልፎ ይሰጣል›› በሚል ስሌት እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ይህን ተግባር የሚፈጽሙት ግለሰቦች ግን ከዚያም ያለፈ አረመኔያዊ ባህርያቸውን፣ የሰውን ስቃይ በማየት የመርካት ጥማቸውን የሚወጡ ለመሆናቸው በዓይኔ ያየሁት ድርጊት ምስክር ነው፤›› በሚል የትናንቷ ወጣት ታደለች ስታስነብበን ደርግ ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት ፍጅት ዋናው መመርያው እንደነበር ያሳየናል::
የግንባር ጥሪ
ሚያዝያ 12 ቀን 1968 ዓ.ም. በደርግ ስለታወጀው የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምና በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የተደረገው የግንባር ማቋቋም ጥሪ ግንባሩ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በኢሕአፓ በኩል እንዲሟሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ብርሃነ መስቀል ሲወነጅል፣ ‹‹ . . . ክሊኩ ስምምነት ላይ የተደረሰበትን ውሳኔ ትርጉም ለማሳሳት ሥራዬ ብሎ መንግሥት ሊቀበላቸው የማይችላቸው ጥያቄዎችን መደርደር ጀመረ፡፡ . . .›› ይለናል፡፡
መቼም ኢሕአፓ በወቅቱ በእያንዳንዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ ጨምሮ በተከሰቱ ሁኔታዎች በዲሞክራሲያ ዕትሙ ያልዳሰሰው ጉዳይ አልነበረም፡፡ እነዚህ የዲሞክራሲያ ዕትሞች “የክሊኩ” ናቸው ካልተባሉ በቀር ዛሬም አሉ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ በኅብረት ግንባር ላይ ያለው አቋም›› ዲሞክራሲያ ልዩ ዕትም ቁጥር ሦስት ግንቦት ወር 1968 ዓ.ም. (ሙሉውን ለማንበብ http://yatewlid.com/images/PDF/Democracia/Demo_01/Demo_Vol_1_LeyuEtim_No_03_Hibret.pdf) ባወጣው ዕትሙ፡-
‹‹. . . ወታደራዊው መንግሥት ሚያዝያ 12 ቀን 1968 ዓ.ም. ለአብዮታዊ ግንባር መቋቋም ያቀረበውን ጥሪ በመሠረተ ሐሳቡ የምንቀበለው ለዚህ ነው፡፡ . . .›› በሚል አቋሙን በመግለጽ ካስቀመጠ በኋላ ስለግንባሩ ከመንግሥት ጋር ውይይት ለመጀመር በቅድሚያ በግዴታ መሟላት አለባቸው በሚል የተዘረዘሩት ነጥቦች እንደሚከተለው አስቀምጧል፡-
‹‹ሀ. ዲሞክራሲያዊ መብቶች የፀረ ፊውዳል፣ የፀረ ኢምፔሪያሊስት፣ የፀረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት አብዮት ደጋፊ ለሆኑት መደቦች (ላብ አደር፣ አርሶ አደር፣ ንዑስ ከበርቴ) እነዚህን ለሚወክሉ ቡድኖችና እንቅስቃሴዎች ሁሉ ያለገደብ እንዲታወጅ:: አብሮም ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለመገደብ ተብለው የወጡት ግፈኛ ደንቦች ሕጎችና አዋጆች ሁሉ እንዲሻሩ፡፡
ለ. በኤርትራ ላይ የሚካሄደው ማናቸውም የክተት ዝግጅት በፍጥነት እንዲቆምና እንዲሻር፣ በሌሎች ጭቁን ብሔሮች ላይ የሚደረገው ዘመቻ እንዲቆም፡፡
ሐ. የወታደራዊው መንግሥት በሰፊው ሕዝብ ላይ የሚያካሂዳቸው ጭፍጨፋዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመሩና ይፋነታቸው እየተባባሰ እንደሄደ ሰሞኑን በኪነት ሠራተኞችና በሜይ ዴይ ተሠላፊዎች የተወሰዱት የግፍ ዕርምጃዎች እንኳን በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በአዋሽ ሸለቆ የእርሻ ሠራተኞች መሪዎች ላይ አስበ ተፈሪ ውስጥ የተደረገው ፍጅት ሳይበቃ አሁንም አርሶ አደሮችና ላብ አደሮች በየቦታው ይረሸናሉ፡፡ ያለፍርድ የሚገደሉት እስረኞች በተለይም ኤርትራውያን ቁጥር እጅግ ትልቅ ነው፡፡ እነዚህና እነዚህን መሰል በሰፊው ሕዝብ ላይ የሚካሄዱ የጭፍጨፋ ዕርምጃዎች ያለአንዳች መወላወል ባስቸኳይ እንዲቆሙ፡፡
መ. የታሰሩ አብዮታውያንና ዲሞክራሲያውያን በሙሉ በነፃ እንዲለቀቁ መንግሥቱ በተራማጆች ላይ የሚያደርገው ማሳደድና መከታተል በፍጥነት እንዲቆም፣ ይህም ከላብ አደሮች ከመምህራን፣ ከተማሪዎችና ከዘማቾች ሌላ የገበሬ ማኅበራት መሪዎችና አባላትን በየትኛውም የብሔር እንቅስቃሴ የታሰሩ ታጋዮችንና በታጋይነታቸው ምክንያት የታሰሩ ወታደሮችንና ፖሊሶችን የግዴታ ማጠቃለል ይኖርበታል፡፡
ሠ. መንግሥቱ በነዚህ ነጥቦች ላይ መስማማቱና በሥራም ላይ ማዋሉ በሬዲዮ በጋዜጦችና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በይፋ እንዲገለጽ፡፡ ከመንግሥቱ ጋር ለውይይቱ ከመቅረባችን በፊት እነዚህ አምስት ነጥቦች አንዳቸውም ሳይጓደሉና ሳይጣመሙ በሙሉ ግዴታ መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ . . .›› በማለት ነበር ዲሞክራሲያ የፓርቲውን ግልጽ አቋም ያስነበበችው፡፡
ዕውን ይህን “የክሊኩ” አቋም ብሎ መፈረጅ አባላቱንም ሆነ የሕዝቡን ትግል አለማገናዘብ ነው፡፡ እንደ መኢሶን ምንም ጥያቄ ሳናቀርብ ከደርግ እንተቃቀፍ ካልተባለ በቀር ይህ የወቅቱ የኢሕአፓ አቋም ልዩነት ፈጣሪ ይሆናልን? ዕውን ብርሃነ መስቀል በዚህ የእስር ቤት ቃለ ምርመራ እንደምንም የሚለውን ብሎ ሕይወቱን ሊያተርፍ ፈልጓል ወይም እጅጉን ፖለቲካው ተምታቶበታል ያሰኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ መስጠት ቢቻልም አንባቢያን ለግንዛቤ የብርሃነ መስቀልን ቃለ ምርመራና ከላይ የጠቀስኩትን የዲሞክራሲያ ዕትም ማንበቡ እንደሚረዳ በመጠቆም ወደ ሌላው ጉዳይ ልገስግስ፡፡
ኢሕአፓ በዚህ የግንባር ጥሪ ዕትሙ የተቃወመውንና የማይቀበለውንም በግልጽ አስቀምጦታል፣ እንዲህ ይነበባል ‹‹ይህን ጥሪ በመሠረተ ሐሳቡ ብንቀበለውም የወጣውን ፕሮግራም እንደ ኅብረት ግንባር ፕሮግራም አድርገን አንቀበለውም:: ከፕሮግራሙ ጋር አብሮ የወጣውን የአደራጅ ጽሕፈት ቤት ልንቀበል አንችልም፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በመንግሥት ቀጥተኛ ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ከመሆኑም ሌላ በአመራረጡ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ፣ ስለዚህም አሠራሩ አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ ዕቅድ የማይኖረው ይዘቱም የተለያዩትን ተራማጅ ክፍሎች በውከላ መልክ ያልያዘና ግፋ ቢል የአንድ ጠባብ ቡድንን ድምፅና ጥቅም ብቻ የሚያስተጋባ በመሆኑ መቋቋሙን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ . . .›› በሚል በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት አማካይነት በወቅቱ 900 ብር የወር ደመወዝ የሚያስከፍለውን (የመኢሶኑ አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ በነገራችን ላይ ከደረጀ ኃይሌ ጋር ያደረጉት ውይይት) የመኢሶንን ዕቅድና አካሄድ አጋልጧል፡፡
ይቀጥላል
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡