Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየእንግሊዝ ሙዚየሞች ከመቅደላ የዘረፉትን ቅርሶች ለመመለስ ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?

የእንግሊዝ ሙዚየሞች ከመቅደላ የዘረፉትን ቅርሶች ለመመለስ ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?

ቀን:

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከ152 ዓመታት በፊት መቅደላ ላይ ከተሰዉ በኋላ ከአምባው የደረሰው በጄኔራል ናፒር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ወደ አገሩ ባዶ እጁን አልተመለሰም፡፡ መቅደላ አምባ በንጉሠ ነገሥቱ ቴዎድሮስ በተደራጀው ሙዚየም ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ውድ ቅርሶችን ዘርፎ እንጂ፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ሆነ ከእሳቸው ንግሥና ቀጥለው በመጡት መንግሥታት ከፍተኛ ጥረት በተለያዩ ጊዜያት የተወሰኑ ቅርሶችና ንዋየ ቅድሳት (የቤተ ክርስቲያን ንዋዮች) መመለሳቸው ይታወሳል፡፡

መሰንበቻውን በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዘመነ ቴዎድሮስ ከተዘረፉት ተንቀሳቃሽ ቅርሶች መካከል የተወሰኑትን ለማስመለስ በለንደን ከሚገኘው ከቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ጋር መነጋገር መጀመሩን ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡

- Advertisement -

የቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ካሉት ስብስቦች ውስጥ ለመመለስ ካሰባቸው መካከል የወርቅ ዘውድና ዘውዳዊ የሠርግ አልባሳት ይገኙበታል፡፡ የሙዚየሙ ምክትል ዳይሬክተር ቲም ሪቭ፣ “የዕደ ጥበብ ውጤቶቹን ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመለሱበት መንገድ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርበት እየተወያየን ነው፤” ማለታቸውን ዘጋርዲያን ጠቅሷል፡፡

ዓምና በመጋቢት ወር በለንደን ከተማ የሚገኘው ብሔራዊጦር ሙዚየም ለስድሳ ዓመታት በእጁ የነበረውን የአፄ ቴዎድሮስ ሁለት ቁንዳላዎች ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (/) ማስረከቡ ይታወሳል፡፡

በርክክቡ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ልዑካን  በለንደን የብሪቲሽ  ሙዚየምን ሲጎበኝ

ሚኒስትሯ፣ በሙዚየሙ  የሚገኙ ጽላቶች  ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመናን ልዩ  ክብርና  ቦታ  ያላቸው፣  ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙባቸው ሕያዋን በመሆናቸው  ወደ ትክክለኛ  ቦታቸው እንዲመለሱ  መጠየቃቸውና የሙዚየሙ ኃላፊዎች ሐሳቡን እንደሚጋሩትና የሕግ ጉዳይ ሆኖ መወሰን ባይችሉም፣ ወደፊት  በሚኖረው ስብሰባ ለአገሪቱ

 ሙዚየም ባለአደራ ቦርድ አቅርበው  ምላሽ እንደሚሰጡ  መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የአፄ ቴዎድሮስን መስዋዕትነት ተከትሎ በ1868 ዓ.ም. ከመቅደላ አምባ የተዘረፉት ቅርሶች በተለይ ከ500 በላይ የጽሑፍ ቅርሶች፣ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች፣ የንጉሣውያን የወርቅ ዘውዶችና ጌጣጌጦች፣ እንዲሁም አሥር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታቦታት በእንግሊዝ የተለያዩ ሙዚየሞች ከመገኘታቸው በተጨማሪም በርካታ ቅርሶች በግለሰብ እጅ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

የተዘረፉትን ቅርሶች ለማስመለስ ባለፉት መንግሥታት ከተደረጉት ጥረቶች ባሻገር “አፍሮሜት” የሚባለው የመቅደላ ቅርስ አስመላሽ ተቋም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ጥቂት ቅርሶች መመለሳቸውም አይዘነጋም፡፡

በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ አማካይነት በ2000 ዓ.ም. የመቅደላ አምባ ቅርሶች እንዲመለሱ በደብዳቤ ቢጠይቁም ተቋማቱ አዎንታዊ ምላሽ አልሰጡም፡፡

በእንግሊዝ ሠራዊት ከመቅደላ አምባ የተዘረፉት ቅርሶችኢትዮጵያ ፍላጎቱ ካላት ለረዥም ጊዜ በውሰት ልንሰጥ እንችላለንየሚለውን የቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየምን የሚያዝያ 2010 ዓ.ም. መግለጫባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አልተቀበለውም፡፡

በእንግሊዝና በተለያዩ የአውሮፓ ሙዚየሞች፣ አብያተ መጻሕፍትና በግለሰቦች እጅ የሚገኙ በርካታ ቅርሶችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅትን (ዩኔስኮ) ጨምሮ ስለቅርስ ማስመለስ የተደነገጉ ዓለም አቀፍ ሕጎች ቅርሶችን ለማስመለስ ዕገዛ እንደሚሰጡም በወቅቱ ሚኒስቴሩ በሰጠው ምላሽ አንፀባርቋል፡፡

ቅርሶቹን “ኢትዮጵያውያን ፈቅደውና ወደው በስጦታ መልክ ስላልሰጡ አሁን ያለው የእንግሊዝ ትውልድ ከ150 ዓመታት በፊት የተፈጠረውን ስህተት በማረም የኢትዮጵያን ሀብቶችን መመለስ ይገባዋል፤” ሲሉም የቀድሞዋ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር) ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ መንግሥት ቅርሶችን ለማስመለስ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ሌሎች አካላት በሒደቱ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ለማመቻቸት አፍሮሜትን እንደገና ለማደራጀት አገራዊ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የእንግሊዝ ሙዚየሞች ከመቅደላ የዘረፉትን ቅርሶች ለመመለስ ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?

ዘረፋው እንዴት ነበር?

የቴዎድሮስ አሟሟትና የመቅደላው ዘረፋ” በሚል ርዕስ ጥናት ያከናወኑት ግርማ ኪዳኔ፣ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ካጠፉ በኋላ የመቅደላ አምባን የወረሩት እንግሊዞች የፈጸሙትን ዝርፊያ በዝርዝር አቅርበውታል፡፡ እንዲህም አሉ፡-  

“እንደ እንግሊዝ ጦር አዛዦች አባባል ተልዕኳቸውን የእንግሊዝ እስረኞችን ለማስፈታት ነበር፡፡ ከዚህ የተልዕኮ ሽፋን በስተጀርባ ግን ዓላማቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸውን ቅርሶች ለመዝረፍ ጭምር መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡ ሪቻርድ ሆምስ የተባለው የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ከእንግሊዝ ጦር ጋር አብሮ እንዲመጣ መደረጉ ለዚህ የዘረፋ ተግባር መከሰት እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡

“የመጀመርያው ዘረፋ ቡድን ያተኮረው በሟቹ ንጉሥ ሬሳ ላይ ነበር፡፡ የአንገት መስቀልና የጣት ቀለበታቸውን፣ ሸሚዛቸውንና ሽጉጣቸውን ከመዝረፋቸውም ባሻገር ሹሩባቸውን ሳይቀር ሸልተው የወሰዱ ለመሆኑ በታሪክ መዛግብት መረዳት ይቻላል፡፡

“ሁለተኛው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው የቤተ መንግሥት ሕንፃ በመድፈር ነበር፡፡ ንጉሡ በሕይወታቸው ሳሉ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም የሰበሰቧቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ መጻሕፍትን እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ የመንግሥት ሰነዶችንና የተለያዩ መረጃዎችን ሳይቀሩ ዘርፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶችና ማኅተም፣ በተለይም ክብረ ነገሥት የተባለው ታላቁ መጽሐፍ ይገኙባቸዋል፡፡ ቀጥለውም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ማዕድ ቤት ውስጥ በመግባት ሃያ እንሥራ የሚሆን የተጠመቀ ጠጅና የእህል አረቄ ዘርፈው ከመጠን በላይ ሰክረው ነበር፡፡ ከዘረፏቸው ቅርሶች ይልቅ ጥፋት ያደረሱባቸው አመዝነው ታይተዋል፡፡ ብዙ ቅርሶች ጥለዋል፣ ሰባብረዋል፣ መጻሕፍትንም ቀዳደዋል፣ አልባሳትንም ሸረካክተዋል፡፡

“የሦስተኛው የዘረፋ ቡድን ከወሰዳቸው መካከል ከወርቅ የተሠራ የአቡነ ሰላማ አክሊል ወይም ዘውድ ጫማና ቀበቶ፣ ከወርቅ የተሠሩ ሁለት ጽዋዎች፣ ከወርቅ የተሠራ በአንገት ላይ የሚጠልቅ የአፄ ቴዎድሮስ የሰሎሞን ኒሻን እንዲሁም ንጉሡ ሲነግሡ ለብሰውት የነበረው የማዕረግ ልብስ ይገኙባቸዋል፡፡

“አራተኛው ቡድን በዘረፋቸው መካከል የተለያዩ ጋሻዎች፣ ከእነዚህ ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚገመተውና የፊታውራሪ ገብርዬ ጋሻ፣ ልዩ ልዩ ጦሮችና ጎራዴዎች፣ ያሸበረቁ የፈረስ ዕቃዎች፣ በተጨማሪም የቴዎድሮስ እስረኞች የታሰሩበት የእግር ብረት ይገኙበታል፡፡

“አምስተኛውና የመጨረሻው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው አፄ ቴዎድሮስ በየአገሩ ሲዘዋወሩ ያርፉበት በነበረው ድንኳናቸውና ይጠጡበት በነበረው ዋንጫቸው፣ የማንነቱ  ባልታወቀ የፈረስ ልባብ ላይ ነበረ፡፡ ወታደሮቹ በዚህ ሳይገቱ የደረሱበትን በማሰስና እያንዳንዱ ቤት ውስጥ በመግባት ተመሳሳይ ዘረፋ ከማካሄዳቸውም ባሻገር ከተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች የተገኙትን መንፈሳዊ ሥዕሎችና እንዲሁም ቁጥራቸው አሥር የሚደርሱ ታቦቶችን ሳይቀሩ ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ጀምሮ በአነስተኛ ጎጆ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ሳይቀሩ ተዘርፈዋል፡፡

“ምንም እንኳ ጄኔራል ናፒየር ባዘዘው መሠረት በመቅደላ ተሰብስበው የነበሩት ሁሉ ቅርሶች ለጨረታ ቀርበው ነበር በማለት ለማስመሰል ተሞከረ እንጂ፣ አንዳንድ ባለ ሀብቶች በተለይም ሲቪሎችና ኦፊሰሮች ራሱ ጄኔራል ናፒየር ሳይቀር ቀደም ብለው ጨረታው በይፋ ከመጀመሩ በፊት ለየራሳቸው ያከማቿቸው ቅርሶች በብዛት እንደነበሩ ድርጊቱ ካለፈ በኋላ ሊታወቅ ችሏል፡፡ ለምሳሌ ለጨረታው ካልቀረቡት ቅርሶች መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶች፣ የክብርና የማዕረግ ልብሶቻቸው፣ በሺሕ የሚቆጠሩ የብራና መጽሐፎችና የቴዎድሮስ ማኅተም፣ የአቡነ ሰላማ የወርቅ አክሊል፣ በብር ያሸበረቀ ጋሻ፣ በክብረ በዓል ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል የቴዎድሮስ ከበሮና የመሳሰሉት ከሌሎች ንብረቶች ጋር ከመቅደላ ቤተ ክርስቲያን አጥር ግቢ በነበሩት ጎጆዎች ወስጥ ታምቀው እንደነበር ይነገራል፡፡

“በተለይም ከአቡነ ሰላማ መቃብር ላይ ተፈጽሞ የነበረውን የስርቆት ወንጀል አስመልክቶ ሲናገር ‹በጣም ከሚያስገርመውና ከሚያሳዝነው ነገር ሁሉ ከእስረኞቹ መካከል አንዱ ከስድስት ወር በፊት ተቀብረው የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መቃብር ድረስ በመሄድ መቃብሩን አውጥቶና ሰብሮ ብዙ ሺሕ ዶላር ሊያወጣ የሚችል ከአልማዝ የተሠራ መስቀላቸውን ከአንገታቸው ላይ መንጭቆ መውሰዱ የቱን ያህል የተረገመ ሰይጣን እንደነበር ነው ሲል በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡

“የአቡነ ሰላማን ከወርቅ የተሠራ አክሊልና የቁርባን ጽዋ ከአንድ ጦር ሜዳ ላይ ከዋለ ወታደር የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሆልምስ በአራት የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ ገዝቶት እንደነበር ቀደም ሲል ተጠቅሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግሊዞች ድል አገኘን ብለው ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የተጠቀሱትን ሁለት ቅርሶች ሪቻርድ ሆልምስ ከኮሎኔል ፍሬዘር፣ ከኮሎኔል ሚልወርድና ከኮሎኔል ካሜሩን ጋር ለብሪትሽ ሙዚየም በሁለት ሺሕ የእንግሊዝ ፓውንድ እንዲሸጥላቸው እ.ኤ.አ. ጁላይ 1 ቀን 1868 አቅርበውት እንደነበር የደብዳቤ ወረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

“በሽያጭም ሆነ በስጦታ መተላለፋቸው ለጊዜው ባይታወቅም በአሁኑ ጊዜ ከመቅደላ የተወሰዱት ቅርሶች በእንግሊዝ አገር ሙዚየሞች ውስጥ ባመጧቸው ሰዎች ስም ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ በጻፈው ዘ ፕሬስተር ጆን ተብሎ በሚጠራው መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ተርጓሚዎቹና አዘጋጆቹ ሀንቲንግፎርድና ቤክንግሃም እንደጠቀሱት በብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ “ሆልምስ ኮሌክሽን” እየተባሉ የሚጠሩ አሥር ታቦቶች ከመኖራቸውም  በላይ ብዛታቸው ከአንድ ሺሕ በላይ የሚደርስ የኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፍ መጽሐፎች በተጠቀሰው ሙዚየም ውስጥ ተደርድረው ይታያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...