ሰላም! ሰላም! ‹‹ኦ ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ!›› የሚል መጽሐፍ ድሮ ማንበቤ ትዝ ሲለኝ ዕድሜዬ መንጎዱም ይታወሰኛል፡፡ ‹‹ሰላምን ለማግኘት አጥብቄ ብጥርም…›› የሚለው ተማፅኖ የሞላበት ዘፈንም ትዝታው አይረሳኝም፡፡ ፖለቲከኞች ሲራቀቁ ሰላምን ከታንጎ ዳንስ ጋር በማነፃፀር ሊያስረዱን ይዳዳሉ፡፡ ሁለት ባላጋራዎች ከሌሉ እኮ ሰላም እንደማይደፈርስ ከጥንቱም የታወቀ ነው፡፡ ‹‹ታንጎ ለመደነስ ሁለት ሰዎች ያስፈልጋሉ›› እያሉ ሰላምን ከዳንኪራ ጋር ማነፃፀር ይከብደኛል፡፡ ያም ሆነ ይህ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ማብራሪያ ስጠይቀው፣ ‹‹ለዘመናት የፈሰሰ ያልተወራረደ የደም ዕዳ አለብን…›› ሲለኝ፣ ‹‹ምን ማለትህ ነው?›› ብዬ ለምን እኔም የደም ዕዳ እንዳለብኝ በድንጋጤ ስጠይቀው፣ ‹‹ለዘመናት የፈሰሰው የንፁኃን ደም እያክለፈለፈን በቅጡ ማሰብ ባለመቻላችን ነው በቀላሉ ተስማምተን ሰላም ማስፈን ያቃተን…›› ብሎ ቁርጡን ነገረኝ፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ ቁጭ ብለን በሰከነ መንገድ ብንነጋር እኮ የችግራችን ምንጭ እኮ ወለል ብሎ ነው የሚታየው፡፡ አንዱ ስክር ብሎ እየተንገዳገደ ሲሄድ ሌላው፣ ‹‹አንተ እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ…›› ቢለው፣ ‹‹የጠጣሁት እየገፈተረኝ እንዴት ልቆጣጠረው…›› አለ አሉ፡፡ እኛንም ሰላም ነስቶ የሚያባላን ይኼ ዓይነቱ አባዜ ነው፡፡ አይደለም እንዴ!
አዛውንቱ ባሻዬ ሬዲዮናቸውን ይዘው ጋቢያቸውን አጣፍተው ይለፈልፋሉ። ብርዱ ነው ግብሩ እንዳትሉኝ። ምን የማያስለፈልፈን ነገር አለ ዘንድሮን ሁሉም ለፍላፊ ሆነና አዳማጭ ጠፋ እንጂ። እና ጠጋ ብዬ ሳዳምጣቸው፣ “አንድ ቋንቋ አላግባባን ብሎ እየተደነቋቆርን ጭራሽ አዲስ ቋንቋ?” ይላሉ። ‘ለግዕዝ ቋንቋ ትኩረት አልተሰጠም’ የሚል ፕሮግራም ሥራዬ ብለው እያዳመጡ። ቋንቋው ቀርቶ ዜጋው ትኩረት የተሰጠው ይመስል፣ አሁን እስኪ በዚህ ሰዓት ይኼ ይወራል? ማለቴ ሰሚ ያለ ይመስል ለማለት ነው። እና ጠጋ ብዬ፣ “ባሻዬ ምናለበት ቢተውት? ይልቅ ገና ብዙ የሚቀሩ ነገሮች ስላሉ ምን አስበዋል?” ብዬ ወሬ ጀመርኩ። እሳቸው ግን የሰሙኝ አይመስሉም። “ሰማህ? ስማ! ስማ! ጀርመን እስከ ማስተርስ ድረስ የግዕዝ ቋንቋን እንደምታስተምር ታውቅ ነበር? ስማ! ስማ! ሰማህ? ለካ ጀርመኖች የደረሱበት የሕክምና ጥበብ በሙሉ የተገለበጠው በግዕዝ የተጻፉ ድርሳናትን መርምረው ነው? ስማ! ስማ!” እያሉ ልቤን ሲያወልቁት ቆዩና ድንገት ዕንባ በዓይናቸው ግጥም ብሎ ግድግዳውን ተደግፈው ዓይናቸውን ጨፈኑ። ዓይኔን ጨፍኜ ሳሰላስል ሰዓቱ ኮበለለ፡፡ እንዲህ እየሆንን ይዘለቃል ወይ!
ወዲያው ደንግጬ፣ “አመመዎ እንዴ? ሰው ልጥራ?” እያልኩ ስወራጭ፣ “ማንን ትጠራለህ ልጅ አንበርብር? ሰው ያለ ይመስል ሰው ልጥራ የምትለኝ። ሰው ቢኖርማ ሕመም በጅምላ ይታደለን ነበር? ቁጭት በደቦ እንሰፍር ነበር? ሰው ልጥራ? ሰው ያለ ይመስል…” እያሉ ተደግፈውኝ ተነስተው ወደ መኝታ ክፍላቸው ገቡ። እኔም የመጣሁበትን ሌላ ጉዳይ በይደር ከድኜ ወደ ሥራዬ ከነፍኩ። ዘንድሮ የሚሠራና ከላይ የወረደለት ኑሮአቸው የሰማይና የምድር ያህል ነው፡፡ አንዳንዱ ደሙ እየተመረመረ መሬትና ኮንዶሚኒየም ይታደለዋል፡፡ የእኔ ቢጤው ደግሞ ማገሩ በተጣመመና ልስኑ በፈረሰ የቀበሌ ቤት እየኖረ ከወር ቀለቡ ላይ ቀንሶ ቢቆጥብም፣ በሥርዓት ወረፋ ሲጠብቅ ከአፉ ላይ ይነጠቃል፡፡ ተስፋ ባይኖር ኖሮ ሕይወት ጎምዛዛ ይሆን ነበርና በተስፋ ተሞልተን ሕይወትን ጣፋጭ ለማድረግ መጣጣሩ መልካም ነው፡፡ ለዚህ መድኃኒቱ ሥራ ነው፡፡ ሥራ ብቻ!
የዘንድሮ ወኔ መቼም ከአፍ አያልፍም። ‹‹ሁሉም ወኔ! ወኔ! ይላል . . .›› አለኝ በቀደም ዕለት የባሻዬ ልጅ። “ወይኔ! ወይኔ! ለማለት ፈልጎ ይሆናላ!” አለው እንደ እኔው ደላላ የሆነ ወዳጄ እየቀለደ። ድሮም ሐሳብ ጠፍቶበት በስሜት ልጥ ለታሰረ ሰው ከዘራፍ ሌላ ምን መላ ይታየዋል ብላችሁ ነው? ‹ናደው፣ ደርምሰው፣ ገንጥለው፣ እጨደው . . .› ይላሉ። ዞሮ በራሳቸው የማይደረስ የሚመስላቸው ቀልደኞች ሁላ። ይኼን የምላችሁ ምክንያት ስላለኝ ነው። በቀደም አንዱ መጣና ያውም ቤቴ ድረስ፣ ‹‹እኔ የምለው በቃ ለምን ዓባይን በቶሎ አንጨርሰውም? ግድቡን በፍጥነት ጨርሰን ብንገላለገል ግብፅ የለ፣ የውስጥ ተላላኪ የለ ምን እንደሚሆኑ አስበኸዋል?” ሲለኝ ቆይ ግን ደላላው አንበርብር ምንተስኖት እንኳን በታላቁ ዓባይ ግድብ በገዛ ጎጆዬ ብቻዬን እወስናለሁ እንዴ? ዘመኑ የእኩልነት ነው። ጠንካራ ሆነ አልሆነ የብዙ ሰዎች ሐሳብ ጥቂቶችን የሚያሸንፍበት ነው። በአጭሩ የዴሞክራሲ ነው። ካልጠፋ ሰው አምቶ ሊያሳማኝ ካልሆነ በቀር ቤቴ ድረስ መጥቶ በቶሎ ወስን የሚለኝ በጤናው ይመስላችኋል? እኔ ስላልመሰለኝ፣ “በኋላ እንወያይበታለን አሁን ወደ ሥራ እየሄድኩ ነ…” ብዬ ገፍቼ አስወጣሁት። ለብቻ የሚወሰን ነገር መብዛቱ መስሎኝ ሰላም የሚነሳን፡፡ ሰላማችን እንዳይቃወስ በጋራ ብንመክር መልካም መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ጥራት ያለው ሐሳብ ለማግኘት ጭምር እንደሚያገለግል ብነግራችሁ ደላላ ነው ብላችሁ ትንቁኝ ይሆን? አይመስለኝም ብዬ ተስፋ ላድርግ!
ሳላስበው አንድ ሙሉ ኮንቴይነር መወልወያ አሻሻጥኩ። በዚህ አጋጣሚ ስገረም ወድቆ የተነሳ አንድ ሲኖትራክ ጆሮውን ተባለ። ፈጣሪዬ አለ እኮ። ከላይ ሆኖ ሲያየኝ ያዝንልኛል፡፡ ለሥራ አንቅቶ እንጀራ ያበላኛል፡፡ ለዚህም ነው ተመሥገን የምለው፡፡ የኑሮን ነገር ለሚያውቀው መቼም የፈጣሪን ቸርነትና ረድኤት አይረሳውም። አንዱ፣ ‹‹የልማቱን ነገር ተውት፣ ሆድ ይፍጀው። እኛ ልማት ሲባል አገር ማልመት መስሎን እንጂ፣ ሰው እያመነመኑ አንዳንዶች ብቻ የሚለሙበት ልማት መሆኑን ቀደም ተብሎ ቢነገረን እኮ ወራጅ እንል ነበር በሰላም። እኛ ካልወረድን እነሱ አይወርዱማ። እና ኪሴ አበጥ ሲል ወደ ባንክ ሄድኩ። ላስገባ ነዋ። እህ ስል ሠልፍ። ምንድነው ስል የብር ቅያሪ ነው ተባልኩ። የበሰበሰ ብር በፌስታል ታቅፈው የቆሙ ሰዎች የባንክ ደብተር እየከፈቱ ያስገባሉ፡፡ ለእናንተ እንጂ እኛ ከጥንትም በባንክ የመጠቀም ሲስተም ነበረን አልኩ በሆዴ። ስልቻ ውስጥ፣ ጎተራ ውስጥ፣ መሬት ቆፍረን እየቀበርን ብዙ ሺሕ ዓመታት ኖረናል፣ ይብላኝላችሁ ለእናንተ . . .›› ሲል እኔ ድግሞ ወደ ባሻዬ ሄድኩ። አንዳንዱ ከጀመረ ማቆሚያ የለውም!
እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ላይ ባሻዬ ናቸው በምሳሌ የሚያስረዱኝ። አባት አያሳጣችሁ መቼም። ማለቴ ሲስተም ከሌለው አባት ምንም ማድረግ የማይችል ደግ አሳቢ ሰው ለማለት ነው። ኧረ ተውኝ ዘንድሮ። እና ባሻዬ ዘንድ ስደርስ ባሻዬ፣ ‹‹ምን ጉድ ነው ዘንድሮ?›› እያሉ ከሞባይላቸው ጋር ይታገላሉ። ‹‹ምነው ተበላሸ?›› ስላቸው፣ አድርጎት ነው። እኔ እኮ እንደ ድሮዬ በፖስታ ብጻጻፍ ይሻለኛል። ዝም ብላችሁ ነው እናንተ ልጆች ዕዳ የምታስገቡኝ፤›› ብለው ወቀሳ ጀመሩ። ‹‹ምን ሆኑ?›› ብዬ ስልካቸውን ሳየው የጽሑፍ መልዕክት ነው። ‘ይኼን ቁጥር በመላክ ስኬታማ ትዳር እንዲኖርዎት ያድርጉ። ስለመልካም ትዳር ወሳኝ እውነታዎችን እንነግርዎታለን . . .’ ይላል። ነገሩ ገባኝ። ባሻዬ ዘመኑ በፍጥነትና በቴክኖሎጂ ስም እያሳበበ አንዳንድ ነገሮችን ያለ ቦታቸው ሲያስቀምጣቸው አይመቻቸውም። ግን ችግሩ ባሻዬ ተመቻቸውም፣ አልተመቻቸውም ዘመኑ ገንዘብ ማሳደጃ ነው። አይደለም እንዴ!
እናም ለማረሳሳት የባጥ የቆጡን ስቀባጥር፣ ‹‹ወይ ትዳር? ትዳር እንዲህ በጽሑፍ መልዕክትና ጥቅስ ስምር ሲል። ኧረ ለመሆኑ ስኬትና ትዳር ምንድነው የሚያገናኛቸው? ቋንቋውን ከየት ነው የሚያመጡት?›› እያሉ ቆይተው አንድ ነገር አጫወቱኝ። ምናሉኝ፣ በአንድ ቀዬ ትዳራቸው የሚያስቀና አካላቸው ቢያረጅም ከሚስታቸው ጋር ያላቸው ፍቅር እያደር የወጣት የሆነ አዛውንት ነበሩ አሉ። ‹‹መቼም አበባ ካለ ንብ ያንዣብባል። ስኬታችሁና ደስታችሁ እያደር ምቀኛ ሲያፈራ ስታዩ ጽጌሬዳ ጉያ እሾህ ጠፍቶ እንደማያውቅ አስታውሱ። ምነው ስንት መርሳት የሚገባንን ነገር አንረሳም እያል በጎሳ እያበርን? የማይገነባ ነገር ከማስታወስ በሜዳ ሳር ጤዛ መመሰጥ ለኑሮ የሚበጅ ሚስጥር ያካፍላል ይባላል። እናም አንድ ቅናተኛ የአዛውንቱን ጎጆ ማፍረሻ መላ ሲፈልግ ሰነባብቶ ማምለጫውንም አዘጋጅቶ ጠጋ ብሎ “አንቱ! ኧረ ይህች ሚስትዎ ትሄዳለች። ምን ሆና ነው?” ይላቸዋል። “አይተሃታል?” ይላሉ በቸልታ። “በዓይኔ በብረቱ . . .” ይመልሳል። ሰውዬው ሚስታቸውን ወዲያው ጠርተው፣ “ሰማሽ ስምሽን? ሂያጅ ነች ይሉሻል። ይኼው ወሬኛው ፊት ጠየቅኩሽ . . .” ሲሏቸው ሚስታቸውን ወሬኛው ጣልቃ ገብቶ፣ “አንቱ! እንዴት ያሉ ሰው ነዎት ግን? ትሄዳለች ስልዎ በሐሳብ ትነሆልላች ማለቴ እንጂ ትወሰልታለች መቼ ወጣኝ?” ብሎ ሲቆጣ፣ “በል ተወው ወንድሜ። ያለ ዛሬም ሐሳብ ሲዎሸም አልሰማሁ” ብለው አባረሩት። ሰላም አደፍራሽን እንዲህ ነው እንጂ በአደባባ ማዋረድ፡፡ የምን ይሉኝታ ነው!
በሉ እንሰነባበት። ከትናንት ወዲያ የጠፋ መብራት ዛሬ ገና መምጣቱ ነው። ትናንት የሄደችው ውኃችን ነገ ወይ ከነገ ወዲያ ትመጣለች ተብሎ ይጠበቃል። ለዝርዝሩ መብራትና ውኃ መሥሪያ ቤቶች አነጋግሩ አልላችሁም መቼስ? መልስ በሌለበት አገር ጥያቄ ማብዛት ራስን ማስጠቆር ብቻ እንደሆነ ላለፉት ሃያ ምናምን ዓመታት ዓይተነዋል። ዓይተነው ዓይተነው ዓይናችን አለመጥፋቱ፣ ሰምተነው ሰምተነው ጆሯችን አለመደንቆሩ በራሱ ተዓምር ነው። ‹‹ሰማይ ያለ ባላ መቆሙ ምን ያስደንቅሃል? እኛ አለን እኮ ያለ ምግብና ውኃ፣ ያለ በቂ ትራንስፖርት አቅርቦትና የዜጋ አክብሮት ወጥተን እየገባን ሠርተን እየገበርን የምንዘረፍ። ተዘርፈን የማንጠይቅ። ጠይቀን የማይሳካልን። መልሰን ራሳችን ራሳችንን የምንዘርፍ…›› አለኝ በቀደም ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። እንግዲህ አስቡት ይኼን የሚያነፃፅርልኝ ያለ ባላ ከቆመው ሰማይ ጋር ነው። ‘አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስገርሙኛል’ ነበር ድሮ ዘፈኑ። አሁን መገረማችሁ አስገርሟችሁ ዘፈን ካላደረጋችሁት በቀር፣ አንዳንድ ነገሮች ዛሬም የሚያስገርሟችሁ ከሆነ እናንተ ገና አዲስ ትውልድ ናችሁ ማለት ነው። አብራራው ስትሉ ሰማሁ መሰለኝ። ‘ይቅርታ ሲስተም የለም፣ ትንሽ ይጠብቁኝ አደራ፣ አንድ ሳምንት ብቻ . . . ‘ እንዳልል አቅሙ የለኝም፡፡ ማን ነበር ‘የበረቱትማ እያዩሽ አለፉ . . .’ ያለው? እንዳላየን አልፈን ነገር ብናበርድስ!
ዘመናችን ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ባደርግም፣ በመረጃ የተደገፈ ጥናት ለማቅረብ ብቁ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ከሥራ በፊት ጥቅም፣ ከአገልግሎት በፊት ክብርና ዝና፣ ከሕዝብና ከአገር በፊት ሥልጣን የምናስቀድም እየበዛን ነው መሰል ነገራችን ሁሉ እየተወለጋገደ ነው፡፡ ትናንት ራሱን በነፃ አውጪነት መንበር ላይ ሰይሞ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል የነበረ በዘራፊነትና በአውሬነት ሲፈረጅ ዓይተናል፡፡ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ልሳኑ እስኪዘጋ ድረስ ሲጮህ እንደነበረ የሚደሰኩር፣ ዛሬ ወገንን ከወገን ደም እያቃባ አገር ለማፍረስ ሲያደባ ታዝበናል፡፡ ሥልጣን ሲሰጠው ከመላዕክት ዝማሬ የማይተናነስ ውዳሴ አቅራቢ፣ ከሥልጣኑ ሲገፈተር እሳት እንዲዘንብ ሲፀልይ አስተውለናል፡፡ ለሰላም የሚከፈለው ዋጋ እነዚህን ሁሉ ችግሮችና የችግር ጠንሳሾች ታሳቢ ካላደረገ ዕርባና የለውም፡፡ የሳምንቱ መልዕክቴም ለሰላም የሚዘረጉ እጆች ብፁዓን ናቸው የሚል ነው፡፡ መልካም ሰንበት!