ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በእልህና በቂም ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ገመድ ጉተታ፣ አገሪቱንና ሕዝቡን ዛሬም የመከራ ገፈት ቀማሽ እንዳደረገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት በበጎውም ሆነ በክፉ ጊዜ እርስ በርሱ እየተደጋገፈ እዚህ ደረጃ ያደረሳት አገሩ፣ በገዛ ልጆቹ መቅኖ እንድታጣ ሲደረግና የባዕዳን መዘባበቻ ስትሆን እንደማየት የሚያሳዝን ነገር የለም፡፡ ለዓመታት በአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የተካሄደው ደም አፋሳሽ ግጭትና በቅራኔ የተሞላው የፖለቲካ ግንኙነት በርካታ ወርቃማ አጋጣሚዎችን አሳጥቷል፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንን በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመቀባበል ይቅርና በቅጡ ለመነጋገርና ለመደራደር የሚያስችል ባህል ባለመኖሩ ምክንያት በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ በየእስር ቤቱ ተጥለዋል፣ ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ የነበሩት ዓመታት ጉዞም በዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ ነው የቀጠለው፡፡ ይህ አሳዛኝ ምዕራፍ ተዘግቶ ኢትዮጵያውያን ለሰላማዊ፣ ለፍትሐዊና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያበቃቸው አዲስና ሥልጡን ምዕራፍ እንዲጀመር የሽግግር ጊዜ ውስጥ ቢገባም፣ አሁንም በሴራና በአሻጥር ለመጠፋፋት መፈላለጉ ሊቆም አልቻለም፡፡ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ማዕከል ማድረግ ባለመቻሉ፣ የቁልቁለት ጉዞው እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የሕዝብ ፍላጎት ተረስቶ ሥልጣን ላይ ብቻ ማነጣጠር የዘመኑ ፋሽን ሆኗል፡፡
በዚህ ዘመን በቁጭት፣ በእልህ፣ በንዴት፣ በቂም በቀል፣ በጥላቻና በመሳሰሉት ለአገር የማይጠቅሙ አረንቋዎች ውስጥ ሆኖ ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለዕድገት መነጋገር አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታጋሽ፣ ጨዋ፣ ኩሩና አርቆ አሳቢ በመሆኑ ይህንን አኩሪ የጋራ እሴት ለሚመጥን ፖለቲካዊ ግንኙነት መዘጋጀት የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ኃላፊነት ነው፡፡ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት ኋላቀር አስተሳሰብና ጀብደኝነት ሳይሆን፣ በመርህ ላይ የተመሠረተ ውይይትና ድርድር ለአገር እንደሚበጅ መቼም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ልጆቿ እኩል እናት እንድትሆን ከተፈለገ፣ ሁሉም ልጆቿ ያለ ምንም አድልኦ የሚሳተፉበት ዴሞክራሲያዊ ዓውድ መፈጠር አለበት፡፡ ይህ በተግባር ይረጋገጥ ዘንድ ደግሞ መጀመርያ ከጀብደኛ ድርጊቶች መታቀብ፣ ለሕግ የበላይነት መገዛት፣ ከሕገወጥ ተግባራት መራቅ፣ የዴሞክራሲን እሴቶች ማክበር፣ ለሥልጣን የሚደረገው ትንቅንቅ ከአገርና ከሕዝብ ህልውና እንደማይበልጥ ማመን፣ ከአሻጥርና ከሴራ ፖለቲካ መላቀቅና ከምንም ነገር በላይ ሕዝብን ማክበር በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል አገር ሰላም ትሆናለች፡፡ ሕዝብ በሚገባ ይረካል፡፡ ሥልጣን ላይ ብቻ ማተኮር ለአገር አይበጅም፡፡
በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን የተዛባ ግንኙነት በማስተካከል፣ ለአገር የማይጠቅሙ የተወሳሰቡና ፋይዳ የሌላቸው በግትርነት የተሞሉ እንካ ሰላንቲያዎችን ማስቆም ተገቢ ነው፡፡ ወደ ትክክለኛው ጎዳና መመለስ የሚቻለውም ራስን ለመላው ሕዝብ ፈቃድ ማስገዛት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ የአገሪቱ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑን በተግባር በማረጋገጥ፣ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ሰላማዊና ዴሞክራሲያ ግንኙነት መጀመር አለበት፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊኖር የሚችለው መጀመርያ የፖለቲካ ምኅዳሩን ወለል አድርጎ በመክፈት ነው፡፡ እስካሁን የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሒደት የቀለበሱና የፖለቲካ ምኅዳሩን ያሽመደመዱ አላስፈላጊ ድርጊቶች ተወግደው፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት መልካም አጋጣሚ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕግ ዕውቅና ያገኙ መሠረታዊ መብቶች ተከብረው፣ የአገሪቱ ፖለቲካም ከታሰረበት መፈታት ይኖርበታል፡፡ የእስካሁኑ አሳዛኝና አሳፋሪ የፖለቲካ ጉዞ ተገቶ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት መገዛት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትሕ አገር መሆን የምትችለው በሥልጡን ፖለቲካ ብቻ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በተቃውሞ ጎራ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ የአገር ጉዳይ ያገባናል በማለት በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች፣ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ተገዥ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት ለእውነተኛ ውይይትና ድርድር መቅረብ አለበት ሲሉም፣ በእነሱ በኩል ያሉትን ክፍተቶችና ችግሮችም አንጥረው ለማውጣት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር የምትፈጠረው ራስን ለሕዝብ ፍላጎት በሚመጥን ደረጃ ማዘጋጀት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የአንድ ጎራ ደጋፊ መሆን እንደማይችሉ በመገንዘብ፣ ድጋፍና ተቃውሞን በአግባቡ ማስተናገድ የግድ ይላቸዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ በስፋት እንዲከፈትና ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ትግሉ እንዲቀጥል፣ በሠለጠነ መንገድ የተበላሸው ግንኙነት መታደስ አለበት፡፡ ከቂም፣ ከጥላቻና ከበቀል የፀዳ አስተሳሰብ በመያዝ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራስን ማዘጋጀት የወቅቱ ግዴታ ነው፡፡ እልህና ግትርነት የትም እንደማያደርሱ በመተማመን ካረጀውና ካፈጀው አስተሳሰብ መውጣት ይገባል፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል አሰልቺ፣ አስመራሪና ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩበትም፣ በፅናት ታግሎ የሕዝብን ልብ መግዛት መቻል ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው በዚህ መንገድ የሚጓዝ ፓርቲን ነው፡፡ ሕዝብን ማክበር የሚጀመረውም ከዚህ ነው፡፡
በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉ ወገኖችም ይህንን አጋጣሚ በጥንቃቄ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች በተለይ የወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማጎልበትና ንቃተ ህሊናቸውን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ከአጠቃላይ የሕዝቡ ቁጥር ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጣቱና ታዳጊው ትውልድ የጥላቻና የቂም በቀል ፖለቲካ ሰለባ እንዳይሆን፣ ይልቁንም የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ተረካቢ ስለሆነ የዴሞክራሲ እሴቶችን መቅሰም አለበት፡፡ ባለፉት ሁለት ትውልዶች በተበላሹ ግንኙነቶች ምክንያት ደብዛው የጠፋው ፖለቲካ ገዥ እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍንና በሕግ የበላይነት ሥር የምትተዳደር አገር እንድትገነባ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተሳታፊዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ጎራዎች ተሠልፈው አገርን ለትርምስ፣ ዜጎችን ለዕልቂት በዳረጉ ድርጊቶች የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ አገራችን በዚህ የተሳሳተና አውዳሚ አቅጣጫ ስትጓዝ፣ ከብሔራዊ ጥቅሞቻቸው አንፃር ለማዳከም የሚጥሩ ባዕዳን አደጋ መታሰብ አለበት፡፡ ይልቁንም በኢትዮጵያ ካሁን በኋላ ዴሞክራሲ በምልዓት እንዲሰፍን፣ ለጭቆናና ለአምባገነንነት መራቢያ የሚሆኑ አላስፈላጊ ድርጊቶች እንዲቆሙ ሞጋችና ጠያቂ ትውልድ መፍጠር ሲገባ፣ አገሪቱን የሚያተራምሱና የሕዝቡን ደኅንነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ አላስፈላጊ ድርጊቶች መቀንቀን የለባቸውም፡፡ ከሥልጣን በላይ አገር አለች፡፡ ሕዝብ አለ፡፡ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት መገዛት ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ይህንን ነው፡፡
የእዚህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ዋስትናው በአንድነት መቆም መቻል ነው፡፡ ይህ አንድነት የተለያዩ ማንነቶችን፣ ባህሎችን፣ ቋንቋዎችን፣ እምነቶችንና የመሳሰሉ ልዩነቶችን የሚያከብር ሲሆን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሩ ክብርና ዘለዓለማዊነት በጋራ ይቆማል፡፡ ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረ የአገር ፍቅር ስሜት ይበልጥ አብቦ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትገነባ ዘንድ ቅንነትና በጎ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በአምባገነንነት አስተሳሰብ ስላልሆነ፣ ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች መገዛት ተገቢ ነው፡፡ ያረጁና ያፈጁ ለአገር የማይጠቅሙ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ለዚህ ዘመን ትውልድ ስለማይመጥኑ አሽቀንጥሮ መጣል ይገባል፡፡ በብሔርተኝነት ካባ ውስጥ የአገርን ህልውና የሚንዱ ተግባራትም ሆኑ፣ ሥልጣንን ለብቻ ለመቆጣጠር የሚደረጉ ፀረ ዴሞክራሲ ድርጊቶች ፋይዳ የላቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ በሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ግንኙነት ማስፈን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ነው፡፡ በእኩልነት ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖር ነው፡፡ ከጋራ እሴቶቹ የሚመነጩትም በአንድነት መቆም፣ የጋራ ግብና ራዕይ ይዞ ከትውልድ ወደ ትውልድ መቀባበል ነው፡፡ በዚህ መንፈስ የዓመታት ስህተቶችን ማረምና አዲስ ምዕራፍ መጀመር የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን ደግሞ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት መገዛት ባህል ይሁን፡፡ ሥልጣን ከሕዝብና ከአገር በላይ አይደለም!