Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱን የገንዘብ ኖት አስመስሎ የሚያትም ማሽን መያዙን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅያሪው ከ31 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ተገኝቷል

የመከላከያ ሚኒስትሩ ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እና ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ፣ በአንድ ወር ውስጥ ሲከናወን በቆየው የገንዘብ መቀየር ሥርዓት ወቅት፣ አዲሱን የገንዘብ ኖት አስመስሎ በሐሰተኛ መንገድ የሚያትም ማሽን በአማራ ክልል ውስጥ በፀጥታ አካላት መያዙን አስታወቁ፡፡

በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል የተባለው የገንዘብ ለውጥ ሒደት ይህ ነው የሚባል ችግር ባያጋጥመውም፣ ሁለት መጠነኛ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን የመከላከያ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ አንደኛውና ዋናው ችግር አዲሱን የገንዘብ ኖት ተመሳስሎ በታተመ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ለማጭበርበር የተደረጉ ሙከራዎች በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በደቡብ ክልሎች ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች መታየታቸው ተጠቁሟል፡፡ በተለይም አማራና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በአዲሱ የገንዘብ ኖት ተመሳስለው የታተሙ ፎርጅድ ኖቶች ሥርጭት ጎልቶ ታይቶባቸዋል ተብለዋል፡፡   

እንደ ቀንዓ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ሐሰተኛው የገንዘብ ኖት የሚታተምበት ማሽን በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ ‹‹ፎርጅድ ብር የሚታተምበት ማሽን በአማራ ክልል በቁጥጥር ሥር ውሏል፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከማሽኑ ጋር የተያዙ የድርጊቱ ተሳታፊዎች መኖራቸውንና ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችም እየተፈለጉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ማሽኑ ከየት እንደመጣ፣ ለምንና በማን እንደመጣ ከሥረ መሠረቱ ምርመራ እንደሚደረግ የገለጹት የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ የአማራ ክልል የፀጥታ ተቋማት ከመከላከያና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን ባከናወኑት ሥራ ውጤቱ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

ሌላው ችግር መንግሥት ካስቀመጠው የገንዘብ መጠን በላይ ወጪ ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎች እንደነበሩ መጠቀሱ ነው፡፡ ከ100 ሺሕ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር አሮጌውን የገንዘብ ኖት የያዙ ዜጎች በአዲሱ ለመቀየር የተሰጣቸው የአንድ ወር ቀነ ገደብ ዓርብ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. መጠናቀቁን ያስታወሱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር (ዶ/ር)፣ በዚህ ሒደት የፌዴራልና የክልል ኮማንድ ፖስት አካላት የአንድ ወር አፈጻጸሙን ሒደት እንደገመገሙ ገልጸዋል፡፡

ከባንክ ውጭ እንደሚንቀሳቀስ የሚጠቀሰው ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ይህ ገንዘብ በኢኮኖሚው ላይ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ወንጀሎችና ሕገወጥ ተግባራትን ለማስፋፋት እንዳይውል ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ገንዘብ ለባንኮች መሠራጨቱን ገልጸዋል፡፡ ከመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ካለፈው እስከ ሳምንት አጋማሽ ድረስ ከ94 ቢሊዮን ብር በላይ አዲሱ የገንዘብ ኖት ለሁሉም ባንኮች መሠራጨቱን፣ ከ920 ሺሕ በላይ አዳዲስ የባንክ ሒሳቦች መከፈታቸውን የባንኩ ገዥ አስታውቀዋል፡፡ ከአምስት ሺሕ ብር በላይ ነባሩን ገንዘብ ይዘው የሚሄዱ ሰዎች የባንክ ሒሳብ እንዲከፍቱ ስለሚገደዱ፣ ከ31 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ሒሳብ በዚህ አግባብ መገኘቱን ገዥው ጠቁመዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው ከዚህ በኋላ በገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ አርብቶ አደርና አርሶ አደር አካባቢዎች፣ አዲሱን ገንዘብ የማሠራጨት ሥራ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር በዋናነት በተሳተፈበት ሒደት ሁሉም የፀጥታ ተቋማት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልል ፀጥታ አካላት ከፖለቲካ አመራሩ ጋር በቅንጅት በመሥራታቸው ያለ ምንም የፀጥታ ችግር የገንዘብ ቅየራው መሳካቱ ተገልጿል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች