Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሰሚ ያጣው ጃንሜዳ

ሰሚ ያጣው ጃንሜዳ

ቀን:

አዲስ አበባ ከነበሯት ቀደምት የስፖርት ማዘውተሪያዎች መካከል በርካታ ታላላቅ አትሌቶችን በማፍራት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ጃንሜዳ፣ ከዓምና ሚያዝያ ወር ጀምሮ የገበያ ማዕከል ሆኖ ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይሁንና ቦታው ከማዘውተሪያነት ባሻገር ሌላም ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ እንደመሆኑ፣ በተለይም አሁን ላይ የማዕከሉ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆን ቦታው ያለበት ሁኔታና ይዘቱ ጭምር በማዘውተሪያ ዕጦት ለሚቸገሩ አትሌቶች ትልቅ ሥጋት ሆኗል፡፡

ቦታው ኅብረተሰቡ በዋናነት ከሚያዘወትርባቸው ስፖርቶች ማለትም ከአትሌቲክስና ከእግር ኳስ በተጨማሪ ቀደምቶቹ የባህል ስፖርቶች የፈረስ ጉግስና የገና ጨዋታ የሚከናወንበት ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው ዓመታዊ የጥምቀት በዓልን ጨምሮ ሌሎችም ዝግጅቶች የሚደረጉበት ሥፍራ እንደሆነም ይታወቃል፡፡

ማዕከሉ ከመደበኛ የውድድር ስፖርቶች በተጨማሪ በርካታ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግና ውድድሮችን በመመልከት ጊዜያቸውን የሚሳልፉበት እንዲሁም ጤናቸውን የሚጠብቁበት መሆኑ ልብ ሊባል እንደሚገባ የሚናገሩ አሉ፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ የአትክልት ተራ የገበያ ማዕከል ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ማዕከሉ የቀድሞ ስያሜውን ማለትም “ጃንሜዳ ስፖርት ማዕከል” የሚለውን መልሶ ለማግኘት ቦታው እየሰጠ ካለው አገልግሎትና ይዞታው አኳያ አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ይነገራል፡፡

በሚሰጠው መጠነ ሰፊ አገልግሎት “ትልቁ የስፖርት አደባባይ” የሚል መጠሪያ እንዳተረፈ የሚነገርለት ጃን ሜዳ፣ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ከሚያሳስባቸው የስፖርት ማኅበራት መካከል፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

“ማዕከሉ ወደ ቀድሞ አገልግሎቱ እንዲመለስ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አቅርበናል፡፡ ቦታው አሁን ላይ ከሚሰጠው የአገልግሎት ብዛት የተነሳ፣ ማዘውተሪያ ለማለት ይከብዳል፤” በማለት የሚናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ምሩፅ፣ “ማዕከሉ በሚያስተናግደው ነጋዴና በተጠቃሚው ማኅበረሰብ ብዛት የተነሳ ብዙ ነገሩ ተበላሽቷል፤” ብለው በዚያ ላይ ለመኖሪያ በሚመስል መልኩ ለገበያ ማዕከሉ አገልግሎት በሚል የተገነቡ ግንባታዎች ለማዘውተሪያ ማዕከሉ ተጨማሪ ሥጋት መሆናቸውን ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ማዕከሉ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጃቸው መደበኛ ዓመታዊ የውድድር መርሐ ግብሮች መካከል፣ በዓመት አንድ ጊዜ ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ ታላላቅ አትሌቶች የሚሳተፉበት አገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር የሚከናወንበት ቦታ መሆኑን ይታወቃል፡፡ የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ማዘውተሪያው ወደ ቀድሞ ይዞታው እንዲመለስ ተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጃንሜዳን በሚመለከት ከሰሞኑ በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ በምክትል ከንቲባው አቶ ጃንጥራር ዓባይ የተመራ ቡድን ጃንሜዳ የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ፣ በጊዜያዊነት የተያዘውን የገበያ ማዕከል በፍጥነት ነፃ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከስምምነት መደረሱን ያሳያል፡፡ ይሁንና በዚሁ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአትሌቲክሱ ቤተሰቦች ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ጃንሜዳ በገበያ ማዕከልነቱ እንደቀጠለ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

“ጃንሜዳ አሁን የሚገኝበት ሁኔታ እጅጉን ያሳዝናል፣ መንግሥት ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር ካለው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት ኅብረተሰብ አቀፍ ስፖርት (ማስ ስፖርት) አንዲስፋፋ ፍላጎት እንዳለው ያበረታታል፤” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በስፖርት ማዘውተሪያነት የቆየውን ጃንሜዳ ማዕከልን ወደ ቀድሞ ስሙና አገልግሎቱ ሊመልስ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...