በምሥረታ ላይ ከሚገኙ ባንኮች መካከል ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችለውን መሥራች ጉባዔ ማካሄዱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ እንዳስታወቀው በ530 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና በ1.2 ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል በይፋ ተመሥርቷል፡፡ ከሌሎች ባንኮች በተለየ በቤት ግንባታና በባንክ ንግድ ሥራዎች ላይ በማተኮር እንደሚንቀሳቀስ በማስታወቅ ወደ አክሲዮን ሽያጭ መግባቱ ይታወሳል፡፡
ባንኩ ሰሞኑን ባካሄደው መሥራች ጉባዔ እንደተገለጸው፣ የምሥረታ ጉባዔው እስከተካሄደበት ድረስ ከስምንት ሺሕ በላይ ግለሰቦችና ኩባንያዎች የባንኩን አክስዮኖች ገዝተዋል፡፡
በመሥራች ጉባዔው ወቅት ባንኩን በቦርድ አባልነት የሚመሩ ዘጠኝ ግለሰቦች የተመረጡ ሲሆን፣ በምሥረታ ሒደት ላይ ከነበሩት የቦርድ አባላት መካከል የተወሰኑት በአዲስ እንዲተኩ ተደርገው፣ ተጨማሪ ተመራጮች መካተታቸው ታውቋል፡፡
በዚሁ መሠረት የቀድሞው የብሔራዊ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና፣ የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ተመርጠዋል፡፡ አቶ ገብረየስ ኢጋታ የጊፍት ሪል ስቴት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ከነባሩ ቦርድ ተመርጠዋል፡፡ ወ/ሮ ፋሲካ ከበደ የቀድሞ እናት ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ውብሸት ዥቅላ (ኢንጂነር)፣ አቶ ከፈኔ ጉርሙ በአዲሱ የቦርድ አባላት ውስጥ ተካተዋል፡፡ አዲስ የቦርድ አባላት ሆነው የተመረጡት ቀሪዎቹ አባላት የኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ ኃላፊ አቶ በላቸው ሁሪሳ፣ ፅዮን አድማሱ፣ ከሬድዋን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተወከሉት ናቸው፡፡
በምሥረታ ሒደቱ በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ ከነበሩትና በተለያዩ ምክንያቶች በቦርድ አባልነት ያልተካተቱት አቶ አመርጋ ካሳ፣ አቶ እሸቱ ፋንታዬ፣ አቶ ዮሴፍ አሰፋና አቶ አርዓያ ገብረእግዚአብሔር መሆናቸው ታውቋል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በፋይናንስ ኢንዱስትሪው አንጋፋ ከሚባሉት ወገን የሚጠቀሱ ባለሙያዎች ናቸው፡፡