የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (ደቨሎፕመንት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን) በቱሉ ሞዬ የጂኦተርማል ኃይል ማመንጨት ሥራ ላይ ለተሰማራው ኩባንያ ድጋፍ የሚውል የ1.55 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ የቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው የልማት ፋይናንስ አቅራቢውና መድን ሰጪው ተቋም፣ በአፍሪካ ለሚኖሩት እንቅስቃሴዎች ሁለት ኢትዮጵያውያንን በመመደብ መሥራት ጀምሯል፡፡ የአፍሪካ የኢንቨስትመንት አማካሪ ሚና እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ የሾማቸው ብሌን አበበ የተባሉ ኃላፊ ሲሆኑ፣ በመላው አፍሪካ ለሚደረገው የኮርፖሬሽኑ እንቅስቃሴ በዋና ዳይሬክተርነት የሰየማቸው አቶ ወርቁ ጎሹ የተባሉ በኢንቨስትመንትና በፋይናንስ መስክ ሰፊ ተሞክሮ ያላቸውን ኢትዮጵያዊ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ተቋሙ በአፍሪካ እ.ኤ.አ. በጁላይ 2020 እንቅስቃሴ በጀመረ ማግሥት ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኦፕሬሽንስ ለተሰኘው ኩባንያ የተደረገው የ1.55 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ፣ አዲስ ለሚገነባው የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዝርዝር የዲዛይን ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል ነው፡፡ የቴክኒክ ዲዛይን ሥራው ተጠናቆ፣ የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ጣቢያውን ለማስገንባት የሚያስችለው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሚሆን ግምገማ እንደሚያካሒድ የልማት ፋይናንስ አቅራቢው ኮርፖሬሽን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ዕውን መሆን ከቻለ በግል ኩባንያ ደረጃ የለማ፣ ለመንግሥትም 50 ሜጋዋት ኃይል በሽያጭ በማቅረብ ቀዳሚው ሊሆን እንደሚችል ከመጠቀሱ በቀር፣ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ግንባታው ሊጠናቀቅ እንደሚችል የሚጠቁም መረጃ አልቀረበም፡፡
ከአዲስ አበባ ከ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከአሰላ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ የተጀመው የጂኦተርማል ወይም ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት እንቅስቃሴ ከተጀመረ ጥቂት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡
ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኦፕሬሽንስ የተሰኘው ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ2017 ተመሥርቶ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመነጨውን የጂኦተርማል ኃይል በሽያጭ ለማቅረብ ስምምነት ፈጽሟል፡፡ ይሁን እንጂ በመጋቢት ወር በተደገ ስምምነት በሁለቱ ወገኖች መካከል ቀድሞ የተደረሰው ስምምነት በአዲስ ተተክቶ ኩባንያው ራሱን ችሎ ኃይል የሚያመርትበትና ለመንግሥት መሸጥ የሚችልበት ተጨማሪ ዕድል ተሰጥቶታል፡፡