Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ባንክ ለትምህርት ግብዓቶች ማሟያና ለገበታ ለአገር ድጋፍ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የብር ኖት ለውጡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ፣ ከ66 ሺሕ በላይ አዲስ ሒሳብ የከፈቱ ደንበኞች ማፍራቱን፣ በአንድ ወር ውስጥ የደንበኞቹን ቁጥር ከሰባት በመቶ በላይ ማሳደግ መቻሉንና 836 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን ገለጸ፡፡

ከብር ኖት ምንዛሪ ለውጡ ጋር በተያያዘ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ እንዳመለከቱት፣ ባንኩ እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ከብሔራዊ ባንክ የተላኩለትን 966.2 ሚሊዮን አዳዲስ የብር ኖቶች በመላው አገሪቱ በሚገኙ ቅርንጫፎቹ በኩል አሠራጭቷል፡፡

የብር ኖቶች ለውጥ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ በተከፈቱት አዳዲስ የባንክ ሒሳቦች ውስጥ 836 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ የተቻለ መሆኑን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ ይህ አፈጻጸም ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ ጋር ሲነፃፀር የ52 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑን ነው፡፡

በተመሳሳይ ይህ የብር ኖት ለውጥን ተከትሎ የተከፈቱ አዳዲስ የሒሳብ ካውንቶች ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ከፍተኛ ዕድገት የታየበት በመሆኑ፣ ከዚህ ቀደም ከተለመደው የሒሳብ አካውንት አከፋፈት አንፃር ሲታይ የ49 በመቶ ዕድገት ያሳየ ስለመሆኑም የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ ማብራሪያ አመላክቷል፡፡ ይህም በአንድ ወር ውስጥ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የደንበኞች ቁጥር በ7.7 በመቶ፣ እንዲሁም የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ደግሞ በሰባት በመቶ እንዳሳደገለትም ታውቋል፡፡

አዲሱ የብር ለውጥ በገበያ ውስጥ ያለው የገንዘብ ዝውውር ሕጋዊ የባንክ ሥርዓትን እንዲከተል ከማገዙ በተጨማሪ፣ ባንኮች የኅብረተሰቡ የቁጠባና የባንክ አጠቃቀም ባህል እንዲዳብር በማስቻል ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረጉን ባንኩ አስታውቋል፡፡

የዚህ የብር ኖት ለውጥ ከኅብረተሰቡ የተሰባሰበውን 1.78 ቢሊዮን ብር ነባሩን የብር ኖት ለኢትየጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዳደረገው የባንኩ መረጃ አመልክቷል፡፡ በተያያዘም ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዘንድሮም የተመሠረተበትን 11ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ ይፋ ለተደረገው ‹‹የገበታ ለአገር›› ፕሮጀክት የአሥር ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡

ከዚህ ሌላ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቀርፆ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ላለው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምና የትምህርት ግብዓቶች ማሟያ የሚውል የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም አቶ ሙሉጌታ ገልጸው፣ ባንኩ የሚያደርጋቸው መሰል ድጋፎች ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን አክለዋል፡፡

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የባንክ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለ 11 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በመላ አገሪቱ በ245 ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች