በአዲስ አበባ ክፍላተ ከተማ የአደረጃጀት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ዛሬ እየመከረ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት 8ኛ አመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ሲሆን ምክር ቤቱ ከሚመለከታቸው ጉዳዮች አንደኛው ፤ የከተማ አስተዳደሩ ስራ አስፈጻሚ አካል የሚያቀርበውን የሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ማዳመጥ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በመቀጠልም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክፍላተ ከተሞች እና ወረዳዎችን እንደገና ለማቋቋም በማቀርብለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት በማካሄድ መወሰን እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ክፍላተ ከተሞችን እና ወረዳዎችን እንደገና ለማቋቋም የሚቀርበው ረቂቅ አዋጅ በአሁኑ ወቅት የሚገኙትን አስር ክፍላተ ከተሞች ቁጥር በአንድ የሚጨምር እንደሚሆን ምንጮቹ ገልጸዋል።
በዚህም አሁን ካለው የቦሌ ክፍለ ከተማ የአስተዳደር ወሰን እና ከየካ ክፍለ ከተማ የአስተዳደር ወሰን ላይ የተወሰኑ ወረዳዎች ተቀንሰው አዲስ ክፍለ ከተማ ሊዋቀር እንደሚችል ምንጮቹ ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ክፍላተ ከተሞቹን እንደገና ለማደራጀት በሚቀርብለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከመወሰን በተጨማሪ ፤ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚያቀሩቧቸውን የተለያዩ እጩ ሾመኞች ገምግሞ ውሳኔ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።