Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከ95 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ያስፈልገዋል የተባለው እንቦጭ አረምን የማስወገድ ሥራ ተጀመረ

ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ያስፈልገዋል የተባለው እንቦጭ አረምን የማስወገድ ሥራ ተጀመረ

ቀን:

የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ ብቻ ሳይወሰን ወደ ሌሎች ሐይቆችና ተፋሰሶች እየተስፋፋ መሆኑንና አፋጣኝ ዕርምጃ ካልተወሰደ፣ ሐይቆችን ለአደጋ ማጋለጥ ብቻ ሳይሆን የዓሳ ምርትንና ቱሪዝምን ጉዳት ላይ እንደሚጥል ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ተከትሎ፣ ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ፣ ከጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ አረሙን የማስወገድ ሥራ በጎንደር ዙሪያ ወረ ምፅረሃ ቀበሌ ተጀምሯል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዳነች ያሬድ (ዶ/ር) በእንቦጭ ላይ የተደረገውን ጥናት በሚኒስትሮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ መንግሥት ውሳኔ እንዲያሳልፍ ማሳሰቢያ ጭምር በማቅረባቸው፣ ሁሉም ከባለድርሻ አካላት ይሁንታ በመገኘቱ የእንቦጭን አረም ማስወገድ ንቅናቄ ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ለመጀመር ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡

‹‹ይኼ ውይይት ዝም ተብሎ እንደዘበት የሚታለፍ ሳይሆን፣ ሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከበጀቱ ላይ የሚያዋጣውን ድርሻ በትክክል ወደ ተግባር በማዋል፣ ሥራው በተባለበት ቀን መጀመር እንዳለበትና በተያዘለት የሥራ ጊዜ መጠናቀቅ አለበት፤›› በማለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም የምክር ቤቱ አባላትን አሳስበው ነበር፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው ውይይትና ስምምነት መሠረት ባለድርሻ አካላቱ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ኢንሳ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲ ፎረም፣ የአብክመ መንገድ ሥራዎችና የጣና ትራንስፖርት ኢንተርፕራይዝን ጨምሮ 14 ተቋማት ንግግራቸውን ወደ ተግባር የሚቀይር ሥራ ከትናንት በስቲያ ጀምረዋል፡፡

በውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰብሳቢ የሆነበትና፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ አካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኮሚቴ አባልነት የሚሳተፉበት፣ እንቦጭ አረምን የማጥፋት እንቅስቃሴ እስከ ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. ድረስ አረሙን ነቅሎ፣ አድርቆና አቀጭጮ የማጥፋት ሥራውን ለማከናወን አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

የእንቦጭ አረም ለጊዜው ጣናንና ሌሎች ሐይቆችን እያዳረሰ ቢሆንም፣ በቀጣይ ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የመድረስ ኃይል እንዳለው፣ ወይም የጣናን ሐይቅ በማድረቅ የታላቁ ህዳሴ ግድብንም የማጥቃት ሒደቱ ስለሚቀጥል፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተረባርቦ ማጥፋት እንዳለበት የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹የህዳሴ ግድቡ ያለ ዓባይ፣ ዓባይ ያለ ጣና አይታሰብም›› በሚል መሪ ቃል የአንድ ወር ንቅናቄ ለማድረግ ከትናንት በስቲያ የእንቦጭ አረም ነቀላ በጎንደር ዙሪያ ወረ ምፅረሃ ቀበሌ ያስጀመሩት ሚኒስትሩ የጣና ሐይቅ ለአደጋ መጋለጡን ጠቁመው፣ ጣና ሐይቅ የውኃ ክምችት ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የአገር ሀብቶችን የያዘ፣ ዓለም አቀፍ ሀብት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሐይቁ ውስጥ ያሉትን የዓሳ ዝርያዎች፣ የቱሪዝም ሀብትና ሌሎችንም ሀብቶችን የሚጎዳ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥትና ሌሎች የክልል መንግሥታትም የድርሻቸውን በመወጣት አረሙን ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡         

የእንቦጭ አረም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምዕራብ ደንቢያ ስምንት ቀበሌዎች፣ ምሥራቅ ደንቢያ አምስት ቀበሌዎች፣ ጎንደር ዙሪያ አምስት ቀበሌዎች፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከሞ ወረዳ አራት ቀበሌዎች፣ ፎገራ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች፣ ደራ ወረዳ አራት ቀበሌዎች፣ ባህር ዳር ከተማ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ባህር ዳር ዙሪያ ሮቢትና አንደንሳ ቀበሌዎች ላይ መዳረሱን የተፋሰስ ልማቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዳነች ያሬድ (ዶ/ር) ለውይይት ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ አስረድተዋል፡፡

እንደ አዳነች (ዶ/ር) ገለጻ፣ የእንቦጭ አረም 4,316 ሔክታር ወይም 196 ኪሎ ሜትር ሸፍኗል፡፡ አረሙን በዘመቻ፣ በሰውና በማሽኖች ለማስወገድ በ30 ቀበሌዎች በእያንዳንዱ ቀበሌ ከ400 ሰዎች በላይ በ30 ቀበሌዎች በቀን 12,000 ሰዎች መሳተፍ አለባቸው፡፡ ለአራት ተሽከርካሪ ማሽኖች ለአንድ ወር የሚከፈል 7,080,000 ብር ያስፈልጋል፡፡ ለ65 ተሽከርካሪዎች ለአንድ ወር 1,430,400 ብርና የሚሰበሰበውን አረም ማቃጠያ ናፍጣ 2,880,000 ብር (ለአንድ ወር) እንደሚስፈልግ ዳይሬክተሯ  አስረድተዋል፡፡

አረሙ ከተነቀለ በኋላ ቦታዎቹ መታጠር ስላለባቸው ለአጥር ማጠሪያ 736,050 ብር፣ ለደኅንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶች 7,516,000 ብር፣ ለኮሮና ቫረስ መከላከያ ግብዓቶች 2,375,000 ብር፣ ለመስክ ተሽከርካሪዎች (በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሟሉ) ለ30 ቀናት እንደሚያስፈልጉ፣ ለመንገድ ጥገና 17,000,000 ብር እንደሚያስፈልግም አዳነች (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ 95,424,316 ብር ወጪ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ 91,259,180 ብር ከክልሎች፣ ከፌዴራል ተቋማት፣ ከምርምር ተቋማትና ከሲቪክ ማኅበራት ወጪ የሚደረጉ መሆኑናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ መሥሪያ ቤቶች አሥር ሚሊዮን ብር፣ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች 19 ሚሊዮን ብር፣ ክልሎች 20 ሚሊዮን ብር፣ ዩኒቨርሲቲ ፎረም 24,709,337 ብር ወጪ ሲያደርጉ፣ ሌሎች ተቋማት ከእያንዳንዳቸው (5 ተቋማት) 3,509,968 ብር ወጪ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡ ባለድርሻ አካላት በራሳቸው የክፍያ ሥርዓት ሲፈጽሙ፣ ሌሎች ግን ለዚሁ ተግባር በተከፈተ ትረስት ፈንድ ሒሳብ ገቢ እንደሚያደርጉም አክለዋል፡፡

የታቀደው በጀት በወቅቱ ተሟልቶ አለመገኘት፣ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት የሚያስፈልገውን ሀብት ይዘው አለመገኘት፣ የተሽከርካሪ እጥረትና የመንገድ አለመጠገን፣ የአረም ማከማቻ ቦታ እጥረት፣ የግብዓት ግዥ ቀልጣፋ አለመሆንና ሌሎችም ተግዳሮቶች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸው አዳነች (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ክትትል ማድረግና ከመጠባበቂያ በጀት እንዲመደብ ማድረግ፣ በትረስት ፈንድ ውስጥ ያለውን 35 ሚሊዮን ብር ወደ ሥራ ማስገባት፣ የመገናኛ ብዙኃን (የመንግሥትና የግል) ሽፋን እንዲሰጡ ማድረግ፣ በዓይነት ድጋፍ ሊሰጡ የሚችሉ የፌዴራል ተቋማት ቃል እንዲገቡ ማድረግ፣ በተዘረጋው ክትትልና ግምገማ ሥርዓት ንቅናቄው በትክክል መተግበሩን ለመከታተል የመንግሥት ውሳኔ ‹‹አሁኑኑ ያስፈልገዋል›› በማለት ባቀረቡት ጥናት ለከፍተኛ የመንግሥት አካላት አስታውቀዋል፡፡ በወቅቱ የተገኙት የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሰጡት አስተያያት፣ ጥናታዊ ጽሑፉን አድንቀውና ደግፈው፣ ለተግባራዊነቱ ሳያድር ሳይውል ወደ ተግባር መገባቱን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...