Friday, October 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትአትሌቲክሱን ያነቃቃው የሰሞኑ ዓለም አቀፍ ውድድር

  አትሌቲክሱን ያነቃቃው የሰሞኑ ዓለም አቀፍ ውድድር

  ቀን:

  በውድድር ድርቅ ተመትቶ የሰነበተው የአትሌቲክሱ መድረክ በጥቂቱም ቢሆን የተስፋ ጭላንጭል የታየባቸው ውድድሮችን በተለያዩ ከተሞች መካሄድ ጀምረዋል፡፡ ዓመታዊ የብሔራዊ ቡድን ሆነ የግል ሻምፒዮናዎችን ማድረግ ያልተቻለባቸው የኮሮና ወረርሽኝ ስምንት ወራት ለአትሌቶች የጭንቅ ጊዜያት ነበሩ፡፡ በሳምንት ሦስትና አራት ቀናት ጠዋትና ማታ በልምምድ ጊዜያቸው ሲያሳልፉ የነበሩት አትሌቶች ባለፉት ወራት በግልና አኅጉራዊ ውድድሮች ላይ መታየት ጀምረዋል፡፡ በበርካቶች ዘንድ ሲጠበቅ ከነበረው የለንደን ማራቶን ጀምሮ ቀድሞ የነበረው የአትሌቲክስ ውድድር ድባብ የመጣ ይመስላል፡፡

  ከፍተኛ ግምት ከተሰጠው የለንደን ማራቶን በኋላ በተለይ የምሥራቅ አፍሪካ የአትሌቲክሱ ፈርጦች ፉክክር ድምቀት ሆነዋል፡፡ በለንደን ማራቶን ሹራ ቂጣታ ከኬንያው ኬፕቾጌ ጋር ያደረገው ትንቅንቅ፣ ለተሰንበት ግደይ በቫሌንሺያው የሰበረችው ክብረ ወሰን እንዲሁም ደግሞ በፖላንድ ጌዲነያ የተደረገው የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና አትሌቲክሱን ያነቃቁ የሰሞኑ ክስተቶች ናቸው፡፡

  በተለይ ጥቅምት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በፖላንድ የተከናወነው የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ምንም እንኳ በግል ያደረጉት ውጤት ባይሳካም በቡድን ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

  አትሌቲክሱን ያነቃቃው የሰሞኑ ዓለም አቀፍ ውድድር

   

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወንዶችም በሴቶች ጥሩ የሚኒማ ሰዓት ያሟሉ አትሌቶችን ማሳለፍ ቢችሉም በውድድሩ ወቅት መውደቃቸውን ተከትሎ ሻምፒዮናውን በተጠበቀው ደረጃ ማሳካት አልቻለም፡፡ ቀድሞውንም ከፍተኛ ግምት ያገኘው የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ክብረ ወሰንን በእጃቸው ማስገባት የቻሉ አትሌቶች በማሠለፉ ነበር፡፡ የዓምናዋ የግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቷ ነፃነት ጉደታ፣ አባበል የሻነህ በሴቶች፣ እንዲሁም በወንዶች ጉዬ አዶላና በ10 ሺሕ ሜትር ልምድ ያካበተው አንዱ አምላክ በልሁ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው አትሌቶች ነበሩ፡፡

  መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊከናወን ታቅዶ የነበረው የፖላንዱ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ቅዳሜ ጥቅምት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡ ኢትዮጵያ በቡድን ሁለተኛ ደረጃ ስትይዝ በግል ግን ኬንያና ዑጋንዳ የበላይነቱን ወስደዋል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንገት ለአንገት ተናንቀው ለሰዓታት ቢያመሩም በተደጋጋሚ መውደቃቸው ውጤቱ እንደተጠበቀው ማሳካት አልተቻለም፡፡ አትሌቶቹ በተደጋጋሚ ለመውደቃቸው እንደ ምክንያትነት የተነሱ በርካታ ጉዳዮችን ቢጠቀሱም ከመላምት ያለፈ ወይም አጋጣሚ ነው ብሎ ከማለፍ ውጪ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ የፖላንዱ ጊዲንያ ከተማ የመሮጫ ጎዳናዎችም አመቺ ያለመሆኑና አትሌቶቹ የተጫሙት ጫማ አመቺ አለመሆኑ እንደ ምክንያትነት ተጠቁሟል፡፡

  አዘጋጁ አካል ሁሉም አትሌቶች የተጫሙትን ጫማ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ናይኪ ቫፖር ፍላይን ጫማ የተጫሙት በወንዶች ዐምደወርቅ ዋለልኝ እና በሴቶች ያለምዘርፍ የኋላ ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

  ዐምደወርቅ 59፡08 ደቂቃ ሦስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በሴቶች ደግሞ ያለምዘርፍ 1፡05፡19 በሆነ የራሷ አዲስ ሰዓት በማስመዝገብ ጭምር ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡ ምንም እንኳ ለውጤቱ ጫማውን እንደ ምክንያት መጥቀስ ባይቻልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አዲስ የሚፈበረኩት ጫማዎች ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መምጣት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ሌላኛው የአትሌቲክሱ አዲስ ክስተትና አትሌቲክሱን እያነቃቃ የመጣው አዲስ ክብረወሰኖች እየተሰበሩ መምጣት ነው፡፡

  በዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናው ከ28 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዑጋንዳዊው ጃኮብ ክፒሊሞ በማሸነፉ አዲስ ታሪክ ለአገሩና ለራሱም ጭምር መጻፍ ችሏል፡፡

  ኪፕሊሞ ርቀቱን 58፡49 በማጠናቀቅ አዲስ ክብረወሰን ሳይቀር ነው ማስመዝገብ የቻለው፡፡ እሱን ተከትሎ ኬንያዊው ኪቢዎታ ኬንዳይ 58፡54 በሆነ ሰዓት ሲያጠናቅቅ ኢትዮጵያዊ ዐምደወርቅ ዋለልኝ በ59፡08 ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡ የመም ንጉሥ በመባል የሚታወቀው ኬንያዊ ጆሹዎ ቺብቼጌ በ59፡21 አራተኛ ወጥቷል፡፡ በቅርቡ እየተመዘገቡ ያሉት የግልም ሆነ የቡድን ውጤቶች ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅት የሚረዱ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኦሊምፒክ ኮሚቴም ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡ እኒዚህም ሻምፒዮናዎች አትሌቶች ምን ዓይነት አቋም ላይ እንዳሉ ለመገምገም እንደሚያስችሉ ይታመናል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img