Thursday, March 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየአንበጣ ወረርሽኝ በምሥራቅ አፍሪካ

የአንበጣ ወረርሽኝ በምሥራቅ አፍሪካ

ቀን:

በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ ከመቼውም ጊዜ የበለጠና ላለፉት አሠርትም ያላጋጠመ ነው፡፡ ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያንና ኬንያን የወረረው የበረሃ አንበጣ መንጋ እስከ ኅዳር ይቀጥላል የሚል ትንበያም አለ፡፡ በተለይ በሶማሊያ አዲስ ዕጭ እየተፈለፈለ መሆኑ የቀጣናውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ፈታኝ ያደርገዋል ሲል ዴይሊማቭሪክ አስፍሯል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2019 መጀመርያ ላይ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ሳይንስን ጭምር የፈተነና፣ በቁጥጥር ሥር ማዋል ባለመቻሉም የሰዎችን በልቶ የማደርና የመኖር ህልውና የፈተነ ነው፡፡ በቀጣናው 39 ሚሊዮን ሰዎችን አደጋ ላይ የጣለው የአንበጣ መንጋ መከሰት ለቀጣናው አዲስ ባይሆንም፣ ችግሩን መከላከል ብሎም መቅረፍ ግን ለዓመታት ሳይቻል ቀርቷል፡፡

በብሔራዊ፣ በክልላዊና በዓለም ማቀፋዊ ደረጃ ያሉ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎችን በአግባቡ አለመተግበርና ለችግሩ መደበኛ በጀት አለመያዝ የአንበጣ ወረርሽኝን ለመከላከል እንቅፋት ከሆኑ ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡ መንግሥታት የሚያስቀምጧቸው ፖሊሲዎችና ሊወስዱ የሚፈልጓቸው ዕርምጃዎችም በሙያው ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች መደገፍ አለመቻላቸው ችግሩን ተቀናጅቶ ከመፍታት አግቷል፡፡

የበረሃ አንበጣ ከፈርዖን ዘመን ጀምሮ አፍሪካንና እስያን ሲመታ እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርዓን ተጠቅሷል፡፡ ዘመን የተሻገረ፣ ተዛማች፣ ምድርን በፍጥነት ምድረ በዳ የማድረግና የምግብ ዋስትናን የመገዳደር አቅም ያለውን አንበጣ የሚማርክ ቴክኖሎጂ ግን እስካሁን ብቅ አላለም፡፡

…. ሲከሰት የኬሚካል ርጭት አሊያም ባህላዊ ዘዴን መጠቀም መፍትሔ አድርጎ የያዘው አሠራርም የበራሪ ነፍሳቱን አውዳሚነት ሊቀንሰው እንጂ ሊገታው አልቻለም፡፡ ይልቁንም አንበጣው በልጦ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ማሳን ሲያወድም ይስተዋላል፡፡

በእንግሊዝ እ.ኤ.አ. በ1945 የፀረ አንበጣ ምርምር ማዕከል ከተቋቋመ ወዲህ እንኳን አንበጣን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወደፊት ሊከሰት ከሚችል የአንበጣ ወረርሽን ለመጠበቅ የተደረጉ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ውይይቶች አራት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም የበረሃ አንበጣ አስተዳደርን ውጤታማነት ፈትኖታል፣ ትኩረት የተነፈገው መሆኑንም ያሳያል፡፡

የበረሃ አንበጣን ለመቆጣጠርም ሆነ ቀድሞ ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብር መሠረታዊ ነው፡፡ ሆኖም መንጋ የሚከሰተው ወቅት ጠብቆ መሆኑ እንዲዘነጋና የትብብር ሥራው እንዲደናቀፍም ምክንያት ሆኗል፡፡  

የአንበጣ ወረርሽኝ በምሥራቅ አፍሪካ

 

በትብብር መሥራት

ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ትንበያን ጨምሮ ተያያዥ ጉዳዮችን የሚሠራ ቀዳሚ ድርጅት ነው፡፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን እ.ኤ.አ. በ1962 የተመሠረተው የምሥራቅ አፍሪካ በረሃ አንበጣ መከላከያና መቆጣጠሪያ ድርጅት በቀጣናው የሚከሰት የበረሃ አንበጣ ትንበያና ቁጥጥር ይሠራል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ጂቡቲ የመሠረቱት ድርጅት ይህንንም ያህል ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡ ድርጅቱ የበረሃ አንበጣን እንዴት መከላከልም ሆነ መቆጣጠር እንደሚቻል በሳይንስ የተደገፈ አሠራርና ዕውቀት አለው፡፡ ሆኖም አሁን በቀጣናው የተከሰተውን ወረርሽን ለመቆጣጠር አልቻለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አባላት ክፍያ ባለመፈጸማቸው ነው፡፡

ኡጋንዳ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና ሱዳን ለድርጅቱ መክፈል የነበረባቸውን  ስምንት ሚሊዮን ዶላር አለመክፈላቸው እንደ መጀመርያ ችግር ይጠቀሳል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ሌላው ፈተና ነው፡፡ መዋጮን መክፈልና በየአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ችግር በጋራ ለመወጣት የፖለቲካ መሪዎች ካልተባበሩ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡ ውጤታማ የአንበጣ ቁጥጥር ሥርዓትም ሰዓቱን የጠበቀና የተባበረ ምላሽ ይፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንቫይሮመንት ፖሊሲ ቢኖርም ውጤታማ ለማድረግ የሀብት እጥረት፣ የመተግበርና የባለሙያዎች ተሳትፎ ይጎድለዋል፡፡ በሶማሊያ ያለው ግጭትና አለመረጋጋት በተወሰኑ አካባቢዎች የሚራባውን አንበጣ ለመከላከል እንቅፋት ሆኗል፡፡ ኬንያ የአንበጣ መንጋውን ብትቆጣጠርም ከመጀመርያው በሙሉ አቅሟ ዝግጁ ባለመሆኗ ዋጋ ከፍላለች፣ ለሌሎችም ምክንያት ሆናለች፡፡ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካና በየመን እየተራባ የሚገኘው አንበጣ በሁለተኛ ዙር ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ሶማሊያና ሰሜን ኬንያ በመሰደድ ሥጋት ሆኗል፡፡ የሚደረገው ርብርብም አላበቃም፡፡

በቅርቡ ፋኦ ያወጣው መረጃ ደግሞ በርካታ መንጋዎች እየተፈጠሩ የተገባዙና ከሶማሊያ ቀይ ባህር አቅራቢያ እየተነሱ ነው፡፡ ኬንያ በኅዳር አጋማሽ በመንጋው የምትጠቃ ቢሆንም፣ በ2019 ካስተናገደችው የከፋ አይሆንም፡፡ መቀመጫውን በኬንያ ያደረገው ኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያና ትግበራ ማዕከል አንበጣን ለመከላከል የሳተላይት ቴክኖሎጂ እየተጠቀመ ነው፡፡ ይህ በቀጣናው አንበጣ ከመራባቱ በፊም ሆነ ከተራባና መንጋ ከሆነ በኋላ ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡

ከ2019 ጀምሮ በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በቀጣናው የምግብ ዋስትናን ፈተና ውስጥ ይከታል ተብሎ ተሠግቷል፡፡ በቀጣናው ለረዥም ጊዜ አብዝቶ የጣለው ዝናብ ለአንበጣው መራባት ዕድል መስጠቱ ሌላ የአንበጣ ትውልድ ያስከትላል ተብሏልም፡፡

በመሆኑም ችግሩን በአንድ አገር ጥረት ብቻ መወጣት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ መንጋውን ሆነ መፈልፈሉን መቆጣጠር አንበጣውን ለማጥፋት አያስችልም፡፡ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ ብሎም የመን ድረስ ዘልቆ በትብብር መሥራት ግድ ነው፡፡   

ፋኦ እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2020 ላይ ያስቀመጠው ትንበያ ኢትዮጵን በበረሃ አንበጣ በአደገኛ ሁኔታ ከሚመቱ አገሮች ተርታ አሠልፏታል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለምግብ እጥረት ይጋለጣሉ ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ 8.5 ሚሊዮን፣ በደቡብ ሱዳን 6.5 ሚሊዮን፣ በሱዳን 5.5 ሚሊዮን በኡጋንዳ 1.4 ሚሊዮን፣ በሶማሊያና በኬንያ በእያንዳንዳቸው 1.3 ሚሊዮን፣ በታንዛኒያ አንድ ሚሊዮን እንዲሁም በጂቡቲ ሩብ ሚሊዮን ሕዝቦች በ2020 የምግብ ዋስትና ችግር የሚገጥማቸው ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...