Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከሞተ ሰው ኩላሊት መቀበል የሚቻልበትን መንገድ በሕግ ማዕቀፍ እንዲገባ ጥረቶች አድርገናል›› አቶ ሰለሞን አሰፋ፣ የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ

የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጋቸው ሕሙማንን ለከፍተኛ ችግርና እንግልት የዳረገው የአገልግሎት አሰጣጡ አነስተኛና ውድ መሆን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካቶች የኩላሊት እጥበት በሚፈለገው መጠን አያደርጉም፡፡ የሚያደርጉትም ቢሆኑ ጥሪታቸውን እየጨረሱ በዕርዳታ ላይ ሲመረኮዙ ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶች ከአቅም በላይ ሆኖባቸው ሲሞቱም ይስተዋላል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍና በተቻለ መጠን ለመደገፍ የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ ሰለሞን አሰፋ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የኩላሊት እጥበትና ታካሚዎችን አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት እንዴት ተመሠረተ?

አቶ ሰለሞን፡- የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የተመሠረተው በ43 የኩላሊት ሕመምተኞች አማካይነት ነው፡፡ ተቋሙም በ2003 ዓ.ም. ከጤና ሚኒስቴር ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ ተቋቁሟል፡፡ ሕሙማኑ ማኅበሩን ያቋቋሙት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ውጭ አገር እየተመላለሱ ሕክምና ሲያደርጉ ለአላስፈላጊ ወጪ በመዳረጋቸው ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ማቋቋም ያስፈልጋል ብለው ስላመኑ ነው፡፡ በዘውዲቱ ሆስፒታል ላይ የሚገኝ አሮጌ ሕንፃን እንደ አዲስ በመገንባት ለዳያለሲስ (ለኩላሊት እጥበት) ምቹ ተደርጎ ተሠርቷል፡፡ ሕንፃውም ላይ ወደ 36 ማሽን የሚይዝ ማዕከል በማቋቋም ለዘውዲቱ ሆስፒታል አስረክበናል፡፡ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመነጋገርም በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎቱ እንዲሰጥ ማድረግ ችለናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ሦስት የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ከክልልም የሚመጡ ሰዎች በቀላሉ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ በየክልሉ ከሚገኙ ጤና ኮሌጆች ጋር በመነጋገር 14 በሚሆኑ የክልል ከተሞች ላይ ዳያለሲስ የሚያደርጉበትን ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህም በመጠኑም ቢሆን የኩላሊት ሕመምተኞችን ችግር መቅረፍ ችሏል፡፡  

ሪፖርተር፡- አገልግሎቱን በምን መልኩ ነው እየሰጣችሁ ያላችሁት?

አቶ ሰለሞን፡- በኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ ለኩላሊት ሕመም ተጋላጭ በመሆኑ ነፃ ሕክምና ለመስጠት የሚከብድ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ለሚገኙ የኩላሊት ሕሙማን ነፃ የኩላሊት እጥበት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ቦታ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ በመጠየቅ ላይ ነበርን፡፡ ይህም ነገር ተሳክቶልን ባምቢስ አካባቢ ላይ 1,410 ካሬ ቦታ ማግኘት ችለናል፡፡ በዚህም ቦታ ላይ ትልቅ ማዕከል በማቋቋም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማስፋት የምንሠራ ይሆናል፡፡ በቅርቡም የቦታ ይዞታውን ካርታ ተቀብለን ግንባታ የምንጀምር ይሆናል፡፡ የግንባታውን ወጪ ቃል የገቡልን ሰዎች ሙሉ ለሙሉ እንደሚሸፍኑልን ነግረውናል፡፡ ይኼ ማዕከል ከተቋቋመ አብዛኛውን የኩላሊት ሕሙማን የነፃ አገልግሎት የሚያገኙበት መንገድ ውስን አይሆንም፡፡ ከዚህ በፊት 105 ለሚሆኑ ሕሙማን ነፃ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ ይህንንም ለማስቀጠል እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የበጎ አድራጎት ሥራውንስ በጋራ ተቀናጅታችሁ የምትሠሩት ከማን ጋር ነው?

አቶ ሰለሞን፡- ይህንን ሥራ አብረውን በመሆን እየሠራን ያለነው ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡ ከክልል ከሚገኙ ጤና ቢሮዎች ጋርም አብረን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በገንዘብ ድጋፍ በኩልም ባንኮች ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱልን ነው፡፡ እነዚህም ባንኮች 17 ሲሆኑ፣ ስምንቱ በአሁን ሰዓት በየወሩ ድጋፍ እያደረጉልን ይገኛሉ፡፡ አምስት ባንኮችም በቅርቡ በየወሩ ለመስጠት ቃል ገብተውልናል፡፡ ቀሪዎችም ባንኮች ድጋፋቸው እንዳይለየን ሌት ተቀን በመመላለስ ድጋፉን እንዲቀጥሉበት ጥያቄ እያቀረብን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም በየወሩ በቋሚነት ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ ቢጂአይም በየወሩ ድጋፍ እንደሚያደርግልን ቃል ገብቶልናል፡፡ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በድርጅቱ ላይ ያሉት ችግሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ሰለሞን፡- በበጎ አድራጎት ድርጅቱ ላይ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ በተለይም የማሽን እጥረት መኖሩ ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡ በዘውዲቱ ሆስፒታል ላይ ለዳያለሲስ በምቹ ሁኔታ የተዘጋጀ ሕንፃ ላይ ስድስት ማሽኖች ብቻ ነው ያሉት፡፡ ማሽኖቹ ላይ የመበላሸት ሁኔታ ይታያል፡፡ በግል ተቋሞች ላይ ግን እስከ 37 ማሽን ያለባቸው ሆስፒታሎች አሉ፡፡ የመንግሥት ሆስፒታሎች ላይ ግን ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ከዚህ በፊትም ለማሽን መግዣ የሚሆን በጀት ተመድቦ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ምን ላይ እንደተደረሰ አልተነገረንም፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ውስጥ ላይ ስምንት ማሽን ብቻ ነው ያለው፡፡ ይኼም የሕሙማን ቁጥርና የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ተመጣጣኝ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጤና ጣቢያዎች ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት ማሽኖችን በማስገባት የአሠራር ሒደቱን ማስፋት አለበት፡፡ መንግሥትም ከግል ተቋሞች ጋር በመነጋገር ያለውን ክፍተት መሙላት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊትም ማሽኖቹን ለመግዛት 12 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ነበር፡፡ ነገር ግን የተመደበው ገንዘብ የት እንደገባ አይታወቅም፡፡ በ2013 ዓ.ም. ግን ጠንከር ባለመልኩ ለመሥራት በእኛ በኩል ዕቅድ ይዘናል፡፡ ከግብዓት አኳያም በጣም እጥረት አለ፡፡ የውጭ ምንዛሪም እጥረት በሚፈጠርበት ወቅት ተቋማችን ላይ ትልቅ ችግር ነበር፡፡ ለሕሙማን የሚሰጥ መድኃኒት ላይ ከፍተኛ የሆነ እጥረት መኖሩ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታትም ከሞተ ሰው ኩላሊት መቀበል የሚቻልበትን መንገድ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ገብቶ እንዲሠራበት ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን አድርገናል፡፡ በቀጣይም በዚህ ጉዳይ ላይ የምንሠራበት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበረሰቡ ከበሽታው አስቀድሞ እንዲከላከል ምን ታደርጋላችሁ?

አቶ ሰለሞን፡- ሰዎች ራሳቸውን ከበሽታው እንዲጠብቁ ለማድረግ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የተለያዩ ምክሮችን ሰጥተናል፡፡ ማንኛውም ሰው በአቅራቢው በሚገኝ ሆስፒታል ሄዶ የኩላሊቱን ደኅንነት ደረጃ እንዲያውቅ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በትምህርት ቤቶችና በድርጅቶች ላይ በመሄድ ስለ ኩላሊት ሕመም አስከፊነት በመንገርና በማስገንዘብ ራሳቸውን እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራም ሠርተናል፡፡ መንግሥትም ጤና ተኮር ትምህርት ላይ በማካተት የኩላሊት ሕመም አስከፊነትን ሰዎች እንዲረዱ የምንሠራበትን መንገድ እያመቻቸን ነው፡፡ ኩላሊታቸው ከጥቅም ውጪ የሆኑ ሰዎች ምን ዓይነት ምግብ መመገብ እንዳለባቸው ሐኪሞችን በመጋበዝና ቃለ መጠይቅ በመሥራት እንዲሁም ዶክመንተሪ በማዘጋጀት ለተለያዩ ክሊኒኮች ዳያለሲስ እንዲያደርጉ እያደረግን ነው፡፡ ያገኙትን ዕውቀት ቤታቸው ወስደው ለቤተሰቦቻቸው እንዲነግሩም መረጃ ሰጥተናል፡፡ ፊልም ላይም በማካተት የበሽታውን አስከፊነት ማኅረበረሰቡ እንዲረዳ ለማድረግ ጥረናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከክልሎች ጋር ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ሰለሞን፡- ከክልል ጤና ተቋማት ጋር በመነጋገር አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ሕክምናውን የሚያደርጉ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሕክምናው እንዲሰጥ እያደረግን ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ላሉ ሰዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ ነን፡፡ በዚያው አካባቢ ላይም የሕክምና አገልግሎቱ መሰጠቱ ሕሙማን ለትራንስፖርት እንግልት እንዳይዳረጉ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋርም በመነጋገር በጤና ትምህርት እንዲካተት እያደረግን ነው፡፡ በጅማ የኩላሊት ሕሙማን ሕክምና በነፃ እንዲሆን ከከንቲባው ጋር ንግግር አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡-  በቀጣይስ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

አቶ ሰለሞን፡- በቀጣይነት የምንሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ ለመቀጠል 17 ባንኮችን በዕርዳታው ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ የምንሠራ ይሆናል፡፡ አብዛኛው የኩላሊት ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙና በዘርፉ ላይ ያሉትም ችግሮች እንዲቀረፍ የበኩላችንን እንወጣለን፡፡ መንግሥትም የግብዓት አቅርቦት ችግርን ፈትቶ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባል፡፡ እንደዚህ ከሆነ የኩላሊት ሕሙማን ቁጥር አነስተኛ የሚሆንበት መንገድ ይፈጠራል፡፡ የማሽን እጥረት እንዳይኖር ውጪ ከሚገኙ በጎ ፈቃደኞች ጋር ተነጋግረን ማሽን የምናገኝበትን መንገድ እያመቻቸን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...

የሳባ መንደር

ሼባ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሼባ/ሳባ የጉዞ ወኪል በ1960ዎቹ የተመሠረተና በርካታ እህት ኩባንያዎችን ያፈራ ነው፡፡ ሼባ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ...