Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከብሔርተኝነት አዙሪት መውጣት ግድ እየሆነ ነው!

ከብሔርተኝነት አዙሪት መውጣት ግድ እየሆነ ነው!

ቀን:

በገመቹ ዋቅጅራ

እንደ ልማድ ሆኖብን ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት›› ምንጥርሴ፣ ቅብጥርሴ ማለት ይቀናናል፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ገደማ በፈረጠመው የጎሳ ፌዴራሊዝም ግን እንኳንስ ሕዝብ ለሕዝብ ተባብሮና ተማምኖ ሊኖር፣ እስካሁንም ከመንደሩ አጀንዳ ሊወጣ ያልቻለው ትውልድ ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡

በዚህም በተለያየ ጊዜ ከተከሰተ ግጭትና የንፁኃን ዕልቂት ባሻገር፣ በትንሽ በትልቁ ውዝግብ መነሳቱና በብሔር ጠገግ ተሠልፎ ለመባላት መሰናዳቱም ዘላቂ መፍትሔ አላገኘም፡፡ አገራዊ ማኅበረ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሩም ሲዳከም በመቆየቱ፣ አብሮነቱ ተቀዛቅዞ ነበር የቆየው ማለት ስህተት የለውም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንዲያም ሆኖ በዚህ ጊዜ ውስጥ “የአንድ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ነን” የምንል ተስፈኞች ቁጥራችን ትንሽ አልነበረም፡፡ ሐሳቡ ተወደደም ተጠላም ግን  የማይጨበጥ ጉም፣ በዕውን የማይታይ ህልም ወደ መሆን ከተቃረበበት አዘቅት ለመውጣት ገና ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነው፡፡ ማሟረት ካልሆነ ከክፉ አገራዊ ፈተና በፊት፣ አንዳች ዓይነት የጋራ መፍትሔ ካልተበጀም ዕዳችን መክፋቱ አይቀርም፡፡

ለዚህ ደግሞ የፊተኛው ኢሕአዴግም ይባል፣ ከጎሳ ፌዴራሊዝም አንቀልባ ላይ ለመውረድ ፍላጎትም አቅምም ያላሳየው ብልፅግና ፓርቲ የሚጓዝበትን ሐዲድ ማስተካከል ግድ ይለዋል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችም ቢሆኑ ቅኝታቸውን ሊፈትሹ ግድ ነው፡፡ እንደ ሕዝብም ለአፍ ያህል ‹‹ኢትዮጵያና ለዘመናት የተሳሰሩ ሕዝቦች›› እየተባለ፣ ዕሳቤውን በገቢር ዕውን ለማድረግ መንገዳገዳችን መፍትሔ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

አሁንም የአንድነት ኃይሉ ይጠናከር!

በየትኛውም ዓለም ቢሆን ቅድሚያ ራስን፣ ሲቀጥል ቤተሰብንና በማንነት የሚጋራ ማኅበረሰብን ማቅረብ ወይም እንደ መገለጫ መቁጠር የተለመደ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የትስስር መፈላለግ ግን እንደ አገር አብረው የሚኖሩ ሕዝቦችንም ሆነ የሰው ፍጥረትን እንደ ራስ ከመቁጠር የሚነጥል ግን ሊሆን አይገባም፡፡

በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት በአገራችን ከሕዝቦች አብሮነትና አንድነት ይልቅ፣ በጠባብነት መንፈስ የራስ ዘውግ መፈለግና ማስቀደም በርትቶ መቆየቱን አንስተናል፡፡ ምናልባት በታሪክ አጋጣሚ በመላው አገሪቱ ተበትኖ፣ ተዋልዶና ተሳስሮ የኖረው የአማራ ሕዝብና ኅብረ ብሔራዊነት ያለው ሌላው ማኅበረሰብ ካልሆነ ብዙው ብሔረሰብ የማንነት ፖለቲካን ማስቀደሙ ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአንድነት ኃይልና ኢትዮጵዊ ብሔርተኛ የሚባለው ወገንም ጠቀመውም ጎዳውም፣ ቢያንስ ራሱን ለመከላከልና ወገኑን ለመታደግ  የሚያስችል ብሔርተኝነት እየገነባ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ለዘመናት ‹‹ኢትዮጵያ›› እያለ ወታደርና አገር አቅኚ በመሆኑ ያተረፈው ነገር የሌለው ይህ ሕዝብ፣ እንዲያውም በአንዳንድ ሸውራራ ፖለቲከኞች በአገዛዞችም ስም እንደ ጠቅላይ (ጨቋኝ) ተቆጥሮ እስከ መገለል የደረሰ ነው፡፡ በዚህም ዛሬም ድረስ ዋጋ እየከፈለ መሆኑም ሊካድ አይችልም፡፡

ይህ ሰፊ ሕዝብ ከአገራዊ አንድነት ዕሳቤ ባሻገር፣ የተበታተነ አስተሳሰብ እንዲይዝም የተዘመተበት ጊዜ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን (አብንም በመፈጠሩ ይሁን አላውቅም) አመርቂ ዴሞክራሲ ብሔርተኝነትን እየገነባ ይሆን ያስብላል፡፡ ማንም ይምጣ ማንም ይኼድ በአማራነትና በብሔር ጥቅሙ ላይ ማተኮሩ ችግር ባይሆንም፣ ከአገራዊ አንድነት ዕሳቤው መናጠብ እንደሌለበት ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አንድነትን በመስዋዕትነቱ ቢያጠናክርም ነው ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆነው፡፡

በእርግጥ የዘር ፖለቲካ ለ27 ዓመታት ሲጫንብን፣ እንደ አገር ያልተበተነው በሕዝቡ የማንነት መጋመድ መሆኑን ለመረመረ ለማንም ቢሆን ብሔርተኝነቱ ከአገራዊ አንድነቱ መብለጥ እንደሌለበት ያሳምናል፡፡ ብዙው ሕዝብ በልዩነት ላይ የተመሠረተ አክራሪ ብሔርተኝነት ማቀንቀን የጀመረው ኢፍትሐዊነትና የአገዛዝ ብልሽት ስለነበር እንጂ፣ ከዚህ በኋላ ግን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔራዊነትን ከማጠናከር የተሻለ መንገድ ሊኖር አይችልም፡፡ 

ለዚህ አንዱ አብነት ኃይሌ ወልደ ሚካኤል (ዶ/ር) የተባሉ ምሁር ‹‹አብሮነት በኢትዮጵያ›› (1994 ዓ.ም.) በሚል ርዕስ አነስ ያለ ታሪካዊ ጥናት ላይ የሚያተኩር  መጽሐፋቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ መጽሐፍ ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች ቀደምት ታሪክ፣ አብሮነትና አኩሪ ዕሴቶች ጠቃሚ ሐሳቦችን የሚያነሳ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለመነጣጠል የሚከብድ ጠንካራ የማንነት መሰናሰል እንዳለን የሚያስረዳ ነው፡፡

ከመጽሐፉ በአጭሩ የተወሰደው ሐሳብም ሁሉም የአገራችን የጎሳና የብሔር ፖለቲከኞች መንገድ የብዙኃኑን ተቀባይነት የማያገኝና ፉርሽ መሆኑን እንደሚያሳይም ዕሙን ነው፡፡ በአክራሪ ፖለቲከኞች ሴራ እየተመረዙ እንጂ የአገራችን ሕዝቦች ለዘመናት የገነቡት ትስስር፣ መስተጋብርና ውህደት ሲፈተሽ፣ ኢትዮጵያዊያን ምንም ያህል ሴራ ቢጎነጎንባቸው፣ ለአፍታም የማይለያዩና የተሳሰሩ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያንፀባርቃል፡፡ እንዲህ ይላል፣ ‹‹ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች መስተጋብር ስንጠቅስ ጥንት የአክሱም መንግሥት በዮዲትና በቤጃዎች ሲደመሰስ፣ አክሱማውያን ወደ ሰሜንና ወደ መሀል አገር ፈልሰው ኑሮ መመሥረታቸው በቅድሚያ ይወሳል፡፡ የዛጉዬ መንግሥትም ሮሃ ላይ ከተመሠረተ በኋላ የአክሱማውያንን ዕደ ጥበበኞችን ስቧል፡፡

‹‹የሸዋ መንግሥት በጀመረው የመስፋፋት ጉዞ ደግሞ ቋሚ የጦር ሠፈሮችና የአካባቢ ጋሻ ጃግሬዎች በሐረር፣ በሶማሌ በአፋር፣ በደዋሮ፣ በባሌ በሃዲያ፣ በከምባታ፣ በወላይታ፣ በጋሞጎፋ በሸዋ፣ በቢዛሞ፣ በዳሞት፣ በእናርይ፣ በጉራጌ ወዘተ. እንደነበሩትና በዚህም ሰፊ መስተጋብር እንደተፈጠረ ይታወቃል፡፡

‹‹ዛሬ ድረስ ወላይታ ውስጥ ትግሮ (ትግሬ)፣ ቡልጎ (ቡልጋ)፣ መንዞ (መንዝ)፣ ቄሶ (ቄስ)፣ መራቤቶ (መረሐቤቴ) ወዘተ. የሚባሉ ጎሳዎች አሉ፡፡. . . ከምባታ ውስጥ ኦያ የሚባለው ጎሳ ከጎንደር ከመጣ ሀመልማል ሠራዊት የሚመነጭ መሆኑ ሲታወቅ፣ ሃድያ ውስጥም ጋስ አማራ (የጥንት አማራ) የሚባል ጎሳ እንደነበር ተመዝግቧል፡፡

‹‹የጉራጌም ሕዝብ በአመዛኙ፣ የእናርያ፣ የሲዳማ፣ የሐረር፣ የኦሮሞና የሃዲያ ሕዝቦች መስተጋብር ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል በ16ኛው ምዕተ ዓመት መጀመርያ ሩብ አጋማሽ ግራኝ መሐመድ ከሐረር ተነስቶ ከብዙ ሕዝቦች የተውጣጣ ሠራዊት መሥርቶ ኢትዮጵያን እንዳጥለቀለቀ ይታወሳል፡፡

‹‹ከግራኝ ሽንፈት በኋላ የግራኝ ሠራዊት እንደሟሸሸ ቢታወቅም፣ ጦርነቱ የፈጠረው መስተጋብር የኦሮሞ ሉባዎችን ወደ ባሌ፣ ደዋሮ (አርሲ)፣ ሐረር፣ ሸዋ፣ ቤተ አማራ (ወሎ)፣ ጎንደር፣ ከፋና ጎጃም አሰባስቧል፡፡ በዚህ ምክንያት ኦሮሞዎች ከነባር የየአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር ተወራርሰዋል፣ ተዋህደዋል፡፡

‹‹እዚህ ላይ የባሌ፣ የደዋሮ፣ የዳሞት፣ የቤዛም፣ የእናርያ፣ የሃዲያ (በከፊል)፣ የጉራጌ (በከፊል) ሕዝቦች ማንነታቸውን ትተው ኦሮሞዎች ሲሆኑ፣ በተለዋጩ ወደ ቤተ አማራ፣ ጎንደር፣ ትግሬና ጎጃም የዘለቁ ኦሮሞዎች ደግሞ ማንነታቸውን ትተው አማራዎችና ትግሬዎች ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል የማዕከላዊ መንግሥት ግዛት አካል የነበረው ባህረ ነጋሽ (የዛሬው ትግራይና ኤርትራ) ብዙ የጎንደር፣ የጎጃምና የቤተ አማራ ሕዝቦችን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ስቧል፡፡ ስለሆነም በኤርትራ ውስጥ ሐማሴን የሚባለው ሕዝብ በአመዛኙ ከጎንደር የፈለሰ ሕዝብ መሆኑ ታውቋል፡፡. . . ›› (ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም ገጽ 60 ከተጠቀሰው ይኼው ይበቃል፡፡)

እንግዲህ ላለፉት በርካታ መቶ ዓመታት በጠንካራ አገረ መንግሥትም ይሁን፣ በየአካባቢው መሳፍንቱ እየተነሳ ሕዝቡ ሲዋሀድና ሲዋለድ ዘልቋል፡፡ ታዲያ ይህን አብሮነት የመሠረተውን ውህድ ማኅበረሰብ በዘር ፖለቲካ ለመነጣጠል መጣደፍ ይሻላል? ወይስ ዴሞክራሲንና ፍትሕን እያረጋገጡ አንድነቱን ማጠናከር? መልሱን ለአንባቢያን እተዋለሁ፡፡

ከእውነታው አንፃር ግን ከተጠመደልን የዘረኞችና የጠባቦች የኪሳራ መንገድ ቀስበቀስ በመውጣት፣ በዜጋ የፖለቲካ ትግል በኅብረ ብሔራዊ አንድነት የምታኮራ አገር በጋራ ለማስቀጠል መትጋት ነበር የሚበጀው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያለውን ማኅበረሰብ ማነቃቃትና መጠናከር አንዱ መንገድ መሆን አለበት፡፡

ያም ሆኖ ግን ስለምን ይሆን በተለይ የኦሮሞ ጎምቱ ፖለቲከኞች (የትግራዮቹ እርሾ እንዳለ ልብ ይሏል) ባላቸው ተፅዕኖ ልክ ይህን መንገድ አጠናክረው ለመቀጠል ተነሳሽነት ያጡት ብሎ በድፍረት መጠየቅ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ራሳቸውን ፈትሸው ወደ መሀል እንዲመጡም በተናጠል አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ፡፡

አክራሪ ብሔርተኛው ይመለስ!

 1 እነ ፕሮፌሰር መረራ

ቀደም ሲል ጀምሮ የፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አድናቂ ነበርኩ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባያስተምሩኝም በ1990ዎቹ መጀመርያ ላይ ያስተማሯቸውና የመመረቂያ ጽሑፍ ያማከሯቸውን አንዳንድ ጓደኞቼም ስለእርሳቸው የሚሉኝን ስሰማ ቆይቻለሁ፡፡ በጋዜጠኝነት ሕይወቴም አንድ ሁለት ጊዜ ቃለ ምልልስ ያደረኩላቸው ሲሆን፣ በፓርላማ የሚያነሱትን ደፋርና ምሁራዊ ሐሳብም በአድናቆት ነበር የምከታተለው፡፡ እስካሁን ድረስም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ሚና በሚገባ እረዳለሁ፡፡

ምሁሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አክራሪ የሚባሉ የፖለቲካ ልሂቃንን ኦፌኮ በተባለው የፖለቲካ ማኅበራቸው ካቀላቀሉ ወዲህ የአቋም ለውጥ ያሳዩ ቢመስልም፣ በሚዛናዊ የፖለቲካ አካሄዳቸውና በእኩልነት ላይ የተመሠረተች አገር ግንባታን ያስቀድሙ እንደነበር መናገር ይቻላል፡፡ ይህም በ2008 ዓ.ም. ባሳተሙት ‹‹የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችና የሚጋጩ ህልሞች›› ላይ ካቀረቧቸው ጥልቅ ትንተኔዎች ይታይ የነበረ ነው፡፡

‹‹በተቃዋሚው ጎራ ብዙ ሳይንቀሳቀስ እያየሁት ያለሁት የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን ፖለቲካ ነው፡፡ የሁለቱም ልሂቃን ፖለቲካ በዋናነት በሁለት ጫፎች ላይ ቆሞ ገመድ ከመጎተት ወደ መሀል መጥቶ የጋራ ዴሞክራቲክ አጀንዳ መቅረፅ አላስቻላቸውም፡፡ ብዙዎቹ ሒሳብ የማወራረድ ፖለቲካን የዛሬ 30 እና 40 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ከ130 እና 140 ዓመታት በፊትም ወስዶ ማወራረድ እየተመኙ ነው (ይህን የንትርክ ጭቃ ግን እርሳቸውም አሁን እንደገቡበት ልብ ይሏል!)፡፡

የኦሮሞ ልሂቃን ዋናው ችግራቸው የጋራ ፖለቲካ አጀንዳ ለመቅረፅ ከመጣር ይልቅ፣ ለብቻቸው የሚያደርጉትን ትግል የመንግሥተ ሰማያት አስተማማኝ መንገድ  አድርገው ማምለካቸው ነው፡፡ የአማራው ልሂቃን ዋና በሽታቸው ደግሞ በዋናነት በአማራው ልሂቃን የተፈጠረችው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደዚያው ትቀጥል፣ መቀጠልም ትችላለች የሚል ነው፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት የአገሪቱ ፖለቲካ ዋናው የቀውስ ምንጭም ኢትዮጵያ እንደነበረች መቀጠል ያለመቻሏ መሆኑን በውል መገንዘብ ያቃታቸውም ይመስለኛል፡፡

የሁለቱም ልሂቃን ያለፉት 40 ዓመታት ጉዞ ሌኒን እንደሚለው ‹‹የሞኝ ሩጫ ፍጥነትን አይጨምርም›› ዓይነት ነው፡፡ በእኔ እምነት ሁለቱም ከታሰሩበት የታሪክ እስር ቤት ወጥተው በጋራ የዴሞክራቲክ አጀንዳ ላይ ተስማምተው በመሀል መንገድ ላይ ካልተገናኙ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአሁኑ ትውልድ ዘመን ፈቀቅ የሚል አይመስለኝም፤›› ነበር ያሉት፡፡ (ገጽ 11 ላይ)

እንግዲህ በዚህ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ የጎመራውንና ለመላው የአገራችን ሕዝቦች ለውጥ የፈነጠቀውን ብልፅግናም ይባል፣ የተሃድሶው ኢሕአዴግ የለውጥ ኃይል ጥረት የሚዘምቱበት የታሪክ እስረኞች መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ አለፍ ሲልም ለውጥ አደናቃፊዎችና የሁለቱ ወሳኝና ሰፊ ማኅበረሰብ ጥምረት የሚያስበረግጋቸው ዘራፊዎች ናቸው ቢባል ስህተቱ ምን ላይ ነው?

ስለዚህ እንደ ዛሬ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችን የተሻለች አገርን ለማስተላለፍ እንደሚመኝ ዜጋ፣ ነቅተን መነጋገርንና አገራዊ መፍትሔ ማመንጨትን ቸል ማለት አይገባም፡፡ መነጋገርና መቀራረብንም ማበረታታት ነው የጋራ መፍትሔው እንጂ፣ ፕሮፌሰር መረራም ሆኑ ሌሎች ዛሬ እያሳዩት ያለው አቋም፣ ዘላቂ አገራዊ መፍትሔ አምጭ ሊሆን አይችልም ባይ ነኝ፡፡  

2 እነ አቦ ለማ 

የቀድሞ የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበርና ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት፣ በኋላም የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ኦቦ ለማ መገርሳ ለውጡ የፈጠራቸው፣ ተወዳጅ የአገራችን መሪ ተብለው ነበር፡፡ አቦ ለማ በቢሮ ኃላፊነት፣ በፀጥታና በአስተዳደር ዘርፍ መሪነት ለረጅም ጊዜ አገራዊ ግዴታቸውን ሲወጡ የቆዩ አመራር መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የተሃድሶው ኢሕአዴግን (በተለይም ቲም ለማ) በመሪነት ደረጃ ወደፊት ካመጡት አመራሮች ቀዳሚውም ነበሩ፡፡

መሪን የሚያወጣው ሕዝቡ እንደ መሆኑም ለሰውዬው፣ ቄሮን ጨምሮ የተማረው የኦሮሞ ልሂቃንና የተገዳዳሪ ፖለቲካ መሪዎች ከፍ ያለ ድጋፋቸውን ሰጥተዋቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሌላውም ሕዝብ አክብሮት እየቸረው የመጣበት ዋና ምክንያት፣ የአገሪቱን ሕዝቦች በአንድነት አስተሳስረው ለመቀጠል ባሳዩት ምልክት ነበር፡፡ 

ከዚህም በላይ እነዚህን ጎሙቱ ሰው ሕዝቡ ያከበራቸው፣ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ን ለኦዴፓ ሊቀመንበርነት፣ ብሎም ለኢሕአዴግ መሪነትና ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መርጠውና አስመርጠው የምልዓተ ሕዝብ ቅቡልነትን በማስገኘታቸውም ነበር፡፡ ይህም ለሥልጣን ብዙዎች ሲገዳደሉ በኖሩበት ምድር እንደ ተዓምር መታየቱ የሚገርም አልነበረም፡፡

ከሁሉ በላይ ኦቦ ለማም ሆኑ ‹‹ቲም ለማ›› የሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍና ቀልብ ይበልጥ ያገኙት ደግሞ፣ ለአገራቸው ነፃነትና ለሕዝቦች አንድነት ባሳዩት ቁርጠኛ አቋም ነበር፡፡ የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካን (የከፋፍሎ መግዣ መንገድን) በማስቆም፣ ለዴሞክራሲ ማበብና ለሕዝቦች እኩልነትና ነፃነት የሚረዳ የአንድነትና ይቅር የመባባል ችቦ መለኮሳቸው አይዘነጋም፡፡ የሰውየው መንገድ ወዲያው ጥያቄ የተነሳበትም ከአብሮነት ይልቅ፣ መልሰው የኦሮሞ ብሔርተኝነት አጀንዳን ማስቀደም እንደሚገባ በተናገሩ ማግሥት መሆኑ አይዘነጋም፡፡

አቶ ለማ በአንድ ወቅት የኦሮሞ ሕዝብ ትግልና ፍላጎትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ፣ ‹‹የህልሙን ጠሊቅነት ተገንዝበናል፡፡ ቢያንስ የገዳ ሥርዓትና የኦሮሞን አቃፊነትን ያጠናክራል እንጂ፣ በዘርና በማንነት ያሚያሳድድ አመራርና ትውልድ እንዲኖር የሚሻ ሊሆን አይችልም፡፡ ወደ ውድቀቱ ዘመን ልመለስ ካለም የሚያጋጥመውን ውርደት በጥልቅ እንደሚገነዘብ ግልጽ ነው፡፡ ሕገወጥነትን ለመታገልም ቢሆን ክቡሩንና ሰብዓዊነት እንደማይጥስ የታመነ ነው፤›› ባሉበት አንደበታቸው፣ በእነ ጀዋርና መሰል አክራሪ ብሔርተኞች ተፅዕኖ ከለውጡ ሐዲድ እስከ መልቀቅ መድረሳቸውና በዝምታ መዋጣቸው ብዎችን እንዳሳዘነም አይዘነጋም!፡፡

በጥቅሉ አቦ ለማና ቲሙ ለኦሮሞ ሕዝቦች መታገላቸው አንድ ነገር ሆኖ፣ በመላው አገሪቱ ያንዣበበውን የጥላቻና የቁርሾ ፖለቲካ በመቀነስ አንድነት እንዲገነባ ማድረግ የተጣለባቸው ተስፋ ነበር፡፡ የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኞችን ገፊ አመንክዮ በመግራት፣ የሌሎች ብሔር ፖለቲከኞችንም ቀልብ በመግዛት ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው›› እስከ ማለት እንዳልደረሱ ወደ ተፈራው መንገድ ሸርተት ማለታቸው ለማንም የሚበጅ አልነበረም፡፡ 

የለውጥ ኃይሉ በመጭው ጊዜ የወደቀበት አገራዊ ሸክም ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብስ ስለምን ለአቶ ለማ ተሰወረ ማለትም ተገቢ ነው፡፡ አገራዊ ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነት ለመጣስ የሚሹ ዕብሪተኞችን ማስቆም፣ በየክልሎች (በተለይ በደቡብ ክልል)፣ የክልል ልሁን በርካታ ጥያቄዎችን መመለስ፣ የወሰንና ማንነት ማካለል አጀንዳዎች፣ የሕዝብ ቆጠራና የምርጫ ጉዳዮች፣ የልማት ጥያቄዎችና መሰል ተግባራት በጫንቃቸው ላይ መውደቁንስ ለምን ከኦሮሞ ጥያቄ (ያውም ከአገር የተለየ ጥያቄ ሳይኖር) አነሰባቸው የሚለው ተጠየቅ እስካሁንም መልስ አላገኘም፡፡

3 እነ አቦ ዳውድ ኢብሳ

ከ50 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የኦሮሞ ሕዝብን የፖለቲካ ጥያቄዎች ይዞ ሲታገል የቆየው ኦነግ፣ በብዙ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ለዘመናት ያካሄደው የትጥቅ ትግል እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ባያስገኝለትም፣ ከፊውዳላዊና አፋኝ አገዛዞች ጭቆና ለመላቀቅ እስከ መገንጠል የሚደርስ የመብት ትግል ይዞ በመነሳቱ፣ በርካታ የብሔሩ አባላት በግንባሩ ስም ቀላል የማይባል መስዋዕትነት በመክፈላቸው ቅቡልነቱ ከፍ እንዲል አድርጎት ቆይቷል፡፡

በአገር ደረጃ ለውጥ ከመጣ ወዲህም ግንባሩ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ሥልጣን ለመያዝም ሆነ የወከለውን ማኅበረሰብ ጥቅም ለማስከበር ወደ አገር ሲገባ፣ ብዙዎች በተስፋ እንደተቀበሉት አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን በአንድ በኩል ሰላማዊ ትግል በመከተል በሌላ በኩል የኖረበትን የትጥቅ ትግል ባለመልቀቅ “ሸኔ” በተባለው ክንፉ፣ በዚያው በኦሮሚያ ምዕራባዊ ክፍል ቀላል የማይባል ግጭትና መቃወስ እንዳስከተለ አይዘነጋም፡፡

ይህ ድርጊት ደግሞ ከሕዝብም ሆነ ከመንግሥት ጋር የሚያጋጭ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ፍፁም ተቀባይነት ስለሌለው ግንባሩንም ሆነ የእነ ዳውድ ኢብሳን መንገድ ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፡፡ ከዚያም አልፎ በቅርቡ የግንባሩ አመራር የመከፈል ዕጣ ፈንታ ገጥሞታል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ከፓርቲ አመራርነት ተገለዋል (ታግደዋል) የተባሉት አቶ ዳውድ ስለኦሮሚያ የሽግግር መንግሥትም ሆነ ከአብሮነት ይልቅ የመነጠል አዙሪት ውስጥ የሚከት ንግግር ማሰማት የፈለጉት፡፡ የሕወሓት የማይቀየር የብሔር ትርክት ላይ መቸከል የሚሹት!፡፡

በአጠቃላይ ዋናውን የአገሪቱን ግንድ እየወከሉ ግን ከአብሮነት ይልቅ፣ ስለመነጠልና ዛሬም በኖረ ትርክት ጭምር እየናዋዙ ያሉ አንዳንድ ፖለቲከኞችን ማንሳት የተፈለገው፣ በዚህ አካሄድ እንዴት የአብሮነት ፖለቲካን አራምዶ በምልዓተ ሕዝብ የሚገዛ ሐሳብ መንሸራሸር ይቻላል የሚለው ሥጋት እያየለ በመምጣቱ ነው? ወይስ የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ ለመምራት ወይም ነጥሎ ለማስተዳደር (ያውም መነጣጠሉ እንዲህ በቀላሉ የሚሳካ ከሆነ) የማሰቡ ቅዠት ባለመወገዱ ይሆን? የሚል ተጠየቅ ለመወርወር ነው፡፡ ለሁሉም በየትኛውም ወገን ቢሆን የብሔርተኝነቱ ጡዘት ቆም ተብሎ መታየት ያለበት የቁልለት መንገድ መሆኑን ሳይገልጹ ማለፍ አይገባም ባይ ነኝ፡፡

 ከአዘጋጁጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...