Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርምርጫ ሕገ መንግሥትና የሰሞኑ አደገኛ ፍጥጫ

ምርጫ ሕገ መንግሥትና የሰሞኑ አደገኛ ፍጥጫ

ቀን:

በማርቆስ ረታ

ዛሬ በአገራችን ዕልባት የሚያሻው አንገብጋቢ የፖለቲካ ጉዳይ በሕወሓት አመራርና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሚታየው ፍጥጫ ነው። በአደባባይ የምንሰማው የፍጥጫው ምክንያት ከምርጫ ማድረግና አለማድረግ ሕጋዊነት ጋር የተያያዘ ነው። የፌዴራል መንግሥትና ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት ምርጫ ማድረግ ሳያስፈልጋቸው ሥልጣን ላይ ይገኛሉ። በአንፃሩ የሕወሓት አመራር ውሳኔውን ባለመቀበል ብቻውን የክልል ምክር ቤት ምርጫ ማካሄዱ ይታወሳል።

ፌዴራል መንግሥት የሕወሓትን ምርጫ እንዳልተደረገ በመቁጠር ለማለፍ መወሰኑን ካስታወቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በያዝነው ዓመት እንደሚካሄድና ምርጫው ትግራይንም እንደሚጨምር መግለጹ ይታወቃል። በመቀጠል የሕወሓት አመራር የፌዴራሉ መንግሥት ምርጫ ባለማካሄዱ ከመስከረም 25 እስከ 30 በኋላ ሕጋዊነቱ አብቅቷል፣ ውሳኔዎቹም በትግራይ ተቀባይነት አይኖራቸውም ማለቱን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥትም በሕገወጥ ምርጫ ከተቋቋመው የሕወሓት የክልል መንግሥት ጋር ምንም ግንኙነት እንደማይኖረው ማስታወቁን ሰምተናል።

የዚህ ነገር መጨረሻው ምንድነው? ሕወሓት የመረጠው የእንቢታና የእልህ መንገድ የት እንደሚያደርሰው አስቦበት ወይስ ባወጣው ያውጣው ብሎ ይሆን? በዚህ ጽሑፍ የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሕጋዊ ምክንያት አለመኖሩንና ሕወሓት ያካሄደውም ምርጫ ሕጋዊ አለመሆኑን በማስረዳት፣ የሕወሓት አመራር ምርጫው እንዳልተደረገ ተቆጥሮለት በዚህ ዓመት በሚደረገው ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እንዲሳተፍ የተሰጠውን ዕድል ሊጠቀምበት እንደሚገባ፣ የሕወሓት አመራር ከብልፅግና አመራር ጋር ያለውን ፀብ ከቻለ በውይይት ቢፈታ፣ ካልቻለም ቢያስን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በምንም የማይለየውን የትግራይን ሕዝብ ፀቡ ውስጥ ባይከት እንደሚሻል ለማስገንዘብ፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችንና የማይካዱ ጭብጦችን መሠረት በማድረግ ሐሳቦቼን አቀርባለሁ።

የፍጥጫው አመጣጥ በአጭሩ

አምና ነሐሴ ላይ ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የተሰረዘው መጋቢት ወር 2012 ዓ.ም. ላይ ነበር። ምክንያቱም ኮቪድ የደቀነው ሥጋት ነበር። በተለይ በየካቲትና በመጋቢት ወራት በአውሮፓ የረገፈውን ሰው ተመልክቶ ሥጋት ያልተሰማው ብዙ አይገኝም። ሥጋቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወለደ። አዋጁም የተለመደውን የአዘቦት ቀን አሠራርና እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም መብቶችን ገደበ። የምርጫ ቦርድም ምርጫውን በተባለው ጊዜ ለማካሄድ እንደማይችል ገልጾ በመሰረዝ ውሳኔውን ለተወካዮች ምክር ቤት አቀረበ፣ ምክር ቤቱም ውሳኔውን አፀደቀ።

በመቀጠል የፌዴራሉ መንግሥት የምርጫ ጊዜ በተራዘመበት ሁኔታ በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን የሕግ መሠረት አስመልክቶ ሕጋዊ አማራጮችም አቅርቦ ሲያበቃ፣ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ መፍትሔ የማይሰጥ በመሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም እንዲሰጥበት ሲል ጠየቀ። ይኼኔ ተቃዋሚዎች የሕገ መንግሥት ክፍተት አለ የሚለውን የመንግሥት ድምዳሜ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል ተነሱ። ትርጉም የማያሻውን አንቀጽ ተርጉሞ በኮቪድ ሰበብ ምርጫ ሰርዞ ያለምርጫ ሥልጣን ይዞ ለመቆየት ፈልጓል ማለት ጀመሩ።

በተለይ የሕወሓት አመራር የኮቪድ ሥጋት ያላጋጠመን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ያልታወጀ ይመስል ምርጫ በእየ አምስት ዓመቱ ይደረጋል የሚለውን ድንጋጌ ይዞ የተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ያለፈው መሆኑን ብቻ የክርክሩ መነሻና መድረሻ አድርጎ የፌዴራል መንግሥትን ሕጋዊነት የሌለው ራሱን ደግሞ ብቸኛው ሕጋዊ መንግሥት ያቋቋመ ፓርቲ አድርጎ በማቅረብ ዛሬ ካለንበት ፍጥጫ አድርሶናል።

የፍጥጫው አስኳል የሆነውን ምርጫ የማድረግና ያለማድረግ ጥያቄ በቅጡ ለመመለስ በኮቪድና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ከሌሎች የተለመደውን የመንግሥት አሠራር ከሚመለከቱት ድንጋጌዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት መመልከት ያስፈልጋል።

ስለሆነም ዋነኛ የብዥታ ምንጭ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከሕገ መንግሥቱ አንፃር እንመለከትና ቀጥለን የምርጫ መራዘም ወይም መደረግ በራሱ ሕጋዊ ወይም ሕገወጥ ይባል እንደሆነ እንመረምራለን።

የሕገ መንግሥቱ አውጪዎች ክፍተት ትተዋል?

በርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሕገ መንግሥቱ አውጪዎች ‘የምርጫ ጊዜና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሊገጣጠሙ ይችላሉ ብለው አስበው መፍትሔ የሚሰጥ አንቀጽ አልጨመሩም፤’ ማሰብ ነበረባቸው ማለት ባይቻልም ‘ችግሩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጾች መሠረት ሊፈታ አይችልም’ ሲሉ ተደምጠዋል። ስህተት ነው። በመንግሥትም ምርጫ ተሰርዞ የምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ሲገባደድ ክፍተት ይፈጠራል ማለቱ ስህተት ቢሆንም፣ እስከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ መንግሥት በሥልጣን የሚቆይበትን የሕግ አግባብ የሚከተለውን ጥያቄ ራሴ ትርጉም ልስጥ ከማለት ይልቅ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡ ተገቢ ነበር። እንዳስረዳ ይፍቀድልኝ።

የሕገ መንግሥቱ አውጪዎች በአገርና ሕዝብ ላይ ‹‹ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፤›› ለየፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን ‹‹ሲሰጡ፣ (93) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲወጣም የተለመደው ያዘቦቱ [Normal] ሕግና ሥርዓት፣ የዜጎችም መብቶች ለጊዜው እንደሚገደቡ ያውቁ ነበር። ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሠረት የአገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብን ደኅንነት፣ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል››፡፡ (93/4/ሀ) ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የተለመደው የሕግና ሥርዓት ሒደት ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች›› ስለሚተካ ለጊዜው ይገደባል። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊገደቡ ከማይችሉት ጥቂት መብቶች በስተቀር የፖለቲካ መብቶችንና የአዘቦት አሠራሮችን የሚደነግጉት አንቀጾች ሊገደቡ ይችላሉ። ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችል ነው››፡፡ (93/4/ለ) አደጋው ወይም ሥጋቱ ተወግዶ የተለመደው ሰላማዊ ሁኔታ ሲመለስ በመብቶች ላይ የተጣለው ገደብ ይነሳል፣ ተገድበው የቆዩት ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሒደቶችም እንደ ተለመደው ተፈጻሚ ይሆናሉ። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም እንደተለመደው ይቀጥላል።

እንግዲህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት፣ የተለመደው የአዘቦት ጊዜ ሕግና አሠራር እንደ ቀድሞው እንዲተገበር መጠበቅ፣ መጠየቅ ወይም መከራከር በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አደጋ በሌለበት ጊዜ በሚተገበረው ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ አሠራር መካከል ያለውን ልዩነት አለማየት ነው። ሁለቱም የሕግ ዓይነቶች ሕገ መንግሥታዊ ቢሆኑም አንዱ ለአዘቦት [Normal] ሌላው ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ እንደመሆናቸው፣ ለምሳሌ አንዱ መብት ሲጠብቅ ሌላው ለጊዜውም ቢሆን ይገድባል።

ስለዚህ መንግሥት በአገርና ሕዝብ፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማስወገድ ልዩ የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን ይዞ አደጋውን የመቀልበስ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በሚጠበቅበት ሰዓት ‹‹የሥልጣን ዘመኑ አብቅቷል›› የሚል ወገን፣ ለክርክሩም የሕገ መንግሥቱን አንድ ወይም ሌላ አንቀጽ የሚጠቅስ ፓለቲከኛ የሕግ መርሆችን ባያውቅ ቢያንስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የደቀነውን ሥጋት ለማየት አይቸግረውም። የተደቀነውን አደጋ በሚመለከት ጥርጣሬ አለኝ ማለት ሌላ ጉዳይ ነው። አደጋው መኖሩ ታምኖበት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ግን አዋጁን እንዳልነበረ በመቁጠር የአዘቦቱን ሕግና ድንጋጌ በመጥቀስ ሊነሳ የሚችል ምንም ዓይነት ሕጋዊ ክርክር የለም።

የምርጫ መራዘምና የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊነት

የሕወሓት አመራር የያዘውን የፌዴራሉ መንግሥት ሕጋዊነቱ አብቅቷል የሚለውን አቋም በይፋ ከገለጹት የሕወሓት ላይ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አንዱ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው። መስከረም 2012 ዓ.ም. አጋማሽ ከትግራይ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ከመስከረም 25 እስከ 30 በኋላ የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊነቱን ያጣል ብለው ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምርጫ ስላልተደረገ፣ ሥልጣኑን ለማራዘም ሲል ትርጉም የማያስፈልገውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ ትርጉም መስጠቱ፣ ምሁራንም የምርጫው መራዘም ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲሉ አስተያየት መስጠታቸውን እንደሆነ ገልጸዋል።

የሕወሓት አመራር የፌዴራል መንግሥትን ሕጋዊነት አልቀበልም ያለበት ምክንያት ምርጫ ሳያደርግ የሥራ ዘመኑ አልፏል በሚል ሲሆን፣ ራሱንም ብቸኛው ሕጋዊ መንግሥት ያቋቋመ ድርጅት ለማለት ያስደፈረው አምስት ዓመቱ ሳያልፍ ምርጫ አካሄድኩ በሚል ነው። በእየ አምስት ዓመቱ መደረግ የነበረበት ምርጫ አለመደረጉ ብቻ መንግሥት የለም ወይም ሕጋዊነቱ አብቅቷል ያስብላል? በአገርና ሕዝብ ላይ የተደቀነ አደጋን ለመከላከል የታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዜጎች መብት ላይ በጣላቸው ገደቦች ምክንያት ምርጫ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ዝግጅት ለማድረግ ባለመቻሉ ምርጫው ቢሰረዝ የምርጫው መሰረዝ ብቻ በራሱ ስህተት ነው ለማለት ምን ሕጋዊ መሠረት ይገኛል? በበርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ‹‹ማንበብ የሚችል ሰው ሁሉ አንብቦ ሊረዳቸው የሚችልና ትርጉም የማያሻቸው›› የተባለላቸው ሁለት የሕገ መንግሥት አንቀጾች እነሆ፣

አንቀጽ (54/1) ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚፈጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ፤›› አንቀጽ 58/2 ‹‹የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ሰላሳ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው። የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል፡፡››

ሁለቱም የሚሉት ያው ‹‹ምክር ቤቱ የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው›› እና አባላቱ ‹‹በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ›› ነው፣ በቃ። ምርጫ ካልተደረገ መንግሥት የለም አይሉም። አንቀጾቹን ጠቅሶ መንግሥት የለም ማለት የሚቻለው ለድንጋጌዎቹ ትርጉም በመስጠት ብቻ ነው። ትርጉም አያስፈልገውም፣ ግልጽ ነው የተባለውን ድንጋጌ ትርጉም ካልሰጡ በቀር ‹‹በየአምስት ዓመቱ ይመረጣሉ›› ወይም ምክር ቤቱ ‹‹የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው›› የሚለውን ይዞ ምርጫ ሳይደረግ ቢቀር ‹‹ሕጋዊነቱ አብቅቷል›› ለማለት አይቻልም። ትርጉም ግድ ነበር ማለት ነው። ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ይሰጥ ከተባለም ሁለቱን አንቀጾች ብቻ ነጥሎ ማየት አይበቃም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን (አንቀጽ 93) እና ሌሎችንም ማየት ግድ ይላል።

የሕገ መንግሥት ትርጉም አስፈላጊነት

ከላይ እንደተባለው በአገርና ሕዝብ ደኅንነት ላይ ሥጋት የሚደቅን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝም ሆነ ጦርነት ሲያጋጥም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ በሌሎች የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች የተደነገገው አሠራርና የዜጎች መብት እንዳስፈላጊነቱ ለጊዜው ተገድቦ ይቆያል። ሊገደቡ የማይችሉ መብቶችና የአሠራር ሥርዓቶች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚያ ውጭ እንዳስፈላጊነቱ የሚጣሉ ገደቦች በሕገ መንግሥቱ የተከለከሉ አይደሉም። በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት፣ የመሰብሰብ መብት ተገድበው መቆየታቸው ይታወቃል። በነዚህ መብቶች መገደብ ምክንያት ሊጠበቁ የማይችሉ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ የጊዜ ሰሌዳዎችም እንዲሁ መገደባቸው አይቀርም። ስለሆነም በሕገ መንግሥቱ አንቀጾች 54/1 እና 58/2 የተቀመጠው የአምስት ዓመት የጊዜ ሰሌዳም ሊተገበር የማይችል በመሆኑ የግድ መገደቡ አይቀርም።

ይህ ትርጓሜ ከእውነታው ጋር የሚስማማ ነው ባይ ነኝ፣ ሆኖም ትርጉሙን የማይቀበል አይጠፋም። እንዲያውም ከላይ የተጠቀሱት አንቀጾች ‹‹ግልጽ ናቸው፣ ትርጉም አያሻቸውም›› ባዮቹ ክርክራቸውን ለመደገፍ የሚያቀርቧቸው ትርጉሞች ነበሩ። ለምሳሌ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቶችን ሊገድብ ቢችልም የመንግሥትን የሥልጣን ጊዜ ግን ሊያራዝም አይችልም›› የሚል “ትርጉም” ይዘው የሚከራከሩ ወገኖች ነበሩ፣ አሉ። ለፖለቲካ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ የሚመቻቸውን ትርጉም መርጠው ቢቃወሙ መብታቸው ቢሆንም የእነሱ ትርጉም የእኔ ቢጤው ተራ ዜጋ ከሚያቀርበው ትርጉም በምንም አይለይም። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የፌዴራሉ መንግሥት የመሰለውን ትርጉም በመስጠት ፋንታ ጉዳዩን ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ወዳለው አካል የማቅረቡን ተገቢነት ለመገንዘብ የሚቻለው።

በተጨማሪ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብት ቢገድብ እንጂ የመንግሥትን ሥልጣን አያራዝምም›› የሚለውን ትርጉም ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑ ቢታወቅም እንደ ሙግትም ተጨባጩን እውነታ ያገናዘበ አለመሆኑን እንመልከት። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ከገደበ የተጣለው ገደብ የሚያስከትለው ውጤት መኖሩ አይካድም። ምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈጻሚዎችንና ታዛቢዎችን ሰብስቦ ሥልጠና መስጠት ነበረበት፣ ካልሰበሰበ አያሠለጥንም፣ ሊዘጋጅ አይችልም፣ ምርጫ ማድረግ አይችልም። በሌላ በኩል የኮቪድን ሥርጭትን ለመከላከል ሰው እንዳይሰበሰብ በሕግ [በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ] ተከልክሎ ነበር። የመሰብሰብ መብትም ሆነ በሕግ የተጣለው ክልከላ ሕገ መንግሥታዊ ናቸው። በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ይካሄዳል የሚለው ድንጋጌ ቢኖርም ለጊዜው መገደቡ አይቀርም። ምርጫ ማካሄድ ካልተቻለ መሰረዝ ግድ ነው።

በሕግ በተጣለ ገደብ ምክንያት ተተኪ የፓርላማ አባላት ለመምረጥ የሚያስችል ምርጫ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ለማስፈጸም ባልተቻለበት ሁኔታ የፓርላማው የሥልጣን ጊዜ የሚወስነው አንቀጽ ብቻውን ከመገደብ አምልጦ አየር ላይ ሊተገበር አይችልም። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የምርጫ ጊዜ የግድ መለወጥ ካለበትና ወደፊት መሸጋገር ካለበት በዚያ ልክ የፓርላማው የሥራ ጊዜ ምርጫ ማድረግ እስከ ሚቻልበት ጊዜ ድረስ የግድ መራዘም ይኖርበታል። ሕገ መንግሥቱም ይህን አይከለክልም። “. . . በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችል ነው፤›› ይላል። (93/4/ለ)

ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድን የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሄድ፣ የምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመን አምስት ዓመት መሆኑን የሚደነግጉትን የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች [54/1 እና 58/2] አንቀጾቹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊገድቡ ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ የምርጫ ጊዜ በመራዘሙ ምክንያት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሥስልጣን ጌዜው አብቅቷል ለማለት የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት የለም።

ሕወሓት ያካሄደው ምርጫ ሕጋዊ መሠረት የሌለው ስለመሆኑ

የሕወሓት አመራር ኮቪድ በተስፋፋበትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ ሕጉ ይፈቅድለታል? በአጭሩ አይፈቅድለትም። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 መሠረት በኢትዮጵያ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫዎችን የማቀድና በገለልተኝነት የማስፈጸም ሥልጣን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው።

ምርጫ ቦርድ ራሱ ያስቀመጠውን የምርጫ ጊዜ ለመሰረዝ መወሰኑ፣ ውሳኔውም በተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ እየታወቀ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በኮቪድ ምክንያት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ምርጫ ለማራዘም የተደረገውን ውሳኔ ተመልክቶ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት የፌዴራልና ክልል ምክር ቤቶች በየሥልጣናቸው እንዲቆዩ መወሰኑ ሲታወቅ፣ በማን አለብኝነት ምርጫ አካሄኩ ማለት ሕገወጥነት ነው።

በምርጫ ሕግ መሠረት ምርጫን በሚመለከት የክልሎች ሥልጣን በአካባቢ ምርጫ [የዞን፣ የወረዳን፣ የከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ] የተወሰነ ሲሆን፣ በዚህ ላይም ቢሆን ክልሎች ምርጫ የሚካሄድበትን ጊዜ በሕግ ከሚወስኑ በቀር አፈጻጸሙ ‘በምርጫ ሕግና የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው ደንብና መመርያ መሠረት ይከናወናል።’

በሕገ መንግሥቱ የተቋቋሙ ተቋሞችን ውሳኔ ሳይቀበሉ ሕገ መንግሥት ተጣሰ እያሉ ለመክሰስ አይቻልም። የሕወሓት ሊቀመንበር ከ“ምርጫ”ው በኋላ የሕግ አንቀጽ እየጠቀሱ መከራከር ዋጋ እንደሌለው፣ ወሳኙ የትግራይ ሕዝብ ምርጫ ነው፤›› ብለው ነበር። የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች አንድ ፓርቲ ሲፈልግ የሚጠቅሳቸው ሲሻው የሚጥሳቸው አይደሉም። ካከበሩ ሙሉውን ነው ማክበር፣ ለመጣስ ግን አንዱን አንቀጽ መጣስ ይበቃል። ሕግ ባለበት አገር አንቀጽማ ገና ይጠቀሳል እንጂ፣ እንዴት አይጠቀስም?!

አይቀሬው ስድስተኛ አገራዊ ምርጫና የሕወሓት ተሳትፎ

ሕወሓት ምንም ጥረት ማድረግ ሳያስፈልገው በሥልጣን መቆየት ሲችል የግድ ምርጫ ለማድረግ ሲነሳ የሕዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መጥቀሱ ቢታወቅም በምርጫ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ ፓርቲ እንደ መሆኑ ብዙ ሊያሳስበው ባልተገባ። ምናልባት ሳይመረጥ ለአንድ ቀንም ቢሆን ሥልጣን ላይ ለመቆየት የማይፈልግ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በመሆኑ ነው እንበል። በእርግጥ የሕወሓት ምርጫ የክልል ምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ሳይጠናቀቅ የተደረገ ቢሆንም ብቸኛው ገለልተኛ ባለ ሥልጣን በሌለበት የተደረገ በመሆኑ፣ ከሕገወጥነት ሊያመልጥ አይችልም። ይሁንና በፌዴራል መንግሥት በኩል ምርጫው እንዳልተደረገ ቢቆጠርም ምርጫ ማድረጉ የመርህ ጉዳይ ነው ቢል ሊያስኬድ ይችላል፣ ያለ ምርጫ፣ ያለ ውክልና ሥልጣን አይያዝም የሚል መርህ ግድ ብሎት ነው እንበል።

ሆኖም ፌዴራሉ መንግሥት ስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ሲጀምር ሕወሓት ‹‹አንዴ ተመርጫለሁ›› በማለት በክልሉ ምርጫ እንዳይካሄድ አሻፈረኝ ቢል መርህ የለሽ ሕገ ወጥነት ይሆንበታል። ምክንያቱም ሕገወጥም ቢሆን ምርጫ ማድረግን የሞት ሽረት ጉዳይ ሲያደርግ እንደ ምክንያት ያቀረበው የክልሉን ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ቢሆንም በፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚነት የሚካሄደውን ስድስተኛ አገር አቀፍ ምርጫ አይካሄድም ካለ የእምቢታው ምክንያት የሕዝቡን መብት ማስከበር ሊሆን አይችልም። ይልቁንም እምቢታው ሕወሓት የክልሉን የመንግሥት ሥልጣን በሕገወጥ መንገድ ነጥቆ ራሱን ሥልጣን ላይ ለማቆየት ያለውን ፍላጎት የሚያረጋግጥ ይሆናል። ሕዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ ሊከበርለት የሚችለው ተፎካካሪዎች በነፃነት ሐሳባቸውን ለሕዝቡ አቅርበው መወዳደር ሲችሉና ምርጫውም ገለልተኛ በሆነው የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት ሲደረግ ብቻ ነው። ይህን መቃወም የሕዝብን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማፈን ይሆናል።

አገር አቀፍ ምርጫ እንዲደረግ ብቸኛው ባለ ሥልጣን የሰጠውን ውሳኔ አልቀበልም የሚል ፓርቲ ራሱን ከምርጫው የማግለል መብቱ የተጠበቀ ሲሆን የሌሎችን ፓርቲዎች መብት እንዲጋፋ፣ በተለይም የመራጩን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዲጥስ ሊፈቀድለት አይችልም።

ማጠቃለያና ቀጣይ ዕርምጃዎች

ማጠቃለያ

ሕወሓት የፌዴራሉ መንግሥት ሕጋዊነት አብቅቷል ለማለትም ሆነ ራሱን ብቸኛ ሕጋዊ መንግሥት ያቋቋመ ድርጅት አድርጎ ለመመልከት ብቸኛ መለኪያ አድርጎ የወሰደው የራሱን ምርጫ ማድረግና የፌዴራሉን አለማድረግ ነው ብለናል። ሕወሓት ምርጫ በማድረጉ አከበርኳቸው፣ የፌዴራሉ መንግሥት ደግሞ ምርጫ ባለማድረጉ ጣሳቸው የሚላቸው አንቀጾች [54/1 እና 58/2] ናቸው። ሁለቱም አንቀጾች ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚሄካድ የሚደነግጉ መሆናቸውን ተመልክተናል። ሆኖም ድንጋጌዎቹ ቢኖሩም በአገራችን በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ የምርጫ በማድረግና አለማደረግ ጉዳይ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ቁልፍ ሚና የነበራቸው የኮቪድ ሥጋት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የምርጫ ቦርድ ውሳኔና የሁለቱም ምክር ቤቶች ውሳኔዎች ናቸው። ሕወሓት ግን እነዚያን ውሳኔዎች በመፃረር ምርጫ የማድረጉን ተገቢነት ለማስረዳት ‹‹ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ይደረጋል›› የሚለውን ድንጋጌ ብቻ ይዞ ቢከራከር አያስኬደውም። ሕወሓት በተለይ ለምርጫ ቦርድ ውሳኔ ዋነኛ ምክንያት የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ባለመገንዘቡ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቶችን ሊገድብ ቢችልም የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን አያራዝምም›› የሚል ሕጋዊ መሠረት የሌለውን “ባለሙያዎች” ምክር በማዳመጡ ስህተት ውስጥ ወድቋል። ከላይ በቀረቡት ነጥቦች መሠረት መግቢያው ላይ የተነሱትን ሁለቱን የሕጋዊነት ጥያቄዎች ለመመለስ፣ ሕወሓት ያደረገው ምርጫ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት ያልተደረገ በመሆኑ ሕገወጥ ነው። የሕወሓት አመራር የፌዴራሉ መንግሥት ምርጫ ባለማድረጉ ምክንያት ከመስከረም 25 እስከ 30 በኋላ ሕጋዊነቱ አብቅቷል ለማለት ሕጋዊ መሠረት የለም።    

ቀጣይ ዕርምጃዎች

የሕጉ ነገር እንዲህ ከሆነ የቀረን ጥያቄ ፍጥጫውን እንዴት እናርግበው? የሚለውን ነው። የሕወሓት ዕርምጃዎች የሕግ ድጋፍ እንደሌላቸው ስንገነዘብ የሕወሓት አመራር ሌላውን መክሰስ ትቶ የገዛ ጥፋቱን አምኖ አካሄዱን ለማስተካከል ካልወሰነ በቀር የተካረረው ፍጥጫ የሚረግብበትን መንገድ ለመጠቆም እጅግ ያስቸግራል። የፌዴራሉ መንግሥት ሕገወጡን ምርጫ ዓይቶ እንዳላየ በማለፍ ያሳየው ትዕግሥት የሚመሠገን ነው። እንደ ፌዴራሉ መንግሥት ሁሉ ሕወሓትም ነገሮችን ከእልህ በፀዳ የይቅርታ መንፈስ በመመልከት ፍጥጫውን ለማርገብ መወሰን አለበት። በዚህ መንፈስ ሁለቱም ወገኖች የሚከተሉትን ዕርምጃዎች መውሰድ ይችላሉ፣  

    የሕወሓት አመራር የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊነቱን አጥቷል የሚለውን ሕጋዊ መሠረት የሌለውን አቋሙን ያርም፣ ስህተቱን ተቀብሎ ለፌዴራሉ መንግሥት ተገቢውን ዕውቅና እንደሚሰጥ በይፋ ያስታውቅ፣ ራሱ ያደረገውን ምርጫ እንዳልተደረገ በመቁጠር ከሕገወጡ ምርጫ በፊት ለነበረው የክልል መንግሥት ዕውቅና እንዲሰጠው የፌዴራሉን መንግሥት ይጠይቅ፣

     የፌዴራል መንግሥትም አስቀድሞ በሰጠው ውሳኔ (ቃል) መሠረት በትግራይ ተካሄደ የተባለውን ምርጫ እንዳልተደረገ በመቁጠር ሕወሓትም እንደሌሎች ፓርቲዎች ሁሉ በቀጣዩ ምርጫ እንዲሳተፍ ይፍቀድለት፣ ከሕወሓት አመራር የሚቀርብለትን ጥያቄ ተቀብሎ ከምርጫ በፊት ለነበረው ምክር ቤት ተገቢውን ዕውቅና ይስጥ። እውነት ለመናገር ከላይ የቀረበውን መተግበር ማንንም አይጎዳም፣ አገርን ግን ይጠቅማል፣ ሁሉም ዕፎይ ይላል።

ሕጋዊ መሠረት የሌለው ሥራ አንዴ ከተሠራ በኋላ ስህተትን ተቀብሎ፣ አርሞና ተራርሞ ከመሄድ የተሻለ ብዙ አማራጭ ባይኖርም የተለያዩ ሰላማዊ የመፍትሔ አማራጮችን ለማፍለቅ የሚችሉ አስተዋይ ሽማግሌዎች አይጠፉ ይሆናል። ከሆነ መልካም።

በአንፃሩ ሕጋዊ መሠረት በሌለው ፍጥጫ እንግፋበት ቢባል መጨረሻው ምን ይሆናል? ሕወሓት በጀመረው መንገድ ልሂድ ቢል መዳረሻው የት ይሆናል? ፍጥጫውን እንደ ትግል ብንቆጥረው ድሉ ምን ይሆናል? ፌዴራል መንግሥት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ግዴታ ያለበት መሆኑ ይታወቃል። ስለዚህ ለፌዴራል መንግሥት ድል ማለት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕግና ሥርዓት መስፈኑን ማረጋገጥ መሆኑ አይቀርም፣ ይኸውም የውዴታ ግዴታው ነው። በበኩሉ ሕወሓት ሕገወጥ ዕርምጃዎቹን እንደ ትግል የሚመለከት ቢሆን ድል አደረግኩ የሚለው ምን ሲሆን ነው? የሕወሓት የድል ትርጓሜ ምንም ይሁን ምን ከሕግ ውጭ ለማሳካት ከመሞከር መቆጠብ ግድ ነው። በተለይ የጦርነትን አማራጭና ብቅ ጥልቅ የሚለውን የዋዛ ዋዛ (De facto) አገረ መንግሥትነትን አደገኛ መንገድ መዝጋት አለበት። እንዳስረዳ ይፈቀድልኝ።

ትግራይን እንደ ዋዛ ከኢትዮጵያ መለየት አይቻልም

ከሕወሓት አመራር መካከል የትግራይ ሕዝብ ከገዛ አገሩና ከወገኑ መለየት አለበት የሚል እምነት የያዘ ቢኖር በሕገ መንግሥቱ መሠረት መጠየቅ ይችላል። ይህን ለማድረግ ፀብ አያስፈልግም፣ ጦርነት አያስፈልግም። ከሕግ ውጪ ሕዝቡን በውሸት ሰበካ ወደ ግጭት ለማስገባት መሞከር በኢትዮጵያና በትግራይ ላይ የሚፈጸም ወንጀልና ክህደት ነው።

ዲፋክቶ (De facto) የሚባል እንደዋዛ፣ ቀስ በቀስ ይፈጠራል ተብሎ የሚታሰብ አገረ መንግሥትነት ማዕከላዊ መንግሥቱ በፈረሰበት አገር ውስጥ ተኩኖ ሊታሰብ የሚችል መሆኑ ይታወቃል። የሕወሓት አመራር ሥልጣን ከእጁ ከወጣ በኋላ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፣ መንግሥት አልባ ትሆናለች የሚል ድምዳሜ ላይ ሳይደርስ አልቀረም። እግዚአብሔር ይመስገን፣ አልፈረሰችም፣ መንግሥት አልባም አልሆነችም። ዛሬም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለ። ያለ ሕግ በዋዛ ዋዛ [በተጨባጭ ላለማለት] ወይም ዲፋክቶ (De facto) ሳይሆን በሕግ ወይም ዲጁሬ (De jure) የሚታወቅ መንግሥት ነው። የትግራይ ክልል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ አባል መሆኑ በሕግ የታወቀ ነው። መንግሥትና ሕገ መንግሥት ባለበት አገር በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሕጋዊ ዕውቅና ያለውን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወደ ዲፋክቶ መንግሥትነት ለመለወጥ አይቻልም። ስለሆነም በፌዴሬሽኑ ጥላ ሥር ሆኖ ከሌሎች አገሮችና ድርጅቶች ጋር በተናጠል ለመገናኘትና ቀስ በቀስ፣ እያዋዙ ዕውቅና ለማግኘት መሞከር ወንጀል መሆኑ ታውቆ በሩ መዘጋት አለበት።

ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመለየት የሚፈልጉ የሕወሓት አመራር አባላት ፍላጎታቸው ከሕዝቡ ጥቅም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አሳምረው ያውቁታል። ዛሬ ‹‹ታግለን ነፃ ባወጣን አሃዳዊው ኃይል ሊወጋን ነው›› በማለት በፍርኃት የሸበቡት ሕዝብ የግድ እንዲመርጣቸው ማድረግ ቢችሉም፣ ከኢትዮጵያ እንገንጠል ቢሉት እንደ ማይሰማቸው ያውቁታል። ሕዝቡ ይሰማናል የሚሉ ከሆነ ሕጉን በተከተለ መልኩ ሕዝቡ ምርጫውን እንዲገልጽ ዕድል መስጠት ይቻላል ሳይቸኩሉ፣ ሳያዋክቡት።

የሕወሓት አመራር ነፃ አገር የመመሥረት ነሻጣውን ለማሳካት ቢፈልግ ቅድሚያ በቀጣዩ ምርጫ ተወዳድሮ የክልሉን ምክር ቤት በቂ ወንበሮች መያዙን ያረጋግጥ። ከዚያ በኋላ ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቅርብ። የፌዴራል ምክር ቤትም በሦስት ዓመት ውስጥ ሪፈረንደም ያዘጋጅለታል። ከዚያ የሚሆነው ይሆናል።

መቼም ለቸኮለ ሰው ሦስት ዓመት ረዥም ጊዜ ነው። ታዲያ አገር መገንጠልን የሚያክል ትልቅ ነገር ፈልጎም ተቸኩሎም አይሆንም። ከእዚያ ውጭ ሕዝቡን በሐሰት ወደ ግጭትና ደም መፋሰስ በማስገባት በከንቱ ከሚፈሰው ደም ለመገንጠል የሚሆን ምክንያት ለማግኘት መሻት ደንታ ቢስነትና የለየለት ፀረ ሕዝብነት ነው።

የሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ ፍላጎቶች ተቃርኖ

የሕወሓት አመራር አባል የሆኑት አቶ አስመላሽ ከላይ በጠቀስነው መስከረም አጋማሽ ላይ በተለቀቀው ቪዲዮ የቀድሞ ኦህዴድና ብአዴን አመራር በለውጡ ዋዜማ የፈጠሩትና “ኦሮማራ” ተብሎ ስለሚታወቀው “ጥምረት” ተጠይቀው የተናገሩት በአንድ በኩል በፓርቲ መሪዎችና በሕዝቦች ጥቅም መካከል ያለውን ልዩነት፣ በሌላ በኩል የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎትና ጥቅም አንድነት በሚመለከት ምንም ብዥታ እንደሌለባቸው የሚያረጋግጥ ነው ለማለት ይቻላል። ልጥቀስ፣

‹‹ጥምረቱ የኦሮሞና አማራን ሕዝብ ጥቅም የሚወክል አይደለም። ምክንያቱም የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ጥቅም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የተለየ አይደለም። ጥቅማቸው አንድ ነው። ሕዝብና ሕዝብ የሚያጣላ ነገር የለም። ይኼ ጥምረት ግን ልሂቃን ተሰብስበው የፈጠሩት ነው። ጥምረቱ ለመሸዋወድ የተመሠረተ ነው፤›› ብለዋል። የአቶ አስመላሽን ትንታኔ ወስደን በሕወሓት አመራርና በትግራይ ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት እንመልከት።

በመሠረቱ የትግራይ ሕዝብ ችግርም ሆነ ጥቅም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ የማይለይ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም በአቶ አስመላሽ አንደበት በዚህ ጊዜ መነገሩ ግን በሕወሓትና ኦሮማራ ነባር ብልፅግና አመራር መካከል ያለው ፀብና ፍጥጫ የትግራይን ሕዝብ የማይወክል መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ይህን አሳምረው በሚያቁውት በአቶ አስመላሽና ጓዶቻቸው የተያዘው ጠባጫሪ አቋም በስሙ የሚምሉለትን የትግራይን ሕዝብ ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ለመገንዘብ ይረዳናል።

ዘርዘር ለማድረግ ያህል ከአቶ አስመላሽ ትንታኔ የሚከተሉትን እንገነዘባለን

1 በሕወሓትና “የኦሮማራ ጥምረት” በመሠረቱት ልሂቃን መካከል የተፈጠረው ፀብ ወይም “መሸዋወድ” በልሂቃን መካከል የተፈጠረ መሆኑን፣ “ኦሮማራ ጥምረት” አይወክላቸውም የሚሏቸው የኦሮሞና አማራ ሕዝቦች ጥቅም ከትግራይ ሕዝብ ጥቅም ጋር አንድ መሆኑን፣ እንደ አማራውና ኦሮሞው ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ጥቅም ‹‹ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የተለየ›› አለመሆኑን፣ ሕወሓት ሸወዱኝ ከሚላቸው የቀድሞ ኦሮማራ፣ የአሁኑ ብልፅግና አመራር ጋር ያለው ፀብና ቁጭት የትግራይን ሕዝብ የሚወክል አለመሆኑን በግልጽ እንደሚገነዘቡ፣ የሕወሓት አመራር የትግራይን ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመጥቀስ ያካሄዱት ሕገወጥ ምርጫም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ላይ የሚሰነዝሩት ትንኮሳና በዕብሪት የገቡበት አደገኛ ፍጥጫ የትግራይን ሕዝብ እንደማይወክል ከማረጋገጡም ባሻገር፣ አቶ አስመላሽና ጓዶቻቸው የሚያራምዱት ሕገወጥ አካሄድና ፀባጫሪነት ከሕዝቡ ጥቅም ጋር የሚጋጭ የአውቆ አጥፊ ሥራ መሆኑን ያስረዳል።

ሕወሓት ከትግራይ ልጆች ጉዳት ሲያተርፍ የኖረ ድርጅት ስለመሆኑ

የሕወሓት አመራር የክልሉ ሕዝብ በሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ እንደሚጠላ፣ እንደሚገለል፣ እንደሚፈናቀልና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጥርጣሬ ዓይን እንደሚታይ በመግለጽ፣ መጣብህ፣ አለቀልህ እያሉ ራሱን ከገዛ ወገንኖቹ ለይቶ እንዲመለከት ሲኮረኩሩት መኖራቸው ይታወቃል። ሆኖም የትግራይ ሰው በሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በጥርጣሬ ዓይን መታየት የጀመረበት ጊዜና መነሻው ለብዙዎች ግልጽ ላይሆን ይችላል። ጊዜው 1970 ዓ.ም. ነበር። መነሻውም የሕወሓት አመራር ከልቡ አፍልቆ የተገበረው የተንኮል ሥራ ነበር።

እነሆ ማስረጃ። ከአቶ ገብሩ አሥራት መጽሐፍ በረዥሙ ልጥቀስ፣ ‹‹. . . በ1970 ዓ.ም. ደርግ ካካሄደው የማጋለጥና የመመንጠር ዘመቻ በኋላ ቁጥራቸው የማይናቅ የትግራይ ተወላጆች ደርግን ማገልገል ጀምረው ነበር። እነዚህም በሁሉም የአውራጃና የወረዳ ከተሞች ሕዝቡን ያውኩ ስለነበር ሕወሓት እነሱን ለማጥፋት አንድ ዘዴ ቀየሰ። የሐሳቡ አመንጪ ዕውቁ የከተማ የሕዝብ ግንኝኑነት ሠራተኛ ተክሉ ሐዋዝ ሲሆን ዕቅዱን ለማስፈጸም ሦስት ታጋዮች እንዲመደቡለት ጠየቀ። ሦስቱ ታጋዮች ከተማ ገብተው ሕዝቡን የሚያውኩትን ግለሰቦች ደርግ ራሱ እንዲያጠፋቸው የተቀየሰውን የረቀቀ ዕቅድ እንዲያስፈጽሙ ተልዕኮ ተሰጣቸው።

ተክሉ አንድ ረዥም የሐሰት ደብዳቤ አዘጋጀ። ከተክሉ ሐዋዝ በወቅቱ የፖለቲካ ኃላፊ ለነበረው ዓባይ ፀሐዬ የተላከ የሚል ነው። ‘ጥብቅ ሚስጥር’ የሚል ተጽፎበት በሙጫና ስቴፕራል ታሸገ። ደብዳቤው ውስጥ በኮድ የተጻፈ የብዙ ሰዎች የስም ዝርዝር ሰፍሯል። ከስም በተጨማሪ ማን ከማን ጋር በሕዋስ እንደተደራጀና የአመራር ኮሚቴ አባላቱ ማንነት በማመልከት ሐሰተኛውን ‘የከተማ መዋቅር’ ቁልጭ አድርጎ ያሳይ ነበር።

ስሞቹ በኮድ ቢጻፉም ኮዱ የደርግ ባለሙያዎች በቀላሉ እንዲፈቱት ተደርጎ የተዘጋጀ ነበር። በደብዳቤው ሕወሓትን ሲያውኩ የነበሩት አብዛኞቹ የደርግ ጋሻ ጃግሬዎች ስም ሰፍሮ የሕወሓት እጅግ ታማኝ አባላት እንደሆኑ ተጠቁሟል። እንዲያውም ከአንዳንዶቹ ስም ጎን ሆን ተብሎ አስተያየት ጭምር ታክሎበታል፣ ‘ይህ ሰው ቁልፍ ሚና የሚጫወትና ከበላዮቹ ጋር እየተገናኘ ጠቃሚ ሚስጥር የሚያቀብለን ነው’ የሚለው ተሰምሮበት ነበር። በኮዱ መሠረት አ=12 ብ=16 ር=70 ሃ=20 በ=08 ላ=63 ቸ=74 ው=32 ሆኖ እንዲወከል ተደርጎ በደብዳቤው ’12 16 70 20 08 63 74 32 ጥሩ እየሠራ ነው’ የሚል ብቻ ተጽፏል። ኮድ ሰባሪ ባለሙያዎች ቁጥሩን በቀላሉ ሰብረው አብርሃ በላቸው ይሉና ከሚቀጥለው ሐረግ ጋር በማዛመድ ‘አብርሃ በላቸው ጥሩ እየሠራ ነው’ ብለው ያነቡታል። ሌሎቹንም እንዲሁ።

‹‹ሦስቱ ታጋዮች ደብዳቤውን እንደያዙ አክሱም ለሚገኘው አስተዳደር እጃቸውን ሰጡ። ከተኽሉ ሐዋዝ ለዓባይ ፀሐዬ የተጻፈ ደብዳቤ ይዘው መምጣታቸውን ገለጹ። የአክሱም ካድሬዎችና አስተዳዳሪዎች ተክሉ ሐዋዝና አባይ ፀሐዬ በድርጅቱ ውስጥ ያላቸውን ሚና ያውቃሉ። ሚስጥራዊ የተባለውን ደብዳቤ ይዘት በመገመት በአስቸኳይ መቀሌ ለነበሩት የበላያቸው አስታወቁ። የበላይ ኃላፊውም እጅግ ተደስቶ ወዶ ገቦቹ በአስቸኳይ ወደ መቀሌ እንዲላኩ አዘዘ። ታጋዮቹ ከነደብዳቤው በሄሊኮፕተር መቀሌ ተላኩ። ደብዳቤው ተከፍቶ የኮድ ባለሙያዎች በቀላሉ ፈቱት። ደብዳቤው ሲነበብ በርካታ በታማኝነታቸው የታወቁ የኢሠፓአኮ ካድሬዎችና አስተዳዳሪዎች የሕወሓት አባላት መሆናቸው ተረጋገጠ። ለደርግ እጅግ ታማኝ የነበሩት እነ አብርሃ በላቸውና አፈወርቅ ዓለም ሰገድ ሳይቀሩ ስማቸው ዝርዝሩ ውስጥ ተገኘ። በሁኔታው እጅግ የተደናገጠው ደርግ ወዲያውኑ ሁሉንም ለቃቅሞ አስሮ በግርፋት ፍዳቸውን አሳያቸው።

‹‹. . . ከመቀሌ ማዕከላዊ ምርመራ ለደኅንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በተጻፈ ደብዳቤ ‘ራሱን ሕወሓት ብሎ የሚጠራው ፀረ አንድነት የወንበዴዎች ድርጅት በረሐ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ሌላ በከተማ በቂና ወቅታዊ መረጃ፣ የማቴርያልና ሞራል ድጋፍ ለማግኘት በየክፍላተ አገሮች የወንበዴ ሕዋስ [ሴል] በመዘርጋት የትግራይ ክፍለ አገር ተወላጆችን በአባልነት በማሰባሰብ ፀረ አንድነት ድርጊቱን በማካሄድ ላይ ይገኛል. . . የማዕከላዊ ምርመራ ቅርንጫፍ የሆነው የትግራይ ክፍለ አገር ማዕከላዊ ምርመራ ዋና ክፍልም  የአብዮቱ ወገኖች መስለው ሥውር ፀረ ሕዝብ ደባ በመፈጸም ላይ የሚገኙትን የውስጥ ቦርቧሪዎችን ለማጋለጥና የወንበዴውን ሴል ለመበጣጠስ በወሰደው ዕርምጃ 209 የሕወሓት ወንበዴ አባላት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራውን በሰፊው ቀጥሏል’ ይላል።

‹‹ሕወሓት በዚህ ዘዴ ቀንደኛ የደርግ ካድሬዎቻና ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አደረገ። የኢሠፓአኮ ማ/ኮ አባልና የፖለቲካ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበረው ታደሰ ገብረ እግዚአብሔር ሳይቀር በቁጥጥር ሥር ውሎ መጨረሻ ላይ ከወህኒ ቤት ተወስዶ በደርግ አፋኞች ተገደለ። የክፍለ አገሩ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የነበረው ኅሩይ አስገዶም የሕወሓት የውስጥ አርበኛ ነው ተብሎ እጁን ለመያዝ ሲሞከር በተከፈተው ተኩስ ሞተ። ሕወሓት ውስጥ በደኅንነት ሥራ ተመድቦ ሲሠራ ቆይቶ እጁን ለደርግ ሰጥቶ በፀጥታ ሥራ ተመድቦ የነበረው ዓለማየሁ በቀለም እንዲሁ በሰርጎ ገብነት ተጠርጥሮ እጁን እንዲሰጥ ሲጠየቅ እንቢ ብሎ በጥይት ተመትቶ ሞተ።

‹‹በተደረገው የምንጠራ ዘመቻ ከአንድ ሺሕ በላይ የማኅበራት መሪዎች፣ የመንግሥት ሹመኞች የኢሠፓአኮ ካድሬዎችና ታጣቂ ሚሊሻዎች ታስረዋል። (‹‹ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ››፣ ገጽ 127 እስከ 129] ይህን ተግባር የሕወሓት አመራር ለትግሉ ሲል የወሰደው ብልህ ዕርምጃ ነው በማለት የሚያሞካሽ አይጠፋ ይሆናል። ያኔ የተነዛውና ጥርጣሬ ያጫረው መርዝ ግን ዛሬ ድረስ መዝለቁን መካድ አይቻልም። ከላይ የተጠቀሰው በወቅቱ የነበሩትን የትግራይ ተወላጅ የደርግ አባላት ለጥቃት ያጋለጠ ሲሆን ከዚያ ባሻገር ደርግ በሕዝቡ ላይ የነበረውን እምነት ያስለወጠ ነው ለማለት ይቻላል። የደርግ ጥርጣሬና ዕርምጃዎችም ለሕዝቡ የሥጋት ምንጭ እየሆነ በሁለቱም ወገን አለመተማመን በመስፈኑ ሕወሓት የዘራው ጥርጣሬ ደርግ በስተመጨረሻ ሲያራምደው ለነበረው በሕዝቡ ላይ ያነጣጠረ የሚመስል አቋም ሳይዳርገው አልቀረም። ሕወሐትም ያን የጥርጣሬ መርዝ ከረጨ በኋላ ደርግ የሚሰነዝረውን ጥቃት ሸሽቶ ለሚመጣው መጠጊያና አለኝታ ሆኖ በመቅረብ አትርፏል። ሕወሓት በራሱ ላይ የተነጣጠረውን የደርግ መንግሥት ጥቃት በሕዝቡ ላይ እንደመጣ የፀረ ሕዝብና ጨፍጫፊ መንግሥት ሥራ በማቅረብ በሕዝቡና በድርጅቱ መካከል ልዩነት የሌለ አስመስሎ ሲያቀርብ ኖሯል። ዛሬም አያሌ የዋህ ተንታኝ ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው አይደለም የሚል አሳዛኝ ጥያቄ ማንሳቱም ከዚያ ድሮ ከተዘራው ጥርጣሬ መቀዳቱ አይቀርም። የሕወሓት አመራር መንግሥት ከሆነ በኋላም የትግራይን ሕዝብ ማሸበሩን አልተወም። ችግር ባጋጠመው ጊዜ ሁሉ የትግራይን ሕዝብ ለጥቃት ሲያጋልጥ መኖሩ አልያም “ና ሙትልኝ” ሲል መኖሩ ይታወቃል። ለምሳሌ በምርጫ 97 የቅንጅት ሰፊ ተቀባይነት አስደንግጦት ኢንተርሃምዌ መጣብህ በማለት ሕዝቡን አሸብሮ ከጎኑ እንዲሠለፍ ማድረጉ ይታወቃል። ልክ በረሐ እያለ የውሸት ሰነድ አዘጋጅቶ ንፁኃን አገር ወዳድ የትግራይ ልጆችን እንዳስመታ ሁሉ ዛሬም በመላው ኢትዮጵያ ያሉት የትግራይ ልጆች ቢሞቱለት ደስታውን አይችለውም። የሕወሓት አመራር የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ለቆ ከሄደ በኋላም የራሱን ሽሽትና ፍርኃት ወደ ሕዝቡ በማጋባት፣ በራሱ ላይ የሚሰነዘረውን ክስና ስድብ በሕዝቡ ላይ የተሰነዘረ በማስመሰል፣ ያልተባለውን ተባለ፣ ያልተደረገውን ተደረገ በማለት፣ ስብከቱን አልቀበል ያለውንም “ባንዳ” የሚል ስም ሰጥቶ ከሥራ በማፈናቀል በትግራይ ተወላጁ ደምና መስዋዕትነት የራሱን ሕይወት ለማቆየትና የክልል ሥልጣኑን ዕድሜ ለማራዘም ይዳክራል። በመላው ኢትዮጵያ ለአሥርት ዓመታት ተጭኖ የነበረው የጭቆና ቀንበር ከነዝርፊያው፣ መሬት ወረራው፣ ከነጭንቀቱ ዛሬ ትግራይ ላይ ብቻ ተንሰራፍቶ ይገኛል።

የሕወሓት አመራር የዛሬ 30 እና 40 ዓመት በርካታ ታጋዮች ፈንጂ ረግጠው እንዲሞቱላቸው አድርገው ሲያበቁ፣ ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለለትን የሟች ጓዶቻቸውን ፍትሕና እኩልነትን የማረጋገጥ አደራ በመብላታቸውም ሳያዝኑ፣ ጭራሽ አሁን ደግሞ የእነዚያን ጀግኖች ልጆች፣ ብሎም የልጅ ልጆች በሐሰተኛ ሰበካ “ኑ ሙቱልን” በማለት ለጦርነት ይቀሰቅሳሉ። የሕወሓት አመራር ነገር ሁሌም እናንተ ሙቱልኝ እኔ ልሰንብት ነው። ዛሬ ደግሞ የያዙት ዕቅድ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በምንም የማይለየውን የትግራይ ሰው እንዲሁ በከንቱ ከገዛ የአገሩ ልጆች ጋር ደም ማቃባት ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም ደም በማቃባት እንለየዋለን ካሉ የተለየ ጥቅም ሳይኖረው ከገዛ ወገኑ ለመለያየት ካጩት ጠላቶቹ እነሱና እነሱ ብቻ ናቸው።

እስቲ ዛሬ እንኳን የእኛ ለምትሉት ሕዝብ እዘኑለት!

የትግራይ ሕዝብ ወዶም፣ ተገዶም ለሕወሓት አመራር በትግል ጊዜ ስንቅ፣ ትጥቅና ወጣት አቅራቢ ሆኖላችሁ፣ ወደ ሥልጣን ስትወጡ መወጣጫ መሰላል፣ ወንበራችሁ ሲነቃነቅ የግዱን ድጋፍ ሆኗችሁ ኖሯል። እነሆ ከሥልጣን ስትወርዱ ደግሞ መደበቂያ ሆኗችኋል። እንደ ገና ጦርነት? አያሳዝናችሁም? ከዚያ በላይ ምን ይሁንላችሁ? ዛሬስ ሙትልን የምትሉት ለምን ዓላማ ነው? ለመገንጠል? ለምን? ምነው አሁን እንኳን ብትተውት? ምነው ለኢትዮጵያውያን ከመጣው ነፃነትና ተስፋ ቢቋደስበት? ዛሬ በኢትዮጵያ የሕዝቦችን እኩልነት ለማረጋገጥ ቆርጦ የተነሳ፣ ጠመንጃን ከፖለቲካ ቋንቋነት ውጭ ለማድረግ ግማሽ መንገድ ሳይሆን ሙሉውን መንገድ ተጉዞ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ካሉበት ድረስ ሄዶ እጃቸውን ስሞ አገር ቤት ያስገባ፣ እናንተንም የይቅርታ እጁን ዘርግቶ በትዕግሥት የሚጠብቅ መንግሥት መኖሩን ታውቃላችሁ። ተጠቀሙበት።

ካላመናችሁት በሽማግሌ ፊት በር ዘግታችሁ አስምሉት። ካልተጣላኸን ግን አትበሉት። የጠየቃችሁትን ሁሉ ሲሰጣችሁ የኖረውን፣ የእኛ የምትሉትን ሕዝብ ታይቶ በማይታወቅ ትዕግሥት ከሚጠብቃችሁ የኢትዮጵያ መንግሥትና ከገዛ ወገኑ ጋር ደም አታቃቡት። ፍጥጫውን አርግቡት። ዛሬ ከናንተ የሚጠበቅ የጀግንነት ሥራም ይኸው መሆኑን እወቁት።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...