Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያልተገራ ሥልጣን!

የዛሬው መንገድ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ነው። አጀማመራችን በፀጥታ ስለሆነ ተሳፋሪዎች በሙሉ የሚተነፍሱ አይመስሉም። ወያላው እንጀራው በለቅሶ ተጀምሮ በጩኸት በሚገባደድ ሕዝብ መሀል ያለ ዕረፍት ይጮኻል። ሥራው ሆኖ ነው እንጂ ከጩኸት የሚገላግለው ቢያገኝ አይጠላም።  እንደምንም ብሎ የመንጃ ፈቃድ ማውጣት ግድ ይለዋል፡፡ ካልሆነም ወደ ሌላ ማንጋጠጥ አለበት፡፡ ጥሪ በማይፈልገው የትግል ጎዳና ላይ የወያላው ልፋት መና የቀረ ባይመስልም፣ ታክሲውን ለመሙላት የፈጀበት ጊዜ ግን ብዙ ሳያሳስበው አይቀርም፡፡ ሰው የሚደርስበትን ቦታ እያሰበ ስለአዋዋሉ፣ ስለኑሮው፣ ስለቤተሰቡና ስለሥራው እያውጠነጠ ባላሰበው በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣ የህልማችንና የሩጫችን ውጤት በአብዛኛው አንገት ያስደፋል። ከደሳሳ ጎጆ መፈናቀልም አለ፡፡ ይህ ደግሞ ከሚችሉት በላይ ነው፡፡ ምን ይደረግ!

ሲዘሉ መሰበር የመንገዱ ህልውና መሠረት ቢሆንም ቅሉ፣ በዚህ በአገራችን የአረማመድ ዘዬ ሳንዘል በተቀመጥንበት የተሰበርን ጥቂት አይደለንም። የዚህ ጎዳና ትርክት ብዙ ነው። መውጣትና መውረድ አክርማና ስንደዶ ሆነው ያልቀየሱት ጎዳና የለም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ነፃ ብሎ መንገድ፣ እንደ ጨርቅ የሚጠቀለልና አልጋ በአልጋ የሆነ ጎዳና ለሰው ልጅ አይገባውም የተባለ የተፈጥሮ ሕግ ነው። በዚህ ግጭቱ፣ ተንኮሉ፣ ተግዳሮቱና ሸሩ በማያልቅ የሰው ልጅ ሕይወት ሁሉም እንደ ራሱ አረማመድ እየተጓዘ፣ እንደ ሕዝብ ደግሞ በጋራ መጓጓዣ ሆኖ የደቦ ታሪኩን ይፈትላል። ዓመት ይመጣል ዓመት ይሄዳል። በፈተለው ልክ ሁሉም የድርሻውን ሕይወት እየሸመነና እየለበሰ፣ ለታሪክ ደግሞም ለታዛቢ በሩን ይከፍታል። መንገድ ሁሉን ይዳኛል። ዘመን ሁሉን ያስተዛዝባል። የፍትሕ ያለህ ባዩ ወዮታ ግን አድሮም ይባባሳል። መልካሙና በጎው ነገር እየናፈቀ ዕድሜ ይነጉዳል፡፡ ዓለም እንዲህ ናት!

ጉዟችን ተጀምሯል። ‹‹ጠላም ይጠጣና ይፈሳል አተላው፣ ጠጅም ይጠጣና ይፈሳል አንቡላው፣ ሥጋም ይበላና ይጣላል አጥንቱ፣ ዕዳም ይከፈላል እየሰነበቱ፣ ዓይኑን ያፈጥና ይቀራል ትዝብቱ፤›› ይላል በክራር የሚቀኘው፡፡ ዕድሜና ዘመን አሳላፊው መንገደኛ ታክሲያችን ጣራ ሥር ተሰባስቦ አንገቱን እየወዘወዘ ያፏጫል። እኩል ሲያፏጭ የቆየው መልሶ፣ ‹‹ማን እያለቀሰ ማን ያፏጫል?›› ብሎ ሲያፈጥበት፣ ‹‹እገጭ እገው ይላል ቆርቆሮ ሲመታ፣ ዘንድሮ ልወዝወዝ በሃቻምናው ፋንታ፤›› ብሎ ዘፋኙ ያቋርጣቸዋል። ‹‹ይወዘውዘኛል ይወዝውዝ አባቱ አለ ያገሬ ሰው። እንዲህ ከተፈጠርኩ ጀምሮ በመወዝወዝ አዲስ ዓመት ተቀብዬ አንዱን ወር ጨርሼ ሁለተኛውን አጋምሼ አላውቅም፤›› ብለው ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ አዛውንት ተናገሩ። ክራሩ ይከራል። ተጫዋቹ፣ ‹‹ዝንጀሮ በገደል አድጦት አይወድቅም፣ እንዲህ ያለ ዘመን አጋጥሞኝ አያውቅም፤›› ሲል ከአዛውንቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ሐዘን ውስጥ ከወደቁ ጋር አንድ ላይ ያለ ይመስላል። እንዲያ ነው!

‹‹እሱንስ ማን አየብዎ? ጨለማ በመልበስ ከጀመሩት ጎራ ቢሆኑስ ኑሮ?›› ሲላቸው ከጎናቸው የተሰየመ ወጣት ከጀርባቸው የተሰየመች ወይዘሮ ደግሞ፣ ‹‹እሱንማ መብራት ኃይል ቀድሞ ጀመረው። እንዲሁ ብልጭ ድርግም ሲያደርግብን ዋለ፤›› ብላ አሽሟጠጠች። ‹‹ብልጭ ድርግሙንማ ለመድነው እኮ። እኛ መልመድ ያቃተን ከኃይል ብዛት የተነሳ እየተቆራረጠ ያስቸገረንን መግባባት ነው፤›› አላት አጠገቧ የተሰየመ ጎልማሳ። ‹‹ ለካ እሱም አለ? ነገር እየበዛ ሚሞሪዬ ሞላ እኮ እናንተ?›› ብላ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ዘመናይ ፈገግ አለች። ‹‹ለምንዴሊትአታደርጊም የተወሰነውን?›› መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት ወጣቶች አንድ ፀጉረ ጨብራራ ሲያናግራት፣ ‹‹እስኪ መጀመሪያ የውስጣችንን ቆሻሻ በቅጡ ማስወገድ እንቻል። መጀመሪያ ሰው በሰው ዴሊት መደረጉ ይረሳ። ከዚያ ሚሞሪ እናፀዳለን፤›› ብላ ጮኸችበት። በትንሽ ትልቁ የሚጯጯኸው ሰው ግን አልበዛባችሁም? ‹‹ምን ይደረግ ደህና ጊዜ መጣ ሲባል ተረኛ አስለቃሽና አልቃሽ በመብዛቱ እኮ ነው. . .›› የሚለን ልጅ እግር ቢጤ ነው፡፡ ገብቶታል ማለት ነው!

ጋቢና የተሰየመ ወጣት በስልኩ ይነጋገራል። ወያላውና ሾፌሩ በመሀል በመሀል የሆዳቸውን ያወራሉ። ወጣቱ፣ ‹‹አንተ አንድ ሥራ ብሰጥህ በዚያው ትጠፋለህ? እኔ እኮ ከእናንተ የፈለግኩት በትብብር ለመሥራት ነው፡፡ ምናለበት ቢያንስ የሚመለከተውን ሰው ብታገናኘኝ?›› ሲል፣ ‹‹ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ የእኛ ሰው ተባብሮ መሥራት የጀመረው?›› ጎልማሳው ማማት ሲጀምር አጠገቤ የተሰየመችው ዘመናይ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹የእኛ ሙያ እኮ አንድ ላይ ተሰብስቦ መብላት አይደለም እንዴ?›› አለችው። ‹‹ምነው ልጄ የማንሰማው የለ ዘንድሮ?›› አሉ አዛውንቱ። ‹‹አይዞዎት ስለሐሜት ነው የማወራው፤›› አለቻቸው። ‹‹ሐሜትን የመሰለ ጎረድ ጎረድ የታለ ብለው ነው!›› ብላም አከለች፡፡ እውነት ነው!

እሳቸው ነገሩ ሲገባቸው፣ ‹‹እንደ እሱ አትይም ታዲያ?›› ብለው ነፍሳቸው መለስ ስትል፣ ‹‹ሐሜትማ ዘንድሮ ዘምና ዘማምና የቴክኖሎጂ ቆቧን ጭና በየፌስቡክ ማኅበር በማዋቀር የትና የት ሄዳለች። ምላስ ቀደም ቀደም እግር ቀረት ቀረት ብሎ ሥራና ሠራተኛ እንደ ዋዛ ታዩ፤›› ብለው ደረቅ ሳላቸው ብን ብን ማለት ጀመረችና ማውራት አቆሙ። ይኼኔ ጋቢና የተሰየመው ወጣት ንዴት በተቀላቀለው ድምፅ ስልኩን እንደያዘ ጮኸ። ‹‹ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዓለምን በሚመራበት በዚህ ዘመን ለስሙ ኢንተርኔት ላይ አፍጠህ ብትውልም፣ የምነግርህ የሚገባህ አይመስለኝም፤›› ብሎ ሳይጨርስ ስልኩ ባትሪ ጨርሶ ዘጋ። ይኼኔ ወደ ሾፌሩ ዞሮ፣ ‹‹በአስተሳሰብና በአመለካከት ሰው እንደ አዲስ ባልተፈጠረበት አገር ሥራ ፍጠሩ የሚሉን ግን ምን አድርገናቸው ነው?›› ብሎ ጠየቀው፣ መሪ የጨበጠ ሁሉ ለሁሉም ነገር መልስ ያለው ይመስል፡፡ አልሰማም እንዴ በሥርዓት መምራትና መመራት ብርቅ እንደሆነ!  

ወያላችን ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ሁለት ወጣቶች ጭቅጭቅ ጀመሩ። አንደኛው፣ ‹‹እንዴት ያልተጣራ ወሬ እንደ ወረደ ትነግረኛለህ? መቼ ነው ግን አንተ የምትሠለጥነው?›› ይላል። ያኛው ደግሞ፣ ‹‹ይኼ ከመሠልጠን ጋር ምን ያገናኘዋል?›› ይለዋል። ወያላው አፈፍ ብሎ፣ሒሳብ!ሲለው አንደኛው ወያላውን ትኩር ብሎ ዓይቶት፣ ‹‹አንተ ደግሞ ዘለህ ሒሳብ አምጡ የምትለው ምን ሰምተህ ነው?›› ሲል አጉረመረመ። ‹‹አትበሳጭ ወንድሜ ምንም አልሰማሁም፣ ነገር ግን ጓደኛህ በሕልሙ ያየውን ጭምር እውነት አስመስሎ ይነግርሃል…›› አለው ወያላው። ‹‹ኧረ ተወኝ! ሞባይል ሲጎረጉር ሲውል አንደኛ ስለሆነ ሥልጣኔ እሱ  ቤትፌስቡክላይ የሚወራውን ሁሉ እንደ እውነተኛ ዜና ማነብነብ ነው። ሥራ ላይ ደግሞ ያለምጣል፤›› ሲል ስለባልደረባው ተረከለት። ስለስንቱ ስንቱ ይተረክ ይሆን!

‹‹መቼ እሱ ብቻ ሆነ ብለህ ነው? በሥልጣኔና በዘመናዊነት ስም መስሎኝ ሁላችንም አሳራችንን የምናየው። ደርሰው ሠለጠንን ባዮች ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ምጥቀት በመገንባት ፈንታ ሲያፈርሱ፣ አንድ በማድረግ ስም ሲሰነጣጥቁ ስንታዘባቸው እንውላለን፤›› ካለው በኋላ የአፍታ ዝምታ ነገሠ። ወያላው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይመስላል አምጦ፣ ‹‹ሒሳብ!›› አለው።ከዚህ በኋላ ብታስጮኸኝ አንተ ታውቃለህይመስላል፡፡ ወጣቱ ሒሳቡን ከፍሎ ሲያበቃ በሐሳብ እንደተዋጠ ተክዞ ቀረ። ይኼን የሚታዘቡ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ ሁለት ጎልማሶች፣ወጣት ሁሉ ስሜታዊ፣ ግዴለሽና አቁስል ተደርጎ በሚታሰብበት አገር ይኼንን ወጣት እንዲህ ሆኖ ማየት አይገርምም?› ይባባላሉ። ቆም ብለው ሲያጤኑት ሁሉም በራሱ ጭንቀት ተውጦ የሰው የሚያዳምጥበት ጊዜ አጥሮታል። ይኼኔ ችግርና ችግርተኛ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እየተላከኩ በመፍትሔ ዕጦት ዘመን የሚቆጥረው ወገን እያደር በእጥፍ ይጨምራል። ማጣፊያው ሲያጥር መጥኔ ያሰኛል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ምን ዓይነት ዘመን ነው ዘመነ ድሪቶ፣ አባቱን ያዘዋል ልጁ ተጎልተፐ፤›› ብለው አዛውንቱ ሲያንጎራጉሩ፣ ‹‹ምን ይደረግ? ይኼ አሁን ያሉት በደስታ ተቀብለን በመከራ የምንሸኛቸው ጊዜያት ድምር ውጤት ነው፤›› አላቸው ከጎናቸው የተሰየመ ወጣት። ‹‹እንዲህ አይደለም ወይ ሰው ያለቦታው፣ ብሳና ይሆናል ሸንኮራ አገዳው የተባለው ታዲያ እኮ ለእኔ ነው። ሰንብት ብሎ ይኼን የሚያሳየኝ፤›› ይሉታል። ‹‹ተመሥገን ነው። ደግ ደጉን ካዩ እኮ ብዙ ለውጥ አለ። ግን አንዳች ከሚያህል ነጭ ይልቅ ትንኝ የምታህል ጥቁር ነጥብ ትጎላለች፤›› ብሎ ሳይጨርስ ከወደ ጋቢና፣ ‹‹ተው! ተው! እንዲህማ ነገር አታቃል፤›› ብሎ አንዱ አቋረጠው፡፡ አታካብድ ቀርቶ አታቃል ዘመኑን ወርሶታል። ወይ ጊዜ!

አዛውንቱ ይኼኔ ፈገግ ብለው፣ ‹‹አይ ወጣት መሆን እንዴት ደስ የሚል ነገር ነው። አደራ ልጆቼ ይኼ ያገባኛል ባይነታችሁ፣ ይኼ ለአገር ለወገን የማሰብ ስሜታችሁ መቼም ቢሆን አይቀዝቅዝ። ብቻ. . .›› ብለው ድምፃቸውን ሲውጡ፣ብቻ ምን?” አለች ከጎኔ። ‹‹ብቻ ከክፉ መካሪ፣ ከገደል ቆፋሪና በነፍስ ከሚሸምቁ ክፉ ባልንጀራዎች እየራቃችሁ። ይኼ በነፍስም በሥጋም እየተጋለጡእኔ! እኔ!ማለት አያዋጣም። መጀመሪያ ለአገር ነው ማሰብ። አገር ማለት እያንዳንዳችን ነን። እርግጥ ነው የሥራ እንጂ የሐሳብ ደቦ የለውም። በልዩነት ዕመኑ። ልዩነትን ማክበር ራስን ማክበር ነው፣ አገር ማክበር ነው፣ መሠልጠን ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ፈጣሪን አትርሱ፣ በገዛ ወገናችሁ ላይ ሰይፍ አትምዘዙ፣ ድሆችን አትበድሉ፣ ጊዜ ሰጠን ብላችሁ አትመፃደቁ፣ ሥልጣን ስትይዙም ለደሃ እዘኑ፣ አገራችሁን አስቡ. . .›› ሲሉ ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ቆማለች። በዚህ ጊዜ እኮ መካሪ አያሳጣ ማለት ተገቢ ነው። ‹‹አዛውንቱ በተለይ ሥልጣን ስትይዙ ለደሃ እዘኑ ያሉት ልብ ይነካል፡፡ ያልተገራ ሥልጣን የደሃ ጠላት ነው ማለታቸው ይመስላል. . .›› የሚለው ታዳጊ ነበር፡፡ እውነት ነው! መልካም ጉዞ

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት