ያ! ታላቁ ባለቅኔ ሎሬቱ. . .
ያገር አድባር-የሕዝብ ዋርካው «እ…!» እያለ፤
ስለጥበብ፥ ስለ ሕዝበ-ዓለም ዕድሜ ልኩን እንደተብሰለሰለ
ቢቸግረው ”አብረን ዝም እንበል” እንዳለ፤
ከነቁጭቱ – ከነህልሙ እንደዋዛ ከንበል አለ፡፡
ግርምቴ . . .
ተፈጥሮ በነጠላና በህብር በፈጣሪ ጥበብ መዋቀሩን ላስተዋለ
የተነጣጠለ፥ የተቃረነ ቢመስልም
በፈጣሪና በተፈጥሮ ሕግጋት ነው’ኮ ተገማምዶ፥ ተሳስቦ በአብሮነት የተሳለ፡፡
የሰው ልጅ ግና…!
«በሕግ አምላክ! . . . በሕገ መንግሥት!” » እየተባባለ
ቁርጥራጭ ብረታ ብረት እየሳለ፤
በሆነ ባልሆነው እርስ በርሱ አንገት ለአንገት ሲቀላላ ስለምን በከንቱ ዋለ?
የኛ ጉዶች፡-
በምላስና-ጠመንጃ እየተቋሰሉ¡
በዛቻ-በፉከራ ተጋግለው ሲገዳደሉ እየዋሉ
በየቤተ-ሃይማኖታቱ ደጃፎች ራሳቸውን ብፁዕ ለማስመሰል እየታገሉ፣
በየሸንጐው -በየፓርላማው እጃቸውን ሰቅለው <ፍትሐዊነት¡ እኩልነት¡> እየተባባሉ፤
በዕውንም ሆነ በህልማቸው ግን? ለበቀል ለየጣዖታቱ-ለየአድባራቱ ሳይቀር ስለምን ስለት ተሳሳሉ፤
ስንት ሰውስ ሲሰዋ ይበቃ ይሆን? ዕርቅ ለማውረድ-ለአብሮነቱ ተባባሉ፡፡
ጡንቻ ለጡንቻ ተገጫጭተን
ትከሻ ለትከሻ ተለካክተን
በቃላት ድምቀት፥ በዲስኩር ብልጫ ተወናብደን
በባህል፥በታሪከ ትርክት ተቀራርነን
ከእስራቱ-ግርፋቱ፥ ከደም አዙሪቱ መውጣት ቢያቅተን
ምነው ለሕዝቡ እፎይታ ብንሰክን አብረን፡፡
ወገኖቼ . . .
በማናውቀው፥ በማያስማማን ሚዛን ተመዛዝነን
በቃላት ጋጋታ በሕግ መሰል አንቀጻት ተደናቁረን
መደማመጥ መግባባት ካልቻልን
እባካችሁ ሕዝብ አናጫርስ፥ አገር አናፍርስ በደመ-ነብስ ተደናብረን፡፡
ከአልቦ በታች ቁልቁል እንዳይሆን ነጋ’ችን፤
ምናለ ብንሰክን አብረን
ሕዝብና አገርን ለማዳን ብለን፡፡
ቃል-እምነት-መሀላ በሥጋ ተበልጦ ቁልቁል ከምንወድቅ
በምድር በሰደድ፥ በሰማይ በሲዖል እሳት ከምንነድ
አይሻልም እንዴ ወገኔ?
አብረን ሰክነን በአገራችን ፍቅርና ሰላምን ብናጸድቅ፡፡
ሁሉም በየጐራው እኔ ነኝ መነሻው፥ አቅኚው ካለ
ያም ይህም እርስ በርሱ ተጧጡዞ ያለልኬት «ገፋZኝ-ጨቆንከኝ» ከተባባለ
በጥላቻ . . . በንቀት አገር ምድሩ ከተበከለ
የሥነ- ኅሊና ሚዛኑ ከተከነበለ
ከዚህ በላይ ውድቀት- ድቀት- ሞትማ የታለ፡፡
ወገኖቼ . . .
ይሻል ይሆናል-ካልን እስቲ በጋራ እንሂድ
ወደ የ…ክልሎቹ አብረን እንንጐድ…
ሕገ መንግሥት «ይቀደድ!…አይቀደድ!» ብለን፥ ቸኩለን ሳንፈርድ
እባካችሁ! በቅድሚያ፥ የሕዝባችንን ዕንባ፥ አብረን እናድርቅ፡፡
ከድምፅ ማጉያና ከእጅ መዳፍ ጭብጨባ እንገለል፡፡
ለአንድ አፍታ እንኳን- ከየአደባባዮቹና ከየአዳራሾቹ እንነጠል፡፡
እንደጥንቱ በዛፎች ጥላ ስር እንጠለል፡፡
በጋራ ሆነን በየወጋችን-በየባህላችን አብረን «ሰላም-እርቅ» እንበል፡፡
ከዓባይ ማዶ ወደ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ወደ ህዳሴው ግድብ አብረን እንውረድ
እጅ ለእጅ ተያይዘን በፋሲል ግንብ . . .በጣና ዙሪያ እስክስታ እናውርድ፡፡
አብረን እንሂድ ጋምቤላ ከለማለሙ አገር
በባሮ ወንዝ ላይ በፍቅር መርከብ አብረን እንሸርሸር፡፡
ላሊበላ ሂደን «እግዚኦ ማረን» እንበል
የፈጣሪን ቡራኬ መለኮቱን እንቀበል፡፡
ወደጥንታዊቷ አክሱም እንዝለቅ …
ከአዴታቱ እጅ ተቋድሰን አንባሻውን
በበረከቱ እንፈወስ እርስ በእርስ ተመራርቀን፡፡
«ሆ!ያ ማሬዎ! -ማሬዎ!» አብረን እያልን
ቢሾፍቱ-ሆራ አርሰዲ ለኢሬቻ እንውረድ
ሀባቦ-መርጋ ጉራቻ … እርቁን በእጃችን ጨብጠን፡፡
ወደ አርባ ምንጭ እንዝለቅ …
ለሕዝብ ክብር፥ ለወገን ፍቅር ብለን፥ ከኒያ ደጋግ ሕዝቦች ጋር ሆነን
እርጥብ ሳር ይዘን፥ በመሬት ላይ እንውደቅ አብረን፡፡
ወደ ቦረና ከአንጋፋዎቹ መገኛ አብረን እንዝለቅ
የገዳ-ዲሞክራሲ ችግኙ በሁሉም ሥፍራ እንዲጸድቅ፤
በአንደበተ ርቱዓኑ፥ በንፁሀኑ አባገዳዎቹ እንመረቅ፡፡
ወደ ጅማ -ወደ ከፋ ሽምጥ እንጋልብ
ከቡና ረከቦት ዙሪያ እንሰብሰብ!
«አቦል ጀባ!» እየተባባልን እንዋዋብ፡፡
ሐረር ጀጐል፥ ደገሃቡር ሶማሌ፥ ድሬ ሼህ ሁሴን አብረን እንዝለቅ
«አስቶፍሩላህ!…አላሁ አክበር! » ብለን ከፈጣሪያችን እንታረቅ፡፡
ግርምቴ . . .
እንሂድ አፋር፥ ከቅድመ ዘራችን ከእናታችን ሉሲ አገር
እንድትተርክልን በእሳተ ገሞራ የመኖርን ሚስጥር
ለሚሊዮን ዓመታት አጽሟ ሳይፈራርስ የመዝለቁን ቀመር፡፡
እኛው በየአምስት ዓመቱ «ውረድ!…አልወርድም!» ከምንባባልበት
ለ4 ኪሎው ወንበር ከምንዶልት፥ ከምንፋጅበት
ለሕዝባችን ፥ ለአገራችን ብለን በቅድሚያ አብረን ብንሰክንለት፡፡
ምናለ ጐበዝ! ለዚህ ምስኪን ሕዝብ በቅድሚያ ብናስብለት፤
በሰቀቀን ባይባዝንበት፥ በችጋር- በጠኔ ባይረግፍበት፣፣
ሎሬቱ እንዳለው፡-
« . . . . . . .
ዳግመኛ ሞት ሳንሞት፥ አዲስ ቀን ሳይጨልምብን
ድፍን ደመና ሳይቋጥር፥ ክረምት ውርጅት ሳይወርድብን
. . . . . . . ፡፡»
ወገኖቼ . . .
በኮሮና እና በብረት መሃል ተወጥረን
ጦርነቱ ከሚፈጀን፣ በሽታና ረሃቡ ከሚያረግፈን
ምናለ ፉከራው ቀረርቶው ቢቀርብን፡፡
እናም፡-
ለአንድ አፍታ እንኳን «አሐዳዊ!…ፊዴራላዊ» ቃለ ግነቱን ገተን
ሕዝባችንን-አገራችንን ብናድን አብረን ሰክነን
ለጊዜው እንኳን ባንስማማም « ሜ. . . ሃቡልቱ ዱቢን » ብለን ተስማምተን፡፡
አሰፋ ጉያ
01/09 2012 ዓ.ም.
መታሰቢያነቱ፡-
የሥነ ጥበብ ፍቅርንና ለሕዝብ የመቆርቆርን ቀናኢነት ላወረሰኝ ለጋሽ ለማ፤ የክብር ዶክተር፣ ሎሬት አርቲስት ሻምበል ለማ ጉያ ይሁንልኝ፡፡