Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዝም አይባልም!

ሰላም! ሰላም! አንዳንዴ እኮ ምን ሰላም አለ ያሰኛል፡፡ እሳት በጉያቸው ታቅፈው የሚዞሩ መሰሪዎች እያሉ የምን ሰላም ነው ቢባል ምን ይገርማል? ለማንኛውም አንዱ ነው አሉ፡፡ አንዱ ስላችሁ ደግሞ ይኼ ኮምፒውተር ላይ ያለው ማለቴ አይደለም፡፡ እሱንማ መሆን ብንችል በምን ዕድላችን? የኑሮ ሩጫችንን አቋርጠን ኑሮን ራሱ አንዱ እያደረግን አንዘፍንም ነበር? ‹እሱም አውቆ ሰማይን አርቆሆነና ነገሩ ሰው ሕይወቱን አንዱ ማለት ቢያቅተው በአምሳሉ ሮቦት ፈጠረ፡፡ ይኼም እንደ አንዱ ከተቆጠረ ቁጠሩት፡፡ ግን አንዱ ይቆጠራል እንዴ? ለጨዋታው ድምቀት ነው የምጠይቃችሁ፡፡ በጣም ከማዳመቄ በፊት ግን ስለዚያ አንዱ ስላልኳችሁ መከረኛ ልንገራችሁ፡፡ ዓይኔን ጋረደኝ ብሎ ሆስፒታል ይሄድላችኋል፡፡ ቅድመ ምርመራ አስፈላጊ በሆነበት ዘመን ጉዳችንን ማንኛው ሐኪም በነገረን፡፡ የምሬን ነው፡፡ እናም አጅሬ ሲመረመር በደምህ ውስጥ ብዙ ስኳር ተገኝቷል አለው ሐኪሙ፡፡ ሰውዬው እየተወናጨፈ ቀወጠው፡፡ ሐኪሙ ስለስኳር በሽታ ያለው ግንዛቤ መስሎት እንዲያ ያደረገው ዘና አለ፡፡ ከዚያ አንዱ ምን ቢለው ጥሩ ነው? ‹‹ዶክተር ስንት ኪሎ ነው?›› አይለው መሰላችሁ? እንዴት ነው ነገሩ!

እኔ ግን ከኪሎው ጥያቄ የተመቸኝ ታሪኩን ሲነግሩኝ አንዱ ብለው መጥራታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ቅድም ስላችሁ እንደ ነበረው ሕይወትን እንደ ኮምፒዩተር ምትኃት ወደ ኋላ ክሊክ ማድረግ ቢቻል የስኳር እጥረት፣ የውኃ ድርቀት፣ የቤት እጥረትና የአየር ንብረት ምን ቅጡ ባለበት ተመለሰ ማለት እኮ ነው፡፡ ነገር ሁሉ በነበር ቀረ እኮ ጎበዝ፡፡ ይኼን ብዬ ያማረልኝ መስሎኝ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ አጫወትኩት፡፡ በአንዴ አመድ መስሎ ዙሪያ ገባውን ካየ በኋላ፣ ‹‹እንዴት እንዲህ ትላለህ? ጤና፣ ስኳር፣ ውኃ፣ መሬት፣ አየር በነበረት ቢመለስ ባለበት የማይመለስ እኮ በዙ አለ፤›› አለኝ፡፡ ‹‹ምንድነው?›› ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? በሁለት አኃዝ ይምዘገዘጋል ተብሎ በሚወራለት አረፋው ኢኮኖሚያችን ጀምሮ፣ ሰርቆ የከበረን አነሳስቶ በመንገድ መሠረተ ልማት አድርጎ የከተማ ባቡራችንን ተሳልሞ ብዙ ብዙ ጠራልኝ፡፡ ‹‹በቃ አሁን የተናገርኩትን አንዱ በለው፤›› ብዬ ፈትለክ አልኩኝ። ይሞታል እንዴ!

ነገርን ነገር ያነሳዋል፡፡ ያጣነው እንደ ስኳር የሚጣፍጥ እንጂ የሚመርስ አላጣንም፡፡ ያውስ ለጨዋታ? ይብላኝ ለእነ ለዛ ሙጥጥ፡፡ ነገረኛ ሆንኩ እንዴ? ለነገረኛም ነገረኛ ያዝለታል፡፡ አላዝልን ብሎ የተቸገርነው በበሽታችን ልክ መድኃኒት ብቻ ነው፡፡ ‹‹በሽተኛው በዛ መድኃኒት አነሰ. . .›› ያለው ዘፋኙ ወዶ መሰላችሁ? ‘ማንም የወደደውን ያገባና የዘፈነ የለምእንዳትሉኝና እንዳልስቅ፡፡ ውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ሰሞኑን በገባች በወጣች ቁጥር፣ ‹‹ዱባይና ታይላንድ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁት. . . ›› እያለች ትሞዝቅላችኋለች፡፡ እኔ ደግሞመልዕክት ይኖረው ይሆን? ሽርሽር አማረኝ እያለችኝ ይሆን?’ እያልኩ መጨነቅ፡፡ አሥር ጊዜ የባንክ ደብተሬ ወጪና ገቢ ላይ ማፍጠጥ፡፡ ስቀንስ ስደምር፣ የሆቴል መኝታ፣ የምግብና የትራንስፖርት ሳባዛ ሳካፍል መዋል፡፡ ግን ለምንድነው ዘንድሮ ለሽርሽር መጓዝ ሲታሰብ ገና ድካም የሚተርፈን? የኢኮኖሚው ዕድገት ማሳያ ይሆን እንዴ? ቢጨንቀኝ እኮ ነው የምጠይቃችሁ። ለነገሩ እሳት የተሸከሙ ጉዶች በበዙበት በዚህ ጊዜ በእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ጨነቀኝ ማለት አጉል ቅንጦት ነው፡፡ አጉል መቀናጣት!

በኋላ ታዲያ አስቤ አስቤ ሲደክመኝ የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ምን አባቴ ባደርግ ይሻለኛል?›› ብዬ ማማከር። ምን ይለኛል፣ ‹‹ቆይ ትንሽ ታገስ ማንጠግቦሽ ብቻ አይደለችም ዱባይና ታይላንድ እያለች የምትዘፍነው፣ ሁሉም ነው፤›› አለኝ፡፡ ‹‹እንዴት ሁሉም?›› ስለው፣ ‹‹በቃ ነዳጅ ልናወጣ ነው መሰለኝ፣ ሁሉም ሰው መካከለኛ ባለ ገቢ ይመስል የጉዞ ፕላን ያወጣል፤›› ሲለኝ፣ ‹‹ታዲያ ምነው እንዲህ ያለውን የምሥራች ቀደም አድርገህ ሳትነግረኝ?›› ስለው፣ ‹‹ምን ይታወቃል? ‘የህዳሴው ግድብ ሳይጠናቀቅ በድሎት መሞላቀቅ ጥሩ ነው ወይ?’ የሚል መልስ ከመጣ ብዬ ነዋ፤›› አይለኝ መሰላችሁ። ጉድ እኮ ነው እናንተ! ‹‹ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ›› አለች አሉ፡፡ ‹‹እኔ እኮ የከበሩ ማዕድናትና ዩራኒየም ያወጣን መስሎኝ ነው አዳሜ ለዱባይና ለታይላንድ ሽርሽር ሐዋሳ ላንጋኖን ገልብጦ የሚጫወት የመሰለኝ፤›› ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹ተው እንጂ በማለም በመብታችንማ አትምጣ፤›› ብሎ ተቆጣኝ፡፡ ኧረ እንዴት ነው ነገሩ ይኼ ዓለም እያደር የህልም ዓለም ሆነ እኮ ጎበዝ! ባለፀግነትን ተመኝተው የነገዋን ሸጋ ዓለም የሚመኙ የዋሆች ባሉባት አገር፣ እሳት ተሸክመው የሚዞሩ መሰሪዎች መብዛታቸው ደግሞ እርር ድብን ያደርጋል፡፡ የሚያሳርር ያድብናቸውና!

ይልቅ ባለፈው ሰሞን ምን ሆነ መሰላችሁ? እስኪ ደግሞ ስለሥራና አሳሩ ላጫውታችሁ፡፡ ጥጋብና ልክ የለሽነት የዘመናችን መታወቂያ ጉድ ሆኗል መቼም፡፡ እና ከደንበኞቼ ጋር ተደዋውዬ፣ ሚሊዮንን እንደ ሽልንግ ወደ አቃለለው ቤት ሸመጠጥኩ፡፡ ስደርስ ገዥና ሻጭባንኮኒውላይብሉ ሌብልቺርስ እየተባባሉ ደረስኩ፡፡ ያሻሻጥኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ሰዓቴን ሳየው ገና ማንጠግቦሽ ቡና አላቀራረበችም፡፡ እንዳልቀደም ላቤ በጀርባዬ እየተንቆረቆረ ያገናኘኋቸው ደንበኞቼ በሞቀ ፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡ ቢሸጥ ኮንቴይነር ሙሉ ሰልባጅ ገዝቶ የሠፈሬን ነዋሪ በሚያንበሸብሽ ውድ ብርጭቆ ከሚጠጡት ውድ ውስኪ ቀድተውልኝቺርስአሉኝ፡፡ግዴለም ይቅርብኝብል ኮሚሽኔነገር አሳሰበኝ፡፡ ስለዚህ ባዶውን እየጮኸ አሲድ በሚተፋ አንጀቴ ላይ አሲድ ቸለስኩበት፡፡ መስማማታቸውን ባልጠራጠርም ለማረጋገጥ ስለፈለግኩ፣ ‹‹እንዴት ነው ታዲያ?›› እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ እነሱ የእኔ ተራ ወሬ አልጣማቸውም መሰል የያዙትን ወግ ቀጠሉ፡፡ ለነገሩ ደላላ ሲያታልል እንጂ በጨዋነት ማን ያውቀዋል? ቢታወቅም ቅሉ አዳማጭ የሚኖረው አፍ የሚያስከፍት የዝርፊያ ወሬ ሲዘረግፍ ነው፡፡ ያኔ አዳሜ ልቡ ቆሞ ያዳምጣል ብቻ ሳይሆን፣ ሁለመናው ጆሮ ሆኖ ያግበሰብሳል፡፡ ወሬኛ ሁሉ!

አንዴ ወልዳ እንድትመጣ ወደ አሜሪካ ስላሳፈሩዋት ሚስታቸው (ወደ አሜሪካ ሲሉ አሁን እዚህ ጉለሌ እዚህ መካኒሳ እንጂ አትላንቲክን አቋርጠው የሚደርሱበት አኅጉርና አገር የሚጠሩ ይመስላል እናንተ?) አንድ ዓመት ሳያሽከረክሯት ስላልተመቻቸው ዘመናዊ አውቶሞቢልና ሊቀይሩት ስላሰቡት የቅርብ ጊዜ ሞዴል አዲስ መኪና በሰፊው ይጫወታሉ፡፡ ከተጠመቀ ቆየት ካለ ውስኪያቸው እየተጎነጩ ከቁብ አልቆጠሩኝም፡፡ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በአሥር ዓመት አንዴ ከቆጠረህ አይበቃህም?’ ይመስላል ሁኔታቸው፡፡ ነገሩን ላሳጥረውና (እንኳን አንዛዝተነው እንዲሁም አልቻልነው) አንደኛውቼክአውጥቶ ፈረመናኮሚሽኔንከባንክ እንድወስድ ሰጠኝ፡፡በቼክመቀበሌን አደራ ለማንም አልተናገርኩም፣ እናንተም ለማንም አታውሩ፡፡ ደግሞ በኋላ ‹‹አንበርብር ቼክነው የሚጫወተው፤›› ብሎ አንዱ ማጅራቴን ቢያስመታኝ ማን አለኝ? ትቀልዳላችሁ እንዴ! ነው ወይስ ውዷ ማንጠግቦሽአንበርብር ቢሞትምቼኩአይሞትምበሚለው ትፅናናለች ብላችሁ ታስባላችሁ? ኧረ እንዴት ተቀለደ ወገኖቼ፡፡ እኔማ እዚህ ምድር የመጣሁት ሌሎችን ላኗኑር እየመሰለኝ ስበሽቅ ነው የምውለው፡፡ ምን ዓይነቱ ሞኝ ነኝ!

መቼም ይህች ጨዋታ ብዙ ሳታስወራን አትቀርም። ከራስ በላይ ራሳችን ንፋሱን ካላሸነፍን እያሉ የሚገጥሙትን ትግል ለማን ልንገረው የሚያስብል ነው። ይኼውላችሁ እኛ ዘንድ አንድ የጎረቤቴ ልጅ አለች። ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ ዘንድሮማ ካላገባች ጉድ ነው ይባባላል መንደርተኛው። ከሚባባለው መሀል ደግሞ ስንቱ መሰላችሁ ተፋቶ የሚኖረው። ልጅቷ መቼም ሲፈጥራት ውብ ናት። አንድ ቀን ተስቶኝ ማንጠግቦሽ ፊት ስለዚችው ሸጋ ልጅ ሲወራ፣ ‹‹ውቤ ከረሜላ የተዘፈነው መቼም ለእሷ መሆን አለበት   . . .›› ብዬ ሳምንት ሙሉ እህል የማይል ሽሮ ብቻ በልቻለሁ። ኩርፊያ መሆኑ ነዋ። መቼም የማትቀና ሚስት ስጠኝ አይባል ነገር፡፡ ሚስት ለባሏ ባል ለሚስቱ፣ ዜጋ ለአገሩ አገር ለዜጎቿ ካልቀናች ምኑን ኑሮ ምኑን ትዳር ይበላል? ታዲያ ይህችን ውብ ስትወጣ ስትገባ ያም ያም አውቆጓደኛሽን አታስተዋውቂንም እንዴ አንቺ? የት ነው ምትደብቂውእያለ ይጠዘጥዛታል። የዘንድሮ ቅዝቃዜና የዘንድሮ ሰው አላበዙትም እንዴ!

እናላችሁ በቀደም አንዱ፣ ‹‹አንበርብር ለምን ለራስህ አታውቅም?›› አለኝ። ይኼውላችሁ ነገር ፍለጋ መሆኑ ነው። ‹‹እሺ ምን ብዬ ልወቅ?›› ስለው፣ ‹‹አለ የተባለ ሁሉ ገንዘቡን ወደ ውጭ አገር እያሸሸ በዶላርና በዩሮ እያስቀመጠ፣ አንተ ለምንድነው ዝም ብለህ በዲቫሉዌሽን የሚላሽቅ ብርህን የምታየው? ይኼ አገር በዚህ ሁኔታው ተስፋ አለው ብለህ ነው?›› ብሎ ምንም ሳልለው ከመሬት ተነስቶ በአገሬና በእኔ ላይ እኩል ሳቀ። ‹‹አይ ምን መሰለህ. . .›› ምናምን እያልኩ ገና መናገር ስጀምር፣ ‹‹ዝም ብለህ እኔን ብትሰማኝ ይሻልሃል። ከአንተ የበለጠ ስለገንዘብ የሚያውቅ የለም። ምን አለፋህ ይኼን አገር አምነህ የላብህን ፍሬ በከንቱ ከምታበላሸው በቶሎ አሽሸው፤›› ሲለኝ ቀስ ብዬ እንደ ምንም በሰበብ አስባብ ከእሱ ከራሱ ሸሸሁ። ለዓይን ከአፍንጫ የቀረበ አለ እስኪ አሁን? ታዲያ ምን ልክፍት ነው አፍ አፍችንን እያለ አላስቀምጥ የሚለን? ኧረ ምን ጉድ ነው! እኔማ ዘንድሮ ሰውን ምን ነካው ማለት ትቼ ራሴን መመርመር ጀምሬለሁ፡፡ ምናልባት ወፈፍ እያደረገኝ ይሆን? ምን ልበል ታዲያ!

ሰው በሚያገኘው ቀዳዳ ሁሉ ሥራው ጎራ መለየት ሆኗል። ለሌላው አለማሰብና ለራስ ብቻ መኖር ገኗል። በቀደም ምን ሆነ መሰላችሁ? አንድ የሚከራይ ቪላ ቤት ነበርና የሚከራይ ለማግኘት ላይ ታች ስል ውዬ በመጨረሻ ተሳክቶልኝ ተከራይ አገኘሁ። ሰውዬው ብቻውን ነው። ልጅም ሚስትም የለውም። ‹‹እንዴት ነው ቤተሰቦችህ በአገር የሉም?›› አልኩት ጎልማሳነቱንና መልከ መልካምነቱን መላልሼ እያየሁ። ‹‹የለም! ቤተሰብ ምን ይሠራል?›› ቢለኝ ክው አልኩላችሁ። ይህችን ይወዳል አንበርብር ምንተስኖት? ምነው ተዘጋጅ እንኳ ቢለኝ እያልኩ፣ ‹‹እንዴ! ምን ለማለት ነው?›› አልኩት በደረቀ ድምፅ። ‹‹በዚህ ጊዜ ቤተሰብ? ያምሃል እንዴ? ሚስት ከመፈለግ ነዳጅ ብፈልግ ብቻዬን ይሳካልኛል እኮ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ሰው አምርሯል ማለት እኮ ይኼ ነው። ቀላል አምርሯል? ወዲያው ከምሬቱ ጀርባ ምን እውነት ቢኖር ይሆን? ብዬ መመራመር ጀመርኩ። እንዲህ ዓይነት ሰው ጠፍቶ እኮ ነው ምሬታችን ገደቡን ያለፈው፡፡ መልሱን ታዲያ አንድ ወዳጄ ድሮና ዘንድሮ በሚለው ጨዋታው ውስጥ ያገኘሁት መስሎኝ ከእሱ ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜ ያወጋኝን አሰላስል ጀመር። በማሰላሰሌ መሀል ደግሞ ብቸኝነት የሚባለው ነገር አልገባኝ አለ፡፡ ብቸኝነት ከፖለቲካ ለመሸሽ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ ለመገለል፣ ቤተሰባዊ ሕይወትን ላለመቀበል፣ ወዘተ. እያልኩ ሳስብ ውስጡ ንፉግነት ታየኝ፡፡ ለነገሩ ንፉግነት የተጠናወተው ለአገርም አይበጅም ነው የሚባለው፡፡ ልክ ይመስለኛ፡፡! ለምን መሰላችሁ ለአገር የሚበጅ ክብሩ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ነው!

እስቲ እንሰነባበት፡፡ ምሁሩ ወዳጄ ደወለና አንድ አንድ እንበል አለኝ፡፡ እኔም ጊዜ አላጠፋሁ የኮምፓሴን አቅጣጫ በቀጥታ ወደ ግሮሰሪ አደረግኩ፡፡ ስደርስ የባሻዬ ልጅ ያላበው ቢራ አስቀድቶ በአንድ ትንፋሽ እያንደቀደቀ ነበር፡፡ አጠጣጡ እኔንም አበረታታኝ መሰለኝ የቀረበልኝን አንደቀደቅኩት፡፡ግሮሰሪው በደንበኞች ከቢጤያቸው ጋር ወግ ይሰልቃሉ፡፡ እኔና የባሻዬ ልጅ ወጋችንን ስንቀጥል፣ ‹‹ፖለቲካችን ዳዴ ማለት አቅቶት እንደ ሕፃን ሲውተረተር ያናድደኛል. . .›› ብሎኝ ድንገት ቀና ብሎ ሲያየኝ ፊቴ ጭጋግ ለበሰ፡፡ አላውጣው ብዬ እንጂ ይህ ጉዳይ በጣም እያበሳጨኝ ነበር፡፡ እሳት ተሸክመው የሚዞሩ መሰሪዎች ዙሪያችንን ከበውን ዝም እያልን ነው፡፡ አስተዳዳሪው፣ ዳኛው፣ ፖሊሱ፣ ሕዝቡ ጭምር በሚገባ እንደሚያውቁ ግን ዝምታው መብዛቱ አናደደኝ፡፡ መሰሪን ዝም ማለት ጥሩ አለመሆኑ እየታወቀ ዝምታ ይገድለናል እንጂ የትም አያደርሰንም፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ቀልደኛ ደላላ ወዳጃችን አንዱ ቢጤው ከፖለቲካ ሳይንቲስቶች በላይ ራሱን ቆልሎ ሲያወራ ያገኘዋል፡፡ ቀልደኛው ወዳጃችን ገርሞት እያየው፣ ‹‹ሰማህ ይህ ሁሉ ተሰምቶ የማያውቅ ዕውቀት ከየትኛው ዩኒቨርሲቲ ነው የተቀሰመው?›› ሲለው፣ ‹‹ይህችን ትንተና ለመስጠት እኮ የግድ ዩኒቨርሲቲ መሄድ አያስፈልግም…›› አለው ተብሎ ነበር፡፡ ዝምታ ሲበዛ ነው እኮ ጥራዝ ነጠቆች የሚፈነጩት፡፡ ‹‹ዝምታ ለበግም አልበጃት›› እንዲሉ ዝም አንበል፡፡ መልካም ሳምንት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት