ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 1.9 በመቶ ብቻ እንደሚሆን ተነበየ።
የአይኤምኤፍ ትንበያ የኢትዮጵያ መንግሥት ከገለጸው የ6.1 በመቶ አጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ያለ ነው።
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች የ2020 ዓመታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።
የገንዘብ ተቋሙ በሪፖርቱ እንደገለጸው፣ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ በዋናነት የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሽቆልቆል ያጋጥማቸዋል።
በዋናነትም በቱሪዝም ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስባቸው ሲሆን፣ ምርቶችን ኤክስፖርት በማድረግ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮችም በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሦስት በመቶ እንደሚሆን ገልጿል።
በቀጣዩ ዓመትም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከጉዳት እንደማይወጣ የገለጸው ሪፖርቱ፣ እ.ኤ.አ. በ2021 የአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕደገት 3.1 በመቶ እንደሚሆን ከወዲሁ ገምቷል። ለዚህም በምክንያትነት የገለጸው ወረርሽኙ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ባለው ጉዳት ሳቢያ የሚያገኙት የውጭ የገንዘብ አቅርቦትና ብድር በከፍተኛ የሚያሽቆለቁል መሆኑ ነው።
እንደ ተቋሙ ትንበያ በ2021 ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች 290 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ፋይናንስ እጥረት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ በተጨማሪም አገሮቹ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንደሚመቱ የገለጸ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ እንደምትሆን አመላክቷል።
አይኤምኤፍ ባወጣው የኢኮኖሚ ሁኔታ ሪፖርት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 1.9 በመቶ ብቻ ይሆናል ቢልም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይህ ሪፖርት ከመውጣቱ ከሁለት ቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ መጠነኛ መቀነስ ቢታይም የ6.1 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ተናግረዋል።
በ2012 ዓ.ም. የዘጠኝ በመቶ አጠቃላይ የኢኮኖማ ዕድገት ለማስመዝገብ አቅዳ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ 6.1 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን የፕላን ኮሚሽን መረጃዎች ማመላከቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ይህ አፈጻጸም ከዕቅዱ አንፃር የ2.9 በመቶ ቅናሽ ቢታይበትም፣ ዕድገቱ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከገጠመው የኢኮኖማ ፈተና አንፃር ሲመዘን ትልቅ ዕድገት እንደሆነ ገልጸዋል።
ለኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዙ የኮሮና ወረርሽኝ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ በዚህ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ዘርፎች ትራንስፖርት፣ የትምህርት ዘርፍ፣ የሕዝብ አገልግሎቶችና ቱሪዝም መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ትራንስፖርት 1.1 በመቶ፣ ትምህርት 1.8 በመቶ፣ የሕዝብ አገልግሎት 2.3 በመቶ እና ቱሪዝም 9.8 በመቶ የሆነ ዝቅተኛ ዕድገት ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
ከኢኮኖሚ ዘርፎች አንፃር ሲታይ ደግሞ፣ ግብርና የ4.3 በመቶ ዕድገት ሲያስመዘግብ፣ ኢንዱስትሪ 9 በመቶ፣ አገልግሎት ዘርፍ 5.3 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል። ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች አንፃር ሲመዘን ከፍተኛ ዕድገት የተመዘገበው በማዕድን ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።