Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንኮች የሚሰበስቡት ተመላሽ የብድር መጠን እየቀነሰ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ባንኮች እየሰበሰቡ ያሉት የተመላሽ ብድር መጠን እየቀነሰ መምጣቱንና በዘንድሮው የመጀመርያ ሩብ ዓመት ያሰባሰቡት ተመላሽ ብድርም በ15 በመቶ እንደቀነሰ ተገለጸ፡፡

ከተለያዩ ባንኮች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ባንኮች እየሰበሰቡ ያሉት ተመላሽ ብድር መጠን መሰብሰብ ካለበት ያነሰ መሆኑንና ቸግሩም ሊቀጥል እንደሚችል ተሠግቷል፡፡  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2013 ዓ.ም. የመጀመርያ ሩብ ዓመት ይፋዊ መረጃ መሠረት፣ ባንኮች በመጀመርያው ሩብ ዓመት በሦስት ወራት የሰበሰቡት ተመላሽ ብድር 15 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን መጥቀሱ ችግሩን ያሳያል ተብሏል፡፡

ከነሐሴ እስከ መስከረም ባሉት ሦስት ወራት ባንኮች የሰበሰቡት ተመላሽ ብድር 35 ቢሊዮን ብር መሆኑንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ይጠቁማል፡፡

ከብድር አመላለስ ጋር ከፍተኛ ቅናሽ የታየባቸው ብድር የወሰዱ ዘርፎች ተብለው ከተለዩት ውስጥ በኢንዱስትሪ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞናዊ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በተጠናቀቀው ሩብ የበጀት ዓመት የባንኮች ተመለሽ ብድር ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ወደ 15 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ ምክንያትነትም ኮቪድ 19 ያመጣው ተፅዕኖ ሊሆን እንደሚችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አመልክተዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ ከባንኮችና ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር በትብብር በመሥራት የሚሻሻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እንደሚያደረግ ገዥው ገልጸዋል፡፡

የባንኮች ተመላሽ ብድር መጠን በተለይ በተያዘው በጀት ዓመት ሊቀንስ እንደሚችል፣ ቀድሞም ይገመት እንደነበር የሚያስታውሱት የባንኩ ባለሙያዎች በተለይ ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ሁሉም ባንኮች የብድር መራዘሚያ ማድረጋቸው ባንኮች በዕቅድ የያዙትን ብድር የማስመለስ ሥራ እንደሚያከብድባቸው ይገመት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን ባንኮች 27 በመቶ አስገዳጅ የቦንድ ግዥ መመርያ ከተነሳላቸው በኋላ አሁንም ሁሉም ባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔያቸው ላይ ቅናሽ ማድረጋቸውም የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀርም የሚል ትንታኔም የሚሰጡ አሉ፡፡

በዋናነት ግን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በተለይም ደግሞ በእጅጉ የንግድ እንቅስቃሴያቸው የተጎዳ እንደ ሆቴልና ቱሪዝምና ኮንስትራክሽን የመሳሰሉት የንግድ ዘርፎች ከተፅዕኖው ወጥተው የንግድ እንቅስቃሴያቸው ወደ መስመር እስኪገባ ድረስ ብድር ለመመለስ ጊዜ የሚወስድባቸው ስለሚሆን በባንኮች የተመላሽ ብድር አሰባሰብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

እንደ ባንኩ ባለሙያዎች ማብራሪያ፣ ከብድር አመላለስ ጋር በተያያዘ ሊጠቀስ የሚችለውና ምናልባትም በቶሎ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ቢኖር በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የንግድ ሥራቸው ተቀዛቅዞ ብድራቸውን ለመክፈል የማይችሉ ብቻ ሳይሆኑ ብድር ለመክፈል የሚችሉ ተበዳሪዎች ሳይቀሩ ብድር ለመመለስ ያለመቻላቸው ጉዳይ ነው፡፡

እንዲህ ያሉ ተግራት በተለይ ከጥቂት ወራት ወዲህ እየተስተዋሉ መምጣታቸው ተመላሽ ብድርን በታሰበው ልክ ለመሰብሰብ እንዳላስቻላቸው እየተገለጸ ነው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ተመላሽ ብድር አሰባሰቡ ላይ ያለው ውስንነት በእንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ጭምር ችግር የታየበት መሆኑ በዚህ ረገድ ዕርምት መውሰድ እንደሚኖርበት ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመጀመርያው ሩብ ዓመት ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀሩ 15 በመቶ (14.9) ተመላሽ ብድር መቀነሱን ቢያመለክቱም ባንኮች በዚህ ጊዜ ውስጥ ለመሰብሰብ አቅደው ከነበረው አንፃር ሲመዘን አፈጻጸሙ አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ምክንያቱም ባንኮቹ አሁን ካሰባሰቡት ተመላሽ ብድር በላይ ይጠብቁ ስለነበር ነው፡፡ በመሆኑም የብድር አመላለሱን ከፍ ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ባንኮችም ሆኑ ብሔራዊ ባንክ  ተጨማሪ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባ አመላካች መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥም ሰሞኑን በሰጡት ማብራሪያ በብድር አመላለስ ላይ ባንካቸው ተጨማሪ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡             

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች