Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹ለትግራይም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት ዕውቅና እንሰጣለን›› የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን

‹‹ለትግራይም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት ዕውቅና እንሰጣለን›› የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን

ቀን:

‹‹በመንግሥታቱ መካከል ለውይይት ፈቃደኝነት ቢኖርም ቅድመ ሁኔታዎች መቀመጣቸው ፈታኝ ሆኗል››

 ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል

በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሕጋዊነት መካሰስ ቢቀጥልም፣ የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሁለቱም ሕጋዊና ቅቡልነት ያላቸው መሆኑን የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

- Advertisement -

በተለያዩ ምክንያቶች ተከስተው ለዓመታት የቆዩ የቂምና ቁርሾ ችግሮችን በዕርቅ ዕልባት ሰጥቶ፣ ሰላምና ፍቅርን እንዲያሰፍን የተቋቋመው የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ የዕርቀ ሰላሙን የማስፈን ሥራውን ለመጀመር በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቱ ሥፍራዎች እየጨመሩ የመጡ ግጭቶችና በማቋቋሚያ አዋጁ ውስጥ ያልተካተቱ የሕግ ማዕቀፎች እንቅፋት እየሆኑበት መምጣታቸውን ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመርያ ሩብ ዓመት የሥራ እንቅስቃሴውና ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ፣ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ እየሱስ  ሱራፌል፣ ከምክትላቸው ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤና ከአርቲስት ደበበ እሸቱ ጋር በመሆን ኮሚሽኑ ለምን ወደ ሥራ ለመግባት እንደዘገየና አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ የፀጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ የገጠሟቸውን ችግሮች፣ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ሥነ ሥርዓት ላይ አብራርተዋል፡፡

በፌዴራልና በትግራይ ክልላዊ መንግሥታት መካከል ለተነሱት አለመግባባቶችን በተመለከተ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ተገናኝተን ተወያይተናል፡፡ እንደሚታወቀው እኛ የተቋቋምንበትን ዋነኛ ዓላማው በሕዝቦች መካከል ግጭት ሲኖር፣ ቁርሾ ሲኖርና አለመግባባት ሲፈጠር ያለውን ችግር በማጥናትና በመለየት፣ በሕዝቦች መካከል መግባባት እንዲፈጠር በማገዝ ሰላምንና መግባባትን ማምጣት ነው፡፡

ነገር ግን መንግሥት ለመንግሥት አለመግባባት ሲኖር የራሱ የሆነ ችግር መፍቻ መንግሥታዊ መስመር አለ፡፡ በቀጥታ የሚመለከተን ሥራችን ነው ባንልም፣ በመንግሥታት መካከል ያሉትን አለመግባባቶች በውይይትና በመግባባት እንዲፈቱ የራሳችን አገራዊ ኃላፊነት እንወጣለን፡፡

ለዚህም ደግሞ ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ትግራይን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች በመዘዋወር ውይይት አድርገናል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱን ጨምሮ ሁሉም የክልል መንግሥታት ጥረታችንን የሚጋሩትና ሰላም ለማምጣት ያላቸውን ተነሳሽነት አስተውለናል ያሉት ሰብሳቢው፣ በትግራይ መንግሥት በኩልም ያለው የሰላም ፍላጎት ከተጠቀበው በላይ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡

ይህንኑ የሰብሳቢውን ሐሳብ የሚጋሩት ምክትል ሰብሳቢዋ ወ/ሪት የትነበርሽ በበኩላቸው፣ ‹‹ወደ ትግራይ በሄድንበት ወቅት ከክልሉ ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በኩል ያየነው ዝግጁነት ከገመትነው በላይ ያስደሰተንና ጥረታችን የበለጠ ለማጠናከር ያነሳሳን ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥታት በኩል የሕጋዊ ተቀባይነት ጉዳይን በተመለከተ ስለሚካሰሱበት ጉዳይ ለኮሚሽኑ ኃላፊዎች አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ሪፖርተር ጥያቄ አንስቶላቸው ነበር፡፡ ለዚሁ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ካርዲናል ብርሃነ የሱስ፣ ከክልል መንግሥታቶችም ሆነ ከፌዴራል መንግሥት በጎ ምላሽ ቢያገኙም ወደ ውይይት መድረክ ለመምጣት ግን ከሁለቱም በኩል ችግሮች መስተዋላቸውን አመልክተዋል፡፡ ወደ ክልሎች በተጓዝንበት ወቀት ክልሎች ውይይት እንዲያደርጉ በጠየቅናቸው ጊዜ ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውንና ፍቃደኝነቱ እንዳላቸው ገልጸዋልና ያሉት ካርዲናል ብርሃነ የሱስ፣ ችግሩ ለመወያየት ቅደመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ወደ ክልሉ በሄድንበት ጊዜ የክልል አመራሮች ከዝግጁነታቸው ባለፈ ለውይይቱ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጧቸው ጉዳዮች እንዳሏቸው መግለጻቸው ፈታኝ ሁኔታ እየፈጠረብን ነው፡፡ እንግዲህ የሠለጠነ መንገድ የሚባለው ችግር መፍቻ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መወያየት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መደማመጥን ይጠይቃል፡፡ መደማመጥ በሌለበትና የእኔ ብቻ ይደመጥ የሚል አስተሳሰብ ካለ ደግሞ ወደምንፈልገው ውይይት ወይም መቀራረብ ያደርሳል ብዬ አልገምትም፤›› ሲሉ ሰብሳቢው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹እኛ ውይይት እናዘጋጅና ተወያዩ ብለን ለአንዳንድ ክልሎች ስንገልጽላቸው፣ ያነሷቸው ቅድመ ሁኔታ አሉ፡፡ ያ ደግሞ ለማቀራረብ ለምናደርገው ጥረታችን መሰናክል ሆኗል፤›› ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን እንዲወያዩ በተጠየቁት ወገኖች በኩል ስለተነሱት የቅድመ ሁኔታዎች ጥያቄን በተመለከተ ዝርዝር ማብራርያ አልሰጡም፡፡ ይሁን እንጂ በአገሪቱ የችግር አፈታትን ለመተግበር በውይይት ችግርን የመፍታት ልማዳችን ውስጥ ያለብን ችግር መሆኑን አክለዋል፡፡

የሁለቱን መንግሥታት ወቅታዊ ውዝግቦችና የፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ ተጨማሪ ምላሽ የሰጡት ምክትል ሰብሳቢውም ‹‹ከትግራይና ከፌዴራል መንግሥታት ጋር የተፈጠረውን ዓይነት ችግር ለመፍታት ለኮሚሽኑ የተሰጠው የሕግ አካሄድ ባይኖርም፣ ጉዳዩን በተለየ ሁኔታ በማየት ሁለቱ መንግሥታት ቁርlቸውን በውይይት እንዲፈቱ የኮሚሽኑ ጥረት መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡››

‹‹ምንም እንኳን ያለፉን በደሎችንና ግጭቶችን ተከትሎ በሕዝቦች መካከል የተስተዋሉ ቁርሾዎችንና ቂሞችን በዕርቅ እንዲዘጉ ለማድረግ ብቻ የተቋቋምን ቢሆንም፣ የትግራይ ጉዳይ ግን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በአገር ሰላም ላይ ሊኖር የሚችለውን ተፅዕኖ በማየት፣ በተለየ ሁኔታ እኛም ገብተንበታል፤›› ብለዋል፡፡ ወ/ሮ የትነበርሽ ምንም እንኳን የፌዴራሉም መንግሥትም ሆነ የክልሉ መንግሥት አንዱ ለአንዱ ዕውቅና በመንፈግ ቢካሰሱም፣ ኮሚሽኙ ግን ለሁለቱም መንግሥታት ዕውቅና እንደሚሰጥ ምክትል ሰብሳቢዋ ለሪፖተር በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል፡፡

‹‹ለእኛ ሁለቱም መንግሥታት ተቀባይነት ያላቸውና ዕውቅና የምንሰጣቸው ናቸው፡፡ ሁለቱም ቅቡልነት ያላቸው መንግሥታት ናቸው፤›› ያሉት ኃለፊዋ፣ ‹‹እንዲህ ያሉ በመንግሥታት መካከል አለመግባባት ሲፈጠሩ ችግሩን የመፍታት ሚና በሕግ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠን ነገር ባይኖርም እንደ ዜጋና ኃላፊነት እንደሚሰማው አካል፣ የሁለቱ መንግሥታት አለመግባባት ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች ሰላም አንፃር የሚኖረውን ተፅዕኖ በማየት የተለየ አድርገን ነው የገባንበት፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹በእኛ በኩል እንደ ገለልተኛ ኮሚሽን ማድረግ የምንችለው፣ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል ሰክነው እንዲነጋገሩ መጠየቅ ነው፡፡ ለመነጋገርና ለመወያየት ገለልተኛ አወያይ አስፈልጓቸው እኛ ራሳችን ዝግጁ መሆናችንን፣ ሌላም አወያይ ካስፈለጋቸው ኮሚሽኑ እንደሚያቀርብላቸው ለሁለቱም አካላት ገልጸንላቸው ነበር፤›› ሲሉም ጨምረው አክለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ዝግጁነትን በመደበኛ መንገድ ለሚመለከታቸው አካላት ያሳወቀ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ የትነበርሽ፣ ይህን መሰሉ አለመግባት በመንግሥታትና በመንግሥት መዋቅሮች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች ለመፍታት በግልጽ በሕግ ባለመቀመጡ ምክንያት፣ የዕርቀ ሰላም ሥራ ላይ ሥጋት ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ለወደፊት ማስተካከል የሚችልበት ሁኔታ ወደፊት ኮሚሽኑ በሪፖርቱ እንደሚያካትተውና ለሚመለከተው አካል እንደሚያሳውቅ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው በትግራይና በፌዴራል መንግሥታት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በሁለት መንግሥታት መካከል ያለ የሥልጣን ጉዳይ ሲሆን፣ በኢመደበኛ ልውውጦች እንደምንሰማው ፖለቲካ ሲሆን በትግል ሊፈቱን እንደሚፈልጉ የምንረዳው ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን በሁለቱም በኩል ስምምነት ለማምጣት ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ያሉበት ሰብስብ እንደመሆኑ መጠን የሚደረጉ የሰላም ውይቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዋነኝነት በሕግ ደረጃ ይህ ዓይነቱ የማስታረቅ ሥራ ለኮሚሽናችን በአዋጅ ደረጃ ያልተሰጠ ኃላፊነት መሆኑን ሕዝብ እንዲገነዘብላቸው አስምረዋል፡፡

ከዚሁ ከግጭትና ቁርሾ አፈታት ጋር በተያያዘ አዋጁ በበርካታ ጉዳዮች መስተካከል የሚፈልግ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ የትነበርሽ፣ አዋጁን ለማሻሻል ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር እየተወያዩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ባለፈው ሦስት ወራት ከ370 በላይ የሚሆኑ ባህላዊ ግጭት የመፍቻ ዘዴዎችን መሰነዱን ጠቅሰው ለቀጣይም በዋነኝነት ሊፈታቸው ቅድሚያ ያሰባቸውን ከ21 በላይ የተለያዩ ችግሮችን መለየቱን ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ እነዚህ ለዕርቅ ፈታኝ ናቸው የተባሉት 21 ግጭቶች፣ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች ከበርካታ ዓመታት በፊት ጀምሮ የነበሩ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡

ከእነዚህም ግጭቶች የተወሰኑት ጥለው ያለፏቸው ጠባሳዎች ዛሬም ድረስ ለግጭት መነሻ እንዲሆኑ መሆናቸውንና ተመልሰው በሚፈጠሩ ተያያዥ ግጭቶች የሰው ሕይወት መጥፊያ ምክንያት እየሆኑ መቀጠላቸው ተገልጿል፡፡

ለእነዚህም ችግሮች ዕልባት ለመስጠት ኮሚሽኑ በአንድ ወር ውስጥ ከኢትዮጵያ ተሰባስበው ለሚመጡ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣትቶችና ለሴቶች ተከታታይ የውይይት መድረክ እያዘጋጀ መሆኑን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...