Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ አትሌቲክስና የወቅቱ ተፎካካሪዎች

የኢትዮጵያ አትሌቲክስና የወቅቱ ተፎካካሪዎች

ቀን:

በሩጫው ዘርፍ ከሚጠቀሱ የዓለም አገሮች ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተመድባ ቆይታለች፡፡ ምንም እንኳን ከያዘችው ከቀዳሚዎቹ ተርታ ቁልቁል ባትወርድም፣ ነገር ግን የነበራትን አንጸባራቂ ድሎች ለማስቀጠል በርካታ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው የሚጠቅሱ ባለሙያዎች እየተበራከቱ ነው፡፡

በተለይ በረዥም ርቀት ከዚህ ቀደም ተቀናቃኝ ከነበረችው ጎረቤት ኬንያ ባለፈ የኡጋንዳ አትሌቶች በቅርቡ በተካሄዱ ውድድሮች ላይ ድልና ውጤት እያስመዘገቡ መጥተዋል፡፡ በመሆኑም ቀደም ብለን አሠራራችን በመፈተሽ ወጣትና ተተኪ አትሌቶች የማፍራት ሥራን ከወዲሁ መጀመር እንዳለብን አመላካች ነው የሚሉም በርካቶች ናቸው፡፡ ከረዥም ርቀት እስከ ማራቶን ባሉ የውድድር ዓይነቶች በቀደምቱ ኢትዮጵያውያን ተይዘው የነበሩ በርካታ የርቀቱ ክብረ ወሰኖች እየተነጠቁ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በቅርቡ ፖላንድ ባስተናገደችው የዓለም ግማሽ ማራቶን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ሜዳሊያ ካልሆነ እንደ ቀደሙት በግል ልቆ የወጣ አትሌት መመልከት አልተቻለም፡፡ ከዚህ በመነሳት የዘርፉ ሙያተኞች ይህ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሚያመላክተው አንድ ነገር እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህም ሆኖ ኢትዮጵያ አንድ ወርቅ፣ አንድ ብርና ሁለት የነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን አስመዝግባ ተመልሳለች፡፡

ከምሥራቅ አፍሪካ ከኢትዮጵያና ኬንያ ውጪ ብዙም ያልነበረችው ኡጋንዳ በፖላንዱ የዓለም ግማሽ ማራቶን ላይ አትሌቶቿ ያሳዩት ብቃት፣ ለሁለቱ አገሮች በተለይም ለኢትዮጵያ ትልቅ የማስጠንቀቂያ ደወል ሆኖ አልፏል፡፡ ምንም እንኳን ለዚህ ውድድር ትልቅ ቅድመ ግምት ተሰጥቶ የነበረው ከኢትዮጵያውያን ይልቅ ለኬንያውያን ቢሆንም፣ በግምት ደረጃ ኢትዮጵያውያኑም ቀላል የማይባል ግምት አግኝተው የነበረ መሆኑም አይዘነጋም፡፡

ኡጋንዳ ከረዥም ርቀት እስከ ማራቶን ባለው የውድድር ዘርፍ በ2004 በተደረገው የዓለም አገር አቋራጭ በቡድን ያስመዘገበችው የነሐስ ሜዳሊያ ካልሆነ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንዲህ እንዳሁኑ ስም አልነበራትም፡፡ ይሁንና በፖላንዱ ግማሽ ማራቶን በወንዶች በ19 ዓመቱ ታዳጊ ኪፕሊሞ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን በቅታለች፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር በሴቶች በነጻነት ጉዳታ፣ በብርሃኔ አደሬና በመሠረት ኃይሉ ሦስት ጊዜ፣ በወንዶች ደግሞ አንድ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ በፖላንዱ ግማሽ ማራቶን በቡድን ያስመዘገበችው ውጤት አሁንም ዘርፉ ተገቢው ክትትልና ትኩረት ከተሰጠው ለክፉ የሚሰጥ እንዳልሆነ የሚናገሩ ሙያተኞች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ቀድሞ ኦሜድላ በአሁኑ ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ አትሌት የነበሩት የማናጀር ተወካይና አሠልጣኝ ኤርጳሳ ለሚ ይጠቀሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ አትሌቲከስ ውስጥ ትልቅ ስም ካላቸው የቀድሞ አትሌቶች አንዱ የሆኑት አሠልጣኝ ኤርጳሳ፣ በአትሌቲክሱ ላይ ከሚመለከቷቸው ክፍተቶች መካከል ውጤት ብቻ ሳይሆን የአትሌት ምልመላና ዝግጅትም ጭምር ነው፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ቀደም ሲል የነበረው ዝግጅትና ምልመላው እንዲሁም አሠራሩ፣ እንዲህ እንዳሁኑ በዘፈቀደ ሳይሆን፣ በመላ አገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ወረዳ ላይ ማጣሪያዎች እየተደረጉ ለአውራጃና ክፍለ አገር እያለ ተዋረዱን ጠብቆ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ቀድሞ የነበረውን ዓይነት አሠራር መመለስ እንኳ ባይቻል ቢያንስ ያለውን ውጤት ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መነጋገር የሚያስፈልግበት ጊዜ ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ከአበበ ቢቂላ ጀምሮ እነ አበበ መኮንን፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ጌጤ ዋሚና ሌሎችም ለበርካታ ዓመታት በአትሌቲክሱ ትልቅ ስምና ዝና ያተረፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መነሻቸው አሁን እንደሚነገረው ፕሮጀክቶችና የሥልጠና ማዕከላት ሳይሆኑ የጦር ክፍሉና ትምህርት ቤቶች ናቸው የሚሉት አሠልጣኝ ኤርጳሳ፣ “የፕሮጀክቶቹና የሥልጠና ማዕከላቱ መኖር እንደተጠበቀ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና ክልሎች እንዲሁም ክለቦች ቀድሞ እንደነበረው በትምህርት ቤቶችና ወረዳዎች የሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች እንዲቀጥሉ ለማድረግ የጋራ ዕቅድ ማውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም አትሌቶች ገና ለገና ስፖርቱ ገንዘብ ያስገኛል በሚል አቅምን ካላገናዘበ ውድድር ርቀው ራሳቸውን እንዲጠብቁ በዋናነት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር መሥራት ይኖርበታል፤” በማለት አትሌቲክሱ ለገጠመው ተግዳሮት መፍትሔዎችን ማመቻቸት የሚቻልበት ዕድል እንደሚኖር ጭምር አልሸሸጉም፡፡

በአሠልጣኙ አገላለጽ፣ ቀደም ሲል ምሳሌ አድርገው የጠቀሷቸው የቀድሞ አትሌቶች አቋማቸው ሳይዋዥቅ ለረዥም ዓመታት ለመሮጥ የቻሉት፣ አንድ አትሌት ከውድድር በፊትና በኋላ ማድረግ ያለበትን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡ ይሁንና አሁን ላይ ግን ከክለብ አሠልጣኝ እስከ ማናጀር እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ጭምር አትሌቱን የሚፈልጉት ጊዜያዊ ጥቅም እንዲያስገኝ ካልሆነ የዕድገት ደረጃውን ጠብቆ ለብዙ ጊዜ እንዲያገለግል አይደለም፣ ይህ ዓይነቱ የአሠራር ሥርዓት አትሌቲክሱን ብቻ ሳይሆን አትሌቱንም እያሳጣ ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሁን ለገጠመው የአሠራርና ተያያዥ ተግዳሮቶች በተጨማሪ ለወትሮ ጃንሜዳን ጨምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለአትሌቶች ልምምድ የሚያመቹ በርካታ ጥርጊያ መሬቶች አሁን ላይ መጥፋታቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚያ ላይ አትሌቶች በመኖሪያነት የሚጠቀሙባት አዲስ አበባና አካባቢዋ የአየር ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ተበክሏል፡፡ ለዚህም ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ በርካታ የዘርፉ ሙያተኞች አትሌቶች ከአዲስ አበባ ውጪ ወደሚገኙ አካባቢዎች በመሄድ ልምምድ የማያደርጉ ከሆነ በአዲስ አበባ አየር የትም መድረስ እንደማይችሉ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በትራፊክ መጨናነቅና መሰል ችግሮች የሞት አደጋ የገጠማቸው አትሌቶች ቁጥርም ቀላል የማይባል እንደሆነም ሲነገር ይደመጣል፡፡

“ቀደም ሲል ትምህርት ቤቶችን ምሳሌ አድርጌ ስናገር የነበረው አንዱና መሠረታዊ መነሻዬ ይህ አሁን የብዙ ሙያተኞች ሥጋት ሆኖ የሚነገረው የአዲስ አበባ አየር ብክለትና የትራፊክ መጨናነቅ እንዲሁም ለአትሌቶች ምቹ የሆኑ የልምምድ ቦታዎች ዕጦቶች ናቸው፤” የሚሉት አሠልጣኝ ኤርጳሳ፣ “የተጠቀሱት የማዘውተሪያ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆኖ፣ ብዙዎቹን ትተን ሻምበል አበበ ቢቂላን ያፈራው ጃንሜዳ አሁን ላይ ዕጣ ፈንታው ምንድነው? በግሌ እጅጉን ያዘንኩባቸው ቀናቶች ቢኖሩ፣ ጃንሜዳ ለገበያ ማዕከልነት ዋለ የተባለበት ቀን አንዱ ነው፡፡ እንዴት ነው እንዲህ ዓይነት የአሠራር ሥርዓት ባለበት ሁኔታ አትሌቲክሱን ውጤት ማስቀጠል የሚቻለው? የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ራሱ እንዴት ነው ይህ ሁሉ ሲሆን ዝም ብለው የሚመለከቱት? እንደነ ኃይሌና ሌሎችም ታላላቅ አትሌቶች ዛሬ የትልልቅ ኢንቨስትመንት ባለቤት ሆነው ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉት በአትሌቲክሱ እኮ ነው፣ መለስ ብለን ራሳችንን መመልከት ካልቻልን በአትሌቶቹ ስለምናገኘው የውጭ ምንዛሪ አይደለም፣ ይህ ጠዋትና ማታ እየወደቀ ነው የምንልለት የአትሌቲክሱ ውጤት አሁን ባለው ሁኔታ የትም ሊደርስ እንደማይችል ለመገመት ሊቅ መሆን አይጠይቅም፤” በማለት የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

“የአሁኑን አያድርገውና” የሚሉት አሠልጣኙ፣ ጃንሜዳ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጇቸው የአገር አቋራጭና ሌሎችም ውድድሮችን ጨምሮ የተለያዩ የባህል ስፖርቶች የሚከናወንበት ቦታ መሆኑ ልብ ሊባል እንደሚገባ የሚናገሩት አሠልጣኙ፣ “ለማዘውተሪያዎች ትኩረት የማንሰጥ ከሆነ ዝም ተብሎ ውጤት ውጤት ለማለት ያህል ጣት መጠቋቆም ውኃ የማይቋጥር ነገር ነው፡፡ ጃንሜዳ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በግሌ የማስብ የነበረው፣ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዙሪያ ልምምድ ሲሠሩ በትራፊክ አደጋና መሰል ችግሮች የሕይወትና የንብረት ጉዳት ሲደርስባቸው የነበሩ አትሌቶች አደጋው እንዳይደርስባቸው የኢትዮጵያም ይሁን የአዲስ አበባ ኤትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመነጋገር አትሌቶች ከትራፊክ አደጋ ነጻ ሆነው ልምምድ የሚሠሩባቸው ጥርጊያ የልምምድ ቦታዎች ይዘጋጃሉ በሚል ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ጃንሜዳ የገበያ ማዕከል ሲሆን መመልከት እጅጉን ያማል፣ ይሰማል፤” በማለት የጃንሜዳ ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

አትሌቶች ቀደም ባሉት ዓመታት ማዘውተሪያን ጨምሮ ለልምምድ የሚንቀሳቀሱባቸው ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ አልባሳት ተሟልቶ ይቀርብላቸው የነበረበትን ጊዜ የሚያስታውሱት አሠልጣኝ ኤርጳሳ፣ “አሁን ላይ ግን አትሌቶቹ ከፌዴሬሽኑ ይልቅ ማናጀሮችን በተሻለ ደረጃ እንደሚያምኑ እየተመለከትን ነው፡፡ ድሮ የማራቶን አትሌቶች በአንድ መኪና፣ የረዥም ርቀት አትሌቶችም እንደዚሁ ምንም ዓይነት መከፋፈልና ልዩነት ሳይኖር አብረው ይለማመዱ ነበር፡፡ የነበረው ያ ሁሉ አንድነትና መተሳሰብ አሁን የለም፣ ለምን ብሎ በችግሩ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ማሳያ አድርጌ የማነሳው ዓመተ ምሕረቱን እርግጠኛ ባልሆንም በ1980 አልያም 81 ይመስለኛል፣ የዓለም ወጣቶች አገር አቋራጭ ውድድር ላይ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ውድድር ላይ ሆና የቡድን አጋሮቿን ትታ ላለመሄድ እየጠበቀች ኑ እያለች ስታበረታታ የነበረበትን ሁኔታ ቦታው ስለነበርኩ አስታውሰዋለሁ፣ ይህ በወቅቱ ምን ያህል መተሳሰብና መቀራረብ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ የኢትዮጵያ አትሌቲከክስ ፌዴሬሽን እዚህ ላይ ጠንክሮ ሊሠራ ይገባል፤” ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ችግር ለምን ሊፈጠር ቻለ ለሚለው አሠልጣኙ፣ “አንዱና ዋናው ችግር ስፖርቱ እያስገኘ ካለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አኳያ የማናጀሮች መብዛትና የፍላጎት መጨመር ነው፡፡ በእርግጥ እኔም ከእነዚህ ማናጀሮች አንዱ ብሆንም፣ እኛ ጋ ያለው ሁኔታ አትሌቶች ምን ዓይነት ብቃትና አቅም እንዲሁም የዕድሜ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ጉዳያችን አይደለም፡፡ አትሌቱ አቅም አለኝ እስካለ ድረስ ግባ ነው የምንለው፣ ይህ ደግሞ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ አትሌት አንድ ማራቶን ከሮጠ በኋላ የማገገሚያ ጊዜውን ልንጠብቅለት ሲገባ ያንን የማናደርግ አለን፤” ብለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለዚህ አስፈላጊውን መመርያ በማውጣት ሥርዓት ሊያበጅለት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አትሌቲክስ ገንዘብ ከመሆኑ አኳያ አብሮ ለመሥራት ቀርቶ አንዱ የሌላውን ልምምድ እንኳ ለመመልከት የማይቻልበት ሁኔታ አለ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከዚህ አኳያ አስገዳጅ መመርያ ቢያወጣ ምን ያህል ቅቡልነት ይኖረዋል? ለሚለው አሠልጣኝ ኤርጳሳ፣ “አንዳንድ ጊዜ ለአገርና ለሕዝብ ሲባል ከመጥፎ የተሻለውን መጥፎ መምረጥ ግድ ይላል፡፡ አትሌቶቹ የተሻለ ድጋፍና ክትትል ከተደረገላቸው የሚነገረውን ያህል አስቸጋሪዎች አይደሉም፡፡ በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ አሠልጣኞችን ሲመርጥ አትሌቶች የሚፈልጉት ዓይነት ችሎታ አለው የለውም የሚለውን መለየት ከቻለ ምንም ችግር ሊፈጠር አይችልም፡፡ ምክንያቱም አትሌቱ የሚፈልገው ውጤታማ የሚያደርገውን ሥልጠና ነው፤” በማለት ያን ያህል ችግር እንደሌለው ያስረዳሉ፡፡

“ቀደም ሲል የነበሩት እንደነ ኃይሌና ቀነኒሳ የመሳሰሉት ያን ሁሉ የዓለም ክብረ ወሰን ሲሰባብሩ አሁን ያለው ዓይነት ችግር አልነበረም፣ ለምን የፌዴሬሽኑም ሆነ በወቅቱ የነበሩት ብሔራዊ አሠልጣኞች ብቃት አትሌቶቹ የሚፈልጉት ዓይነት በመሆኑ ነው፤” የሚሉት አሠልጣኙ፣ አሁንም ያንን ዓይነት የልምምድ ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ደግሞ መንግሥትም ጭምር በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ በማድረግ ወደቀደመው አሠራራችን መመለስ እንደሚያስፈልግ፣ ይህ ካልሆነ ግን አይደለም ኬንያውያንን ኡጋንዳውያኑንም ለመቋቋም እንደሚከብድ ያስረዳሉ፡፡

አሁን ባለው አሠራር አንድ ማራቶን ሮጦ የሚጠፋ አትሌት ብዙ እንደሆነ እንደሚናገሩት አሠልጣኝ ኤርጳሳ አገላለጽ፣ ይህ የሚያሳየው ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው ብሔራዊ ፌዴሬሽን አቅምን ነው፡፡ ቅንጅት ያለው ምንም ዓይነት የአሠራር ሥርዓት ስለሌለ አትሌቶቹ እንዲበታተኑ ምክንያት ሆኗቸዋል የሚሉት አሠልጣኝ ኤርጳሳ፣ “ሁሉም ድርሻ ድርሻውን እስካልወሰደ ድረስ የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡፡ ለዚህ ነው ጃንሜዳ የሚያህል ማዘውተሪያ ሊጠፋ የቻለው፣ ነገሩ ሁሉ የፉክክር ቤት እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል፣ በተለይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ በኩል ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባዋል፤” ይላሉ፡፡

አትሌቶች እንደ ቀድሞ ሰዓቱን ጠብቀው መሥራት የሚችሉበት ዕድል እየጠበበ መምጣቱን የሚናገሩት አሠልጣኝ ኤርጳሳ፣ ሰበታና ሰንዳፋ ካልሆነ ሱልልታ ልክ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ በትራፊክ መጨናነቅ ለልምምድ የማይታሰብ ከሆነ ውሎ ማደሩን ያስረዳሉ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይህን ችግር ታሳቢ በማድረግ ቢቻል አትሌቶች ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ የአገሪቱ ክፍሎች ልምምድ የሚሠሩበትን ሁኔታ ሊያመቻች እንደሚገባውም ይናገራሉ፡፡

እንደ አሠልጣኙ ከሆነ የኡጋንዳውያንን ጨምሮ ኬንያውያን አትሌቶች ዋና ከተሞቻቸውን የሚያውቁ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ብዙዎቹ አትሌቶች ልምምዶቻቸውን የሚሠሩት ከዋና ከተሞቻቸው 800 ኪሎ ሜትርና ከዚያም በላይ ርቀት ወዳላቸው የአገሪቱ ገጠራማ ሥፍራዎች ላይ ነው፡፡ ይህን ዕውን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ፈለግ በመከተል ቀደምቶቹ አትሌቶች የአመራርነቱ ኃላፊነት ለመያዝ ዕድሉን ሲያገኙ ብቻ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በመጨረሻም በአገር ውስጥ የመመረጥ ዕድል የማያገኙ በርካታ አትሌቶች ለሌሎች አገሮች ዜግነት እየቀየሩ መሮጣቸው፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም ወይ? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱም ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደማይኖረው፣ ይልቁን በኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ትክክለኛው የአሠራር ሥርዓት ከተዘረጋ ምቹ ነገር ይፈጠራል ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የአትሌት ችግር እንደሌለ እንዲያውም አትሌቶቹ ለሌሎች አገሮች እየሮጡ ለራሳቸውና ለወገኖቻቸው የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን መልካም አጋጣሚ እንደሚያመቻች ያስረዳሉ፡፡          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...