Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

እናንተዬ ‹‹የጉድ ቀን ሳይነጋ ይመሻል›› የሚለው ብሂል የታወሰኝ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ንጋት ላይ ነው፡፡ ማኅበራዊ ትስስር ገጽን ድንገት ሳስስ ዓይኔ አንድ ልጥፍ ጽሑፍ ላይ አረፈ፡፡ ኧረ እንዴት ነው ነገሩ? ይኼ ነገር ትክክለኛ ልጥፍ ነው ወይስ የተሳሳተ? በማለት ዓይኔን ማሻሻት ጀመርሁ፡፡ በብልፅግና የሚመራው የፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት የሚመራው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የፈጠሩትን ፖለቲካዊ ውዝግብ ተከትሎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በስፖርቱ ዘርፍም እንዲተገበር የስፖርት ኮሚሽን ለየተቋማቱ ማስተላለፉ ነው ‹‹መርዶ›› የሆነብኝ፡፡

ለተለያዩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና ማኅበራት (በእነሱ አጠራር አሶሴሽኖች) እንዲሁም ለብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በስፖርት ኮሚሽን ‹‹የምክትል ኮሚሽነር አማካሪ›› የተፈረመው ደብዳቤ፡- ‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ የትግራይ ክልልን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ 5 ገጽ ከዚህ ሸኝ ደብዳቤ ጋር አያይዘን የላክን ሲሆን በውሳኔው መሠረት እንዲፈጸም እናሳውቃለን፡፡›› የሚል ሲሆን፣ ከግርጌውም ‹‹እንዲያውቁት – ለክቡር ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት›› ይላል፡፡ በዚህ አገላለጽ ጥንተ ነገሩን ምክትል ኮሚሽነሩ ያውቁታል ማለት ነው፡፡ ፈራሚው ‹‹አማካሪ›› ከሚያማክሯቸው ሹም ጋር ሳይመካከሩ ወይም ይሁንታ ሳያገኙ ደፍረው የሚጽፉ አይመስለኝም፡፡

ለስፖርቱ ተቋማት እንዲተገብሩት መላኩ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ መታሰቡ በስፖርት ኮሚሽን ውስጥ ያለው ስብስብ ምን እንደሚመስል ማንፀባረቁ ነው፡፡ በዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ፌዴሬሽኖች ሕገ ደንብ መሠረት የተቋቋሙትን ተቋማት ከፖለቲካዊ አደረጃጀት ጋር ማዛነቅ መሞከሩ፣ በጸያፍ ሙጫ ማጣበቁ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ኦሊምፒክ ኮሚቴ›› አይደለም’ኮ! የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም እንደዚሁ የመንግሥት ፌዴሬሽን አይደለም፡፡ ሌሎቹም እንዲሁ፡፡ ስፖርት የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ አይደለም ‹‹አላዋቂ ሳሚ…›› ሆነና ነገሩ እነ የምክትል ኮሚሽነር ‹‹አማካሪ›› ስፖርቱን አዘቅት ውስጥ ሊጥሉት ነበር፡፡

ክብር ለብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይሁንና ፈጥኖ ተቃውሞውን ማሰማቱ በጀ፡፡ ኦሊምፒክና ፖለቲካ እንደማይገናኙ በቅጡ በአግባቡ ያውቃልና፡፡ ከዓመታት በፊት በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ መንግሥት ጣልቃ ገብ ሆኖ ሕጋዊው አመራር በማስነሳቱ አገሪቱም ታግዳ ብዙ ዋጋ መከፈሉን ያውቃልና፡፡

‹‹አማካሪ››ው የስፖርቱ ቤተሰብ፣ ስፖርቱን በቅጡ የሚያውቁ አይመስሉኝም፡፡ የስማ በለው እንዳይሆኑ እጠረጥራለሁ፡፡

የትግራይ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ የየአጥቢያ ተቋሞቻቸው አቤት ቢሉ፣ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴም ጉዳዩን ቢረዳ የሚወስዱት ዕርምጃ ሳስበው ይዘገንነኛል፡፡ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ስንወጣ፣ ከዓለም ሻምፒዮናና ከአኅጉራዊ ውድድሮች እግር ኳሱን ጨምሮ መሰናበት ብቻ ሳይሆን ኢንተርናሽናል ዳኞቻችንም ሰለባ ይሆኑብን ነበር፡፡ ያኔ በፊፋ በመታገዳችን እነ ኃይለ መላክ የተሰናከለባቸው መድረክ ወደ ብቸኛ ተወካዮቻችን ባምላክ ተሰማና ሊዲያ ታፈሰ ላይ ያጠላ ነበር፡፡

ደግነቱ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ በጥቅምት 9 ቀን ለወጣው ከሁለት ቀን በኋላ በምክትል ኮሚሽነሩ (በአማካሪያቸው ሳይሆን በራሳቸው) ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ አስቀድሞ የተላከው ደብዳቤ ‹‹የመረጃ ክፍተት ያለው በመሆኑ›› ተሽሯል ይላል፡፡ የእኔ ጥያቄ የመረጃ ክፍተት የተባለው ምንድነው? ይቺ በየመድረኩ የተለመደች ‹‹ክፍተት›› ድክመትንም፣ ስህተትንም፣ ጥፋትንም ለመሸፈን የተበጀች የማርያም መንገድ እንዳትሆን እሠጋለሁ፡፡ ስህተቱን ስህተት፣ ጥፋቱንም ጥፋት ለማለት ለምን አይደፈርም፡፡ እስከመቼስ እናነክሳለን?!

(ተፈራ ናደው ከፍል ውኃ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...