Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉበሃይማኖት መነገድ ይቁም! ሕዝብም መብቱን አሳልፎ አይስጥ!

በሃይማኖት መነገድ ይቁም! ሕዝብም መብቱን አሳልፎ አይስጥ!

ቀን:

በያሲን ባህሩ ረዳ 

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ በግልጽ እንደሰፈረው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሃይማኖት ነፃነት ተረጋግጧል። መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ሆነዋል። ሕገ መንግሥቱ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን ያስቀምጥ እንጂ፣ ሕዝቦች የፈለጉትን ዓይነት እምነት መከተል እንደሚችሉ መብታቸውን አልገደበም፡፡

በአገራችን ለዘመናት የነበሩ አሀዳዊና ፀረ ዴሞክራሲ የአገዛዝ ሥርዓቶችም ላይመለሱ ተቀይረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፉት 27 ዓመታት ተሞክሮ ከችግር ያላወጣንን ነጣጣይና ኢፍትሐዊ ሥርዓት በማስተካከል፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተሻለ መሠረት ላይ ለመገንባት እየተሞከረ ነው። ያም ሆኖ ከፖለቲካው ንትርክ ሳንወጣ ሊያተራምሱን የሚሹ ኃይሎችና የባዕዳን ቅጥረኞች፣ በሃይማኖቶቻችን ውስጥ በመግባት በተራ የትርምስ ሸቀጥ ሊነግዱብን መሻታቸው አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ ሊወገዝም ይገባዋል፡፡

- Advertisement -

አዲሱ የብልፅግና መንገድ ጥቂቶች፣ ብዙኃን እያለ ሳይለያይ መላው የአገራችን ሕዝቦች በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በዘር፣ በቀለም፣ እንዲሁም በሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግባቸው በአገራቸው እኩል ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ሥርዓት የሚዘረጋ ነው፡፡

ለዚህም ሁሉም ክልሎች የሚሳተፉበት አገራዊ መሪ ፓርቲ ከመመሥረቱ ባሻገር፣ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረቱና አንድነትን ያጠናክራሉ የተባሉ ዕርምጃዎችና ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ይህ መንገድ እንኳን ባይሳካ ሌላ የተሻለ አገረ መንግሥት ለማነፅና ሕዝቦችን በእኩልነት ሊመራ የሚችል ኃይል እንዲጎለብት እንሠራለን፣ እንደ ሕዝብም እንመኛለን እንጂ፣ የሃይማኖት ትርምስና መበላላት እንዲበትነን በፍፁም ዕድል አንሰጥም፡፡ ከዚህ አንፃር በእኛ አገር የታዩ ምልክቶችን ከሌላው ዓለም አንፃር እንዴት እንመክት የሚለውን ለማየት እንሞክር. . . 

የሃይማኖት ፖለቲካ ካደቀቃቸው አገሮች እንማር

ዓለም ከቅርብ አሥርት ዓመታት ወዲህ በሃይማኖት ሽፋን በሚንቀሳቀሱ ሽብርተኞችና ፅንፈኞች ፍዳዋን ስታይ ቆይታለች፡፡ በተለይም ‹‹መብታችን ተገፏል፣ ዓለም ለእኛ ሊኖራት የሚገባውን ያህል በረከት እየሰጠችን አይደለም›› ወይም፣ ‹‹ሃይማኖታችን ዓለም በምተከተለው ሥልጣኔና ዘመናዊነት ምክንያት ተናውጣለች›› የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ያደረሱት ጥፋት እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡

እዚህ ላይ በሃይማኖት ስም የፖለቲካ ሥልጣን በመያዝ ያሻቸውን ለማድረግ የሚሹ ሁሉም ፅንፈኞችና ሽብርተኞች መገለጫቸው በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በንፁኃን ላየሚወስዱትን አሰቃቂ የግድያና የአጥፍቶ መጥፋት ዕርምጃዎች ለጊዜው ወደ ጎን ትተን፣ በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አሠራራቸው ዙሪያ ያለውን ተመሳስሎ ለማየት ስንሞክር ታዋቂ በሆኑ ግለሰቦች፣ ተቋማትና የእምነት ቦታዎች ጥቃት አሳበው የበቀል ዕርምጃ እንዲቀሰቀስ ማድረግና የከፋ ጥፋት ማድረስ አንዱ ዓላማቸው ነው፡፡

እንደ የመን፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን (አብዛኛዎቹ እስልምና የሚበዛባቸው መሆናቸውን ልብ ይሏል). . . ባሉት አገሮች ውስጥ ሲፈጸም የነበረውን ሁሉ የምንዘነጋው አይደለም፡፡ አሁንም የንፁኃን ሞት፣ ስደትና መፈናቀል የቆመባቸው ቦታዎች አልሆኑም፡፡

እርግጥ በእኛም አገር ከውጭ ተፅዕኖ አንፃርም ሆነ በአገር ውስጥ በሚፈጠሩ የሃይማኖት ፖለቲካ ግጭቶች መጠኑ ይለይ እንደሆን እንጂ፣ በርካታ ጉዳቶች በዚም በዚህም መድረሳቸው አልቀረም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመንግሥት መረጃ መሠረት “ኦነግ ሸኔ፣ ሕወሓትና መሰሎቻቸው በተቀናጀ ሴራ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን እጅግ ወደ ጭቅጭቅ የሚያስገባ ቃለ ምልልስ በኦኤምኤን ቲቪ ላይ አድርገውታል፡፡ ያም አልበቃ ብሏቸው ንግግሩን እየቆራረጡ ወደ ዓላማቸው የሚወስደውን ብቻ አስተላልፈዋል፡፡ ያንኑ ተከትሎም በሁለቱ ትልልቅ ብሔረሰቦች መካከል ግጭት ለመፍጠርና መንግሥትን ለመገልበጥ ላዘጋጁት ትርምስ ለመጠቀም ወጣቱን ታጋይ እንዲገደል አድርገዋል፤›› ከሚለው የፖለቲካ ውዝግብ በኋላ ሃይማኖት ቀመስ  ግጭትና ጉዳት ደርሷል፡፡

በእርግጥ በወቅቱ የተፈጠረው ሁኔታ በቀትታ ከሃይማኖት ግጭት ጋር የሚያያዝ ባይሆንም፣ ለፖለቲካ ዓላማ እንደተፈጸመ በሚጠረጠረው ግድያ፣  የተጠረጠሩ ገዳዮችና አሸባሪዎችም በሕዝብና በመንግሥት ትብብር በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ እነዚህ ፅንፈኞችና አክራሪ ፖለቲከኞች ግን ሌሎች ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ ግለሰቦችና  ምሁራን ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው አልመው እንደነበር ነው የተረጋገጠው፡፡ ይህም ከተያዙት ሰዎች ምርመራ በተገኘ ማስረጃ መረጋገጡን ሰምተናል፡፡

በዚያን ወቅት በመላው ኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ብስጭታዊ የወጣቶች ዕርምጃ፣ በተለይም በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በጅማና በመሰል አካባቢዎች ከፍተኛ ብሔርና ሃይማኖት የለየ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ በአብዛኛው ሙስሊም የሆኑ ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ክርስቲን በሆኑት ላይ የተፈጸመው ጥቃትና ግድያ ብቻ ሳይሆን፣ በአብዛኛው አክራሪዎች በሌሎች አገሮችም የጥቃት ዒላማ በሚያደርጓቸው ሆቴሎች፣ የንግድ ድርጅቶችና ዘመናዊ የትምህርት ማዕከላት ላይ ያተኮረ እስከ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚገመት የሕዝብ ሀብት ውድመት መፈጸሙ ነገሩ ወዴት እየሄደ ነው የሚያስብል ነው፡፡

በሌላውም ዓለም እንደምናየው አክራሪዎች የሚወስዱት ዕርምጃ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስከትልባቸው፣ የተቃውሞና የውግዘት አቅጣጫ ለማስቀየር የሚጠቀሙበት ያረጀና ያፈጀ ሥልትም በእኛም አገር ሊፈጸም ተሞክሯል፡፡ ይህም ጉዳዩን መካድና በሌላ ተቋም ወይም መንግሥት ላይ ለማሳበብ መሥራት ነው፡፡ በይፋ የተፈጸመን የንፁኃን ግድያ ወይም የሕዝብ ሀብት ውድመት ‹‹የተቀነባበረ ድራማ ነው. . .›› የሚሉት ፈሊጥ አላቸው፡፡ አሁን ከጉዳት በኋላ በተጨባጭም በተለይ በውጭ ያለው የዳያስፖራ ፅንፈኛ እያራገበ ያለው “የአብዬን ወደ እምዬ“ የእዚህ ማሳያ ነው፡፡

የእነሱን ወንጀል የሚያጋልጥ ችግር ሲፈጠርባቸው ለማምለጫ የሚገለገሉበት ዘዴ መካድና በሌላ ማሳበብ ነው፡፡ የታዋቂው አርቲስት ሃጫሉ ገዳይ ማንም ይሁን ማን ድርጊቱን ማውገዝ ሲገባቸው ‹‹ናችሁ›› ሳይባሉ ‹‹እኛ አይደለንም›› ለማለት ሰበብ መደርደርን ያስቀድማሉ፡፡ የአሸባሪዎችን የባህሪ መገለጫ ለሚያውቅ ግን ሕዝብ ያየውንና ፀሐይ የሞቀውን እውነታ መካድና ማስተባበላቸው፣ በታሪካቸው ውስጥ ለዘመናት የቆየና በሃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች መገለጫ ነው፡፡

ይህን እውነት በዛሬዋ ኢትዮጵያ እያየን ያለነው ደግሞ የአክራሪነትን መንገድ በማጠናከር አገራችንን ወደ ትርምስ ለመክተት የሚሹ ፅንፈኛ ኃይሎች ሴራ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም እንዲህ ያሉ የትርምስ መንገዶችን አንቅሮ መትፋት አለበት፡፡ እነ ግብፅን የመሰሉ የውጭ ባላንጣዎቻችንም እንዲህ ያሉትን የጥፋት ፕሮጀክቶች አይደግፉም ብሎ መዘናጋት አይገባም፡፡

የምንታወቅበትን የመቻቻልና የመረዳዳት ገጽታ መጠበቅ ይበጀናል

በአገራችን የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ የአመለካከት፣ የዕድሜና ሌላም ብዝኃነት አለ፡፡ ያም ሆኖ ኢትዮጵያዊያን ብዙ ፈተና እየገጠማቸውም ተቻችለውና “አንተ ትብስ. . .” ተባብለው ነው ለዘመናት የኖሩት፡፡ በአገዛዞች አማካይነት የእርስ በርስ ግጭቶች ቢከሰቱ እንኳን ሕዝቡ መልሶ ይቅር ተባብሎና ተቀላቅሎም ነው እስካሁን የዘለቀው፡፡ የሃይማኖት ልዩነትም ሆነ መድልኦ በዚች አገር ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን ሕዝቡ ለዘመናት የተሰናሰለበት ገመድ፣ መስተጋብሩ ብሎም ፈሪኃ ፈጣሪው የተሻለ ስለነበር ለከፋ አደጋ ሳንጋለጥ የቆየነው ማለት ስህትት የለውም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይ ብሔርና ሃይማኖትን ምሽግ ያደረጉ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ብዙ ጉዳት እያስከተሉ ነው፡፡ በተለይ በሌላው ዓለም እያየን የምናዝንበትን የሃይማኖት ፅንፈኝነት በእኛም አገር ለመትከል የሚደረገው ሴራ መክሸፍ ያለበት መሆኑን፣ ከላይ በቅርቡ በገጠመን ላይ ብቻ በመመሥረት ለመጠቆም ሞክሬያለሁ፡፡

በቅርቡ የሃይማኖት አባቶች እንዳረጋገጡት ዜጎች በሃይማኖታቸው ብቻ ተቀጥቅጠውና ታርደው መገደላቸው፣ ይህም በሚታወቁ አካባቢዎች ሕዝበ ምዕመኑ ለዘመናት በኖረባቸው ቦታዎች መሆኑ የሰላም፣ የዕርቅና የአብሮነት መንገድ ያለው እስልምናን የማይመጥን ድርጊት ነው፡፡ እንዲህ ያለ የጥፋት ፖለቲካ ተያይዞ መጥፋትን እንደሚያስከትልም ልንገነዘብ ይገባል፡፡

እዚህ ላይ ኻሊድ አቡ ኤል ፈድል (ዶ/ር) የተባለ በእስላማዊ የፍርድ ሥነ ትምህርት የተዋጣለት የሎስአንጀለስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (UCLA) የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የተናገረውን ልጥቀስ፡፡ ሰውዬው የወሃቢ ጉዳዮችንና የፅንፈኝነት ችግሮችን አብጠርጥሮ ያውቃል፡፡ በተለያየ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በእስላማዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ መግለጫዎችን በመስጠትም የታወቀ፣ ዕውቀቱና ብቃቱ የተረጋገጠና የተመሰከረለት ምሁር ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ቡሽ (ትልቁ) የዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ነፃነት የአሜሪካ ኮሚሽንን በአማካሪነት እንዲመራላቸው የሾሙት በሳል ፖለቲከኛም ነበር፡፡ አንድ ቀን በእስላማዊ ጉዳዮች ላይ ትምህርታዊ ንግግር (ሌክቸር) እንዲያደርግ ተጋብዞ በሄደበት አዳራሽ ተገኝቶ ንግግሩን አድርጎ ሲያበቃ ከአድማጮቹ ጥያቄ ቀረበለት፡፡

የመጀመርያው ጥያቄ ‹‹የኢስላም አስተምህሮ በጣም ከፍተኛ ደረጃ (ክብር) የሚሰጣቸው የሥነ ምግባር እሴቶች (Moral Values) ወይም ፋይዳዎች የትኞቹ ናቸው?›› የሚል ነበር፡፡ ለዶ/ር ኻሊድ የዚህ ጥያቄ መልስ እጅግ በጣም ቀላል ነው፡፡ ‹‹ሰላም. . . መቻቻል. . . ትዕግሥት. . . ርህራሔ . . . ይቅር ባይነት. . .›› ናቸው ሲል ነበር መልስ የሰጠው፡፡

እንግዲህ የአገራችን ሰላም ወዳድ ሙስሊሞችም ሆኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ማውገዝና ማስቆም ያለባቸው ድርጊት፣ በውስጥ ያሉና ከውጭም በየሃይማኖቱ ስም የሚነግዱ፣ ከእነዚህ እሴቶች በተቃራኒ የቆሙ አካላትን ሊሆን ይገባል፡፡ ሁላችንም ብንሆን አገራችን የምትታወቅበትን የመቻቻልና የመረዳዳት ገጽታ ተግተን መጠበቅ የሚበጀን፣ ነገ በጋራ የምንኖርባትን አገር ለማቆየት ስንል ብቻ ነው፡፡ እንደ መንግሥት ችግሩ እንዳይንሰራፋ ምን መደረግ አለበት?

 አንዳንድ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ በመቼውም ጊዜ የሚነሱ የየትኛውም ሃይማኖት አክራሪዎችንና የፖለቲካ ነጋዴዎችን በተመለከተ መንግሥት ከተገቢው በላይ ትዕግሥት አሳይቷል. . . ምን እስኪሆን ነው የሚጠብቀው?. . . ለምን ጠበቅ ያለርምጃ አይወስድም?. . . ወዘተ. የሚሉ አስተያየቶች አሉ፡፡ ሐሳቦቹ ከሁለት አቅጣጫዎች ሊነሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

በአንድ በኩል የአክራሪዎች ከልክ ያለፈ ድፍረት ያስቆጣቸው፣ ፀረ ሕገ መንግሥትና ፀረ ሰንደቅ ዓላማ አቋማቸው ያበሳጫቸው፣ የመቻቻል እሴቶች የመናድ አዝማሚያቸው ያስጨነቃቸው፣ የወደፊቱ አካሄድ ያላማራቸው. . . የዋህ ዜጎች አሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ኃይል የተሞላበትርምጃ እንዲወስድ የሚገፋፉ፣ የሰላሙ ሁኔታ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሄዶ እየጨሰ ያለው አቧራ ወደ እሳትነት ተቀይሮ እንዲቀጣጠል የሚፈልጉና በውጤቱም የመንግሥት ገጽታ እንዲጠለሽናመውደቂያ ጊዜው እንዲፋጠን በግርግሩ ለመጠቀም ያሰፈሰፉ መሰሪዎች መኖራቸው አይቀርም፡፡

በዓለማችን በሰላማዊ ምርጫ ያጡትን ሥልጣን በሽብርና በሴራ ለማግኘት የሚሯሯጡ እንዳሉ ደጋግመን ዓይተናል፡፡ ‹‹ኤጀንት ፕሮቮኬተር›› ይባላሉ፡፡ ፀብ እየጫሩና እየቆሰቆሱ የመንግሥትና የሕዝብን ትዕግሥት እየተፈታተኑ ማብረጃ ወደሌለው የደም ማጥ ውስጥ ለመጨመር የሚሠሩ ቅጥረኞች አሉ፡፡

በአንፃሩ ከኢሕአዴግ አስኳል ውስጥ እንደወጣ ቢታመንም የለውጥ ኃይል የሚባለው የብልፅግና አመራርና መንግሥት፣ በየዋሆችም ሆነ በሴረኞች ግፊት ተቻኩሎ ወደ ኃይልርምጃ መግባት መፍትሔ እንደማይሆን ይጠፋዋል ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ወደ ዕርምጃ ተቻኩሎ አለመግባቱ ያስከፈለው አገራዊ ዋጋ ቢኖርም፣ ጠቃሚ ነበር፡፡ በቀጣይም አሥር ጊዜ ለክቶ አንዴ መቁረጥ አለበት፡፡ ከተቆረጠ በኋላ ቢለኩት ዋጋ የለውምና፡፡

ሁሉም ነገር በእርጋታ፣ በጥሞናና በትዕግሥት መታሰብ ያለበት ከዕርምጃው በፊት ከወዲሁ ነው፡፡ አንድ የቆየ አባባል አለ ‹‹ለምጣዱ ሲባል አይጧን እናሳልፋት›› ይላል፡፡ ለእሷ ተብሎ ምጣድ አይሰበርም፡፡ በራሷ ጊዜ እስክትወጣ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ክፋት አልነበረውም፣ በሚገባም የተደረገ ይመስለኛል፡፡

ትዕግሥት ሁሉ ሲያልቅና የሕግ ጥሰት ገደቡን ሲያልፍ ለአገርና ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል የሚወሰደው ወቅታዊ ዕርምጃ ቅቡል የሚሆነው ያለ ችኮላና ከትዕግሥት በኋላ የተፈጸመ በመሆኑ ነው፡፡ በቀጣይስ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ምን መደረግ አለበት? ለሚለው ጥያቄ አንዳንድ ሐሳቦችን መሰንዘር ይቻላል፡፡

ተቀዳሚው ተግባር በአክራሪነት ዙሪያ ስላለው ዓለም አቀፋዊ፣ አገራዊ፣ ታሪካዊና ዘመናዊ ሁኔታ ለሁሉም ወገኖች ግንዛቤ ማስጨበጥ ይገባል፡፡ አክራሪነት ምንድነው? ሽብርተኝነት ምንድነው? የት? መቼ? እንዴት? በማን ተጀመረ? ምን ጉዳት አደረሰ? ምን ጥቅም አስገኘ?. . . የእኛ አገር የሃይማኖት መቻቻልና ተከባብሮ የመኖር ታሪክና ባህል ምን ይመስላል? በአሁኗ ኢትዮጵያ አክራሪነትን ለማራመድ የሚጋብዝ ሁኔታ አለ?

በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው መንግሥታዊ ሃይማኖት የለም፡፡ የሃይማኖት እኩልነት ተረጋግጧል፡፡ መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ አይገቡም፡፡ ሌላ ምን አለ? አክራሪነት ምሽግ እያደረገ ለው እስልምናን እየመሰለ እንደ መምጣቱም ቅዱስ ቁርአን ተደፈረ? የነብዩ (ሰዐወ) ክብር ተነካ? ሱናና ሃዲሱ ተሸረሸረ? ለአንዱ እምነት የተሰጠ መብት ለሌላው እምነት ተነፈገ? መስጊድ ፈረሰ? ስግደት ተስተጓጎለ? ኡለማዎች ተዋረዱ? ተጎዱ?. . . ከእነዚህ አንዱም በሌለበት ሁኔታ ነገሮችን ማክረርና ሽብር መፍጠር በይዘቱ ሃይማኖታዊ ሊሆን እንደማይችል ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

– በዓለማዊ ሕግ (ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት) እና በመለኮታዊ ሕግ (ሸሪአ) መካከል ያለውን ልዩነት ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡

– ተራራን የሚያፈራርስ ዕውቀት በመሆኑ ተቀዳሚው ሥራ በጉዳዩ ላይ ዕውቀትን ማጋራት ነው፡፡ በዚሁ የግንዛቤ ማስጨበጥና የማሳወቅ ሥራ አማካይነት የእስላማዊ መንግሥትን ምንነትና ማንነት ግልጽልጽ አድርጎ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ምሁራን፣ ሚዲያዎች፣ ሲቪክ ማኅበራትና የሃይማኖት አባቶች ኃላፊነት አለባቸው፡፡

በመሠረቱ በሌላው ዓለም እንዳየነው ዴሞክራሲያዊ መንግሥትና እስላማዊ መንግሥት እሳትና ጭድ ማለት ናቸው፡፡ የቅርብ ጊዜ ግባቸውም ሆነ የረጅም ጊዜ ራዕያቸው ፈፅሞ አይጣጣምም፡፡ ምናልባት ጥቂት መንገድ አብረው የጎሪጥ እየተያዩ የሚሄዱበት ርቀት አይጠፋ ይሆናል፡፡ ይህ ርቀት መንግሥትን እስከ መጣል ድረስ ብቻ ከመሆን አያልፍም፡፡ ልክ መንግሥት እንደ ወደቀ የአክራሪዎች የመጀመርያ ሥራ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ማውደምና መለኮታዊውን ሕግ (ሸሪአ)ን ማንገሥ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ እንኳን በእኛ ብዝኃነት በሞላባት አገር ይቅርና ሙሉ በሙሉ አንድ ዘርና አንድ ሃይማኖት ባለባቸው (እነ ሶማሊያም) አልተሳካም፡፡

በመሠረቱ አያድርገውና ከመቻቻልና ከአብሮነት ሥነ ልቦና የራቁ አክራሪዎች የበላይነትን ቢያገኙ፣ የመጀመርያዎቹ ተጎጂዎች ሙስሊሞች ራሳቸው ናቸው፡፡ አሁን እዚህ በነፃነት ሰማይ ሥር ሆነው እንደሚያስቡት አይደለም፡፡ የአክራሪነትን አስተሳሰብ በፖለቲካ ምጣድ ጋግረው በሕዝብ ላይ ለመጫን የሚሹ ኃይሎች አይደለም የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ሰላምና ደኅንነት ሊያስጨንቃቸው፣ ሙስሊም ሆኖ የእነሱን ፅንፈኛ መንገድ የማይከተለውንም አያስኖሩትም፡፡ በሌላው ዓለም እንደምናየው፣ እስልምና የማይፈቅዳቸው በርካታ ጥፋቶችም መከተላቸው አይቀርም፡፡ ፈጣሪ ያርቅልን!!

እንዲህ ያለውን አደገኛ አካሄድ ደግሞ ገና በእንጭጩም ቢሆን፣ ሕዝብና መንግሥት ዝም ብለው ያዩታል ማለት ዘበት ነው፡፡ ፈፅሞና ፈፅሞ የማይሆን ነገር ነው፡፡ በቀዳሚነት ይህ ዓይነቱ አካሄድ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ የሚጥስ፣ የሕዝቦችን በአንድነትና በነፃነት የመኖር መብት የሚያውክ ብቻ ሳይሆን የአገር ሉዓላዊነትን የሚያናጋ በመሆኑ የተባበረ ትግል ሊደረግበት የግድ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ሕግና ሥርዓትን በሁሉም መንግሥታዊና ሕጋዊ ተቋማት ከማስከበር ባሻገር የአክራሪዎችን ጩኸትከሌሎች ሚዛናዊ አማኒያን ነጥሎ የፖለቲካ ጭምብላቸውን ገፍፎ ዕርቃናቸውን ማስቀረት ያስፈልጋል፡፡ ከኢያሪኮ በስተቀር በጩኸት የፈረሰች አገር ስለመኖሯ የተመዘገበ ታሪክ የለምና ኢትዮጵያም በጩኸት እንደማትፈርስ በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡

በዚህና በሌሎችም በአገራችን ፀንቶ ስለቆየው የሃይማኖቶች ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር ታሪክና ባህል ዙሪያ ባሉ እሴቶቻችን ላይ የሚካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ከላይ ተንጠልጥሎ የሚቀር ብቻ ሳይሆን፣ እስከ ታችኛው ወለል እስከ ቀበሌ ድረስ የሚወርድ የመቻቻል ጉባዔ መሆንም አለበት፡፡ በየትኛውም ሃይማኖት ቢሆን በአክራሪነትና በሃይማኖት የፖለቲካ ነጋዴነት ጉዳይ ላይ ግልጽ ያለ አቅጣጫና ቀጥ ያለ አቋም ሊኖረን ይገባል፡፡ ትግሉም ገና ከዕንቁላል ጊዜ አንስቶ መጠናከር ያለበት ነው!!

   ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...