Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲጠሩት ይሰማል እንጂ አልጠራም ማለት አይችልም!

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲጠሩት ይሰማል እንጂ አልጠራም ማለት አይችልም!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የሁላችንም የሲቪክስ ትምህርት የመማሪያ ዋናው ሥረ መሠረት የመንግሥት ሦስት ዘርፎች ወይም ቅርንጫፎች ስለሆኑ፣ የእኛም ሕገ መንግሥት በየደረጃው ያሉት ‹‹የሕግ አውጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው›› (50/2) ስለሚል፣ የፓርላማ ሥራ ከሕግ ማውጣት ጋር ብቻ ሲያያዝና ሌላውና ዋናው ነገር ሲረሳ እናያለን፡፡ አጠቃላይ የሕዝብ ግንዛቤና ንቃቱ፣ የሲቪክስ ትምህርቱ ሀሁ ፓርላማ ሕግ ያወጣል፣ መንግሥት (መስተዳድሩ) ሕግ ያስፈጽማል፣ ያስተዳድራል፣ የዳኝነት አካሉ ሕግ ይተረጉማል ብሎ መነሳቱም ከዚህ የተነሳ ነው፡፡

ከአድራጊ ፈጣሪነት ከፈላጭ ቆራጭነት ሕዝብን ወደሚያፍርና ወደሚፈራ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ወደ ተደላደለበት የሽግግር ምዕራፍ የምናደርገው ወይም ማድረግ የጀመርነው ጉዞ ብዙ ውጣ ውረድ የደረሰበት መንገራገጭና አደጋ የበዛበት ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ አለመቀልበሱ ወይም በተለይም የፈነጠቀውን ዴሞክራሲ የግርግር መደገሻ አድርገው እንዳሻቸው መሆን ብቻ ሳይሆን ሥራቸውና ተልዕኮአቸው ባደረጉ ኃይሎች ምክንያት እስካሁን አለመሰበሩና የለየለት ፈላጭ ቆራጭነትን አለመጋበዙ ግን እውነት ነው፡፡

ይህንን የምንጽፈውም ይኸው አሁንም ዴሞክራሲው ስላለ ነው፡፡ የምንጽፈው ደግሞ ጽፈንና ጮኸን የዴሞክራሲውን ጮራ ዓይነስብ እናጥፋ ብለን ሳይሆን የንግግር፣ የመጻፍና ሐሳብን የመግለጽ መብቶቻችንን የዴሞክራሲ መደላድል ለማስፋት ራሱን ዴሞክራሲን ለማበልፀግ ስለሆነ ነው፡፡ ሚዲያውና መናገር መብቴ ነው የሚል ሁሉ ቀዳሚ ተግባርም ይኸው ነው፡፡ መሆንም አለበት፡፡

የፓርላማ ሥራና ተግባር ሕግ ማውጣት ብቻ አይደለም፡፡ ወይም ሕግ አውጪ በሚባል ስሙ እንደሚታወቀው የሕግ ፋብሪካ፣ የሕግ አምራች መሥሪያ ቤት ብቻ አይደለም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚባለው ስሙ እንደሚታወቀውም ሕዝብን መወከልም ሌላው ዋናው ሥራው ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል›› (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 50/ን) የሆነውም የሕዝብ እንደራሲያዊ ዋና ባለሥልጣንነት የተረጋገጠበትና የሚዘልቅበት አካል ስለሆነ ነው፡፡ ስለዝም ብሎ ምርጫ ሳይሆን ስለነፃ ምርጫ፣ ከሆነም ደግሞ ስለ ‹‹ምርጫ  ብሎ ዝም›› የምንጨነቀው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

አሁንም የፓርላማው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተግባር ሕግ ማውጣት፣  የሕዝብ እንደራሴያዊ ባለሥልጣንነት መወከል ብቻ አይደለም፡፡ ሕግ አወጣሁ ብሎ ከዚያ ወዲያ ያለው የእኔ ድርሻ አይደለም ወይም ‹‹ሥራው ያውጣው›› ብሎ ነገር የለም፡፡ እንዲህ ያለ ሰባራ የሕዝብ ውክልና ወይም የሕዝብ እንደራሴያዊ ዋና ባለሥልጣንነት የለም፡፡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በታች ያለውን ራሱም ያቋቋመውንና ያደራጀውን የኢትዮጵያን ከፍተኛ የአስፈጻሚነትና የአስተዳዳሪነት ሥልጣን የተሰጠውን (አንቀጽ 72) የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የሚኒስትሮች ምክር ቤትን፣ በጠቅላላው የመስተዳድሩን ሥራ መቆጣጠርም ምክር ቤቱ ለሌላ በውክልና አሳልፎ የማይሰጠው፣ ወይም ለጊዜው ይቆይ የማይለው አለዚያም ትቼዋለሁ ብሎ ከጫንቃው የማያወርደው ዋናው ሌላው ግዳጁ ነው፡፡ ፓርላማው የመንግሥትን ገንዘብ/በጀት የሚያከፋፍለውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ነው ለውጡና ሽግግሩ የተረከበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋም ራሱ እንኳን በ2008 በወጣውና በተሻሻለው የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ በአንቀጽ 4 የምክር ቤት ዋና ዋና የሥልጣንና ተግባራት ሀ) ሕግ ማውጣት ለ) በጀት ማፅደቅ ሐ) መንግሥታዊ አካላትን መከታተል፣ መቆጣጠርና አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውም ዕርምጃ መውሰድ ብሎ የደነገገው፡፡ የለውጡና የሽግግሩም ዓላማ በሕገ መንግሥቱ የተዘረዘሩት የመብትና የነፃነት፣ እንዲሁም የመንግሥት የሥልጣን አካላትና የባለሥልጣኖቻቸው የግንኙነት፣ የተጠያቂነትና የኃላፊነት ድንጋጌዎች ከስምና ከጌጥ ያለፈ ፋይዳ ይኑራቸው፡፡ እስትንፋስ ያግኙ፡፡ መኗኗሪያ ይሁኑ ማለቱ ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህም ለውጡንና ሽግግሩን የሚመራው መንግሥት ከሌሎች መካከል በምክር ቤቱ የአሠራር ደንብ ውስጥ የተደነገጉትን፣ ከሕገ መንግሥቱ የመነጩትን የክትትልና የቁጥጥር ምዕራፍ ድንጋጌዎች መከተልና ማክበር፣ ትርጉም አጥተው፣ ተፈጻሚነት ተነፍገው ይልቁንም ተረግጠውና መሳቂያ ሆነው የኖሩበትን ጊዜ ማካካስ፣ ትርጉማቸውንና አንድምታቸውን ማስፋፋትና ማበልፀግ ይኖርበታል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በለውጡ ውስጥ ያጋጠመው ዕድል ያጎናፀፈውን ‹‹መናጋት›› እና የነፃነት አየር ተጠቅሞ ከሙትቻነቱ ተምሮ የአዲስ ምዕራፍ አጋዥ መሆን አለበት፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ከዚህ የበለጠ አርአያነትና የአዲስ ዓይነት የመንግሥት አገልጋይነት ተጨማሪ ትጋትና ጥረት ይጠይቃል፡፡

ኢትዮጵያን በዚሁ ሕገ መንግሥት ውስጥ እውነትም ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊና ሪፐብሊካዊ ለማድረግ መወሰድ ያለባቸው የለውጥ፣ የመሻሻያና የሽግግር ዕርምጃዎች በየጊዜው ተገልጸዋል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ አገልግሎት የፌዴራሊዝምን ጉዳይ ለጊዜው አቆይተን (ይህንን የምናደርገው ፌዴራሊዝም ስለማያስፈልግ በአሀዳዊነት ስለተተካ የሚለውን አሉባልታ ለማገዝ አይደለም) የዴሞክራሲያዊነትንና የሪፐብሊካዊነትን ነገር እናንሳ፡፡ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው 547 አባላት ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝቦች እንደራሴያዊ ዋና ባለሥልጣንነት የተረጋገጠበትና ተረጋግጦም መዝለቅ የቻለበት መሠረት አልነበረውም፡፡ የዚህ ምክንያት ደጋግመን እንደገለጽነው ምርጫና የሕዝብ ፍላጎት ኢትዮጵያ ውስጥ ተገናኝተው ስለማያውቁ ነው፡፡ የምርጫዎች ዝግጅት አፈጻጸምና አስተዳደር የቆመባቸው መንግሥታዊ አውታራትም አገራችን ውስጥ ከኢሕአዴጋዊነትና ከእሱ ታማኝነት ነፃ ሆነው ታንፀው አያውቁም ነበርና እንኳንስ ሕዝቡ ውስጥ የሚደርስና የሚጨበጥ ቀርቶ፣ ለእነሱም ለተወካዮች ተብዬዎችም የሚገባ (የሚሰማ) የውክልና ሽታ ዓይቶ የማያውቅ የሥራ ድርሻ ነው፡፡

የሪፐብሊክ ትርጉም ሕዝብ ተወካዮችን ይመርጣል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የመረጣቸውን ተወካዮች ይቆጣጠራል፣ የሕዝብ ተወካዮች ደግሞ ያደራጁትን መንግሥት፣ የሥልጣን አካላቱንና ባለሥልጣናትን ይመራል፣ ይቆጣጠራል ማለት ነው፡፡ ይህ ሆኖ አያውቅም፡፡

ይህንን ለማሳየት አሁንም ድረስ ገና ሙዚየም ያልገባውን፣ ከሥልጣን ቢንሸራተትም የለውጡ ንቁና መሪ ተቃዋሚ ሆኖ ያረፈውን የሕወሓት/ኢሕአዴግ ፓርቲና መንግሥት አስተዳደር ባህሪይ እንመልከት፡፡ በፓርቲውና በአባላት መካከል ያለው ግንኙነት ለዴሞክራሲያዊነት ባዳና እንግዳ ነበር፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አባላት የድርጅቱ የገደል ማሚቶዎች ነበሩ፡፡ የድርጅቱ አቋምና አካሄድ ፈታይ የድርጅቱ ቁንጮ አመራር ነበር፡፡ የድርጅቱ ቁንጮ አመራር ደግሞ የመንግሥታዊ ሥልጣኑም ቁንጮ ነበር፡፡ ሕግ የማውጣት፣ አስፈጻሚውን የመመርመርና የመጠየቅ አስፈጻሚው ተሸፋፍኜ እተኛለሁ ቢል ገልጬ አይሃለሁ የማለት፣ ሕግ ተርጓሚውን የመሾምና መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃንን የመምራት በሕግ ሥልጣን የተጣለበትና በኢሕአዴግ ተመራጮች የተሞላው የተወካዮች ምክር ቤት ዞሮ ዞሮ በፓርቲው የበላይ መሪ መዳፍ ውስጥ ነበር፡፡

ሕወሓት/ኢሕአዴግን የሚመሩት አቶ መለስ ዜናዊና ጥቂት ግለሰቦች (ኋላ ላይ ደግሞ ከአቶ ኃይለማርያም ጀርባ ያሉ ሰዎች) የመንግሥቱን ሥራ አስፈጻሚ አካል ሲመሩ ኖሩ፡፡ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ቧንቧና ቱቦ በኩል ደግሞ በፓርላማ ውስጥ ያሉትን ተወካዮች ሲያዙና መናገር፣ መደገፍና መቃወም ያለባቸውን ሁሉ ሲሠፍሩላቸው ኖሩ፡፡ አገር ትተዳደር የነበረው እንዲህ ነበር፡፡ ሥራ የማስፈጸም፣ ሥራ አስፈጻሚውን የመመርመርና የመጠየቅ፣ ሕግ የማውጣትና ዳኛ የመሾሙ ሥራ ሁሉ በአንድ ቡድን፣ ከዚያም በላይ በአንድ ግለሰብ፣ ከዚያም በኋላ ወደ አንድ ቡድን እጅ ተቃልሎ ገባ፡፡ ይህም ቀጥሎ የመንግሥት የፍፁማዊ አገዛዝ አደጋ የአገር ነቀርሳ ሆኖ ኖረ፡፡ በዚህ ብቻም አልተወሰነም፡፡ የመበስበሱ ችግር የራሱ የቡድኑ/የግንባሩ ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ በዚህ ስም የተጠራው የመበስበሱና የመሰንጠቅ አደጋ የራሱ የፓርቲው ችግር ሆኖ የሚቀርብበት ሁኔታ ባለመፈጠሩ፣ የዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ግንባታ ንጣፍ ባለመዘርጋቱ የገዥው ፓርቲ ወይም ቡድን ዳፋ የአገር ዕዳ መሆኑ ቀጠለ፡፡

ለውጡ የመጣው በ2007 ምርጫ በሕዝብ ድምፅ ተደራጀ የተባለው ፓርላማ መስከረም 2008 ዓ.ም. ሥራ እንደጀመረ በዚያው ዓመት ኅዳር ወር ጀምሮ በተቀጣጠለ፣ ነገር ግን አገር ባልፈረሰ መንግሥት ባልገረሰሰ) አመፅ ነው፡፡ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወዲህ የፓርላማው የፓርቲ ቅንብርና ‹‹ውክልና›› ተናግቶ፣ የድምፅ አሰጣጥ ‹‹ፓርቲያዊ መስመር››ም ተለዋውጦ በመምጣቱ ይህ ከገዥው ግንባር ውስጥ ተፈልቅቆ ከወጣው አመራር ጋር የሽግግሩ እርሾ መሆን ቻለ፡፡

አሁን ሥራ ላይ ያለው (ሥራ ላይ ያለው ስንል እየሠራ ያለው፣ ተፈጻሚነቱን በማረጋገጥ ላይ የሚገኘው ማለት ሳይሆን በሕግ ፀንቶ እንደ ሕግ ፀንቶ ያለው ለማለት ነው) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የሥነ ምግባር ደንብ፣ በዚሁ በአምስተኛው ምክር ቤት ዘመን መጀመርያ ላይ የፀደቀ የ2008 ዓ.ም. ሕግ ነው፡፡ ይህ ከመስከረም 27 ቀን 2008  ዓ.ም. ጀምሮ የፀና ይሆናል የተባለውና ጥር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ‹‹የተፈረመው›› ሕግ ከፓርላማው ዋነኛ ተግባርና ግዳጆች መካከል አንዱና ዋናው አድርጎ በደነገገበት በምዕራፍ አሥራ አንድ፣ ‹‹የክትትልና ቁጥጥር›› ምዕራፍ ውስጥ ለስምና ለወግ ያህል እንኳን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 17ን (ንዑስ አንቀጽ 16ን በነካ እጁ) አላነሳም፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 የሕዝብ ተወካዮችን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር የሚዘረዝረው ዋናው አንቀጽ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ በንዑስ ቁጥር 17፣ ‹‹ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ሌሎች የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ሥልጣን አለው፤›› ይላል፡፡ የሕግ አስፈጻሚው አካል ማለት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 72 የአገሪቱ/የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት ከፍተኛው የአስፈጻሚነትና የአስተዳዳሪነት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡

ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ጉዳዮችና አካላት የሚለው መቶ በመቶ የኢሕአዴግ ግንባርና አጋሮች ድል የተሞላው ፓርላማ (የመጀመርያ ቀን) ሕግ ግን፣ ምክር ቤቱ በሚከተሉት አካላት ላይ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል ብሎ የተዘረዘረው ‹‹ሀ) የፌዴራል መንግሥት አካላትን ለ)በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 መሠረት የሰብዓዊ መብቶችን መጣስ ሊያስቆምና ሊቆጣጠር ያልቻለን ክልል›› ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት አካላት ማለትና ‹‹የአስፈጻሚው አካል›› ማለት አንድና ተመሳሳይ አይደለም፡፡ የፌዴራል መንግሥት አካላት የአስፈጻሚው አካል አባላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሁሉም ግን አይደሉም፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን፣ ‹‹ማንኛውም ክልል ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም ሳይችል ሊቀር፣ በራሱ አነሳሽነትና ያለ ክልሉ  ፈቃድ ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ ያቀርባል፣ በተደረሰበት ውሳኔ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት መመርያ ይሰጣል፤›› የሚለውን የሕገ መንግሥቱን የአንቀጽ 55/16 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን የጠቀሰው የምክር ቤቱ ደንብ ግን፣ ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለጥያቄ ይጠራል የሚለውን አንቀጽ 55/17ን ዝም ብሎ ማለፍና መግደፍ ቢችልም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ጥያቄውን ግን ሙሉ በሙሉ አላፍታታም፡፡ ይልቁንም በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ በአንቀጽ 79/1/ለ እና በተለይም በአንቀጽ 92 እንደ ተደነገገው፣ ሁልጊዜ በየሳምንቱ ሐሙስ ሚኒስትሮች በቃል መልስ የሚሰጡበት፣ በየወሩ ሐሙስ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቃል መልስ የሚሰጡበት የአንድ ሰዓት የጥያቄ ጊዜ አለ፡፡ ይህ በሳምንትና በወር አንድ ጊዜ ሐሙስ በቃል መልስ የሚሰጥበት የጥያቄ ጊዜ በእግርጥ ፍፁም አይደለም፡፡ አፈ ጉባዔው በሌላ ሁኔታ ሊወስንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት በሚያቀርብበት ወር ውስጥ የተባለው የጥያቄ ጊዜ አይኖርም፡፡

እስከ ዛሬ ድረስ ሐሙስ በየሳምንቱም ሆነ በወር በመጣ ቁጥር የአንድ ሰዓት የጥያቄና መልስ ጊዜ ሳናይ የኖርነው፣ ወይም ከእንዲህ ዓይነት አሠራር ጋር ሳንተዋወቅ የቀረነው አፈ ጉባዔው (ሦስት አፈ ጉባዔዎች ዓይተናል) በሌላ ሁኔታ ስለወሰኑ፣ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሮች (ሁለቱም) ሪፖርት ያቀረቡበት ሐሙሶች ስለነበሩ አይደለም፡፡ እንደ ማንኛውም ሕግ አለማክበር የሚቻል ስለሆነ ነው፡፡ ሕግ ማክበር የቢሻን ውሳኔ ስለነበር ነው፡፡ አዲሱም ጠቅላይ ሚኒስትር ከብዙ አስቸጋሪና ከባድ ችግሮች ጋር የወረሱት አሠራር ስለሆነ ነው፡፡

ወደ ሰኞው አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ ልዩ ስብሰባ ጥያቄና መልስ፣ የተጠያቂነት ጉዳይ እንግባ፡፡ ይህንን ጉዳይ የምናነሳውና መነጋገሪያ የምናደርገው በሕግ የተደነገገ የጥያቄ ቀን ስላለ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሕጉንና ደንቡን ያነሳነው ዋናው ጉዳያችን ይኸው የሰኞው የጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ተጠየቅ አልጠየቅም›› ጉዳይ ስለለ ነው፡፡

እርግጥ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ዕለት ውሏቸውም ቢሆን፣ ቢዘገይም ያስመዘገቧቸው አዳዲስ ሪከርዶች አሉ፡፡ ዘግይተዋል፣ የፓርላማው መድረክ እስኪመጣ ጠብቀዋል እንጂ፣ ‹‹የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃ ይሁን ያለው ይህ ኃይል የፍትሕ ሥርዓቱን ነፃነት የሚቃረን መሆን የለበትም፡፡ ፍርድ ቤቱ ለሚሰጧቸው ፍርዶች/ብይኖች ምንም [ሳናወላውል] መቀበል ያስፈልጋል፡፡ እኛ ያላከበርነውን ፍርድ ቤት ነፃና ገለልተኛ ሁን ማለት ከንቱ ነገር ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡ እዚህ ሁሉንምና ሙሉውን እንዳለ ባልጠቀስነው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማክበር የአስፈጻሚው በተለይም የፖሊስ አደገኛ አሠራር የሚመለከት ምላሽ ውስጥ ብዙ የምንነጋገርባቸውና የምንማማርባቸውና መጥራት፣ ሊታረቁ (ማረቅ) የሚገባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ትልቅ የአቋም መግለጫ ነው፡፡ በዚያ ለዳኝነት ነፃነት ንቀት ማሳየት በተለመደበት፣ ነውር መሆኑ ተገልጾ እንኳንስ ውግዘት ጥያቄ እንኳን ተነስቶ በማያውቅበት ‹‹ሌባ ዳኞች›› እያሉ ደግሞ ደጋግሞ እንደ ብሔራዊ መዝሙር ነፃነቱን ማሸማቀቅ በተለመደበት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዳኞች አስተዳደር ‹‹ውክልና›› ስም የምክር ቤት አባልነት ውስጥ የተደበቀ የፓርቲ ከፍተኛ ቁንጮና ‹‹የመንግሥት ተጠሪ›› ፍርድ ቤቶችን የመቆጣጠር ፈቃድ ተሰጥቶት በሠለጠነበት መድረክ፣ እኛ ያላከበርነውን እኛ ያልታዘዝንለትን ፍርድ ቤት ነፃና ገለልተኛ ሁን ማለት ከንቱ ነው ብሎ መናገር ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህ ግን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ ዘግይቷልም፡፡ ባለፈው ሳምንት በዚህ ዓምድ እንደገለጽኩት፣ ይህንን መንግሥት ወዲያውኑና የፓርላማ መድረክ ሳይጠብቅ ‹‹ወዲያውኑ ማረምና ማስተካከል አጥፊውንም በግላጭ ማውገዝና ተበዳዩንም በአደባባይ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡››

በዚህ የጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥያቄና መልስ ረዥም ውሎ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግመው ደጋግመው ስለቁጥጥርና ድጋፍ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ የተቻለኝንም ያህል መቁጠር እችል እንደሆነ ብዬ ሞክሬያለሁ፡፡ የፓርላማው ‹‹የተለመደውን ቁጥጥርና ድጋፍ›› ደግመው ደጋግመው ተማፅነዋል፡፡ ‹‹የእናንተ ቁጥጥርና ድጋፍ›› ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ የፓርላማው ‹‹ክትትልና ቁጥጥር›› ከዋና ዋና ተግባርና ግዳጁ መካከል አንዱ መሆኑን ዓይተናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ቱሪዝምን በአጠቃላይ፣ ‹‹ገበታ ለሀገር››ን በተለይ የሚመለከተውን ሲመልሱ ‹‹የሥራውን ዕሳቤና መሠረት›› በእኔ ግምት በሚገባ አስረድተዋል፡፡ እኔ እንደገባኝ ብዙው  እየተብከነከነ፣ ግራም እየገባው አሁን አንበጣ፣ ጎርፍ፣ ኮቪድ አገር በሚያምስበት አገር የእንጦጦና የሸገር ነገር ቢቀር ቢቆይ ተብሎ ለተጠየቀው ጉዳይ የሰጡትን መልስ ሰምተናል፡፡

ያልገባኝና ፍፁም የማልስማማበት ምላሽ ግን የምክር ቤቱ ቁጥጥር ከሚመድበው በጀት ጋር የተያያዘ ነው ያሉበት የእንጦጦ ፕሮጀክት መልሳቸው ነው፡፡ ‹‹የተከበረው ምክር ቤት እንጦጦን ብሠራም ባልሠራም ሊጠይቀኝ አይችልም፡፡ [ምክንያቱም] ለእንጦጦ አንድ ብር አልሰጠኝም፡፡ እናንተ መጠየቅ ያለባችሁ ለመንገድ 56 ቢሊዮን ብር ሰጥተንህ ስናበቃ መንገድ አልተሠራም … [ብላችሁ ነው] …፡፡ አንድ ብር ባልወጣበት ፕሮጀክት ከዚህም ከዚያም ተለምኖ ሲሠራ ግን አቃቂር ማውጣት….›› ልክ አይደለም ብለዋል፡፡

ይህ ልክ አይደለም፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ የአስፈጻሚነትና የአስተዳደርነት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የአገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር ናቸው፡፡ ተጠሪነታቸውም ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ጋር ለተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥራ የሙሉ ጊዜ ሥራ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የትርፍ ሰዓት ሥራም አይደለም፡፡ ሌለ የትርፍ ሰዓት ሥራ የሚፈቅድም አይደለም፡፡ ለዚህ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ፣ ተጠያቂና ኃላፊ ነው፡፡ ሲጠሩት መስማት ሲጠይቁት መመለስ አለበት፡፡ ምክር ቤቱ ‹‹አንድ ብር ባልወጣበት›› ያልከውን ፕሮጀክት ገንዘብ ከየት አገኘህ? ማን ፈቅዶልህ ሰበሰብክ? ያ ገንዘብ አንተ እጅ ሲገባ የመንግሥት/የሕዝብ ገንዘብ መሆኑ ቀረ ወይ? ይህስ ገንዘብ ከመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ሕግ ውጭ ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ እሳቸውም መመለስ አለባቸው፡፡

በ1999 ዓ.ም. ታኅሳስ ወር ሶማሊያ የገባው የኢትዮጵያ ጦር ተልዕኮውን አጠናቅቆ በድል  መመለሱ ፓርላማ መድረክ ላይ በተነሳበትና የኢትዮጵያ ጦር ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ በተጠየቀበት ጊዜ፣ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የሰጡትን መልስ አስታውሳለሁ፡፡ የመልሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ጥያቄ የቀረበበት መረጃ (ከኢትዮጵያ ሠራዊት ምን ያህል ሞተ? ተጎዳ?) ምንም አይጠቅማችሁም የሚልና ይህንን መረጃ የመግለጽ ግዴታ የለብኝም የሚል ነበር፡፡ መለስ የኢትዮጵያ ወታደር ጉዳት ይህን ያህል ነው ብሎ በቁጥር መግለጽ ለሥራችሁ ምንም የሚሰጠው ፋይዳ የለም ያሉት ያውም በሕግና በቲዮሪ ደረጃ ለ‹‹ፈጠራቸው›› ፓርላማ፣ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት (በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13/2 እና አንቀጽ 29) መረጃ ለመጠየቅ፣ የጠየቅሁት መረጃ ምን እንደሚያደርግልኝ ማስረዳት የሌለብኝ መሆኑ እየታወቀ ነው፡፡ ለምክር ቤቱ መግለጽ ግዴታ የለብኝም ያሉት ሌላው ቢቀር ይህ ‹‹ሚስጥር›› የፓርላማው የሚመለከተው (ደኅንነት/መከላከያ) ኮሚቴ እንዲያውቀው እናደርጋለን ሳይባል ነው፡፡

ዝርዝር ማነፃፀሩ ‹‹የሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተጠሪነት ወግ›› ለሚል ሰፊ ጽሑፍ የሚያበቃ ቢሆንም፣ ልዩነቱና ተመሳሳይነቱ ግን ትናንትም ዛሬም ‹‹ፓርላማው ዝም›› ብሎ አለፈው ተብሎ የሚዘለል አይደለም፡፡ ዓብይ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክታቸውን አስረድተዋል፡፡ በ‹‹ከንቱ›› ነገር ላይ ይብከነከናል ያሏቸውን ከፓርላማው ውጪ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በሰብዓዊ መብቶች ተቋማት፣ በሬዲዮ/ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ውስጥ ሰርገው የገቡትን ቅጥር አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ጩኸት መልሰዋል፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያን ሀብት ዕምቅ አቅም ምሳሌ እየሰጡ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ሰፊ ሀብት አለን፡፡ ሀብታችን ሰፊ ነው፡፡ ግን ዓይን ይፈልጋል፡፡ የተገለጠ ዓይን፣ የሚያይ ዓይን ይፈልጋል፡፡ ከሠፈራችን ወጥተን ማየት ስንጀምር ቶሎ አልሙኝ የሚል የሚያስደነግጥ ሀብት አለን፤›› ብለዋል፡፡

እዚህ ቁጣም ቁጭትም የተደባለቀበት ማለፊያ ማብራሪያ ውስጥ የገቡበት ስሜት ግን፣ ምክር ቤቱ አምስት ሳንቲም ባልመደደበበት ነገር ምን አገባው ለምን ይጠይቀኛል የሚል ስህተትና ጥፋት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ ‹‹አንድ ብር ባልወጣበት ፕሮጀክት ከዚያም ከዚህም ተለምኖ ሲሠራ ግን አቃቂር ማውጣት አገር እንዴት እንደሚገነባ ካለማወቅ የሚነሳ ነው፤›› ማለታቸው ውስጥ፣ በተለይም መጨረሻው ላይ ይህን ስሜት እናያለን፡፡ የመናደዱ ምክንያት ቢገባንም መልሱ ግን ትክክል አይደለም፡፡ የምክር ቤቱ ቁጥጥር ከተመደበ በጀት ጋር ብቻ የተገናኘ አይደለም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሸፋፍነው ቢተኙም ገልጦ የሚያይ  አለቃችን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመልሰው ሊናገሩበት፣ ተሳስቻለሁ ሊሉበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በአፋጣኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...