Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከለውጥ በኋላ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መልኩን ቀይሮ ብሔር ተኮር ሆኗል›› አቶ መስዑድ ገበየሁ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኅብረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

አቶ መስዑድ ገበየሁ ተወልደው ያደጉት በደቡብ ወሎ ዞን ወግድ ወረዳ ሌንጮ ቀበሌ ውስጥ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ነው፡፡ በተወለዱበት ወረዳ ውስጥ የበላይ ዘለቀና የዋለልኝ መኮንን የጀግንነት ታሪክ ከመስማት ባለፈ ዘመናዊ ትምህርት መማር የማይታሰብ ነበር፡፡ በሕፃንነታቸው ከስምንት እህትና ወንድሞቻቸው ጋር በግብርና ሥራ ላይ የአቅማቸውን ያህል ከመሥራት ባለፈ፣ ስለፊደል ቆጠራ የማይታሰብ ቢሆንም፣ ከዕለታት አንድ ቀን አባታቸው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት እንዲያስገቡ የሚያስገድድ ነገር ተፈጠረና የወረዳው ሚሊሻ አስገደዳቸው፡፡ የአባታቸው መገደድ የአቶ መስዑድን የሕይወት መንገድ መቀየሪያ ሆነ፡፡ አቶ መስዑድ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተደረገ፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን (ከኬጂ እስከ ስድስተኛ) በሌንጮ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤትና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ መካነ ሰላም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ሰባተኛና ስምንተኛ) ተማሩ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቦረና መሰናዶ ትምህርት ቤት በመማር ከፍተኛ ውጤት በማምጣታቸው ወሎ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ ትምህርት አግኝተዋል፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት በቆዩባቸው ዓመታት ‹‹የወሎ ባህል ማዕከልን›› ከማቋቋም ጀምሮ የተለያዩ ክበባትን በማቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አቶ መስዑድ መጀመርያ ሥራ የጀመሩት በአፋር ክልል ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በሕግ መምህርነት ነው፡፡ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት በሠሩባቸው ጊዜያቶች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የነበሩ ብልሹ አሠራሮች ከመቅረፍ አንፃር በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ የሠሩበት ጊዜ አጭር ቢሆንም የሕግ አገልግሎት ኃላፊ በመሆን ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተያያዙ የክስና ሌሎች ሥራዎችን ከዳር በማድረስ ዩኒቨርሲቲው የሚሻሻልበትንና የሚጠናከርበትን አሠራር ዘርግተዋል፡፡ አቶ መስዑድ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንተርናሽናል ፐብሊክ ሎው ሠርተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እየተማሩ ባለበት ወቅት የሥራ ላይ ልምምድ (ኢንተርንሽፕ) ያደረጉት የሰብዓዊ መብት ላይ በሚሠሩ ድርጅቶች ውስጥ ነበር፡፡ የቆዩበት የልምምድ ጊዜ አጭር ቢሆንም፣ በዘርፉ ላይ የመሥራት ፍላጎታቸው ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ቢመለሱም በሰብዓዊ መብት ላይ መሥራታቸውን በመቀጠል ከሰመራ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ለስምንት ወራት ያህል ከሠሩ በኋላ፣ የማስተማር ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ በመተው በሰብዓዊ መብት ላይ መሥራትን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው አድርገው ቀጥለዋል፡፡ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ላይ ሲሠሩ ቆይተው፣ በመሥራችነት የተሳተፉ አምስት በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን የያዘ ‹‹የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኅብረት›› የተባለና በአሁኑ ጊዜ ከ12 በላይ ድርጅቶች የተካተቱበት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኢትዮጵያ እየሠሩ ስላለበት ሁኔታና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች በማንሳት ታምሩ ጽጌ ከአቶ መስዑድ ገበየሁ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኅብረት የተመሠረተው መቼ ነው? የስንት ድርጅቶች ስብስብ ነው?

አቶ መስዑድ፡- መሥራቾቹ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፣ ቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ፣ አድቮኬትስ ኢትዮጵያ (ክርስቲያን ሎየርስ አሶሴሽን ይባል የነበረው)፣ ሳራ ጀስቲስ ፎር ኦል ውሜን አሶሴሽን፣ ጄቨሎፕመንታል ጀስቲስና ናሽናል አሶሴሽን ናቸው፡፡ ድርጅቱ ከተመሠረተና የተወሰነ ጊዜ ከሠራን በኋላ እ.ኤ.አ. በ2019 አዲስ የፀደቀው የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች አዋጅ እንደ አዲስ በቅርቡ ከፀደቀ በኋላ፣ በርካታ ድርጅቶች ወደ ኅብረቱ በመቀላቀላቸው አባላቱ 12 ደርሰዋል፡፡ ሌሎችም እያመለከቱ ነው፡፡ በክልሎች በኦሮሚያ በማረሚያ ቤት፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሰብዓዊ መብቶች፣ በደቡብ በሐዋሳ ላይ በወጣት የሕግ ባለሙያዎች፣ ትግራይ ክልል መቐለ ላይ የሕግ አገልግሎት ድጋፍና በሰብዓዊ መብት ግንዛቤ ላይ የሚሠሩና ሌሎቹም በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚሠሩ ድርጅቶችም አብረው የሚሠሩ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኅብረት በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራው በምን ላይ ነው?

አቶ መስዑድ፡- ኅብረቱ በዋናነት የተቋቋመበት ዓላማ በቀድሞ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2009 በዴሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብቶችና ግጭት አፈታት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች የመጥፋት አደጋ ውስጥ በመግባታቸው ያ ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ቢቀጥል፣ ሁሉም ታሪክ ሆነው የሚቀሩበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ሥጋት ነበር፡፡ ስለዚህ የዚህ ኅብረት ትልቅና ዋና ዓላማ እነዚህን ድርጅቶችን መታደግ ነበር፡፡ በመሆኑም ሕጉ እንዲወጣና እንዲሻሻል ብዙ ግፊትና ጥረት አድርገናል፡፡ በመቀጠልም የድርጅቶቹን አቅም ማጠናከር ነበር፡፡ ለዚህም ፕሮጀክቶችን መቅረፅ፣ ድጋፍ ማሰባሰብ ወይም ሀብት ማሰባሰብ፣ ዓላማቸው ላይ ትኩረት አድርገው ውጤታማ ሥራ መሥራት እንዲችሉ ማድረግና በዋናነት ደግሞ በሰብዓዊ መብት ላይ ይሠራል፡፡ በእርግጥ እዚህ አገር ባይለመድም፣ የሰብዓዊ መብት ሥራ ሲሠራ ብዙ ከፖለቲካ ጋር ያምታቱታል፡፡ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ግለሰቦችና ተቋማት ብዙ ችግሮችንና ወከባዎችን አሳልፈዋል፡፡ ለዚህም ኢሠመጉ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህ ችግር ቢቀጥልም ወይም ባይቀጥልም በተለይ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የደኅንነት ሥልጠና (Security) ማለትም አካላዊ ደኅንነትና ዲጂታል (ዌብሳይት፣ ኢሜል) መጠበቅ አለት፡፡ በሰብዓዊ መብት ላይ በሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ቢሮ ሰብሮ መረጃ መውሰድ፣ በድርጅቱ ኃላፊዎች ላይ ማስፈራራትና ዛቻ ማድረስ፣ ለሕይወትም ሆነ ለደኅንነት ሥጋት ስለሚፈጥር፣ ይህንን መታገልና ማስቆም የማኅበሩ አንዱ ተግባር ነው፡፡ እንዲያውም ለድርጅቶቹ የሚሟገትና የሚደርስባቸውን ወከባና ጥቃት የሚከላከልና የሚያስቆም ማኅበር ሆኖ እንዲሠራ ማድረግ ዓላማው አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን የሚያጠናክርና ከለላ የሚሰጥ አሠራር እንዲኖር የሚያደርግ ሕግም እንዲወጣ ኅብረቱ ግፊት ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ትግል ውስጥ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችና ድርጅቶች ዕውቅና እያገኙ እንዲቀጥሉና ሌሎችንም የሚያበረታታ እንዲሆን ጥረት ያደርጋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ትግል ሙያ እንዲያድግ በማስተባበርም ይሠራል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግለሰብና በቡድን በተለያየ መንገድ ይፈጸማል፡፡ ኅብረቱ ይህንን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል ወይም ለመሞገት የሚችለው በምን መልኩ ነው?

አቶ መስዑድ፡- በዋናነት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት፣ እንደ ኅብረትነቱ የሚያተኩረው በዝርዝር ጉዳዮች ላይ አይደለም፣ አባላትን ያስተባብራል፡፡ ክፍተት ሲኖር አቅማቸውን ያጎለብታል፡፡ አጋርነትን ይገነባል፡፡ በፖሊሲ ደረጃ ያለ የመብት መሟገትን በዋናነት ይሠራል፡፡ ለምሳሌ ችግር ያለባቸው ሕጎች እንዲሻሻሉ ኅብረቱ አባላትን በማስተባበር፣ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ የተለያዩ ሐሳቦች የሚሰጡባቸው መድረኮችን በማመቻቸትና ግፊት በማድረግ፣ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ በዜጎች ላይ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፍትሔ እንዲያገኙ ጥረት ያደርጋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2009 እና 2014 ኢትዮጵያ በሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግምገማ (Universal Periodic Review) ከተደረገባት በኋላ፣ መንግሥት ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር አውጥቶ ነበር፡፡ ይኼ የድርጊት መርሐ ግብር ማንም የሰብዓዊ መብት ድርጅት ክትትል ሳያደርግበትና ሳይሳተፍበት በኢትዮጵያ ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ድምፃቸው ሳይሰማ እ.ኤ.አ. 2016 ላይ በሌላ የድርጊት መርሐ ግብር እንዲተካ ተደርጎ በመጪው ኅዳር ወር ላይ ያልቃል፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሦስተኛውን የድርጊት መርሐ ግብር እያዘጋጀ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ በኢትዮጵያ የሙስሊም ማኅበረሰብ እንቅስቃሴን፣ የኦሮሞ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን እንቅስቃሴ፣ የኦሮሚያና የአማራ አካባቢዎች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የነበረ የሰብዓዊ መብት አፈና፣ እንግልት፣ እስራትና የተለያዩ ድርጊቶች፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር ፈታኝ የነበረ ቢሆንም፣ ያ ሁሉ ታልፎ ሪፎርም በመምጣቱ የተሻለ ነገር ተደርጓል፡፡ በተለያዩ ምክንያት የታሰሩ ማለትም ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ከእስር ተለቀዋል፡፡ ብዙ አፋኝ ሕጎች እንዲሻሻሉና ሙሉ በሙሉ እንዲቀየሩም ተደርገዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩም በመሻሻሉ፣ በውጪ አገሮች በስደት ላይ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ይህ ሁሉ መሻሻል ሲመጣ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ሰብዓዊ መብትን በሚመለከት አብዛኛውን ጊዜ በመንግሥት የደኅንነት አካላት፣ በአስፈጻሚው አካል፣ በፖሊስ፣ በደኅንነትና በማረሚያ ቤት ይደርስ የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ጋዜጠኞች የጋዜጠኝነት ሥራቸውን ብቻ በመሥራታቸው የታሰሩ፣ የተሰደዱና ብዙ ስቃይ የደረሰባቸው ነበሩ፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ሲታሰሩና እንዲሰደዱ ሲደረጉ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ የሚፈጸመው በመንግሥትና በመዋቅር ጭምር ስለነበር ነው፡፡ ከሪፎርም በኋላ ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መልኩን እየቀየረ መጥቶ፣ ብሔር ተኮር በመሆን ከመንግሥት መዋቅር ውጪ በመሆን በውል ኃላፊነት የማይወስዱ የተለያዩ ኢመደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል፡፡ የመንጋ ፍትሕ በመስጠትም ኢሰብዓዊ የሆነ ግድያ፣ ማፈናቀልና (በኦሮሚያና በሶማሊያ፣ በጌዴኦና በጉጂ…) ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጥሯል፡፡ በቅርቡ ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወርና በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተጠረው ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት የሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከት ሦስት ግዴታዎች አሉበት፡፡ የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ አለበት፡፡ አንድ መንግሥት ሕዝቡንና አገሩን ለማስተዳደር ኃላፊነት እስከወሰደ ድረስ፣ ሦስቱን የመፈጸም ግዴታ አለበት፡፡ መንግሥት አስፈላጊውንና ተመጣጣኝ የኃይል ዕርምጃም ቢሆን ተጠቅሞ፣ በተለይ ኢመደበኛ አደረጃጀቶችንና የመንጋ ውሳኔዎችን የማስቆምና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚህ መልኩ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት አለ፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ሲያጋጥም ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይደርስባቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ  እንደ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኅብረት የምናደርግው፣ ድርጅቶቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በተፈጸመበት አካባቢ በመሄድ ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ አስቸኳይ መግለጫ ያወጣሉ፡፡ መደበኛ መግለጫ ያወጣሉ፡፡ በምርመራ የተገኙ ውጤቶችን ለሕዝብና ለመንግሥት ይፋ ያደርጋሉ፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በድርጊቱ ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ ግለሰቦችም ይሁኑ ቡድኖች ለፍትሕ እንዲቀርቡ ግፊት ያደርጋሉ፡፡ ላለፉት 27 ዓመታትም ሲሠራበት ነበር፡፡ አሁንም ይቀጥላል፡፡ አባል ድርጅቶቹን በማስተባበር በመንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር  የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል፡፡ ይህንን ከደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ ያሉ ተማሪዎች በታፈኑ ጊዜ በመተባበር፣ በርካታ እንቅስቃሴዎችን አድርገናል፡፡ በዚህና በተለያዩ ሁኔታዎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ በግለሰቦችም ሆነ በቡድኖች ላይ የሚደርስን የመብት ጥሰት በሚመለከት ተጠያቂነት እንዲመጣ ግፊት ማድረግ ነው፡፡ ይህንን እያከናወንን ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ግን ከመንግሥት ጋር በቅርበት ከምንሠራቸው ስለሰብዓዊ መብት ከሚሠራው ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በቅርበት በጋራ ከምንሠራው ውጪ ነው፡፡ መንግሥት ትኩረት ያላደረገባቸውንና ትኩረት የነፈጋቸውን  ለመብት ጥሰት ተጋላጭ በሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ግፊት ማድረግና መጫን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዋና ተግባር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተፈጸመ ጊዜ ብዙ ሰዎች ‹‹የት አላችሁ?፣ ምንድነው ሥራችሁ?›› ይላሉ፡፡ አንድ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ነገር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ባጋጠመ ጊዜ ጥሰቱ ወዲያውኑ እንዲቆም ማድረግ አንችልም፡፡ ድርጊቱን መቃወም የምንችለው ድርጊቱ ተመርምሮ የተረጋገጠ ነገር በእጃችን ሲኖር ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሌሎች አገሮች በዜጎች ላይ ማንኛውም ዓይነት የመብት ጥሰት ሲፈጸም፣ የድርጊቱን ፈጻሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከራካሪ ድርጅቶች ወይም ማኅበራት ጉዳዩን ወደ ፍትሕ ተቋም በመውሰድ ክስ የሚያቀርቡበት አሠራር አለ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የሲቪል ማኅበሰብ ድርጅቶች ያለው አሠራር እስከ ምን ድረስ ነው?

አቶ መስዑድ፡- የሕዝብን ጥቅምና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አስመልክቶ ችግሮች ሲፈጠሩ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ፣ ክርክር የሚያደርጉና በሕግ ተጠያቂነት ላይ የሚሠሩ  አገሮች አሉ፡፡  እነዚህን ስትራቴጂክ ‹ሊቲጌሽን› እንላቸዋለን፡፡ ወደ ኢትዮጵያ አሠራሩን ለማምጣትና ለመተግበር መጀመርያ የሕግ ማዕቀፉ የሚፈቅድ አይደለም፡፡ በአንድ አካባቢ ላይ ችግር ሲደርስ የፍትሐ ብሔር ክስ ማቅርብ የሚቻልበት አሠራር አለ፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ግን እንደዚህ ዓይነት አሠራር የተመደ አይደለም፡፡ የአካባቢን ጥበቃ በሚመለከት፣ የአንድ አካባቢን ማኅበረሰብን በመወከል ክስ ማቅረብ እንደሚቻል በአዋጅ ስለተደነገገ፣ በውክልና ክስ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 ድንጋጌ መሠረት ፍትሕ የማግኘት መብትን በሚመለከት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዚያ ደረጃ መብት የሚሰጣቸው አይደለም፡፡ በሕግ ማሻሻል ማዕቀፍ ውስጥ ከወጡ ሕጎች አንዱ የአስተዳደር ሕግ ነው፡፡ በዚያ ሕግ ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አስተዳደራዊ በደሎች ባጋጠሙ ጊዜ ክስ ማቅረብ እንደሚችሉ የሚያሳይ አሠራር ተዘርግቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎች አንፃር፣ ምንም እንኳን አገራዊ ሕጎች ባይፈቅዱም የመብት ጥሰት ሲፈጸም ክሱን ማቅረብ የማይቻለው ለምንድነው?

አቶ መስዑድ፡- ትክክል ነው፡፡ መሆን ነበረበት፡፡ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ ስንመጣ ግን፣ መፍትሔዎችን አሟጦ የመቅረብ ነገር መኖር አለበት፡፡ ክሱን መጀመርያ ወደ ሬጅስትራር ይዘህ ስትቀርብ፣ ሬጅስትራሩ መዝገብ አይከፍትልህም፡፡ በዚህ ጊዜ ይግባኝ ጠይቀህ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልትሄድ ትችላለህ፡፡ በመካከልም የተለያየ መሰናክል ይገጥምሃል፡፡ ይህ የሚሆነው ግልጽ የሆነ መብት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተሰጠ ነገር ስለሌለ ነው፡፡ አንተ እንዳልከው የሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከት ኢትዮጵያ ዋና ዋና ከሚባሉት ስምንት የሰብዓዊ መብቶች ውስጥ ሰባቱን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ፈርማለች፡፡ በዚያውም አግባብ ተጠያቂ የምትሆንበትም አግባብ አለ፡፡ በተለይ እኛ አገር የሚፈጸሙ ትልልቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስም አይሰጣቸውም፡፡  ምክንያቱም የወንጀሉ ተግባር ሲተነተንና ሲመረመር የዘር ማጥፋት ሆኖ ይገኛል፡፡ ወይም ደግሞ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሆኖ ይገኛል፡፡ ይኼንን በስሙ ጠርቶ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ያለው አሠራር እጅግ በጣም ፈታኝና ከባድ ነው፡፡ ‹‹ጉዳዩን ያባብሳል›› በሚልና በተለያየ መልኩ ጫና ይመጣበታል፡፡ የኢትዮጵያን የፍርድ ቤቶችን ሥርዓት አልፎ በአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለማቅረብና በተለያየ መልኩ የተቋቋሙ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚመለከቱ አሠራሮች አሉ፡፡ ያንን ለማቅረብ ግን እዚህ አገር ያሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አቅም ያላቸው አይደሉም፡፡ አብዛኛውና ትልቁ ችግር ያለው የተግባር አፈጻጸም፣ አገራዊ አፈጻጸሙን ተከትሎ ማለፍ ስላለበት በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ በቀጥታ ቢሄድ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ከዚህ በፊት በሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተሞክሮ አልተሳካም፡፡ ለምሳሌ የሙስሊም ማኅበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጉዳይ ለአፍሪካ ኮሚሽን ቀርቦ ኢትዮጵያ ላይ ተወስኖባታል፡፡ ነገር ግን ያንን ያደረጉት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ሳይሆኑ በውጭ አገር የሚኖሩ የሕግ ባለሙያዎችና ሲቪል ሶሳይቲስ ናቸው፡፡ ሌሎችም ነበሩ፡፡ ግን የተፈለገውን ውጤት አላስገኘም፡፡ የተወሰኑ ሙከራዎች የነበሩ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከስፋቱና ዓይነቱ እንፃር ያሉት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ እነዚያም ከአቅም በታችም የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይኼ የሆነው በተለይ አዋጅ ቁጥር 621/2001 ያመጣው ጫናና የፋይናንስ ችግር ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ሰፊ ከመሆኑ አንፃር፣ ተከታትሎና ጊዜ ሰጥቶ ለመሥራት ችግሮች ይገጥማሉ፡፡ ድርጅቶቹ አቅም ኖሯቸውና ነፃ ሆነው ለመሥራት  በሚያስችላቸው ጫና ውስጥ በመሆናቸው የተፈለገውን ውጤት ማግኘት አልተቻለም፡፡ በክልል ያሉት ድርጅቶችም ደካሞች ናቸው፡፡ በፌዴራል ያሉት ደግሞ የተሻለ ነገር ቢሠሩም፣ በክልል ጽሕፈት ቤት ስለሌላቸው፣ ባለሙያ ተልዕኮ ጥናት ተደርጎ በቂ መረጃ እስከሚገኝ ድረስ ነገሩ መረሳት ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ በዚህ መሀል ግን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ‹‹አልሠሩም? ወይም ዝም ብለው ስም ብቻ ናቸው›› የሚል ወቀሳ ይሰነዘራል፡፡

ሪፖርተር፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አብዛኞቹ የሚንቀሳቀሱት የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥና አንዳንድ ትልልቅ የክልል ከተሞች ላይ ነው፡፡ አብዛኛው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚፈጸመው ደግሞ በክልሎች ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኅብረት ከዚህ አንፃር ሊሠራው ያሰበው ነገር አለ?

አቶ መስዑድ፡- አንድ ድርጅት ለተለያየ ዓላማ በተለያዩ አካባቢዎች ሊቋቋም ይችላል፡፡ የኅብረቱ አንዱ መርሁም የሰብዓዊ መብትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በኢትዮጵያ ሸፍኖ እስከሠራ ድረስ በመላ አገሪቱ መዳረስ አለበት የሚል ነው፡፡ አሁን ላይ እንኳን በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራና ሌሎች ክልሎች ላይ አባል ድርጅቶች አሉን፡፡ ወደፊትም በሰብዓዊ መብት ላይ አተኩረው የሚሠሩ ድርጅቶችን ለማምጣትና ተጠናክረው እንዲሠሩ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ላይ ነን፡፡ በቅርቡም በሰባት ክልሎች ላይ ተግባራዊ የሚሆን በኮሮና (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ላይና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ እየተሠራ ያለ ፕሮጀክት አለ፡፡ በየክልሉ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የምንከታተለው፣ በክልሎች ባሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አባሎቻችን በኩል ነው፡፡ ይህንን የምናደርገው አቅማቸው እንዲጎለብት በማድረግ ነው፡፡ ማለትም የሰብዓዊ መብት ማለትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምን እንደሆነ እንዲያውቁ በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ኅብረት መቀመጫውን አዲስ አበባ ከተማ ላይ ቢያደርግም፣ በሁሉም ክልሎች በሰብዓዊ መብቶች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ድርጅቶችን በአባልነት ይዞ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ያለ ኅብረት ነው፡፡ ከእኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት ከሌላቸውና በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ከሚሠሩ ድርጅቶችም ጋር ጥሩ የሥራ ግንኙነት በመፍጠር፣ በዜጎች ላይ የሚፈጠሩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል  እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰት አገር አቀፍም ዓለም አቀፍም ወንጀል ነው፡፡ ጥሰቱ ደግሞ በግለሰብም በመንግሥትም ይፈጸማል፡፡ በዚህ የመብት ጥሰት ላይ ለመሥራት የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመብት ጥሰት ተፈጽሟል ከማለት ባለፈ፣ በመንግሥት አካላትና በማኅበረሰቡ ላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሰብዓዊ መብት ምን ማለት እንደሆነ ግንዛቤ ከመፍጠር አንፃር ምን የሠሩት ነገር አለ?

አቶ መስዑድ፡- የሰብዓዊ መብት ሥራ ሰፊ ሥራ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት ያልሆነም ነገር የለም፡፡ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ እንኳን ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነው ስለሰብዓዊ መብት የሚናገር ነው፡፡ ምንም እንኳን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ብሎ ቢከፋፍለውና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የተቀዳ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያም ዕውቅና ሰጥታ የሕገ መንግሥቷ አካል አድርገዋለች፡፡ ሁለቱም እያደጉና እየተሻሻሉ የሚሄዱ ናቸው፡፡ መንግሥት ዴሞክራሲውን እያሻሻለና እያሰፋው ሲሄድ የሰብዓዊ መብትም እየተሻሻለ ይሄዳል፡፡ ያም ቢሆን ሥራው በመንግሥት ብቻ የሚሠራ አይደለም፡፡ ተባብሮና ተጋግዞ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ኅብረታችን አንዱ የሚሠራው ከሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ተቋማት ጋር ተባብሮ መሥራት ነው፡፡ ከምርጫ ቦርድ፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከዕንባ ጠባቂ፣ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሁሉ በቅርበት መሥራትና የተሻለ ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲኖር ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ዓላማው ነው፡፡ ውጤታማ ከሆንባቸው ሥራዎች አንዱ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ አዘጋጅተን በየወሩና በተለያዩ ጊዜያት የምንገናኝበት መድረክ ማቋቋማችን ነው፡፡ ኮሚሽኑ መንግሥታዊ ተቋም ቢሆንም ግብሩ ከፍ ብሎ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንዲሠራና ተናቦ ለመሄድ ጥሩ ጅማሮ አለ፡፡ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ‹‹ተቋማዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ችግሮች ምንድናቸው?›› የሚለው በሕግ ባለሙያዎች ዕይታ፣ በፖለቲካ ባለሙያዎች ዕይታና በማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ዕይታ፣ በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ዕይታ እያየነው፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ አመራሮችና ሠራተኞች ስለ ሰብዓዊ መብት ግንዛቤ እንዲያገኙ የማድረግና ሚዲያው ስለሰብዓዊ መብት ምንነት ግንዛቤ የሚፈጥሩ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩር የውይይት መድረክ ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ተደርጓል፡፡ በጥሩ ሁኔታ የተካሄደና ጥሩ ግንዛቤ የፈጠረ መድረክም ነበር፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሰብዓዊ መብቶች ድርጊት መርሐ ግብር የሚባል ጽሕፈት ቤት አለው፡፡ ያ ጽሕፈት ቤት መርሐ ግብሮችን እያዘጋጀና ወደ ታች እያወረደ ግንዛቤ እንዲፈጠር የሚያደርግ አሠራር አለው፡፡ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የእኛ ድርጅት ከአንድ የውጭ ድርጅት ጋር በመተባበር የሁለቱን የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብሮች ዲሴምበር ላይ የሚያልቀውን የመጀመርያውንና ሁለተኛውን መርሐ ግብሮች አፈጻጸምና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፏቸው ምን እንደነበር፣ እንዲሁም መንግሥት ሪፎርም ከጀመረ በኋላ በሰብዓዊ መብት ላይ ለመሥራት ምኅዳሩ ከመስፋቱ አንፃር፣ ይህንን በሚመጥን ደረጃ ድርጅቶቹ መሥራት እንዲችሉ አማራጭ የድርጊት መርሐ ግብር ለመንግሥት ሐሳብ ለማቅረብ እናስባለን፡፡ መንግሥት ባይቀበለን እንኳን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በራሳቸው መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉበት ሰብዓዊ መብትን በሚመለከት ያለው አሠራር እርስ በርስ ያለው ግንኙነት፣ ማለትም ከማቀድ፣ ከመፈጸም፣ ከመገምገምና አጠቃላይ ያለውን አሠራር እንደ አገር ከመውሰድ አንፃር አንዲሠራ፣ ጥናቱ እንደተጠናቀቀ ከመንግሥትና ከአጋር ድርጅቶቻችንና ከዲፕሎማሲ ኮሙዩኒቲው ጋር በመሆን ተወያይተንበት፣ ሥራችንን የምናስፈጽምበት ሰነድ እናደርገዋለን፡፡ ቀጣይ ጊዜ የምርጫ ወቅት እንደመሆኑም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ደግሞ በተለይ ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ምንድነው?›› በሚለው ዙሪያ ከድርጅቶቹ  ከፍ ያለ ሥራ ይጠበቃል፡፡ ምርጫና ሰብዓዊ መብት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው፡፡ በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብት ተጋላጭነት ከፍ ይላል፡፡ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት በማስተማር፣ የመራጮች ትምህርት በማስተማር፣ ምርጫን በመታዘብ፣ ተፈናቅይ ዜጎች በምርጫ ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ ምን ይመስላል? የሚለውን መሥራት ግድ ነው፡፡ እስካለፈው ወር መስከረም 2013 ድረስ በአገሪቱ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃይ ሕዝብ አለ፡፡ ይኼ የሕዝብ ቁጥር በአንዳንድ አገሮች ካሉ የሕዝብ ብዛት በላይ ነው፡፡ አገር መንግሥት ሊያቋቁም የሚችል ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ምክንያቶች የተፈናቀለ ነው፡፡ ከእነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ ዕጩ የፓርቲ አባል ሊኖር ይችላል፡፡ ባሉበት ቦታ ላይ ሄዶ ‹‹ምረጡኝ›› እያለ የሚቀሰቅስና የፖለቲካ አስተሳሰቡን ወይም ፕሮግራሙን የሚያስረዳ ፓርቲ መኖር አለመኖርን፣ ተፈናቃዩ በምን ሁኔታ ነው በምርጫው ሊሳተፍ የሚችለው?›› በሚለው ላይ ሁሉ ድርጅታችን ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፡፡ ተፈናቃዮች የተሟላ ሰነድ እንዴት ነው የሚያገኙት፣ ከተፈናቀሉ ሦስት ወራት ከሆናቸው በምርጫ ለመሳተፍ  ስድስት ወራት መቆየት እንዳለባቸው የተደነገገው ሕግስ እንዴት ይሆናል? በርካታ መሠራት ያለባቸው ነገሮች ስላሉ፣ ድርጅቶቹ ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ ጉጂንና ጌዴኦን ብንወስድ፣ ከጉጂ ተፈናቅሎ ወደ ጌዴኦ የገባና ከጌዴኦ ወደ ጉጂ ተፈናቅሎ የሄደ ድምፁን ለማነው የሚሰጠው? በሁለቱም በኩል ሰላማቸውን ሊያስከብርላቸው ያልቻለ የአካባቢ መንግሥትን ሊመርጥ ነው? በመፈናቀል በሄደበት ቦታ ደግሞ ከማያስተዳድረው የአካባቢ አስተዳዳሪ ጋር ግንኙነት የለውም? ስለዚህ እነዚህ ዜጎች በቀጣይ የሚመራቸውን አካል መምረጥ የሚችሉት እንዴት ነው? በዚህ ላይ እየሠራንበት ነው፡፡ ሌላው የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት፣ ከምርጫ አስፈጻሚው ምርጫ ቦርድ ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት በሚመለከት፣ የምርጫ ስትራቴጂ አዘጋጅተን ጨራርሰናል፡፡ ስለዚህ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የምርጫ ስትራቴጂያቸው ምን መሆን አለበት? እያንዳንዱ ፓርቲ በሰብዓዊ መብት ላይ ትኩረት አድርጎ አንዲከራከር እንፈልጋለን፡፡ በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአረጋውያን፣ ለከፋ ነገር ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ፣ በትምህርት ጥራት፣ ማኅበራዊ ደኅንነትን በማምጣት፣ ድህነትን በመቀነስ፣ ወዘተ እነዚህ ሁሉ የሰብዓዊ መብት ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ ማኒፌስቷቸውን ከሰብዓዊ መብት አንፃር እንዲፈትሹ ጫና ማድረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና መሆን አለት፡፡ ክርክር ሳይሆን ሰብዓዊ መብትን በሚመለከት ፓርቲዎች ይዘው የቀረቡትን ለሕዝብ ይፋ የሚያደርጉበትንና አንዱ ከሌላኛው የሚለይበትን የሚገልጽበት መድረክ ማዘጋጀትም የድርጅቶቹ ሚና ለማድረግ እንሠራለን፡፡ ማኅበረሰቡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ይዞት ስለቀረበው አማራጭ በደንብ ማወቅ የሚችልበትን ሒደት እናስተምራለን፡፡ ይህን ሁሉ የምንሠራው ከምርጫ ቦርድና ሰበዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር ነው፡፡ ዕንባ ጠባቂ ተቋምም አስተዳደራዊ በደሎችን ከሙስና፣ ከሰብዓዊ መብትና ሌሎች አሠራሮችን በሚመለከትም የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ እንደ አጠቃላይ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን እንሠራለን፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ጋር በነበረን የውይይት መድረክ አንዱ ያነሳነው ጉዳይ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በልዩ ሁኔታ ጉዳት ላይ ስለነበሩ፣ ወደ ሥራ እንዲገቡ ሕግ ማሻሻል በቂ ባለመሆኑ ትኩረትና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚል ነው፡፡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካውን ጡዘት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንደ አንድ ሁነኛና አጋር ታይተው ሊሳተፉ እንደሚገባም ጠይቀናል፡፡ እንደ ትምህርት፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎች ታይቶና ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሴክተር›› ተብሎ በራሱ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችል ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠይቀናል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ገለልተኛ ነን፡፡ ከፖለቲካ፣  ከፓርቲ አመለካከትም ነፃ ነን፡፡ በእርግጥ ዘርፉ ሕግ ወጥቶለት የተደቆሰና መሥራት እንዳይችል ተደርጎ የቆየ ከመሆኑ አንፃር፣ አሁን ላይ በአንድ ጊዜ ተደራጅቶና አንድ ሆኖ የተፈለገው ደረጃ ላይ ይደርሳል ባይባልም፣ የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ጠንክረን እንሠራለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለመንግሥትም ሆነ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሞዴል ለመሆን ዘርፉ ቆርጦ ተነስቷል፡፡ ከመንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት፣ ውስጥ ለውስጥ ያላቸውን ግንኙነት አሠራራቸውን የሚፈትሽ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ይቋቋማል፡፡ ምክር ቤቱ ገለልተኛ ሆኖ ድርጅቶቹ ከለጋሾች ጋር፣ ከመንግሥትና እርስ በርሳቸው ያላቸውን ግንኙነት እየፈተሸ ይፋ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ከመንግሥትም ጋር የሚኖረን ግንኙነት የተሻለና እንደ ሌሎች አገሮች ለአገር ጥቅም እንሠራለን የሚል ቁርጠኝነት አለን፡፡ ግብፅና ሱዳን ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ከመንግሥት ጋር ብዙ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ የእኛም መንግሥት ከድርጅቶቹ ጋር አብሮ በመሥራት፣ ድርጅቶቹ በተንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉ ስለአገር፣ ሕዝብና መንግሥት በማስረዳት የአገራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ሥራ እንዲሠሩ መደረግ አለባቸው፡፡ ዜጎች ፍትሐዊ አመለካከትን እንዲይዙ በማድረግ በኩል የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የማይናቅ ሚና ስላላቸው፣ መንግሥት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ልማት አንዱ ሰብዓዊ መብት በመሆኑ፣ በሁሉም መስክ ተሰማርተው ውጤታማ ሥራ ሊሠሩ ስለሚችሉ ድርጅቶቹ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እነዚህ የትኩረት አቅጣጫዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በነበረን ውይይት አስረግጠን በመናገራችን በጎ ምላሽ ይሰጡናል የሚል እምነት አለን፡፡ ከፍርድ ቤቶች ጋርም እየሠራናቸው ያሉ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች በኅብረተሰቡ ቅቡልነትንና ተሰሚነትን ማግኘት አለባቸው፡፡ ተዓማኒነትን ማምጣትም አለባቸው፡፡ ስለዚህም የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ መሆን አለባቸው፡፡ የሚሰጡትም ፍትሕ ተገማች መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከሪፎርም በፊት ወይም ከሁለት ዓመታት በፊት የነበረን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከሁለት ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ መስዑድ፡- አንድ የመብት ጥሰት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ሊያስብለው የሚያስችለው ተቋማዊ ሲሆን ነው፡፡ እንደዚህ ካልሆነ ተራ ወንጀል ይሆናል፡፡ መንግሥት ፈልጎ ወይም ደግሞ በመንግሥት ግዴለሽነት የሚፈጸሙ ድርጊቶች ናቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚባሉት፡፡ ከለውጥ በፊት ያለውን ወይም ከሁለት ዓመታት በፊትና በኋላ ያለውን አነፃፅሮ ለመናገር እንደ ማሳያ ፍርድ ቤትን ላንሳ፡፡ ፍርድ ቤቶች ከሁለት ዓመታት በፊት በኦነግ፣ ግንቦት ሰባትና በሌሎች አሸባሪ ተብለው በተፈረጁ መንግሥትን የሚተቹ ሚዲያዎችና መንግሥትን የሚቃወሙ ፖለቲከኞች እስር ቤት የነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ሪፎርሙ ከመጣ በኋላ ግን እነዚህ ነገሮች ለጊዜውም ቢሆን ቀርተዋል፡፡ ትልልቅ ሙስና ፈጽመዋል የተባሉ፣ ጥፍር ነቅለዋል፣ ዜጎችን አሰቃይተው ገድለዋል የተባሉ ተለይተው ታስረዋል፡፡ ከሪፎርም በኋላም መቀጠል ቀስ በቀስ የተለያየ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ከድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘም በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው የታሰሩ አሉ፡፡ ሚዲያዎች ተዘግተዋል፡፡ ጋዜጠኞች ታስረዋል፡፡ ይህም እንደ ሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ያሳስበናል፡፡ እንደ ግለሰብ እኔ ከባድ ወንጀል አውቀውና ተዘጋጅተውበት የፈጸሙ ሰዎች በዕርቅና በግልግል ይፈቱ የሚል እምነት የለኝም፡፡ በሕግ የበላይነት መከበር አምናለሁ፡፡ የሕግ የበላይነት ለሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም ዋስትና ነው፡፡ ሁሉም በሥርዓት እንዲሠራ፣ እንዲቃወም፣ እንዲዘግብና እንዲንቀሳቀስ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡ ይኼ የሕግ የበላይነት መከበር ግን ለሁሉም በእኩልነት ሲሠራና ሲያገለግል ነው፡፡ ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ፣ በተጠረጠሩበት ጉዳይ ማስረጃ ቀርቦና ክርክር ተደርጎ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በሕጉ አግባብ ሊቀጡ ይገባል፡፡ በተለያየ ነገር እየተፈረጁና ማስረጃ ቀርቦባቸው ባልተረጋገጠባቸው ሁኔታ፣ እውነትነቱ ያልተረጋገጠ ዘጋቢ ፊልም እየተሠራባቸው ከፍርድ በፊት ይፈረጁ የነበረበት ድርጊት ከሪፎርም በፊት በብዛት የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም የቀጠለበት ሁኔታ አለ፡፡ ዋስትና የተፈቀደለት ተጠርጣሪ አይለቀቅም፡፡ ነገር ግን ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ዋስትናን የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ነበር የሚከለክለው እሱ ተሽሯል፡፡ በተለይ ፍርድ ቤት የዋስትና መብት ከፈቀደ ፖሊስም ሆነ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ የሚሉበት የሕግ አግባብ የለም፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ንፁህ ሆኖ እንደሚገመት በሕገ መንግሥት ሳይቀር ተደንግጎ እያለና ፍርድ ቤትም በዋስ እንዲቆይ ፈቅዶ እያለ፣ አስፈጻሚው መከልከሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ ከቀናት በፊት ይህንን ድርጊት አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረግጠው መናገራቸውን ሁላችንም ሰምተናል፡፡ ተከታትለናል፡፡ በደንብ አድርገው ከሪፎርሙ በኋላ ያለውን የአስፈጻሚውና አልታዘዝም ባይነት ያረጋገጡበትና ያለ ፍትሕ መከበርና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መፈጸም የሚመጣ ሰላምና ደኅንነት እንደሌለ በማረጋገጥ ለፍትሕ ተገዥ እንዲሆኑ ያሳሰቡት ሁኔታ ትክክለኛ መልዕክትና ለሁሉም ዜጋ የሚያገለግል ነው፡፡ የፍርድ ቤቶች ሥራ ግልጽነት ያለበትና ተጠያቂነትን የሚያመጣ መሆን አለበት፡፡ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የፍርድ ቤት አሠራሮችን እየተከታተሉና ከሰብዓዊ መብት አንፃር እያዩ፣ የተከሳሾች መብት እንዲከበር፣ የሕዝብ ጥቅም እንዲከበርና የፍርድ ቤቱ ተዓማኒነት እንዲጎለብት፣ የፖሊስ፣ የዳኛ፣ የጠበቆችና የዓቃቤ ሕግ አሠራር እንዲሻሻል ምክር በመስጠትና ግፊት የማድረግ ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡ የተሻለ ነገር ቢኖርም ከለውጥ በፊት ይታዩ የነበሩ ነገሮች ከሪፎርሙ በኋላም በብዛትም ባይሆን የቀጠሉበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ሚዲያ ለአንድ አገር ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት፣ የሰብዓዊ መብት እንዲሻሻል ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ያ የሚሆነው በጉዳዮቹ ላይ ምንም ዓይነት ጥቅም ወይም ያዘነበለ ፍላጎት ሳያሳይ ሁሉንም ባማከለ ሁኔታ መሥራት ሲችል ነው፡፡ ነገር ግን ከጥቂት የግል ሚዲያዎች በስተቀር አብዛኛው ሚዲያ ወገንተኛ ሆኖ የሚሠራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም፡፡ የሚዲያም ሥራ የሰብዓዊ መብት ሥራ ነው ብለን ስለምናስብና ሕዝቡ መረጃ የማግኘት መብት ስላለው መረጃ ለሕዝቡ ለማድረስ፣ የአገር ዕድገትና ለውጥ እንዲጎለብት ፈቃድ ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ከመሆናቸው አንፃር፣ ሁሉንም በእኩልነት ማገልገል አለባቸው፡፡ ነገር ግን ከሪፎርምም በፊት ሆነ ከሪፎርም በኋላ ያለው ነገር መጠኑ የተለያየ ቢሆንም ተመሳሳይ ሥራዎች አሉ፡፡ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ያላቸውን ያህል፣ ተጠርጣሪዎችም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዴት እየቀጠለ እንደሆነ መረጃው ለሕዝብና መንግሥት እንዲደርስላቸው ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም ይህ በተስተካከለና ሕጉን ባከበረ መልኩ መፈጸም አለበት፡፡ ሒደቱ በሕዝቡ እየገመገመ ተገማች የሆነ ፍትሕ መሠራቱን ያረጋግጣል፡፡ በሕግና ፍርድ ቤትም ላይ እምነቱን እያጠናከረና ለአገሩና ለወገኑ ያለውን እምነት እያዳበረ ይሄዳል፡፡ የሚጠብቁት መንግሥትና ተቋማት እንዳሉ አረጋግጦ ያለ ሥጋት ኑሮውን ይመራል፡፡ ሥራውንም ይሠራል፡፡ ይህ በአንድም ሆነ በሌላ የሰብዓዊ መብት መከበር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከሪፎርሙ በኋላ የተሻለ ነገር ቢኖርም፣ አሁን አሁን ላይ ግን እየታዩ ያሉ አሠራሮች ዕርምት ካልተደረገባቸው ወደ አሥጊና አደገኛ ደረጃ እየሄዱ በመሆናቸው፣ እኛም እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ይህንን እንኮንናለን፡፡ እንዲስተካከልም በተለይ ለባለድርሻ አካላት እናሳስባለን፡፡ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ በመተባበር ለውጤታማ ሥራ ተግተን እንሠራለን፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 ተደንግጎ እንደሚገኘው፣ የመንግሥት አሠራር ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በኃላፊነት ላይ የተቀመጠውም አካል ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ ፍርድ ቤቶች ችሎቶችን ግልጽ ማድረግ አለባቸው፡፡ ሕዝቦች አሠራሩን እንዲከታተሉ መደረግ አለበት፡፡ ውሳኔዎቹ እንዲፈጸሙ ማድረግ አለበት፡፡ አስፈጻሚው ትዕዛዝ ካላከበረ ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ በማቅረብ አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ያ ሲሆን ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ የሚሰጡት ፍትሕም ተገማች ይሆናል፡፡ እኛ እንደ ሰብዓዊ መብት ድርጅት ፍርድ ቤቶችን እንከታተላለን፡፡ ሚዲያዎችም ነፃና ገለልተኛ ሆነው የሕዝብን ጥቅም ያማከለ ሪፖርት እንዲሠሩ የአቅም ግንባታ ሥራ እንሠራለን፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ያላቸው ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማድረግም እንሠራለን፡፡ ይህ ማለት በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች፣ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሠሩትን ሥራ ሚዲያዎች ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ግልጽ የሆነ አሠራር እንዲኖር የማድረግ ሥራ እንዲሠሩ መደረግ አለበት፡፡ በዚህ ላይም የሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ከሚዲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ እንሠራለን፡፡ አሁን ላይ ሆነን ከሪፎርም በፊት የነበረውንና ከሪፎርም በኋላ ያለውን ለማነፃፀር ይከብዳል፡፡ ከሪፎርም በኋላ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን ማሰር አይታይም፡፡ አዳዲስ ተቋማትን የመፍጠርና ተቋማት አቅም ባላቸው ሰዎች እንዲመሩ ተደርጓል፡፡ የመንግሥት ፍላጎት ሕግና ሥርዓት የተከበረበት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚቆምበት አሠራር እንዲሰፍን ማድረግ ይመስላል፡፡ ይህንን እኛም እንደግፋለን፡፡ ዕውቅና መስጠትም እንፈልጋለን፡፡ እኛም ተጠናክረን ለመንቀሳቀስ የቻልነው በመንግሥት መልካም ፈቃድ ነውና፡፡ መተቸት ያለበትን እየተቸን፣ በመንግሥት እንዝህላልነት የሚደርሱ ጥፋቶችን እያወገዝን፣ መስተካከል ያለበትን እንዲስተካከል ምክረ ሐሳብ እየሰጠን ሪፎርሙ ተቋማዊ ሆኖ ወደ ተግባር እንዲለወጥ  እንሠራለን፡፡ ለውጡ በሰብዓዊ መብት ላይ ትኩረት ያደረገ እንዲሆንና በአገሩ ጉዳይ ሐሳብ ያለው ሁሉ ሐሳቡን እያቀረበ ገዥ የሆነ፣ ሁሉንም  የሚያስማማና በመርህ ላይ የተመሠረተ አሠራር እንዲመጣ የማበረታታትና የመደገፍ ሥራ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብስበው ሲያነጋግሯችሁ ያነሱት ጥያቄና ማኅበረሰቡም በግልጽ እንደሚናገረው፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የራሳቸውን ጥቅም ማግኛና ኑሯቸውን ለማደላደል እንጂ በሌሎች አገሮች እንደሚታየው ያን ያህል ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ተቆርቋሪ ሆነው አይሠሩም ይላሉ፡፡ የእናንተ ምላሽ ምንድነው?

አቶ መስዑድ፡- ክሶች አሉ፡፡ ክሶቹ መሠረተ ቢስ ናቸው ማለት አልችልም፡፡ እውነት ናቸው ማለትም አልችልም፡፡ ሁለቱንም ለማለት ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡ ግን እዚህ አገር የነበረውን የሲቪክ ማኅበረሰብ ታሪክ ለማየት እንኳን ከየት ተነስቶ የት ደረሰ የሚለውን ማወቅም ያስፈልጋል፡፡ መረዳዳት፣ የሰብዓዊ ቀውስ ባጋጠመ ጊዜ ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ሲአርዲኤን ብንወስድ በ1977 ዓ.ም. በወሎ ድርቅ ጊዜ የተቋቋመና አሁን ላይ ተጠናክሮ በአሁኑ ጊዜ ከ400 በላይ አባላት ያሉት ድርጅት ነው፡፡ ይኼ ድርጅት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በተለያዩ የልማትና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ እየሠራ ነው፡፡ አሠራሩ ላይ ሊኮነን የሚችል ነገር ቢኖረው እንኳን ጨርሶ ሊረገም አይገባም፡፡ ሊበረታታ እንጂ፡፡ ግን መጀመርያ በጎ ሥራውንና በጎ ያልሆነ ሥራውን አጥንቶ እንጂ በአየር ላይ የመፈረጅ ነገሮችን መተው አለብን፡፡ ነፍስኄር መስፍን ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) ኢሕአዴግ አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ማግሥት አንስቶ፣ በመላው የአገሪቱ ክፍሎች ከፖለቲካና ፖለቲካ ነክ ግጭቶች ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ ይታወቃሉ፡፡ የራያ፣ የቅማንት፣ በሶማሌና ኦሮሚያ፣ በጉጂና ጌዴሆ፣ በደቡብና በተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየጠቀሱ ሪፖርት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አስቸኳይ  መፍትሔ ካልተሰጠም ወዳልተፈለገ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችልም ሲናገሩ ነበር፡፡ ያ እየተጠናከረ መጥቶ በ1997 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ ላይ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ብዙ ሥራዎች መሥራታቸው ይታወሳል፡፡ ለዚህ ምስክር ከሚሆኑት ውስጥ ዛሬ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ እንቅስቃሴውና ጅምሩ ጥሩ የነበረ ቢሆንም በአዋጅ ጭምር እንዳይቀጥል ተደርጓል፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ሳይሆን ቅንጡና በሐመር መኪና የሚሄዱ፣ የራሳቸውን ሀብት የሚያከማቹ ናቸው እየተባለ በገዥው መንግሥት ሲሰደቡና ሲወገዙ ነበር፡፡ ሰዎች ናቸውና የሚያደርጉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመንግሥት ቤትም ሌባና ዘራፊ አለ፡፡ ግን በጥቅሉ መንግሥት ዘራፊ ነው ልንል አንችልም፡፡ በሁሉም ውስጥ ግለሰቦች ዘርፈው ያላግባብ ለመበልፀግና ለመጠቀም የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ ማኅበራዊ እውነት ነው፡፡ ወደፊትም ቢሆን መቶ በመቶ ይጠፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ግን ሥርዓት እየተበጀለት መልክ እየያዘ ከሄደ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ግን እንደ አጠቃላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በአስተሳሰብ ደረጃ፣ በፖሊሲ ደረጃ፣ በተቋም ደረጃ እንዳይሠሩ ተደርግው እያለ፣ በራሳቸው ጥረት የሠሩትን ሥራ ግን ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ትችትና ዕርግማን ብቻ ከሆነ ግን የሠሩትንም ማሳዘን እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ምኅዳሩ ሰፋ ተደርጋ ከተለቀቀ ገና አንድ ዓመቱ ስለሆነ ለመኮነን ትንሽ ጊዜ ሰጥቶ ማየትም ጥቅም አለው፡፡ ለመፈረጅም ሆነ ለማመስገን አሠራሮችን መመርመር ስለሚያስፈልግ፣ የአሠራር ሥርዓቶችን መዘርጋት አስፈላጊ ነው፡፡ በዜጎች ስም ገንዘብ ሰብስበው ለራሳቸው ጥቅም የሚያውሉ ካሉና ከተደረሰባቸው፣ በወንጀል ጭምር ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር እየዘረጋን ስለሆነ ይስተካከል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ግን ሁሉም መተባበር አለበት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...