Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተቀማጭ ገንዘብን ወደ 100 ቢሊዮን ብር ያሳደጉ የብሔራዊ ባንክ ክንውኖች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ ውሎዋቸው የፋይናንስ ዘርፉ ዕድገት ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች አብልጫ ዕድገት እንደተመዘገበበት አስታውቀው ነበር፡፡ ዘርፉ በጠቅላላው ከአሥር በመቶ በላይ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

ባንኮችም ለመጀመርያ ጊዜ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችለዋል፡፡ ይህም በዘርፉ የተመዘገበ ትልቅ ውጤት ተደርጓል፡፡ የባንክ ደንበኞች ቁጥር ከ31 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱ፣ የባንኮች ቅርንጫፎች ቁጥር በ18 በመቶ ማደጋቸው የፋይናንስ ዘርፉን እንቅስቃሴ ጤናማነት እንደሚያመላክቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በብድር አሰጣጥ ረገድ ሲታይ የግሉ ዘርፍ የተሻለ ተጠቃሚ እንደነበር ተመላክቷል፡፡ በ2012 ዓ.ም. በባንኮች ከተሰጠውም ከተፈቀደውም 270 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 85 በመቶው ለግል ዘርፉ በመዋሉ፣ ዘርፉ ከፍተኛው ተበዳሪ በመሆን ከመንግሥት አብላጫውን ድርሻ እንደያዘ ተጠቅሷል፡፡ መንግሥት እጁን ሰብሰብ ማድረግ እንደጀመረ የሚያሳይ ሲሆን፣ በመንግሥት ብድር ጫና ምክንያት ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ፣ የዋጋ ግሽበትም እንዳይባባስ በቀጥታ ከመበደር ይልቅ ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ተጠቅሞ የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ለውጦችን በማስተናገድ ያለፈው ዓመት ክንውን ብዙ ተብሎለታል፡፡ በተያዘው ዓመትም ተመሳሳይ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ፣ የመጀመርያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም አመላካች እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የሩብ ዓመቱን የፋይናንስ ዘርፉን አፈፃፀምን ብሎም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱ የለውጥ ዕርምጃዎቹ አማካይነት ያከናወናቸውን ሥራዎች አብራርቷል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉን ለማሳደግ በተወሰዱ ዕርምጃዎች የተገኙ ውጤቶች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ በሪፖርቱ የዋጋ ግሽበትን ዝቅተኛ ማድረግ ተግዳሮት እንደሆነበት ገዥው ባንክ ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

የባንኩ የሦስት ወራት አፈጻጸም እንዳሳየው፣ ብሔራዊ ባንክ ከተጣሉበት ኃላፊነቶች መካከል የዋጋ ንረትንና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ማረጋጋት፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ማስጠበቅ፣ ለኢኮኖሚው የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽና አካታች ማድረግ ከሚጠቀሱት ውስጥ ናቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማበራከት እንዲሁም ቁጠባና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስጠበቅ የሚያስችሉ የፖሊሲና የትግበራ ዕርምጃዎችን መውሰድ የባንኩ ሥራዎች ስለመሆናቸው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አመልክተዋል፡፡

የዋጋ ንረትና የባንኩ ዕርምጃ

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ፣ በ2013 መጀመሪያ ሩብ ዓመት ከባንኩ ዕቅድ አኳያ ምን እንደተከናወነ ማብራሪያ ሲሰጡ ቅድሚያ ያደረጉት የዋጋ ንረትን ነበር፡፡ የዋጋ ንረት እንዲረጋጋ ከማድረግ አንፃር ወደ ነጠላ አኃዝ ዝቅ እንዲል ማድረግ የባንኩ ዕቅድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዋጋ ንረት መንስዔ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ የሆነው የገንዘብ አቅርቦትና ሥርጭት ላይ አስፈላጊውን ገደብ በማድረግ ለመንቀሳቀስ ዕቅድ መያዙን የገለጹት ገዥው፣ በበጀት ዓመቱ የመሠረታዊ ገንዘብ አቅርቦት ዓመታዊ ዕድገት ባለፈው ዓመት ካደገበት የ22.8 በመቶ መጠን ዝቅ ተደርጎ ከ12 በመቶ እንዳይበልጥ የታቀደው የዋጋ ንረት መቆጣጠሪያ አንዱ መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ መንግሥት ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ የሚበደረው መጠን ዝቅ እንዲል መታቀዱን ይናገር (ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት የሚበደረው የገንዘብ መጠን ዓምና ከተበደረው 30 ቢሊዮን ብር አኳያ፣ ዘንድሮ ከ16 ቢሊዮን ብር እንዳይበልጥ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ይህም የዋጋ ግሽበት እንዳይጨምር ስለሚያግዝ ነው፡፡

በአንጻሩ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን የሚሸፍንበት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ መጠን እንዲጨምር መታቀዱን ያስታወቁት ገዥው፣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ያስችላሉ ከተባሉ ዕርምጃዎች አንዱ በመሆኑም ጭምር ይህ መንገድ መመረጡን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ዕርምጃዎች በመንግሥት በጀት አቅርቦት በኩል ያሉትን ማነቆዎች መፍታት እንዲያስችሉ በጥብቅ የበጀት ፖሊሲ መታገዝ እንዳለባቸው ይናገር (ዶ/ር) ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በይናገር (ዶ/ር) ማብራሪያ መሠረት፣ ባለፉት ሦስት ወራት መንግሥት የበጀት ጉድለቱን በግምጃ ቤት ሽያጭ በመሸፈኑ ምክንያት ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይወስድ አስችሎታል፡፡ በሒደቱም ከባንኮችና ከሌሎች ተቋማት 33.46 ቢሊዮን ብር በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አማካይነት መሰብሰብ ተችሏል፡፡

የውጭ ምንዛሪና የመጠባበቂያ ክምችት

ብሔራዊ ባንክ የሚከተለው የውጭ ምንዛሪ ተመን ፖሊሲ ዋና ዓላማው፣ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስፈን፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ የንግድ ሚዛንን ማሻሻልና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማበረታታት በመሆኑ፣ ይኸው ግብ ተቀምጦ እየተሠራበት ይገኛል ተብሏል፡፡ በመሆኑም ባንኩ የአገሪቱን የዕድገት ደረጃ ያገናዘበ ከፊል አስተዳደራዊና ከፊል ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ፖሊሲ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝና፣ በተያዘው ዓመትም ተጨባጭ የውጭ ምንዛሪ ተመንን (Real Effective Exchnage Rate) በመከተል የአገሪቱን የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን መሠረት ባደረገ መልኩ እንደሚተገበር፣ በሒደት ግን ይህ እየቀነሰ ገበያ መር ሆኖ እንዲጓዝ መታሰቡን ባንኩ አስታውቋል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ ስትራቴጂካዊ ግቦች አንዱ በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መያዝና ማስተዳደር ነው፡፡ ይህንን ግብ ለማሳካት የአገሪቱን የክፍያ ሚዛን ብሎም የራሱንና የንግድ ባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ፍሰት የተመለከቱ ትንበያዎች በመሥራት አፈጻጸሙን  በመገምገም ላይ እንደሚገኝ ባንኩ ገልጿል፡፡

በመጀመርያዎቹ ሦስት ወራት የባንኩ መጠባበቂያ ክምችት እ.ኤ.አ. መስከረም 30 ቀን 2020 ላይ 3.1 ቢሊዮን ዶላር አስመዝግቧል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአሥር በመቶ ጭማሪ እንደታየበት ይናገር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ወጪና ገቢ ንግድ

ባለፉት ሦስት ወራት ውጤታማ ከተባሉ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎች መካከል የወጪ ንግድ ዕድገትና የገቢ ንግድ መቀነስ ይጠቀሳል፡፡ በሦስት ወራት ውስጥ ከሸቀጦች ወጪ ንግድ 832 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ይናገር (ዶ/ር) ገልጸው፣ ዕድገቱ በቀላሉ እንዳልተገኘ፣ የወጪ ንግድ ዘርፉ ባለፉት አምስት ዓመታት እያሽቆለቆለ እንደነበር አስታውሰው፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ15 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከአምስት ዓመታት ማሽቆልቆል በኋላ የተመዘገበ ለውጥ ነው፡፡ የሸቀጦች ወጪ ንግድ ዕድገት እየጨመረ እንደሚሄድ በመታመኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ተስፋ የሚጣልበት ዕድገት እንደሚኖረው አመላካች ተደርጓል፡፡

በሦስት ወራት ውስጥ ከተገኘው ገቢ ውስጥ የወርቅ ሚና ትልቅ እንደነበር ያመለከቱት ገዥው፣ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን አመልክተዋል፡፡ ከወርቅ የተገኘው ገቢ ከፍተኛ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ብሔራዊ ባንክ በ2011 ዓ.ም. የወሰደው ዕርምጃ አንዱ ነው፡፡ ወርቅ ለሚያቀርቡ አምራቾችና ነጋዴዎች ከዓለም አቀፍ ዋጋው ብልጫ ያለው ክፍያ እንዲያገኙ በማድረጉ ነው፡፡ በተመሳሳይ ወቅት አገሪቱ ለገቢ ሸቀጦች 3.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያደረገች ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ7.1 በመቶ ቅናሽ የታየበት ነበር፡፡

በወጪና ገቢ ንግድ መካከል በሦስት ወራት ውስጥ የተመዘገበው የንግድ ሚዛን ጉድለት፣ ዘንድሮ ወደ 2.6 ቢሊዮን ዝቅ ብለዋል፡፡ ዓምና የሦስት ቢሊዮን ዶላር ጉድለት ተመዝግቦ ነበር፡፡

የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ለማሻሻል አስመጪ ድርጅቶች የተፈቀደላቸውን የውጭ ምንዛሪ ለተፈቀደለት ዓላማ ስለማዋላቸው፣ ገንዘቡ እንዲገዙበት ወጪ የተደረገላቸው ዕቃዎች ስለማስመጣታቸው፣ ላኪዎችም ያገኙትን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ወደ አገር ውስጥ ስለማስገባታቸው ክትትል መደረጉ፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ መጨመር አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል፡፡ ግዴታቸውን በወቅቱ ላላወራረዱ አስመጪና ላኪ ድርጅቶችና ግለሰቦች የውጭ ምንዛሪ እንዳይሰጣቸው ስም ዝርዝራቸው በየወሩ ለንግድ ባንኮች እየተላከ የማሳወቅ ሥራ መሠራቱም የውጭ ምንዛሪ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ያስገኘው ለውጥ እንዳለ ማሳያ ተደርጓል፡፡

በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት አኳያ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን ለማረጋጋትና የውጭ ሐዋላ ወደ አገር ውስጥ ያለውን ፍሰት ለማሻሻል የሚረዱ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ባንኩ አስታውቋል፡፡ በጠቅላላው የአሠራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ከተደረጉ ማሻሻያዎች መካከል በወጪ ንግድና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሠማሩ ድርጅቶች የሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሪና የአገር ውስጥ ብድር ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ማግኘት የሚችሉበት መንገድ እንዲመቻች ማድረግ አንዱ ነበር፡፡ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ከውጭ አገር መድኃኒቶችን፣ የአፍ መሸፈኛና ሌሎች ግብዓቶችን ለሚያስመጡ ድርጅቶች፣ ለውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ እንዲሰጣቸቸው መደረጉን ያብራሩት ይናገር (ዶ/ር)፣ የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ የቁጥጥር ሥራዎች በተለያዩ መንገዶች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ያህልም የቡና ላኪዎች የሽያጭ ውል ሲያስመዘግቡ ከዝቅተኛ ዋጋ በታች እንዳይሸጡ፣ ከቡናና ሻይ ባለሥልጣንና ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት መሥራቱ ተጠቃሽ ነው፡፡

500 በመቶ ያደገው ቁጠባ

በ2013 የመጀመርያ ሩብ ዓመት በባንኮች ታሪክ ያልተመዘገበ ክስተት ቢኖር፣ ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ባወጣው ሪፖርት፣ ባንኮች 105.1 ቢሊዮን ብር አዲስ ቁጠባ ሰብስበዋል፡፡ ይህ በ2012 የመጀመርያው ሩብ ዓመት ጋር ከነበረው የ17.5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ቁጠባ አኳያ፣ የ500.6 በመቶ ዕድገት የታየበት ነበር፡፡ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ በዚህ ደረጃ ዕድገት ለማሳየቱ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው ዕርምጃዎችና ማሻሻያዎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡

ይህን ያህል መጠን የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት መታየቱ፣ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች በየዕለቱ ወጪ የሚደረገው መጠን ላይ ገደብ መጣሉና ከባንክ ውጭ መያዝ የሚቻለው ጥሬ ገንዘብ መገደቡ ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርቡ የተለወጠው የገንዘብ ኖትም ለባንኮች ቁጠባ ማደግ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አመልክተዋል፡፡

የግል ዘርፉ ከፍተኛ ተበዳሪ የሆነበት ጊዜ

በተሸኘው ዓመት ከጠቅላላው የባንኮች ብድር ውስጥ ለግል ዘርፉ የተሰጠው 85 በመቶውን እንደሚሸፍን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ገልጸው ነበር፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ በሰጡት መግለጫም በሦስት ወራት ውስጥ ከተሰጠው ብድር ላይ አሁንም የግሉ ዘርፍ 85 በመቶውን እንደወሰደ አረጋግጠዋል፡፡

ባንኮች 55 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር አቅርበዋል፡፡ ይህ መጠን ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ የ14.7 በመቶ ዕድገት አለው፡፡ ከዚህ ውስጥ 85.3 በመቶውን የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ አግኝቷል ማለት ነው፡፡ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራሙ መሠረት፣ የግሉን ዘርፍ የብድር ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰበውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል ጅምር እንደሆነ ይናገር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡  

በሌላ በኩል ባለፉት ሦስት ወራት ባንኮች የሰበሰቡት ተመላሽ ብድር የ14.9 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ 35 ቢሊዮን ብር ሰብስበዋል፡፡ በተመላሽ ብድር ላይ ከፍተኛ ቅናሽ የታየው በኢንዱስትሪ፣ በሆቴል፣ በቱሪዝም፣ በቤቶችና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ ነው፡፡ የኮሮና ተፅዕኖ ያመጣው ሊሆን እንደሚችል በመገመቱ፣ ከባንኮችና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በመነጋገር የተመላሽ ብድር መጠን የሚሻሻልበት መንገድ ይፈጠራል ተብሏል፡፡

የጥሬ ገንዘብ እጥረት

ባንኮች በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ላይ ያጋጠማቸውን እጥረት ለመፍታት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ልማት ባንክ የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነት የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የመገምገም ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በተለይ ከመስከረም መጨረሻ እስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት አጋጥሟቸው ስለነበር፣ ብሔራዊ ባንክ በወሰደው ወቅታዊ ዕርምጃ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ መሻሻሎች እንደታዩ ተጠቅሷል፡፡ አሁን ላይ ግን ባንኮች በሕግ ከሚጠበቅባቸው አነስተኛ መልህቅ (Minimum Liquidity Requirement) በእጅጉ የላቀ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም ከቅርብ ወራት ወዲህ እያሰባሰቡ ያለው የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ባንኮችን ከገጠማቸው የጥሬ ገንዘብ እጥረት አላቋቸዋል፡፡

የተበዳሪ መረጃና ብድር ቁጥጥር

አንድ የባንክ ደንበኛ ከስንት ባንኮች ብድር እንደወሰደ የሚያሳውቅ የተጠናቀረ መረጃ ማግኘት ከባድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከባንክና ከአነስተኛ ገንዘብ ተቋማት ብድር የሚወስዱና የወሰዱ ተበዳሪዎች መረጃ ወደ ገዥው ባንክ እንዲገባ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህንን መረጃ በተለይ ባንኮች እንዲያገኙት ተደርጓል ያሉት ይናገር (ዶ/ር)፣ ከተሰናዳው የመረጃ ቋት ተበዳሪው ከስንት ባንኮች ብድር እንዳለበት፣ ጥሩ ብድር ከፋይ ስለመሆን አለመሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች ለባንኮች በቀላሉ ይደርሳቸዋል፡፡ ይህም ብድር ለመስጠትም ሆነ ለመከልከል ያግዛቸዋል ተብሏል፡፡  

ብሔራዊ ባንክ ከሚያከናውናቸው የሪፎርም ሥራዎች ውስጥ ባለፉት ሁለት ወራት ከ47 በላይ መመርያዎችን ማሻሻሉና አዳዲሶችን ማውጣቱም በገዥው ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ ባንኮች ጤናማነታቸውንና የውጭ ዕዳ ክምችት መጠንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከሦስተኛ አካል በውጭ ምንዛሪ ብድር እንዲበደሩና የተበደሩትን ገንዘብ የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኙ የሥራ ዘርፎች ላይ ለተሠማሩ ተቋማት በውጭ ምንዛሪ እንዲያበድሩ የሚያስችል መመርያ ተግባራዊ መደረጉ አንዱ ማሻሻያ ነው፡፡

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የክፍያ መፈጸሚያ መሣሪያን የሚመለከት መመርያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣ ሲሆን፣ ሌሎቹ የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሙበት የወኪል፣ የባንክና የክፍያ አገልግሎት መመርያም ተሻሽሏል፡፡

የመድን ኦፕሬተሮችን ፈቃድ ለመስጠትና የተከፈሉ የመስኮት አገልግሎት ለሚሰጡ ኩባንያዎች ማረጋገጫ የሚሰጥበት ሁኔታ የሚደነግግ መመርያ፣ የመድን ፈቃድ ኢንቨስት የሚደረግበት ሁኔታ የሚደነግግ መመርያ፣ የአነስተኛ መድን ሥራ ፈቃድ የሚሰጥበት፣ ፈቃድ የሚታደስበት የጠለፋ ዋስትና የሚካሄድበት መንገድና መሥፈርት የሚመለከት መመርያ፣ ለጠለፋ መድን ሰጪዎች ፕሩደንሺያል መመርያ የወጣ ሲሆን በርካታ የሱፐርቪዥን ሥራዎችም መሠራታቸውና ሌሎችም ማሻሻያዎች ተጠቅሰዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ማሻሻያ

የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን በተመለከተ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ላይ ማብራሪያ የሰጡት ይናገር ደሴ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ሰፊ ከመሆኑ አንፃር ለየትኛው ቅድሚያ ይሰጥ የሚለውን በማየትና ጥናት በማድረግ በቅደም ተከተል ወጥቶላቸው በዚሁ መሠረት የውጭ ምንዛሪ እየፈቀዱ የተሻሻለ መመርያ ሥራ ላይ ውሏል፡፡

በዚህ መመርያ መሠረት የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ የሚሰጠው መድኃኒት መሆኑን ነው፡፡ ባንኮቹ ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ አሥር በመቶ ድረስ ለመድኃኒት እንዲሰጥ የሚያስገድድ መመርያ መሆኑም በሁለተኛ ደረጃ ቅድሚያ እንዲሰጠው የተደረገው የግብርና ሥራን ለማዘመንና ለማሳደግ ለግብርናና ማኑፋክቸሪንግ በአንድ ላይ ሆነው የውጭ ምንዛሪ የሚሰጣቸው በሁለተኛ ረድፍ ተቀምጧል፡፡

በዚህ መሠረት ለግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የግል ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 45 በመቶ የሚሆነውን እንዲሰጡ በአስገዳጅነት ተቀምጧል፡፡ ሌሎቹም እያደራጃቸው ተቀምጠዋል፡፡ ይህማለት የውጭ ምንዛሪን ለማይረባ ነገር ባንኮች እንዳያውሉት የሚገድብ መመርያ መሆኑንም ይናገር አስርድተዋል፡፡

የወደፊቶቹ አዳዲስ መመርያዎች

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የውጭ ድርጅቶች የሚሠሩና በውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲከፍቱ የሚያስችል መመርያ በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚሆንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡

ይህ መመርያ በውጭ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ የውጭ ዜጎችም  በዚሁ መመርያ መሠረት በውጭ ምንዛሪ አካውንት ከፍተው እንዲያንቀሳቅሱ የሚያስችልም ነው፡፡

እነዚህ በውጭ ድርጅት የሚሠሩ ዜጎች ብዙዎቹ ገንዘባቸውን የሚያስቀምጡት እንደ ኬንያ ባሉ አገሮችና በሌሎች አገሮች በመሆኑ ይህንን ተቀማጭ ገንዘብ እዚሁ እንዲያደርጉ ለማስቻል ረቂቅ መመርያው መዘጋጀቱንም አመልክተዋል፡፡

እነዚህ የውጭ ዜጎች ገንዘባቸውን በውጭ ባንኮች ለማስቀመጥ የሚደዱበት  የተለያዩ ምክንያቶች እንደነበሩ የገለጹት ገዥው ዶላሩን በምንፈልገው ጊዜ አናገኝም  የሚለው ጥርጣሬ አንዱ እንደነበር እነርሱን በማነጋገር መረዳታቸውን አመልክተዋል፡፡ ሒሳቡን እንዳናንቀሳቅስ ገደብ ስላለብን እዚህ ማስቀመጥ ያለመቻላቸውን የጠቀሱ ጭምር ስለነበሩ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን የሚቀርፍ መመርያ እንድናዘጋጅ ተደርጓል፡፡

ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ከተማ ሆና ብዙዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው የሚከፈላቸውን የውጭ ምንዛሪ ሌላ አገር መስቀመጥ ስለሌለባቸው ይህንን ለማስቀረት የሚረዳው መመርያ በቅርቡ ይፀድቃል ተብሏል፡፡

የገንዘብ አስቀማጮች የመድን ፈንድ ለማቋቋም የሚያስችል ሕገ ደንብ ተዘጋጅቶና በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስተያየት ተሰጥቶበት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረሰ ሲሆን በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ሲፀድቅ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ከዚህም ሌላ የፋይናንስ ተጠቃሚዎች ጥበቃ ሥርዓትን በተጠናከረ ሁኔታ ለመተግበር የሚያስችል መመርያ ፀድቆ በሥራ ላይ የዋለ ሲሆን የፋይናንስ ተጠቃሚዎችን ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ የሚረዳ ብሔራዊ የፋይናንስ ዕውቀትና ክህሎት ስትራቴጂ ፀድቆ ሥራውን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ይኸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞናዊ መረጃ አመልክቷል፡፡

በሰሞኑ የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት በሩብ ዓመቱ ወሳኝ ሥራዎች ከተባሉት ውስጥ አንዱ የብር ኖት ቅያሪ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2013 ድረስ ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር በላይ አዲሱ የብር ኖት የተሠራጨ ሲሆን እስከ ተጠቀሰው ጊዜ ድረስ 1.2 አዲስ ቆጣቢዎችን ማፍራት ተችሏል፡፡ በእነዚህ አዲስ ቆጣቢዎችና በነባሮቹ የቁጠባ ሒሳቦች ወደ 37  ቢሊዮን ብር ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲገባ አስችሏል፡፡ በጥቅል ሲታይ የፋይናንስ ዘርፍ እንቅስቃሴ ውጤታማ የሆነበት ወቅት ስለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ዘርፉ ያሳየው ዕድገት በተለየ የሚታይ መሆኑን ማመልከታቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች