Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአውቶቡሶቹ ነገር እንዳያነጋግር!

አዲስ አበባ ከተማ ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል ሁነኛ መፍትሔ ማግኘት ያልቻለውና ዘመናትን የዘለቀው የትራንስፖርት አገልግሎት አበሳ ነው፡፡

መዲናችን የትራንስፖርት እጥረትና ይህንኑ ተከትሎ እየተፈጠረ ያለው የመንገድ ላይ የሕዝብ ትርምስ አጃኢብ ያሰኛል፡፡ በየጊዜው ሮሮ የሚደመጥበት ጉዳይ የትዬ ለሌ ነው፡፡ አንዱ ችግር ሳይፈታ ሌላው እየተደረበ ውሎ ሲያድር ይዞት የሚመጣው መዘዝ ከባድ እንደሚሆን ቢታወቅም፣ የትራንስፖርት ችግር ግን ሊቀረፍ የማይችል ሰንኮፍ መስሏል፡፡ መንግሥት መፍትሔ አስቀመጥሁ ቢልም ጠብ የሚል ለውጥ ማየት አልተቻለም፡፡ የተወሰዱ ዕርምጃዎች በአመዛኙ ጊዜያዊ ወይም እሳት የማጥፋት አዝማሚያ ስለሚታይባቸው ሥር ነቀል እፎይታ አላስገኙም፡፡

ስለ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግር እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጡ አኳያ የሚሰሙና የሚታዩት ችግሮች ሥር የሰደዱ፤ የቆዩ ናቸው፡፡ ለዓመታት የዘለቀውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት የተወሰዱ ዕርምጃዎች ያለውን ፍላጎቱንና መሻቱን ሊሞሉ አልቻሉም፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችና የተጠቃሚዎችን ቁጥር ያገናዘበ አገልግሎት ሊቀርብ አልቻለም፡፡ ከሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ እስከ ባቡር ያሉ በርካታ ለውጦች ቢታከሉበትም፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግር ግን ሊፈታ አልቻለም፡፡ የነዋሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን ተገንዝቦ፣ ከየክልሉ ወደ ከተማዋ የሚገባውንና የሚወጣውን የሕዝብ ቁጥር መዝኖ፣ የትራንስፖርት ፍላጎቱን ከአቅርቦትና ስምሪት ጋር በአግባቡ አመጣጥኖ የሚያስኬድ የተመጣጠነ አሠራር አልሰፈነም፡፡ የትራንስፖርቱ ዘርፍ በዘፈቀደ የሚነዳ፣ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው እንዳሻው፣ ባመቸው ጊዜና ሰዓት የሚሠራበት የእንደልቤ ዘርፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ በመሆኑም ያለመታከት ሁሌም ስለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግር እያወራንና እያማረርን እንድንቀጥል አስገድዶናል፡፡

 የከተማዋን የትራንስፖርት ችግሮች ለመፍታት የኤሌክትሪክ ባቡርን ጨምሮ፣  እንደ አንበሳና ሸገር ያሉ የብዙኃን ትራንስፖርት አቅራቢ ተቋማት ብዙ ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ ሆኖም ስምሪታቸው፣ አቅርቦታቸውና በየተሰጣቸው መስመር በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መንቀሳቀሳቸውን የሚጠቁም የአሠራር ሥርዓት ሲተገበር የሚታይ አይመስልም፡፡ ይህ ተደማምሮ በተቋማቱ ላይ በየዕለቱ የሚጎላውን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ነዋሪው ጠዋትና ማታ ለብርድና ለፀሐይ፣ ለዶፍ ዝናብና ለጎርፍ እየተዳረገ ትራንስፖርት መጠበቅ መፍትሔ የሌለው ግዳጅ ሆኖበታል፡፡

ጠዋት ሥራ ገበታቸው ላይ ለመገኘት በርካቶች፣ ወፍ ሳይጮህ ማልደው ከቤታቸው ይወጣሉ፡፡ የንጋት ጀንበር ሳታዘቀዝቅ ረዣዥም ሽንጣም ሠልፎችን ማየት የአዲስ አበቤዎች የዕለት ተግባር ነው፡፡ አሰልቺውን ወረፋ ጠብቀው በሥራ ገበታ ላይ ለመገኘት እየወሰደባቸው ያለው ጊዜ ሲሠላ፣ ከሥራ መለስ ወደ ቤት ለመሄድ የሚያዩት እንግልት፣ በየመንገዱ ተሰልፈው የሚያጠፉት ጊዜ፣ የሚያባክኑት ጉልበትና ገንዘብ አንገብጋቢና እጅጉን አክሳሪ ነው፡፡

ጉልበቱ ዝሎ ቢሮ የሚደርሰው ሠራተኛ ምን ያህል ምርታማ ሆኖ እንደሚሠራ ማሰብ ነው፡፡ ሥራውን መጨርሶ ቤቱ ለመድረስ አቀበት እንደመቧጠጥ ለራቀበት ከርታታ እንዴት ያለ ውጤታማ ሥራ ሊሠራ እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ይህ ለአገር ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ለዚህ ነው የትራንስፖርት እጥረት ከዚሁ ጋር የተያያዙ ብልሹ የአገልግሎት አሰጣጦች ውጤታማነት እንዲያሽቆለቁል የሚያደርጉት፡፡

የከተማዋ የትራንስፖርት ችግር እንዲፈታ፣ ነገን ያሰበ መፍትሔ መፈለግ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ሲባል፣ ታሳቢ የሚደረገው ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ከጥቃቅኑ ጀምሮ ላለው ጉዳይ ትኩረት በመስጠት መሆን መቻል አለበት፡፡

የትራንስፖርት ዘርፍ በርካታ ውስብስብ  ችግር አለበት፡፡ ተዋናዩም ብዙ እንደመሆኑ፣ ተለዋዋጭና ዘመን አመጣጭ ችግሮችም አብረውት እየታዩ በመሆኑ፣ በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን በማሰማራት ብቻ እንደማይፈታ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የትራንስፖርት ዘርፍ ችግሮች በልማዳዊ አሠራር አይፈቱም፡፡ ሎጂስቲክስና ትራንስፖርን የሚመራቸው ሳይንሳዊ ቀመርና ስሌት ነው፡፡ ይህንን በአግባቡ የሚገነዘብ አመራር ችግሩን ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደተቃረበ ይቆጠራል፡፡

የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ መቀየር፣ ከመንገድና ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተቋማት ማደስ፣ ጨዋ አገልጋዮችን መፍጠርንና ሌሎች ጉዳዮችንም ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ሌብነት የበዛበት፣ ከዘመናዊ አሠራሮች ርቆ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ዘርፉ መጠነ ሰፊ ተሃድሶ ያስፈልገዋል፡፡ የዘርፉን ችግር አጉልቶ ማሳየት ተገቢ የሆነበት ምክንያት ከሌላው ጊዜ በተለየ የትራንስፖርት ተገልጋዮች እየጨመሩ ስለመምጣታቸውና ችግሩ ሥር ስለመስደዱ የሚያሳዩ ሠልፎች ጎልተው በመታየታቸው ነው፡፡

ከመጪው ሳምንት ጀምሮ የትራንስፖርት እጥረቱን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል የሚጠበቀው የትምህርት መጀመር ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን አስቦ ይመስላል የሸገር አውቶቡስ አገልግሎትን ለማገዝ በሚል፣ 427 አውቶብሶችን በኪራይ ወደ ሥራ እንዳስገባ አስታውቋል፡፡ እነዚህ አውቶብሶች በከተማው ውስጥ እንዲሠሩ ማድረጉ ችግሩን ለመቅረፍ መልካም ጅምር ቢሆንም፣ ዕርምጃው ግን እንደተለመደው የእሳት ማጥፋት ሙከራ ነው እንጂ ብዙ ለውጥ ያመጣል ለማለት ይከብዳል፡፡

በአገር አቋራጭ የትራንስፖርት ላይ የቆዩ አውቶብሶች እንደተባለው በተሰጣቸው ሥምሪት መሠረት ከሠሩ፣ መጠነኛ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አሠራሩ ላይ  ጥያቄዎች እንዳነሳበት ያስገድደኛል፡፡

አውቶብሶቹ በዚህ አግባብ ቢሠሩ ችግሩን ለማቃለል እንደሚችሉ ምን ያህል ተጠንቷል? በአገር አቋራጭነት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ እንደመሆናቸው፣ እነዚህ አውቶቡሶች ይሰጡ የነበረውን አገልግሎት በማን ሊሸፍነው ነው? እዚህ ቀዳዳ ለመድፈን ሲሞክር ሌላ ቦታ ሌላ ቀዳዳ መክፈት አይሆንም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሲንሰራፉ የትራፊክ እንቅስቃሴውን እንዴት ይሆናል ብሎ መጠየቅም ክፋት የለውም፡፡

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር ነገን ባለመ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆን አሠራር ካልተበጀ ችግሩ መዝለቁ አይቀርም፡፡ አንዳንዴ ባለው ትራንስፖርት ተሽከርካሪ በአግባቡ በዚሁ ጉዳይ ነገም እንድናወራ ማኔጅ ማድረግም መፍትሔ ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የግል ዘርፉን ማሳተፍ የግድ ይላል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አማራጭ የሚባሉ አሠራሮችን መቅረፅ፣ በጉቦና በሌብነት የተተበተቡ ከዘርፉ ጋር የተያያዙ ተቋማትን ማፅዳት፣ ለአገርና ለሕዝብ የሚተጉ ባለሙያዎችን በማሰማራት ዘርፉን የሚመሩ ተቋማትን ሁሉ ማደስ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ መፍትሔው ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን ባለውም አቅም ቢሆን ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ አሠራሩን ማዘመን ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት