Sunday, June 23, 2024

ሉዓላዊነት የሚከበረው ከብረት የጠነከረ አንድነት ሲኖር ብቻ ነው!

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሰነዘረው ዕውቀት አልባና ኃላፊነት የጎደለው ንግግር፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ አፍሪካውያን ጭምር የሚቃወሙት ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የዓባይን ውኃ ፍትሐዊ ክፍፍልም ሆነ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ መነጋገር ያለባቸው የማንንም ጣልቃ ገብነት ሳይፈቅዱ መሆን አለበት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግብፅ የአካባቢው ኃያል አገር ሆኖ የመገኘት የረዥም ጊዜ ፍላጎቷን ለማሳካት ስትል ብቻ፣ በተለይ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ የውጭ ጣልቃ ገብነትን እየጋበዘች ነው፡፡ አፍሪካውያን ወንድማማች ሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ከመድረስ ይልቅ፣ የዓባይን ውኃ የመቆጣጠርና በአካባቢው የመግነን ዓላማዋን ለማሳካት ስትል ችግር ፈጣሪ ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ከምታስከብርባቸው መስኮች መካከል አንዱ፣ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ እንደማትፈልግ በተግባር ማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ራስን ለመከላከል ብቁ ሆኖ ከመገኘት በተጨማሪ፣ በዲፕሎማሲው መስክ ጠንካራ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያንም ውስጣዊ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በማለት ብሔራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ መስማማት ይኖርባቸዋል፡፡ ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከብረት የጠነከረ አንድነት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የግላቸውም ሆነ የመንግሥታቸው አቋም ምንም ይሁን ምን፣ ኢትዮጵያዊያን ምንጊዜም ቢሆን በአገራቸው ሉዓላዊነት ላይ መደራደር የለባቸውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በተለይ በዲፕሎማሲው መስክ የሚታይበትን እግር የመጎተት ድክመት ማስወገድ ይገባዋል፡፡ የግብፅ መንግሥታት በታሪካቸው የሚታወቁት የዓባይን ውኃ ለውስጥ ፖለቲካ ውጥረታቸው ማስተንፈሻ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ እግር በእግር እየተከታተሉ የኢትዮጵያን እያንዳንዱን ዕርምጃ በማደናቀፍ ነው፡፡ ግብፅ ከዓባይ ውኃ ከመጠን በላይ የሆነ ውኃ ስለምታገኝ የውኃ እጥረት የለባትም፡፡ ለበርካታ ዓመታት የሚበቃ የከርሰ ምድር ውኃ አላት፡፡ ቢቸግራት እንኳ የሜዲትራኒያን ባህርን ውኃ አጣርታ መጠቀም ትችላለች፡፡ ከአንድም ሦስት ትልልቅ የውኃ ግድቦች አሉዋት፡፡ ነገር ግን ከሌሎች የዓረብ አገሮች ጋር የምታከናውናቸው ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ስላሉዋት፣ የዓባይን ውኃ ከምንጩ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፍላጎት አላት፡፡ በዚህም ምክንያት የአካባቢው አለቃ በመሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰሱን አገሮች ማስገበር ትፈልጋለች፡፡ ለዚህ ፍላጎቷ ስኬት የማትፈነቅለው ድንጋይ ስለሌለ፣ በዶናልድ ትራምፕ አማካይነት የሥነ ልቦና ጦርነት ከፍታለች፡፡ ለዓባይ ውኃ 86 በመቶ የምታበረክተው ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ የሚያመነጭ ግድብ ስትገነባ፣ በዓባይ ውኃ እንደፈለገች የምትጠቀመው ግብፅ ግን ጠላት ሆና ተነስታለች፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ ባትፈልግም፣ አሜሪካን የምታህል ልዕለ ኃያል አገር የሚመሩ ኃላፊነት የማይሰማቸው ትራምፕ ያስተላለፉት መልዕክት በዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከፉከራውና ከቀረርቶው ቀነስ በማድረግ መንግሥት የአገሪቱን ሉዓላዊነት በሚገባ እንዲያስከብር ማገዝ አለባቸው፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ የሚታዩ ክፍተቶችን በመድፈን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆም የሚችልባቸውን ማናቸውም ዘዴዎች ማመላከት ያስፈልጋል፡፡ አሜሪካውያን ፕሬዚዳንታቸው የፈጸሙትን አሳፋሪ ድርጊት በግልጽ እንዲረዱትና እንዲያወግዙት፣ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የተጀመረው የሦስቱ አገሮች ውይይት በሰከነ መንገድ እንዲከናወን ጫና መፍጠር ይገባል፡፡ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የተቀናጀና ወጥ የሆነ ዘመቻ በመጀመር፣ የኢትዮጵያን ድምፅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተደማጭ ማድረግ የግድ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ እውነትን ይዛ በግብፅ ሸፍጠኛ ፖለቲካ መበለጥ የለባትም፡፡ በተለይ የአገር ሉዓላዊነትና የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ የተምታታባችሁ ፖለቲከኞች ከአደገኛ ድርጊቶቻችሁ ተቆጠቡ፡፡ ያልበሰለ የፖለቲካ ቁማር ውስጥ ገብታችሁ አገርን ለጠላት አታጋልጡ፡፡ በሌላ በኩል የአገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ወገኖች በሙሉ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋዕትነት መክፈል ይጠበቅባችኋል፡፡ ኢትዮጵያ የገዛ የተፈጥሮ ሀብቷን በፍትሐዊ መንገድ የመጠቀም መብቷን የሚጋፋ ባላጋራ ሲከሰት ማንቀላፋት አይገባም፡፡

ኢትዮጵያውያን መቼም ሆነ የትም በአገራቸው ሉዓላዊነት ላይ ተደራድረው አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚለያዩባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሯቸው እንኳ፣ በአገር ሉዓላዊነት ላይ ግን መቼም ቢሆን የተለያዩ አቋሞችን አያራምዱም፡፡ የውስጥ ጉዳያቸው ተካሮ ወደ ግጭት ቢያመራም፣ የአገር ሉዓላዊነትን የሚደፍር የውጭ ጠላት ሲነሳ ግን በአንድነት ለመቆም ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡ በታሪክ የሚታወቁትም ለአገራቸው ባላቸው ወሰን የሌለው ጥልቅ ፍቅር ነው፡፡ በጊዜያዊ ጠብ ሲኮራረፉ እንኳ ወሳኙ ጊዜ ሲመጣ ስምምነት ፈጥረው አንድ ላይ እንደሚቆሙ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በአገር ሉዓላዊነት ቀልድ የለም ሲሉ መልዕክቱ ግልጽ ነው፡፡ ለእነሱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ማለት ብሔራዊ ጥቅም፣ ደኅንነት፣ ነፃነት፣ መብትና ክብር ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ማንም ጣልቃ መግባትም ሆነ መወሰን አይችልም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከታላቁ የዓድዋ የጀግንነት ድል ታሪክ የቀሰሙት፣ ሉዓላዊነትን በአንድነት ቆሞ ማስከበር ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን በዓድዋ ድል ክብረ በዓል ላይ በኢትዮጵያዊያን የሚተላለፉ መልዕክቶች በግልጽ የሚያመላክቱት፣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ፈፅሞ መደራደር እንደማይቻል ነው፡፡ በተለይ ሰሞኑን የዶናልድ ትራምፕ ታላቁን የህዳሴ ግድብ አስመልክቶ ሉዓላዊነትን የሚጋፋ አሳፋሪ ንግግር፣ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ቁጣ የቀሰቀሰ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች በአንድነት እንዳሠለፈ ይታመናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ ጉልበታቸውና ገንዘባቸው ያለ ማንም አጋዥ በሚገነቡት ታላቁ የህዳሴ ብሔራዊ ፕሮጀክታቸው ላይ የተቃጣው ጣልቃ ገብነት፣ መቼም ቢሆን የማይታገሱትና የማይደራደሩበት እንደሆነ በግልጽ አቋማቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በሉዓላዊነት ቀልድ የለምና፡፡

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በተደረገው ድርድር ከዚህ ቀደም አሜሪካ ጣልቃ በመግባት ለግብፅ ያደረገችው አሳፋሪ ድጋፍ መና መቅረት የሚችለው፣ አሁንም ኢትዮጵያውያን የውስጥ ሽኩቻቸውን አቁመውና ተጠናክረው አንድነታቸውን በተግባር ሲያሳዩ ብቻ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ ለማንኛውም ጉዳይ የሚደረገው ፉክክርም ሆነ ትንቅንቅ፣ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ህልውና በታች መሆን አለበት፡፡ በዚህ ወሳኝና ታሪካዊ ወቅት የዓድዋ ጀግኖችን አርዓያነት በመከተል፣ በፍፁም ጨዋነትና ትዕግሥት ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የጋራ ፕሮጀክትና የአንድነት ተምሳሌት ስለሆነ፣ ይህ የጋራ ፕሮጀክት የውጭ ኃይሎች አደጋ ሲደቀንበት ማፈግፈግ አይታሰብም፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ የሚበግራቸው እንደሌለ ስለሚታወቅ፣ በመከፋፈል ለጠላት ዒላማ ተጋላጭ መሆን አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ ለዓባይ ተፋሰስ 86 በመቶ የውኃ ሀብት እያበረከተች፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ በመገዛት ማንንም ለመጉዳት እንደማትፈልግ በተደጋጋሚ ቃል ገብታለች፡፡ እግረ መንገዷንም ከዚህ የውኃ ሀብቷ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለመጠቀም ግድብ ስትገነባ ግን፣ በተለይ ከግብፅ በኩል በተደጋጋሚ የሚፈጸምባት በደል ከሚታገሡት በላይ ነው፡፡ እዚህ ድርድር ውስጥ የተገባው ከፍተኛ ትዕግሥት በመላበስ ጭምር ስለሆነ፣ በታዛቢነት ስም ገብታ እንደለመደችው የሸፍጥ ድርጊት ውስጥ በገባችው አሜሪካ ሌላ ተጨማሪ በደል ሲፈጸምባት ኢትዮጵያውያን አይታገሡም፡፡ግብፅም ሆነአሜሪካ አመራሮች ከዚህ ድርጊታችሁ ታቀቡ መባል አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን የማንንም ጣልቃ ገብነት የማይፈልጉና ክብር ያላቸው መሆናቸውን ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ኢትዮጵያ በግብፅ የደረሰባት የዘመኑ ፈተና ብቻ ሳይሆን፣ ከግንባታው በፊት በነበሩ የተለያዩ መንግሥታት ወቅት ከፍተኛ በደሎች ተፈጽመውባታል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የነበረው ችግር እንደ ግብፅ ፈጣን አለመሆን ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ ሲበሰር የነበረው የሕዝቡ የዘመናት የቁጭት ስሜት መቼም አይረሳም፡፡ ግድቡ የኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ፕሮጀክት እንደሆነ የጋራ መግባባት በመፈጠሩ፣ በውጭ በተቃውሞ የነበሩ ኃይሎች ሳይቀሩ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ተሳስተው እንኳ በግድቡ ላይ ነቀፌታ ሲሰነዝሩ ቢታዩም፣ አሁን ግን ስህተታቸውን አርመው የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ ይህ አጠር ያለ ምሳሌ የሚያሳየው ኢትዮጵያዊያን ግድቡን እንደ ብሔራዊ ምልክታቸውና የማንነት ዓርማቸው እንደሚቆጥሩት ነው፡፡ ይህንን ብሔራዊ ፕሮጀክት ዳር ለማድረስ በጠንካራ መሠረት ላይ መቆም ያስፈልጋል፡፡ በሳልና ጠንካራ ዲፕሎማቶች፣ የተካኑ የውኃና የጂኦ ፖለቲካ ባለሙያዎች፣ አሉ የተባሉ የሕግ ባለሙያዎችና ሊጠቅሙ የሚችሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ልሂቃንን ለዚህ ዓላማ ማሠለፍ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ግብፅ አንዱ አልሳካ ሲላት ሌላ ግንባር እየፈጠረች በገዛ ራሷ ዛቢያ ውስጥ ስታሽከረክረን የምትጎዳው ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግና በሞራላዊ አስተሳሰብ ብቻ ስንተማመን፣ ራሳችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከተለያዩ ጫናዎች የማላቀቅ ኃላፊነት እንዳለብን መገንዘብ አለብን፡፡ መንግሥትም ልማዳዊውንና ኋላቀሩን ዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ በመቀየር፣ ዘመኑን በሚመጥን ዲፕሎማሲ ለመተካት ብርቱና ንቁ ይሁን፡፡ ሉዓላዊነት የሚከበረው ከብረት የጠነከረ አንድነት ሲኖር ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...