ግብፅና ሱዳን ተመሳሳይ አቋም መያዛቸው ተሰምቷል
ተቋርጦ የነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ማክሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ዳግም መካሄድ መጀመሩ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር፣ ለበርካታ ሳምንታት ከተቋረጠ በኋላ ዳግም ድርድሩ ሊጀመር የቻለው፣ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ከሦስቱ አገሮች መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ድርድሩን ከተቋረጠበት ለመቀጠል በመስማማታቸው እንደሆነ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ድርድሩ ማክሰኞ 11 ሰዓት ገደማ መጀመሩን ሪፖርተር ያረጋገጠ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እና ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በጋራ ሆነው በድርድሩ ላይ መሳተፋቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ድርድሩ በበይነ መረብ አማካይነት በቪዲዮ የሚካሄድ እንደሆነና የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባላትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ውስጥ በተዘጋጀላቸው መሰብሰቢያ አዳራሽ ሆነው እንደተሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ ቀደም ሲካሄድ የነበረው ድርድር የተቋረጠው፣ የሱዳን ተደራዳሪ ቡድን ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ለመመካከር እንደሚፈልግ በመግለጹ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
ቢሆንም የሱዳን መንግሥት ዳግም ወደ ድርድሩ ባለመመለሱ ድርድሩ እንደተቋረጠ ቆይቶ ሰሞኑን በፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ጥረት ዳግም ሊጀመር ችሏል።
‹‹ከሦስቱ አገሮች መሪዎች ጋር ባደረጉት ሰፊ ውይይት ድርድሩን ዳግም ለመጀመር ተስማምተዋል። ይህም መሪዎቹ በአፍሪካ ኅብረት ሚና ላይ ያለቸውን ፅኑ እምነት የሚያረጋግጥ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሲሪል፣ ‹‹በዚህ ድርድር አገሮቹ ባልተግባቡባቸው ጉዳየች በዋናነትም በቴክኒካዊና በሕግ ጉዳዮች ስምምነት እንደሚደርሱ እምነት አለኝ፤›› ሲሉ በመግለጫቸው እርግጠኝነታቸውን ተናግረዋል።
ድርድሩ ከመቋረጡ በፊት የውይይት አጀንዳ የነበሩት ጉዳዮች በመሠረታዊነት ሁለት ሲሆኑ፣ እነሱም ከህዳሴ ግድቡ በላይ ባለው የኢትዮጵያ ክፍል ወደፊት የሚደረጉ የልማት ሥራዎች በስምምነቱ መካተት አለባቸው የሚለው የቴክኒክ ጉዳይና በድርድሩ የሚደረስበት ስምምነት አስገዳጅ ሊሆን ይገባል የሚሉት ነጥቦች ናቸው።
ኢትዮጵያ የወደፊት የዓባይ ውኃ አጠቃቀሟን የሚገድብ ስምምነት ከሉዓላዊነቷ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ፈጽሞ እንደማትቀበል በይፋ ማሳወቋ ይታወቃል።
ድርድሩ ከመጀመሩ አንድ ቀን አስቀድሞ፣ በግብፅ ጉብኝት ያደረጉት የሱዳን የሽግግር መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤልል ሲሲ ጋር ተገናኝተው በህዳሴ ግድብ ዙርያ የመከሩ መሆኑ ታወቋል።
በውይይታቸውም ሁለቱ መሪዎች የዓባይ ውኃ ጉዳይ ለሁለቱም የብሔራዊ ደኅንነታቸው ጉዳይ መሆኑንና በዚህም መሠረት ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የሚደረገው ድርድር አስገዳጅ መሆን እንደሚገባው በመስማማት የጋራ አቋም ለማንፀባረቅ መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ማክሰኞ ዕለት የተጀመረው የሦስቱ አገሮች ድርድር ለኅትመት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ አልተጠናቀቀም፣ በመሆኑም በዚህ ድርድር የተነሱ ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለማግኘት አልተቻለም።