Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየትራምፕ የማናለብኝነት አስተያየትና የኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ምላሽ

የትራምፕ የማናለብኝነት አስተያየትና የኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ምላሽ

ቀን:

ዓርብ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ሌሊቱን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክተው የሰጡት ኃላፊነት የጎደለው አስተያየት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ክፉኛ ከማስቆጣት ባለፈ፣ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው የአሜሪካን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪው ጆ ባይደን ይመረጡ ዘንድ የውትውታ ምክንያትም ሆኗል፡፡

ዓርብ ሌሊት በፕሬዚዳንቱ የተሰነዘረውን ከዓለም አቀፍ ሕግጋትም ሆነ ከሁለት ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት ካላቸው አገሮች አንፃር ያፈነገጠው አስተያየትን ተከትሎ፣ የሳምንቱ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ የሆነ ንግግር ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከእስራኤልና ከሱዳን መሪዎች ጋር በስልክ ውይይት በሚያደርጉበት ወቅት ስለኢትዮጵያና ግብፅ ጉዳይ ያነሱ ሲሆን፣ በዚህ ወቅትም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ግብፅ ‹‹ብታኮርፍ› እንደማይፈረድባት በመግለጽ፣ በዚህም ‹‹ሳቢያ ግብፅ ግድቡን ልታፈነዳ›› ትችላለች በማለት በጋዜጠኞች ፊት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ይህንን አወዛጋቢ ንግግር ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ የሚገኝ ሲሆን፣ የፕሬዚዳንቱ አስተያየት ያስከተለውን ግብረ መልስ በጥቅሉ ለተመለከተው ግን አስተያየቱ ያስከተለው ዋነኛ ነገር ፍርኃትንና መሸበርን ሳይሆን፣ እንዲያውም በተለያዩ ምክንያቶች የተከፋፈለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት መቆሙን የሚያሳይ እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን ካሉባቸው የተለያዩ የዓለም ክፍሎች ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ የትምህርት ደረጃ ሳይለያቸው የፕሬዚዳንቱን አጉራ ዘለል ንግግር በአንድ ድምፅ ተቃውመውታል፡፡ ከዚህ ወጥ የሆነ ታቃውሞ በዘለለ ደግሞ ይህን ክስተት በማውሳት እንዲህ ያሉ ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ንግግሮችና አስተያየቶች የሚሰነዘሩት የውስጥ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችና መስተጋብሮች መሀል በሚፈጠር ስንጥቅ አማካይነት ነው በማለት፣ የውስጥ የቤት ሥራችንን በቅጡ መሥራትና ከሚያንዣብበው አደጋ በፍጥነት መውጣት ይኖርብናል የሚል ማሳሰቢያ የሚሰነዝሩም በርካቶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ለበርካታ ዙሮች  ውይይቶችና ድርድሮች ያለ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ሲያከናውኑ የቆዩ አገሮች መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በታዛቢነት ስም ወደ ድርድሩ መምጣታቸው፣ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የቁጭትና የብስጭትም ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ ምንም እንኳን አሜሪካና የዓለም ባንክ ከመነሻው በታዛቢነት ወደ ድርድሩ ቢገቡም፣ በሒደት ግን ወደ ውሳኔ ሰጪነት ራሳቸውን አሸጋግረው በዋሽንግተን ሲካሄድ በነበረው ድርድር ስምምነት ሳይፈረም ‹‹ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት አትችልም›› የሚል መግለጫ መውጣቱ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ድርድር እንድትወጣ ገፊ ምክንያት መሆኑም የሚታወስ ነው፡፡

የአሜሪካና የዓለም ባንክ መጀመርያ በታዛቢነት ቀጥሎ በአደራዳሪነት፣ በመጨረሻ ደግሞ ብዙዎችን ያስገረመና ያስቆጣ በውሳኔ ሰጪነት መሳተፋቸው የሚተቹ በርካታ የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ምሁራን፣ ከመጀመርያው ይህ እንዲሆን መፈቀዱ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ፈተና ለግብፅ ደግሞ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑን በማውሳት ኢትዮጵያ ከዋሽንግተን ድርድር እንዳትወጣ ሲወተውቱ ሰነባብተው ነበር፡፡

የብዙኃኑ ሥጋትና ጭንቀት ፍሬ አፍርቶ በታዛቢነትና በአደራዳሪነት የሰነበቱት የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ ብዙዎቹ እንዳሰቡት፣ በአሜሪካ ትሬዥሪ ዲፓርትመንት ኃላፊ አማካይነት ለግብፅ የሚያደላ መግለጫ መውጣቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ኢትዮጵያም ይህን ትዕዛዝ አከል መግለጫ ወደ ጎን ብላ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ታሪካዊ የመጀመርያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌት በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. ተከናውኖ፣ ቀጣይ ሥራዎችም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተከናወኑ መሆኑን መግለጿን ቀጥላለች፡፡ ‹‹ግድቡን ከመጠናቀቅ የሚያግደው አንድም ምድራዊ ኃይል የለም›› በሚል የመንግሥት አቋም እየተከናወነ የሚገኘውን ግዙፍ ፕሮጀክትን ነው እንግዲህ፣ ግብፅ ‹‹ልታፈነዳው›› እንደምትችል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የገለጹት፡፡

የፕሬዚዳንቱን ኃላፊነት የጎደለው ንግግር ተከትሎ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ትኩረትን ያገኘ ሲሆን፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች በተናጠል ጉዳዩ እንዲህ ባለ ሁኔታ መሄድ የማይገባው መሆኑን በመጥቀስ የአፍሪካ ኅብረት በጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር ብቻ ሊመራና መቋጫ ሊበጅለት በመወትወት፣ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ጉዳዩን ከማወሳሰብ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡

ጉዳዩ በሦስቱ አገሮች በተጀመረው የድርድር መስመርና ሒደት ብቻ ማለፉ ለሁሉም ጠቃሚ መሆኑንና ለዚህም ሒደት ድጋፍ እንደሚሰጡ ከገለጹ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሀል የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ኢጋድ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በርካታ አገሮችም ሒደቱን የሚደግፍ አስተያየት በመስጠት በፕሬዚዳንት ትራምፕ የተሰነዘረው አስተያየት ኃላፊነት የጎደለውና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የተቃረነው አስተያየት ለሒደቱ እንደማይበጅ ይገልጻሉ፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች በሰነዘሩዋቸው አስተያየቶች የሦስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ከመግለጻቸው ባለፈ፣ የኢትዮጵያ በርካታ ተቋማትም የፕሬዚዳንቱን አስተያየት የሚያጣጥሉና የሚሸነቁጡ አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ነው፡፡ 

ንግግሩ በተደረገ ማግሥት ቅዳሜ ዕለት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይነርን ወደ ጽሕፈት ቤታቸው የጠሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ትራምፕ ከሱዳንና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባቷ አግባብ አለመሆኑንና ግብፅም ግድቡን ልታፈርሰው እንደምትችል፣ እንዲሁም አገራቸው የጀመረችውን ዕርዳታ ማቋረጥን እንደምትገፋበት መግለጻቸውን በመጥቀስ ‹‹ይህ የፕሬዚዳንቱ አስተያየት የተሳሳተ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የታላቁ የህዳሴ ግድብ የዓባይን ውኃ ፍሰት እንደማያቆም እየታወቀ፣ ፕሬዚዳንቱ የሰነዘሩት አስተያየት ግን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ የሚመራ ከመሆኑ ባለፈ በሦስትዮሽ ድርድሩ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ስለሆነ አላስፈላጊ አስተያየት እንደሆነ በአጽንኦት አውስተዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ ንግግር አሜሪካን እየመራ ካለና ኃላፊነት ከሚሰማው ፕሬዚዳንት የማይጠበቅ መሆኑን የገለጹት አቶ ገዱ፣ ከዚህ ባለፈም ንግግሩ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ጦርነት ቀስቃሽ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረዥም ጊዜ አጋርነትና ስትራቴጂካዊ  ግንኙነት የማያንፀባርቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን ከፍፃሜ ከማድረስ ለአፍታም ያህል የሚያቆመን ነገር አይኖርም፤›› በሚል ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግድቡን አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት ኃላፊነት የጎደለውና የአሜሪካ መንግሥትንም ሆነ ሕዝብ የማይመጥን ነው፤›› በማለት የፕሬዚዳንቱን ንግግር በማስመልከት ተቃውሞውን አሰምቷል ‹‹እንዲህ ዓይነቱ ኃላፊነት የጎደለውና የማናለብኝነት አነጋገር ከአንድ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ እቆማለሁ ከምትል አገር ፕሬዚዳንት ሲሰማ ደግሞ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ሆኖ እናገኘዋለን፤›› ሲሉ የፕሬዚዳንቱን ንግግር ክፉኛ ተችቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ለፕሬዚዳንቱ ኃላፊነት የጎደለው ንግግር፣ ‹‹በምንምና በማንም ካሰብነው መንገድ አንቀርም፡፡ ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ አንድ ሆነን የምንይዘው ጋሻ ኃያላኑን ሁሉ ሲመክት የኖረ ነው፡፡ ዛሬም ያንን ጋሻ በአንድነት እናንሳ፡፡ ሁላችንም በየቦታችን 24 ሰዓት ለኢትዮጵያ እንቁም፤›› በማለት፣ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ከመሸበርና ከመንበርከክ ይልቅ በአንድነት ሊቃጡ የሚችሉ ጥቃቶችን ሁሉ መመከት ላይ ትኩረት እንዲረግ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በረዥም ዓመታት ታሪኳ ለማንም ተንበርክካ እንደማታውቅ በማውሳት፣ አሁንም ቢሆን ማንም የፈለገውን ቢል ኢትዮጵያውያንን አንበርክኮና አስገድዶ የሚፈልገው መፈጸም እንደማይቻል አስታውቋል፡፡

‹‹ማንም ገዝቶን አያውቅም፡፡ ወደፊትም ማንም አይገዛንም፡፡ ታሪክ የሠሩ እጆች ዛሬም አሉ፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወደጆቻቸውን ለማክበር እንጂ ጠላቶቻቸውን ለመታዘዝ ተንበርክከው አያውቁም፡፡ ዛሬም ወደፊትም አናደርገውም፤›› በማለት በዘመናት መካከል ሳይዛነፍ የዘለቀው አገርን የመጠበቅና የማስከበር ባህል አሁንም መኖሩን በማውሳት፣ በፕሬዚዳንቱ የተሰጠው አጉራ ዘለል ንግግር ከአስተያየት እንደማያልፍና የሚያሠጋ ነገር እንደሌለው ጠቁሟል፡፡

የፕሬዚዳንቱ ንግግር ለበርካታ አስተያየቶች ምክንያት ቢሆንም ቅሉ፣ በአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ አማካይነት ሲካሄድ የሰነበተውና ለሰባት ሳምንታት ያህል ተቋርጦ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ማክሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም.  የተጀመረ ሲሆን፣ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት አካል ተደርጎ ተወስዷል፡፡

የፕሬዚዳንት ትራምፕን ተከትሎ ከሚሰነዘሩ በርካታ አስተያየቶች መካከል በዋነኛነት የአገሪቱ የውስጣዊ ፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲህ ላሉ የማናለብኝነት አስተያየት ምክንያት መሆኑን በመጥቀስ፣ አሁንም በዚህ ምክንያት በተፈጠረው የአንድነት መንፈስ የውስጥ ችግሩንም መፍታት ዋነኛ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባው የሚያሳስቡ በርካቶች ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዲፕሎማሲው መስክ ትልልቅ ሥራዎችን ለማከናወን ልምድ ያላቸውን ዲፕሎማቶች በዚህ ጉዳይ ላይ በመመደብ አጀንዳውን መቀበልና መመከት ብቻ ሳይሆን፣ ነገሮች እንዲህ ወዳለ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት የሚያርቅ አሠራርና ዝግጁነትን መዘርጋት አስፈላጊነትን የሚወተውቱም ብዙ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...