ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በሥነ ጥበባዊ ገጽታ፣ ብሂልን ከባህል አዛምደው በጥበብ ገበታ ለዓለም ያስተዋወቁ ናቸው፡፡ በሥዕል የለሙ፣ ሥዕልን ያለሙ ሥዕልን በጉያቸው ይዘው ከስድስት አሠርታት በላይ የዘለቁ ናቸው፡፡
በተለይ ከሌሎች ጠቢባን የሚለያቸው በፍየል ቆዳ ላይ የሚነድፏቸው ምስለ አካሎች (ፖርትሬት) በግዝፈት አንግሷቸዋል፡፡ በኩር (ሌጀንድ) ሠዓሊና መምህር የአየር ኃይል ሻምበል ለማ ጉያ፡፡
በደራሲና ተርጓሚ ታደለ ገድሌ (ዶ/ር) የወግ ገበታ ሠዓሊ ለማን እንደገለጻቸው “ከሠዓልያን ሁሉ ለየት ያለ የአሣሣል ጥበብን ይከተላሉ፡፡ በዋነኛነት ትኩረት የሚያደርጉትም ቪዡዋል አርት በሚባለው የአሣሣል ጥበብ ላይ ነው፡፡ ይኸውም የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥ የጥበብ ሥራ ሲሆን የሚጠቀሙበት ቁሳቁስ የፍየል ወይም የበሬ ቆዳ፣ የውኃ ቀለም፣ የዘይት ቀለም፣ ከሰል (ቻርኮል) ነው፡፡”
ልሒቅ ሥነ ጥበበኛ ለማ ገጸ ታሪካቸው እንደሚያሳየው፣ በቆዳ ላይ መሣል የጀመሩት በኅብረተሰብአዊት ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዘመን ጀምሮ መሆኑንና በመጀመሪያ በፍየል ቆዳ ላይ የሣሉትም የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን ሲሆን ከኢትዮጵያ ነገሥታትና መሪዎች መካከል ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድረስ የነበሩትን ሠርተዋል። ሥዕላቱ በቢሾፍቱ ከተማ በገነቡት ሙዚየማቸው ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የየብሔረሰቡን የአለባበስና የአኗኗር ዘይቤን የሚገልፁ በተለይም የኦሮሞን ሕዝብ ትውፊትን የሚያጎሉ ሥዕሎችን በመሣል ይታወቃሉ፡፡፡
በ65 ዓመታት የጥበብ ጉዞአቸው ያፈሩት የጥበብ ሥራ 10,000 እንደሚደርስ ይወሳል፡፡ ሥዕሎቻቸውን በግል በአሥመራ፣ በአዲስ አበባ፣ በደብረ ዘይት በዓውደ ርዕይ ለዕይታ ከማቅረባቸው ባሻገር በውጭ አገሮች በኅብረት ካቀረቡቧቸው መካከል የናይጄርያ መዲና ሌጎስና የሴኔጋሏ ዳካር ይገኙባቸዋል፡፡ በልጃቸው ሠዓሊት ነፃነት ለማ አማካይነትም በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ ያዘጋጁትን ዓውደ ርዕይ የከፈቱት በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ናቸው፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ጥበብ የክብር ዶክትሬት በ2007 ዓ.ም. በሰጣቸው ጊዜ የአንደኛውን ሥዕላቸውን አንድምታ አንደሚከተለው አቅርቦታል፡- “በተለይ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ አድናቆትን የሰጠውና በሹማምንት ልዩ ትርጉምና አቃቂር በማውጣት ከየወቅቱ አዛዦች ጋር እንዲላተም ካስደረጉት የበኩር ሥራዎች ሳትጠቀስ የማታልፈው ቋንጣ የምትባለው ሥዕል ነች፡፡ ቋንጣ የአፍሪካን የሀብት ምዝበራ ወይም ሙስናን ፍንትው አድርጋ ታሳያለች፡፡ በአንድ ቤት ጓዳ ውስጥ ቋንጣ በቀይ መልኩ ተዘልዝሎ ይታያል፡፡ ድመቶች ቋንጣውን መዥርጠው ለመብላት ይታገላሉ፡፡ ጠፍሩ አልጋ ላይ በድምሩ አራት ድመቶች ወጥተዋል፡፡ አንደኛው ግድግዳው በጥፍሩ ቧጥጦ ያወርዳል፡፡ አንዱ ቁመቱ አልደርስ ብሎታል፡፡ አንደኛው ደግሞ በእጁ የገባለትን እንደያዘ ሌላ ለማግኘት አንጋጧል፡፡ በእነርሱ ግፊያና ግርግር ጮጮ ሙሉ ወተት ተደፍቷል፡፡ የወተቱ አወራረድ የዓባይ ፋፏቴን ተመስሎ ቀርቧል፡፡ የመጨረሻው ድመት የሸረሪት ድር የወረሰውን ድብኝት አፍጦ በሸረፋት ድር የተያዘውን ነፍሳት ለመያዝ ያስባል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ ግን ከአልጋው ስር አይጥ እሸት በቆሎ ትቀረጥፋለች፡፡ ይህንን ሥዕል ስትመለከቱት የራሳችሁ ፍርድ ትሰጣላችሁ፡፡”
ቢቢሲ በአንድ ወቅት ስለ ቋንጣውና ስለድመቶቹ እንዲሁም ስለወተቱ ለማ ጉያ እንዲያብራሩለት ጠይቋቸው ሥዕሉን ከሠሩት 42 ዓመታት ማስቆጠሩንና በዚህ ሥራቸውም አፍሪካና ችግሮቿን ያሳዩበት እንደሆነ ገልጸውለት ነበር።
“የአፍሪካ መሪዎችን በድመቶቹ መስለው የሀገራቸውን ሀብት በሙስና ሲመዘብሩ፣ በአልጋው ሥር የሚታዩት የአህጉሪቷ ጠላት አይጦች ደግሞ የአፍሪካን ሀብት ሲቀራመቱ ይታያሉ፡፡ እየፈሰሰ ያለው ወተትም ያለጥቅም ለዘመናት የሚፈሱት የአፍሪካ ወንዞች ምሳሌ ነው።”
ከአባታቸው ከአቶ ጉያ ገመዳና ከእናታቸው ከወ/ሮ ማሬ ጎበና በ1921 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት አድአ ሊበን ውስጥ ልዩ ስሙ ደሎ ቀበሌ የተወለዱት ሻምበል ለማ ጉያ፣ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ እጣ ፈንታው የቆየው እንደ ሌሎቹ የአካባቢው ተመሳሳይ ልጆች ተለምዶአዊው የአባታዊ የሥራ ፈለግ ውርስ ሳይሆን ያልተለመደውን የወ/ሮ ማሬ ጎበናን የዕደ ጥበብ ብቃት ነቅሶ በመያዝ ከዕቃ ዕቃ ጨዋታው በላይና ከሚያዩት የመገልገያ መሣሪያ የሸክላ ውጤቶች ውጪ ከዕድሜያቸው በላይ ወደሠሯቸው ቅርፃ ቅርፆች እንደነበረ ግለ ታሪካቸው ያሳያል፡፡
የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፄ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት ያጠናቀቁ ሲሆን መምህራን ትምህርት ተቋም ለተወሰነ ጊዜ ከተማሩ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ አየር ኃይል በመግባትና በአርሜንት ኮርስ በካዴትነት በመሠልጠን ተመርቀዋል፡፡
አገልግሎታቸውንም በሒደት በአስመራ ከተማ በአየር ኃይል መምህርነት ነበር የጀመሩት፡፡
ሻምበል ለማ ጉያ ከሠለጠኑበት ሙያ በተጓዳኝ ወደ ጥበቡ የዘለቁበትን ክሂል የቀሰሙት በአስመራ የጣሊያኖች የሥዕል ትምህርት ቤት መማራቸው ነው፡፡
በተለይም በወታደር ቤት እምብዛም የሲቪል ጉዳዮችን ባልተለመዱበት ሁኔታ የሥዕል ዓውደ ርዕይን በማቅረብ በአንድ በኩል በወታደራዊ ትምህርቱ የተሰጣቸውን ግዳጅ እየተወጡ በሌላ በኩል የጥበብ ፍቅራቸውን ሠርተው በማሳየትና ለጥበብ ቀናኢነታቸውን ማሳየታቸው ይወሳል፡፡ “ሥዕል ያለ አስተማሪ” መጽሐፍ አዘጋጅቶ በማሳተምም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ሕክምና ሲከታተሉ የቆዩት ሥነ ጠቢቡ ሻምበል ለማ ጉያ በ92 ዓመት ዕድሜያቸው ዜና ዕረፍታቸው የተሰማው ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም ከቢሾፍቱ አቅራቢያ በትውልድ ስፍራቸው በሚገኘው ደሎ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡
ልሒቁ ሥነ ጥበበኛ ሻምበል ለማ ጉያ ሦስት ሴቶችና ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ አምስቱም ልጆቻቸው የአባታቸውን ፈለግ የተከተሉ ሥነ ጠቢባን ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዲን ሠዓሊ አገኘሁ እንግዳ ሥነ ጠቢቡን እንዲህ ገለጹ፡- “ሻምበል ለማ ጉያ አንጋፋ የሥነጥበብ ሰው ነበሩ፡፡ የሥዕል ማስተማሪያ መጽሐፋቸው ብዙዎቻችንን የሥነጥበብ ‹ሀ ሁ› ያስቆጠረ፣ ተሰጧችንን ፈልገን እንደናገኝ የረዳ ነበር፡፡ ይህን የማይረሳ ውለታቸውን የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነጥበብና ጠቢባኑ ሲያስታውሱት ይኖራሉ፡፡ ለሙያው ታምኖና በትጋት ሳያቋርጡ ሠርቶ ስምና ዝና ማትረፍ እጅግ ከባድ በሆነበት በኛ ሙያ፣ ይህን ድልና ገድል መቀዳጀታቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ ጠንካራ ሙያተኛ ነበሩ:: ሻምበል ለማ የሰላም ዕረፍት ይሁንልዎ!!”