Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከወዲሁ ትችት የበዛባቸው አሠልጣኝ ውበቱ የመጨረሻ ቡድናቸውን ዝርዝር ይፋ አደረጉ

ከወዲሁ ትችት የበዛባቸው አሠልጣኝ ውበቱ የመጨረሻ ቡድናቸውን ዝርዝር ይፋ አደረጉ

ቀን:

በአዲስ አበባ ስታዲየም የዛምቢያ አቻውን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ጨዋታው ምንም እንኳ የወዳጅነትና የአቋም መመዘኛ ቢሆንም በሁለቱም ጨዋታዎች መሸነፉ የአሠልጣኝ ውበቱ አባተን አጀማመር ከወዲሁ ማስተቸት ጀምሯል፡፡ ብዙዎች ከሽንፈቱ ባሻገር ቡድኑ ባሳየው ቅርፅ አልባ እንቅስቃሴ ደስተኛ እንዳልሆኑ ሲናገሩ ቢደመጡም፣ አሠልጣኝ ውበቱ በበኩላቸው ጨዋታው ቀጣዩን የቡድናቸውን ስብስብ ለመለየትና ለመመልከት መልካም አጋጣሚ የፈጠረላቸው ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

ከኮቪድ-19 በፊት በምድቡ በጥንካሬዋ የምትጠቀሰውን ምዕራብ አፍሪካዊቷን አይቮሪኮስትን በባህር ዳር ስታዲየም አስተናግዶ 2ለ1 በሆነ ውጤት ያሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ እንዲሰናበቱ መደረጉ አሁንም ድረስ አከራካሪ መሆኑና በዚህ መሀል የአሠልጣኝነቱን ኃላፊነት ለተረከቡት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ሒደቱን ከባድ እንደሚያደርግባቸው የሚናገሩ በሌላ ወገን አልታጡም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተገነባው ቡድን የዛምቢያ አቻውን ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 12 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ገጥሞ በሁለቱም ጨዋታ የ3ለ2 እና የ3ለ1 ሽንፈትን ማስተናገዱ አሠልጣኙን ለትችት ዳርጓቸዋል፡፡

ከአቋም መለኪያው ጨዋታ ቀደም ብለው ወደ አርባ ለሚጠጉ ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉት አሠልጣኝ ውበቱ፣ ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ከኒጀር ጋር ከሜዳቸው ውጪ ለሚጠብቃቸው ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ 26 ተጫዋቾችን ዝርዝር ይፋ አድርገዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ተክለማርያም ሻንቆ፣ ይድነቃቸው ኪዳኔ፣ ምንተስኖት አሎ፣ ጀማል ጣሰው፣ ወንድሜነህ ደረጀ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ታፈሰ ሰለሞን፣ አቡበክር ናስር፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ያሬድ ባዬህ፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ሽመክት ጉግሳ፣ ሙጅብ ቃሲም፣ አስቻለው ታመነ፣ ሃይደር ሸረፋ፣ ጋዲሳ መብራቱ፣ ጌታነህ ከበደ፣ መሱድ መሐመድ፣ ሱሌማን ሐሚድ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ በረከት ደስታ፣ ረመዳን የሱፍ፣ መሳይ ጳውሎስ፣ ይሁን እንደሻው እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ሲሆኑ፣ 27ኛው ተጫዋች ደግሞ በግብፅ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ መሆኑ ታውቋል፡፡

በምድብ “ኬ” ከአይቮሪኮስት፣ ማደጋስካርና ኒጀር ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ በምድብ ማጣሪያው የመጀመሪያ ጨዋታ ከሜዳዋ ውጪ በማደጋስካር 1ለ0 እንዲሁም በምድቡ ሁለተኛ ማጣሪያ ደግሞ አይቮሪኮስትን በሜዳዋ ባህር ዳር ላይ 2ለ1 ማሸነፏን ተከትሎ ምድቡን ማደጋስካር በስድስት ነጥብ አንደኛ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በሦስት ነጥብና በአንድ ጎል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ከምድቡ የማለፍ ቅድመ ግምት የተሰጣት አይቮሪኮስት በሦስት ነጥብና በአንድ የጎል ዕዳ ሦስተኛ ስትሆን፣ ኒጀር በማዳጋስካርና በአይቮሪኮስት 1ለ0 እና 6ለ2 በመሸነፏ ያለምንም ነጥብ በአምስት የጎል ዕዳ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮፌዴሬሽን (ካፍ) ከኮቪድ በኋላ ባወጣው ፕሮግራም መሠረት አይቮሪኮስት ከማደጋስካር ትጫወታለች፡፡ በአራተኛው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአምስት ቀን ዕረፍት በኋላ ማለትም ኅዳር 9 ኒጀርን በሜዳዋ ስትገጥም እንዲሁም ማደጋስካር ከአይቮሪኮስት የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

ካሜሮን በ2021 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የሚበቁት ቡድኖች በመጨረሻው የምድብ ማጣሪያ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጪ ከአይቮሪኮስት እንዲሁም ማደጋስካር ከኒጀር በሚያደርጉት ጨዋታ ይሆናል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...