Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትብሔራዊ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በአፍሪካ መድረክ ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ እሠራለሁ አለ

ብሔራዊ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በአፍሪካ መድረክ ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ እሠራለሁ አለ

ቀን:

ለቀድሞ ተጫዋቾች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ወስኗል

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን 17ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ባለፈው እሑድ ጥቅምት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲያከናውን፣ ቀድሞ በተለያዩ ክለቦችና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት እንዲሁም በክለብና በፕሮጀክት አሠልጣኝነት ላገለገለው አሥር አለቃ ገመቹ ሮባ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ጉባዔው ለሌሎችም ባለውለተኞች የተጀመረው የገንዘብ ድጋፍ ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለፈው እሑድ በሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል ባካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው፣ የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የኦዲት ሪፖርት ከማድረጉም በላይ የዘንድሮን ዕቅድ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ መወያየቱን ፌዴሬሽኑ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል እንድትሆን ዓይነተኛ ሚና ካላቸው ቀደምት የስፖርት ማኅበራት አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን፣ ስፖርቱ ወደ ቀድሞ ስምና ዝናው ይመለስ ዘንድ ክለቦችን በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ እያወዳደረ ይገኛል፡፡ በሊጉ እየተወዳደሩ ከሚገኙት ክለቦች መካከል የካ ክፍለ ከተማና ውቅሮ ከተማ በወንዶች፣ ሐዋሳ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማና ጎንደር ከተማ በሁለቱም ጾታዎች፣ አማራ መንገድ ኮንስትራክሽንና ጅማ ከተማ በሴቶች ይገኙበታል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአትሌቲክስና ከእግር ኳስ ውጭ ሌሎች ስፖርቶች ከስም ባለፈ ይህ ነው የሚባል ተሳትፎ እንደሌላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ከእነዚህ ስፖርቶች ተርታ ተመድቦ የቆየውን ቅርጫት ኳስ የሚመራው ፌዴሬሽን በተለይ በአሜሪካ በትልቁ ከሚጠቀሰው ኤንቢኤ እንዲሁም ከስፔንና ከሌሎች በቅርጫት ኳስ ከሚታወቁ አገሮች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር የሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲደረግለት የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

በዚህ መነሻነት ስፖርቱን በአገሪቱ በማስፋፋት ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ በሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ3X3 ተሳትፎ አድርጎ አበረታች ውጤት አስመዝግቦ መመለሱ ይታወቃል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከዚህም በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ግንኙነቱም በማጠናከር፣ በአኅጉር ደረጃ በዞን አምስት የአፍሪካ ቅርጫት ኳስ ውድድሮች ላይ በክለብ፣ እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከአቻ ፌዴሬሽኖች ጋር ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

ፌዴሬሽኑ ለዚህ ውጤት ሊበቃ የቻለው በዋናነት ለታዳጊ ወጣቶች ትኩረት በማድረጉ እንደሆነ ለጉባዔው በቀረበው ሪፖርት ተመልክቷል፡፡ በ2013 የውድድር ዓመትም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከመገለጹም በላይ፣ ለዚህም ሲባል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጥናት ላይ በመመሥረት በክህሎት ማዕከልነት የተመረጡ ቦታዎች መለየታቸውን ጭምር ለጉባዔው ሪፖርት መቅረቡ ታውቋል፡፡

የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሰጠውን ዕውቅና ተጠቅሞ ስፖርቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መሥራት እንደሚያስፈልግ ጭምር የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ለጉባዔው መግለጻቸው ታውቋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አያይዘውም የ2022 የአፍሪካ ኦሊምፒክ ጨዋታን ኢትዮጵያ እንደምታስተናግድ ገልጸው፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በክለቦች የጀመረውን ተሳትፎ በማጠናከር በአህጉር ደረጃ የሚያደርገውን ፉክክር ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግር ይገባል ማለታቸውም ታውቋል፡፡ በመጨረሻም ፌዴሬሽኑ የቀድሞ የቅርጫት ኳስ ተጫዋችና አሠልጣኝ አሥር አለቃ ገመቹ ሮባ ከሚኖርበት መቐለ ከተማ ሙሉ ወጪውን በመሸፈን አስመጥቶ በጉባዔው ፊት የ10,000 ብር ማበረታቻ የገንዘብ ስጦታ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሙሉ ትጥቅ እንዲበረከትለት ማድረጉ ታውቋል፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...