ኮቪድ-19 ከሰው ወደ ሰው በተለያዩ መንገዶች ሊተላለፍ የሚችል አዲስና ገዳይ ቫይረስ ነው፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየናኘ ያለው የቫይረስ ወረርሽኝም እያስከተለ ያለው የሞት ምጣኔ አንድ ከፍ ሲል በሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ እያለ መያዣ መጨበጫ እስከማሳጣት ደርሷል፡፡ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ከጥቅምት 13 ቀን እስከ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 41 ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት ሌሎች 314 ሰዎችን ደግሞ ለጽኑ ሕመም ዳርጓቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጣቸው መረጃዎች እንዳመለከቱት፣ እስከ ሰኞ (ጥቅምት 16 ቀን) አመሻሽ ድረስ 1,449,170 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው 44,118 ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 48,150 ሰዎች ከበሽታው ሲያገግሙ 93,707 ሰዎች በአሁኑ ሰዓት በበሽታው ተይዘዋል፡፡ እስካሁን በቫይረሱ ሳቢያ ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 1437 ደርሰዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው እንዳሳሰቡት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ10 እስከ 15 ሰኮንዶች ውስጥ በኮቪድ ሳቢያ ሞት ይመዘገባል፡፡ ‹‹እያንዳንዱ ሕይወት ውድ ነውና እባካችሁ እንጠንቀቅ›› ሲሉም ተማጽነዋል፡፡
መሰንበቻውን የጤና ሚኒስቴር ባወጣው ጥበቅ መመርያ መሠረት ማንኛውም አገልግሎት የሚሰጥ የመንግሥታዊና የግል ተቋም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ ተገልጋዮች ሁለት የአዋቂ ዕርምጃ ተራርቀው የሚቆሙበትን ቦታ ምልክት የማድረግና ተገልጋዮችም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውንና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት በተቋሙ ላይ ተጥሏል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ አሽከርካሪ፣ አገር አቀፍም ሆነ የከተማ ውስጥ ትራንስፖርትን በተመለከተ በሕግ ከተወሰነው የመጫን አቅም ልክ ሰዎችን የመጫን፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ ሰዎችን አገልግሎት መስጠት እንደሌለበት መግለጫው አመልክቶ፣ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አሠሪዎች በተመለከተ በግንባታ ሳይቶች ላይ አስፈላጊውን ንጽህና ለመጠበቅ የሚረዱ እንደ ውኃ፣ ሳሙና፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ ሳኒታይዘር ወይም አልኮል፣ የሙቀት መለኪያ መሣሪያ እንዲሁም የፀረ ተህዋሲያን ግብዓት የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸው አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የዘርፉ መሥርያ ቤቶች በየመስካቸው የሚያወጧቸው መመርያዎችና አሠራሮች የኮቪድ-19 በሽታን ለመግታት ወይም ለመቀነስ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባወጣው መመርያ ውስጥ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የማይቃረኑና ተጣጥመው የወጡ መሆን እንዳለባቸው፣ በዚሁ መመርያ የተደነገጉ ክልከላዎችንና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው የወንጀል ሕግ መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ማንኛውም ሰው ከ25/01/2013 ጀምሮ መመርያው የፀና መሆኑን አውቆ ተግባራዊና ተፈጻሚ እንዲያደርግ ኢንስቲትዩቱ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
ተተኳሪ ጉዳዮች
ኮቪድ-19 በወረርሽነት ዓለምን ካካለለ ዘጠኝ ወር ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ወራት ሕዝበ ዓለም ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠበቅ፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ እንዳይያዝ የጤና ባለሙያዎችና ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ ተቋማት ማስገንዘቢያዎችን ከመስጠት ችላ ያሉበት ጊዜ አልነበረም፡፡
ኮቪድ-19 የሚተላለፍበት መንገድ አስመልክቶ እስካሁን ያለው አቋም፣ በሽታው ከሕመምተኛው አፍንጫ ወይም አፍ በሚወጣ ጥቂት ፈሳሽ አማካይነት የሚተላለፍ መሆኑ ነው፡፡ ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ሲያስነጥስም ሆነ ሲተነፍስ ወደ ሌሎች ከማስተላለፍ ባለፈ፣ ከሕሙማን የሚወጣ ፈሳሽ ያረፈበትን ቦታ የነኩ ሰዎችም በበሽታው በቀላሉ ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸው ቅርርብ ከአንድ ሜትር በላይ መሆን አለበት የተባለውም በሽታው በትንፋሽ ስለሚተላለፍ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት ቫይረሱ በአየር ውስጥ ሳይሆን በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የመተንፈሻ አካላት ከወጡ ፍሳሾች ጋር በሚኖር ንክኪ ብቻ የሚተላለፍ መሆኑን ነው፡፡
ይሁን የቅርብ መረጃዎች የኮሮና ቫይረስ በአየር ላይ የመተላለፍ ዕድሉ ሰፊ መሆኑ እየገለጹ ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት በቫይረሱ የመጋለጥ ወይም ያለመጋለጥ ዙርያ የቀረቡ ጥናቶች ላይ እየመከረ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በአየር ላይ ቫይረሱ በመቆየት ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ -19) ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት አገላለጽ፣ ኮሮና ቫይረስ የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶችን የያዘ የቫይረስ ቤተሰብ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ በሰዎችና በእንስሳት ላይ በሽታን ያስከትላል፡፡ በሰዎች ላይ የሚከሰተው ኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት ከተራ ጉንፋን እስከ ከፍተኛ የመተንፈሻ አካል ችግር የሚያደርስ ነው፡፡
ኅብረተሰቡ በሽታው በቀላሉ የሚተላለፍ በመሆኑ ሳይዘናጋ የሚተላለፉ መልዕክቶችንና መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች በሚያገኝበትም ወቅት በተዘረጉ የነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል እንዲያሳውቅና የበሽታውን ሥርጭት በመቆጣጠር በኩል የድርሻውን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ፣ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118 276796 ወይም በኢሜይል አድራሻ [email protected] በመጠቀም ማግኘት ይቻላል፡፡
በተጨማሪም ለተለያዩ ጉዳዮች በአንድ ቦታ መሰባሰብን በማስወገድ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ፣ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታዎች ላይ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) በማድረግ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተውና አካላዊ መራራቅን ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ሥርጭት እንዲከላከል ኢንስቲትዩቱ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መጨመርን ከግንዛቤ በማስገባት ኅብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን አዘውትሮ እንዲተገብር ያሳሰበው የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ዕለት ዕለት በሚደረገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በበሽታው መያዝን የሚወሰን መሆኑን በማስታወስ፣ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ አራቱን የ‹‹መ›› ሕጎች በመተግበር የበሽታውን ሥርጭት ሁሉም እንዲከላከልም በጥብቅ አሳስበዋል፡፡
አራቱ የ‹‹መ›› ሕጎች
- መራራቅ፡ አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣
- መታጠብ፡ እጅን በተደጋጋሚ በውኃና በሳሙና መታጠብ፣
- መቆየት፡ አስገዳጅ ካልሆነ ቤት ውስጥ መቆየት፣
- መሸፈን፡ ከቤታችን ወጥተን ስንንቀሳቀስ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) መጠቀም፡፡