Thursday, February 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአፋር ክልል 300 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የአዮዳይዝድ ጨው ፋብሪካ ማምረቻ ሥራ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአፋር ክልል በአፍዴራ ሐይቅ አካባቢ ቲቲአር አዮዳይዝድ ጨው ማምረቻ ፋብሪካ በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ አስገንብቶ አስመርቋል፡፡ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ስመኝ ውቤ እንዲሁም የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ጥቅምት 15  ቀን 2013 ዓ.ም. የአፍዴራ ከተማ ላይ ተገኝተው አስመርቀዋል፡፡

በቱርክና በኢትዮጵያዊ ባለሀብት የተገነባው ቲቲአር አዮዳይዝድ ጨው ማምረቻ ፋብሪካ ከ1,500 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል እንዳገኙበት ተጠቅሷል፡፡ የቲቲአር አዮዳይዝድ ጨው ማምረቻ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ላይንአዲስ በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሰዓት 1,350 ኩንታል አዮዲን የተቀላቀለበት የገበታ ጨው ያመርታል፡፡ በቀን ሲመነዘር እስከ 20 ሺሕ ኩንታል ጨው ማምረት ማለት ነው፡፡

የቲቲአር የአዮዳይዝድ ጨው ማምረቻ እህት ኩባንያ የሆነው ኤስቪኤስ (SVS)፣ ከዚህ ቀደም በሰመራ ከተማ 250 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደ ሥራ ከገባ አራት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

አቶ ላይንአዲስ እንደሚሉት፣ በአፍዴራ የጨው ሐይቅ አካባቢ የተገነባው የቲቲአር አዮዲን ጨው ማምረቻ የመብራትና የውኃ አቅርቦት  ለማግኘት በራሱ በጀት ተጠቅሞ አገልግሎቱን ለመዘርጋት ወጪውን ከፍ በማድረጉ፣ የኢንቨስትመንት ወጪውን ወደ 300 ሚሊዮን ብር አሻቅቦበታል፡፡

ለፋብሪካ ግብዓት የሚያገኘው የክልሉ መንግሥት ያደራጃቸው 250 ዜጎች በመሠረቷቸው አራት ማኅበራት አማካይነት ሲሆን፣ ለፋብሪካዎች ግብዓት በማቅረብ ሥራ እነሱም ገቢ እንደሚያገኙ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ በአራት ማኅበራት የተከፋፈሉት አቅራቢዎቹ፣ 350,000 ካሬሜትር የጨው ማውጫ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በተለያዩ ባለሀብቶች የተያዘ ሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታም ወደ መሬት ባንክ እንዲካለል መደረጉን የክልሉ የማዕድንና ልማት ጽሕፈት ቤት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገዶ ሐሞሎ ተናግረዋል፡፡

አቶ ገዶ እንዳስታወቁት፣ አንድ ካሬ ሜትር ጨው ሦስት ኩንታል እንደሚያስገኝ፣ በባለሀብት እጅ የነበረ ሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር የጨው መሬት የሕዝብ ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ባላገናዘበ መንገድ ተይዞ ስለነበር ይህንን ለማስተካከል ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል፡፡ የአሠራር ሒደቱን ፍትሐዊ ለማድረግ ባለሀብቱ 25 ሺሕ ኩንታል ጨው ያመርት ስለነበር፣ አሁን በወጣው መመርያ መሠረት ግን ይህ መጠን በ5000  እንዲወሰን ቁጥጥር እየተደረገበት እንደሚገኝ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

አቅም የሌላቸው ወገኖች በወር 420,000 ኩንታል እንዲሸጡና ገቢ እንዲያገኙ ዕገዛ ይደረግላቸዋል ያሉት አቶ ገዶ፣ ባለሀብቱም ሆነ ማኅበረሰቡ ከጨው ሀብቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የቲቲአር እና የSVS አዮዲን የገባበት ጨው ማምረቻዎች፣ በአፍዴራ አካባቢ የመጀመርያ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት የገነቡ ሲሆን፣ በዘንድሮ ዓመት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ተማሪዎችን እንደሚያስተምር ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በአካባቢው ፋብሪካ መገንባት ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ኃላፊነት በመወጣት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ኩባንያዎቹ የአዮዲን ጨው ከማምረት በተጨማሪ በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ሥራ አስኪያጁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች