Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያውያን በውጭ ገንዘብ ሒሳብ ከፍተው እንዲያስቀምጡ የሚፈቅድ ረቂቅ መመርያ ሊተገበር ነው 

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ሥራ ላይ ለማዋል ያረቀቀውና እየተመከረበት የሚገኘው መመርያ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በባንኮች ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ገንዘቡን ማስቀመጥ እንደሚችል ለመደንገግ ያለመ ነው፡፡

ይህ ረቂቅ መመርያ ከዚህ ቀደም ትውልደ ኢትዮጵያውያንና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ ከፍተው ማስቀመጥ እንዲችሉ ከሚፈቅደው መመርያ በተለየ ሁኔታ፣ የውጭ ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ እንዳገኙት ማረጋገጫ ማቅረብ ለሚችሉ ኢትዮጵያውያን በውጭ ምንዛሪ ገንዘባቸውን ማስቀመጥ የሚችሉበት ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከሁሉም በላይ የአዲሱ ረቂቅ መመርያ ዋናው ግቡ፣ አገር ውስጥ ባሉ የውጭ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩና በውጭ ገንዘብ የሚከፈላቸው ሠራተኞች ገንዘባቸውን በውጭ ምንዛሪ ሒሳብ ባንክ እንዲያቀምጡ ለማስቻል ነው፡፡  

በዚሁ መመርያ ዙሪያ ሰሞኑን ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ እንዳመለከቱት፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚገኙባት ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች፣ ይህንኑ ገንዘባቸውን ከኢትዮጵያ ውጪ ለማስቀመጥ ሲገደዱ ቆይተዋል፡፡ ይህ ገንዘብ እዚህ ባሉት ባንኮች መቀመጥ የሚችልበት ዕድል ለመፍጠር ጭምር የተሰናዳ ረቂቅ መመርያ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ መመርያው ላይ ባንኮች አስተያየት እንዲሰጡበት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በውጭ ገንዘብ የባንክ ሒሳብ ከፍቶ የሚያስቀምጠውን የውጭ ምንዛሪ፣ ለሚፈልገው ዓላማ መጠቀም የሚችልበትን መንገድም አብሮ ያስቀመጠ ነው፡፡ በውጭ የሚቀመጥ የውጭ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ የተገኘና የገቢ ምንጩ የሚታወቅ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ባንኮችም በመመርያው በሚደነገገው መሠረት፣ በውጭ ገንዘቦች አካውንት ከፍተው ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ ይፈቀድላቸዋል፡፡  

በውጭ ገንዘብ የባንክ ሒሳብ ማንቀሳቀስ እንደሚያስችል የሚጠበቀው ረቂቅ መመርያ ተፈጻሚ የሚሆንባቸውን አንቀጾችም አካቷል፡፡ በውጭ ገንዘብ የሚከፈት የባንክ ሒሳብ ውስጥ የሚቀመጥ ገንዘብ ወለድ የሚታሰብበት ጭምር ነው፡፡ ሆኖም የወለድ መጠኑ ምን ያህል እንደሚሆን በረቂቅ መመርያው አልተጠቀሰም፡፡ እርግጥ ብሔራዊ ባንክ በሚያስቀምጠው መሠረት እንደሚወሰን የሚያመለክት ነው፡፡

እስከዛሬ ባለው አሠራር በውጭ ገንዘብ አካውንት ከፍተው መጠቀም እንዲችሉ የተፈቀደው ለትውልደ ኢትዮጵያውያንና በውጭ ለሚኖሩ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ መመርያ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ሲወጣ በመጀመርያው ትውልደ ኢትዮጵያውያን እስከ 50 ሺሕ ዶላር በባንክ ማስቀመጥ እንደሚችሉ የሚያመላክት ነበር፡፡ በመመርያው የጠቀመጠው መጠን በ50 ሺሕ ዶላር መገደብ አያስፈልገውም በመባሉ ጣሪያው መነሳቱ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ አዲሱ ረቂቅ መመርያ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሕጋዊ መንገድ የሚያገኘውንና በእጁ የሚገኘውን የውጭ ገንዘብ በባንክ ለማስመቀጥ በሚከፍተው ሒሳብ  ማስቀመጥ የሚችለው የውጭ ገንዘብ መጠን ላይ ገደብ አልተቀመጠበትም፡፡ በመሆኑም የቱንም ያህል ብዛት ያለው የውጭ ገንዘብ በአገር ውስጥ ባንኮች ማስቀመጥ ይፈቀዳል ተብሏል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ዓመታት ወዲህ የውጭ ምንዛሪን በአገር ውስጥ ባንኮች ማስቀመጥን ለማበረታታት ትውልደ ኢትዮጵያውያንና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በአገር ውስጥ ገንዘባቸውን እንዲያስቀምጡ የሚፈቅደው ውሳኔ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በውጭ ገንዘብ የባንክ ሒሳብ ከፍቶ ገንዘቡን ማስቀመጥ እንዲችል ሊፈቅድ መሆኑ በርካታ ጥቅሞችን ለአገሪቱ እንደሚያስገኝ ይገመታል፡፡ የአገሪቱን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለማስተንፈስ እንደሚያግዝ ይጠበቃል፡፡

ረቂቅ መመርያው በቅርቡ ሥራ ላይ እንዲውል የተፈለገባቸው ሌሎችም ምክንያቶች እንዳሉ ሲገለጽ፣ በተለይ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱና ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለውጭ ዜጎች ሠራተኞቻቸው በውጭ ምንዛሪ እየከፈሉ ቢያሠሩም ገንዘባቸውን በሚከፈላው የውጭ ምንዛሪ መሠረት ባንክ ማስቀመጥ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለውጭ ድርጅቶች የሚሠሩ ዜጎች በተለየ መንገድ ገንዘባቸውን በውጭ ምንዛሪ በባንክ እንዲያስቀምጡ ይፈቅድላቸዋል፡፡

በዚህ መመርያ ዙሪያ ይናገር (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፣ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው ሠራተኞች አብዛኛዎቹ ገንዘባቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ባንኮች ለማስቀመጥ ሲገደዱ ቆይተዋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው ሠራተኞች በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ ገንዘባቸውን ማስቀመጥ የሚችሉበት ዕድል ለመፍጠር መመርያው እንደተሰናዳ ተብራርቷል፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ ውጭ የሚቀመጥ ገንዘብ በአገር ውስጥ ማስቀመጥ ያልተቻበትን ምክንያት በመለየት መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮችን በማካተት መመርያውን ለማዘጋጀት፣ ብሔራዊ ባንክ አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግሮ ረቂቁ መመርያውን እንዳዘጋጀ ገዥው አብራርተዋል፡፡

መመርያው ላይ ባንኮችም ሐሳብ እንዲሰጡበት እየተደረገ እንደሚገኝ ሪፖርተር ያገኘው  መረጃ አመላክቷል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማስፋት እንዲህ ያሉ አማራጮችን በማየት ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራበት እንደሚገኝ የባንክ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በመመርያው መካተት ይገባቸዋል ያሏቸውንም ነጥቦች አጋርተዋል፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚገልጹት፣ ረቂቅ መመርያው ትኩረቱን ያደረገው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩና የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ዕድሉ ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በሕጋዊ መንገድ የሚያገኙትን የውጭ ገንዘብ በባንክ ማስቀመጥ የሚችሉበት ዕድል የመፈጠሩ አስፈላለጊነት አያጠያይቅም፡፡ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው መሆኑ ብቻም ሳይሆን የገቢ ምንጫቸውም የሚታወቅ በመሆኑ ጭምር በቀላሉ መስተናገድ የሚችሉበትን ዕድል በመመርያው ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ መመርያው ከውጭ ወደ አገር ቤት የሚላከውን ገንዘብ ተቀባዩ አካል በውጭ ምንዛሪ ሒሳብ ከፍቶ እንዲያስቀምጥ ዕድል መስጠት መቻል ነበረበት በማለት በመመርያው ያልታየውን ጉዳይ አመላክተዋል፡፡

ስለዚሁ ሲያስረዱም፣ ‹‹በርካታ ኢትዮጵያውያን ውጭ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ገንዘብ ይላክላቸዋል፡፡ ከውጭ ገንዘብ የሚላክለት ይህ ሰው የገንዘብ ምንጩ ዘመዱ ነው፡፡ ስለዚህ የገንዘቡ ምንጭ ይታወቃል ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነም እንደ ዌስተርን ዩኒየን ባሉ ሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊያዎች የሚላከው ገንዘብ እዚህ ላለው ገንዘብ ተቀባይ በውጭ ምንዛሪ አካውንት ከፍቶ እንዲያስቀምጥ ረቂቅ መመርያ አለመፍቀዱ ክፍተት ነው፤›› ይላሉ፡፡ ስለዚህ መመርያው እንዲህ ያሉ ተያያዥ ነገሮችንም ቢያካትትበት የበለጠ ጠቀሜታ አለው ብለው ያምናሉ፡፡

በሕጋዊ መንገድ ከባንክ ወደ ባንክ የመጣ ገንዘብ ከሆነ ሕጋዊ ነው የሚል እምነት ያላቸው እኚህ የባንክ ባለሙያዎች ሕጋዊ በመሆኑም እስካሁን ባንኮች ከውጭ የተላከውን ገንዘብ በብር መንዝረው እየሰጡ በመሆኑ የተላከለት ሰው ገንዘቡን በውጭ ምንዛሪ ማስቀመጥ እንዲችል ዕድል ሊሰጥ ይገባል በሚል ይሞግታሉ፡፡ የዶላር ተከፋዮችን ብቻ በዚህ መመርያ ለማካተት ከውጭ የሚላክንም ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ የሚቀመጥበትን አሠራር መዘርጋት ተገቢነት ይኖረዋል የሚለው እንዲህ ያለው አስተያየትም ለብሔራዊ ባንክ እየቀረበ ስለመሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ረቂቅ መመርያ ምንጩ ተረጋግጦ እንዲገባ መደረጉ አግባብ የሚሆንበት አሳማኝ ነገሮች እንዳሉ በመግለጽ በውጭ ምንዛሪ የሚገኝ ገቢ ሕጋዊ መሆኑ ከተረጋገጠ አካውንት ውስጥ እንዲገባና እንዲቀመጥ መደረጉ ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም ሕጋዊ ምንጭ የሌለው ከጥቁር ገበያ ገዝቶ እንዲያስገባም ሊያደርግ ይችላል የሚል ሥጋት ሊኖር እንደሚችል ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን የመቆጣጠሪያ ሥልቶችን በማበጀት ረቂቅ መመርያው በቀጥታ ለቤተሰብ የሚላክ ገንዘብን በውጭ ምንዛሪ ማስቀመጥ ከፈለገ እንዲያስቀምጥ ዕድል ቢሰጥ ሊያስከትል የሚችለው ችግር አይኖርም የሚል እምነት አላቸው፡፡

በዚህ መመርያ ጠቀሜታ ላይ የሰጡ ተጨማሪ መረጃ ደግሞ በተለይ የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ ማግኘት የቻለ ማንኛውም ሰው ወደ ጥቁር ገበያ ወስዶ እንዳይመነዝርና ያለ ገደብ በባንክ አካውንት ማስቀመጥ ማስቻል ነው፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር ‹‹ሕጉ የሚለው የያዝከውን የውጭ ገንዘብ አስመዝግበህ ከገባህ በ28 ቀናት ውስጥ ከአገር ይዘህ መውጣት አለብህ ወይም ወደ ባንክ ሄደህ መመንዘር አለብህ፤›› በማለት የሚደነግግ አሠራር ነው፡፡

በዚህ መሀል ግን ባንክ ሄዶ አንድ ዶላርን በ37 ብር ከመመንዘር በጥቁር ገበያ በ42 ብር ልመነዝረው ይላል፡፡ ነገር ግን በውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ማስቀመጥ ከተፈቀደ ግን ትክክለኛ ምንጭ ያለህ መሆኑ ስለሚረጋገጥ ነገ የውጭ ምንዛሪ ሊለወጥ ይችላል በሚል ወይም በውጭ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ማስቀመጡ ጠቃሚ ስለሚሆን ሕጋዊ አሠራርን በመፍጠርም መመርያው ይጠቅማል፡፡ በሌላ በኩል ግን እንዲህ ያለው ረቂቅ መመርያ እንዲተገበር የተፈለገበት ምክንያት መንግሥት የውጭ ምንዛሪን ግብይት ቀስ በቀስ በገበያ ለመወሰን ካለው ውጥን ጋር ሊያያዝ የሚችል ስለመሆኑ የሚጠቁሙም የባንክ ባለሙያዎች አሉ፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማስፋፋት የተለያዩ አማራጮች እየታዩ ስለመሆኑ እርግጥ ቢሆንም፣ በዓመታት ልዩነት የውጭ ምንዛሪን በገበያ ለመወሰን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት እንዲህ ባለው ሁኔታ በውጭ ገንዘብ አካውንት መክፈትና የመሳሰሉ ዕርምጃዎች መውሰዳቸው አግባብ በመሆኑም ነው ብሏል፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች