በሶፎንያስ ዳርጌ
የመጽሐፉ ርዕስ፡ አፄ ዮሐንስ ፬ኛ
ንዑስ ርዕስ፡ የአገር ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ፋና ወጊ ንጉሠ ነገሥት
ጸሐፊ፡ ተስፋ ኪሮስ አረፈ
የታተመበት ዘመን፡ 2012 ዓ.ም.
የመጽሐፉ ዋጋ፡ 250 ብር/USD/Euro፡ 35
የታተመበት ቦታ፡ Philo Printing (ከተማ፣ አገር አልተገለጸም)
ታሪክ መጻፍ ‹ባለዕዳነት› ነው፡፡ ታሪክን መመዝገብ ከአፈ ንጉሥነትና ከጸሐፌ ትዕዛዝነት በላይ፣ ከዜና መዋዕልና ገድልም ይልቃል፡፡ ምክንያቱም ታሪክ ሕዝቦች የዛሬያቸውን መሠረት የሚጥሉበት፣ ነጋቸውንም የሚወስኑበት አንድ ሁነኛ መንገድ ነው፡፡ የተለያዩ ሕዝቦችን በአንድነት፣ በኅብረት፣ በእኩልነትና በመተሳሰብ ተፈቃቅደው እንዲኖሩ ታሪክ የማይተካ ሚና አለው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን እውነተኛና ሐቀኛ የሆነ ጤናማ የታሪክ ትርክት ሲኖር ነው፡፡ በተቃራኒው ታሪክ በተወላገዱ ትርክቶች ሲከተብ መስመሩን ስቶ ለትውልዶች ጉድጓድ የሚምስ፣ የአባት ዕዳ ለልጅ የሚተርፍበት፣ ለጦርነት የሚያዘጋጅ፣ ዛሬን የሚነጥቅ፣ ነገን የሚያከስም ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ የብዙ አኩሪ ታሪክ ባለቤት አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያውያንም ታሪክን የሚሠሩ፣ ታሪክን የሚያውቁ፣ ‹‹ታሪክን ያወቀ ከጠቢብ ይበልጣል›› የሚል ብሒል ያላቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ‹‹በታሪካቸው ላይ የጋራ መግባባት የላቸውም፣ ከታሪክም ብዙ አይማሩም›› የሚል ወቀሳ ከውስጥም፣ ከውጭም ይቀርብብናል፡፡ ለዚህ አንዱ ገፊ ምክንያቱ ደግሞ ታሪካችን የሚጻፍበት መንገድ ነው፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የአገራችን የታሪክ መጻሕፍትን በመታዘብ በአጻጻፍ ረገድ የተመለከቱትን ግድፈት ‹‹አንደኛውን ለማሞገስ ሌላኛውን መውቀስ›› እንደ የአጻጻፍ ዘይቤ የሚከተሉ መሆናቸውን ‹አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ› በሚለው መጽሐፋቸው አሥፍረዋል፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት እውነተኛና ሐቀኛ ታሪክን እንደ አንደኛ ዘጋቢና ተቋዳሽ ለመጻፍ የታሪክ ጸሐፊዎች ሦስት ነገሮችን (ጸሐፊው ‹የእግዚአብሔር ስጦታ› ነው የሚሏቸው) ገንዘብ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ታሪክ ሲጻፍ ‹‹መጀመርያ ተመልካች ልቦና፣ የተደረገውን ለማስተዋል፣ ሁለተኛ የማያዳላ አዕምሮ በተደረገው ለመፍረድ፣ ሦስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ፣ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ›› በማለት የታሪክ ጸሐፊዎች ሊኖራቸው ስለሚገቡ ስጦታዎች አስቀምጠዋል፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፍት በሩቅ የተፈጸመውን ታሪክ ሲያሰናዱና ሲጽፉ ደግሞ ገንዘብ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ነጥቦችን ደግሞ እዝቅኤል (Ezekiel) እና ጀምስ (James) የተባሉ ተመራማሪዎች ‘History, the Historian and His works: Issues, Challenges and Prospects’ በሚል በጥናታዊ ጽሑፋቸው አቅርበዋል፡፡ የምንጭ ወይም የዋቢ መጻሕፍት አጠቃቀም፣ የደረጀና ጥልቅ ዕውቀት መኖር፣ የአገላለጽ ብቃት፣ ከአድልኦ ነፃ መሆን፣ የርዕሰ ጉዳይ መረጣ፣ ከወቅታዊ ፖለቲካ ነፃ የሆነ ትንታኔና የመሳሰሉትን ማሟላት እንደሚያስፈልግ ተመራማሪዎቹ ይመክራሉ፡፡
ኢኤች ካር (E.H. Carr) ‘What is History?’ በሚለው መጽሐፉ ‹‹ታሪክ የእውነታ ትንታቴ ሆኖ በታሪክ ጸሐፊዎች፣ ያያዙት እውነት፣ ማቋረጫ በሌለው ያለፈውና በወቅታዊ እውነታዎች የሚደረግ ፍጭትም ነው፤›› ይላል፡፡ እንዲሁም በዛሬው የግብረ ገብ ሕግ ትናንትን ለመዳኘት መሞከር ነገንና ዛሬን ለመረዳት ቅርብ አለመሆን ነው በማለት ይጠቅሳል፡፡ ቀጣይነት ያለው የመስተጋብር ሒደት በአገራችን አንዱ ያደባባይ ሙግት ግን ይኸው ታሪካችንና የታሪክ አዘጋገባችን እንደሆነ ገሃድ ነው፡፡ ካለፈው ለመማር ያልፈቀደ ልሒቅና ትውልድ፣ ታሪክን ያዛባል፣ ለመጥፎ አዙሪት የራሱን ድርሻ ያዋጣል፣ ከዛሬ ጋር ይጣላል/ያጣላል፣ የብዙዎች ነገን ያጨልማል፡፡
የነጋድራስ ገብረ ሕይወትን፣ የE.H Carr እንዲሁም የEzekiel እና James ሐሳቦች የጽሑፌ መንደርደሪያ ያደረግኩት ያለነገር አይደለም፡፡ በቅርቡ በተስፋ ኪሮስ አረፈ ተጽፎ ለንባብ የቀረበውን ‹‹አፄ ዮሐንስ ፬ኛ፡ የአገር ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ፋና ወጊ ንጉሠ ነገሥት›› መጽሐፍ ላይ የዳሰሳ ንባብ ለማቅረብ ማዕቀፍና ዓውድ ለማስያዝ እንዲረዱኝ ነው፡፡
የመጽሐፉ አወቃቀር
መጽሐፉ በአራት ምዕራፍና በአሥራ ዘጠኝ ንዑስ ርዕስ የተደራጀና ከምስጋና፣ መቅድምና ዋቢ መጻሕፍት ውጭ 310 ገጽ ያለው ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ነው። ምዕራፍ አንድ ታሪካዊ ዳራ በሚል ርዕስ የቀረበው የኢትዮጵያን ታሪክ ከአክሱማዊት ሥልጣኔ ጀምሮ በተለይም ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የአገረ መንግሥት ግንባታ በወፍ በረር ያስቃኛል። በምዕራፍ ሁለት የአፄ ዮሐንስ መንገሥና የግብፅ ወረራ በሚል ርዕስ የሚጠቃለሉ አፄ ዮሐንስ ከነገሡበት ጊዜ ጀምሮ የግብፅን ተደጋጋሚ ወረራ እንዴት አገራቸውን እንደተከላከሉና አይቀጡ ቅጣት እንደቀጡ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ የተነሱባቸውን ነገሥታት እንዴት ማስገበር እንደቻሉ ያትታል። የሃይማኖት ክፍፍልን በማስቀረትና ዳር ድንበርን በማስከበር እንዴት የአገርን አንድነት እንዳስጠበቁ የሚተረክበት ምዕራፍ ደግሞ በምዕራፍ ሦስት ነው። በምዕራፍ አራት የጣሊያን፣ የማህዲስት ወረራና የውስጥ ዘመቻዎችንና በመጨረሻም የመተማ ዘመቻን በመተረክ ፍጻሜውን ያደርጋል።
መጽሐፉ ምን ይዟል?
ጸሐፊው ይህን የአፄ ዮሐንስ ታሪክ ለመጻፍ ምን አነሳሳው? ጸሐፊው በመቅድሙ መግፍኤውን እንዲህ ያስቀምጣል፡- ‹‹ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአፄ ዮሐንስና በአጠቃላይ በትግራይ ልሒቅ የሰነዱት የተፈበረከና የተዛባ ትርክት ከመንገዴ አስወጣኝ።. . . በመሆኑም አፄ ዮሐንስና በዘመናቸው የነበሩት የትግራይ መሳፍንትና ሠራዊት ሕይወት የገበሩበት የጀግንነት፣ የድልና የአሸናፊነት ታሪክ የሕይወት መስዋዕትነት የሚያስከፍለውን አደራጅቶ ለተደራሲያን ማቅረብ እንዴት ያቅተናል? ከሚል ቁጭት በመነሳት. . .››
መጽሐፉ ከተነሳበት ዓላማ አንፃር ግቡን መትቷል? ምንስ አዲስ ነገር ይዞልን መጥቷል? የሚለውን እንመልከት። ስለአፄ ዮሐንስ አዲስ ነገር አይደለም የተጻፈው፣ ይልቅ ጸሐፊው በመቅድሙ እንደገለጸው የተለያዩ ዋቢ መጻሕፍት ስብስብ ነው። እንዲህ ከላይ ለመጻፍ ያነሳሳውን ነገር ስናስብ መጽሐፉ በምን መልኩ መቅረብ /Framing/ ላይ በአግባቡ መሥራት ያስፈልጋል። ጸሐፊው ፕሮፌሰር መስፍን ከመስመሬ አስወጡኝ ያለውን ሳነብ በቂ በሳቸው መጽሐፍ የተጠቀሱትን ጽሑፎችና የራሱን በቂ መልሶች ጠብቄ ነበር። እንዲህ ዓይነት መግፍኤ ምክንያት ግን ለአድሏዊ አጻጻፍ (Selective Citation) ተጋላጭ እንዲሆን ያደርገዋል። በተለያዩ ጸሐፍት የተጻፉ ‘ስም የማጠልሸት ትርክቶች’ እና መልሶቻቸው እንደ አንድ የመጽሐፉ ክፍል ቢኖሩ ለአንባቢም የተሻለ መረዳት አስተዋጽኦ ይኖረው ነበር።
እንደ እኔ መጽሐፉ በሁለት ትልልቅ ክፍሎች ቢደራጅ የተሻለ ነበር እላለሁ። አንዱ በአፄ ዮሐንስ የሚነሱ ወቀሳዎችና መልሶቻቸውን የያዘ። በዚህ ክፍል (ሀ) በአፄ ቴዎድሮስ ውድቀት ላይ ከእንግሊዝ ጋር አበሩ ስለመባላቸው (ለ) በአንድነትና ነገሥታቶቻችንና (ሐ) አፄ ዮሐንስ በየሙስሊሙ ማኅበረሰብ የወሰዱት ዕርምጃ የሚሉት ቢጠቃለሉ። እንዲሁም በሁለተኛው ክፍል (ሀ) የአገር አንድነት የሃይማኖት ክፍፍልን በማጥራት (ለ) የአገር ዳር ድንበር የማስጠበቅ ገድል (ሐ) ድኅረ መተማና ኢትዮጵያ በሚል ቢቀርቡ ይበልጥ ተነበቢ ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ።
ከላይ ያነሳኋዋቸው ነጥቦች ባልደረጀ መልኩ በመጽሐፉ በተለያዩ ክፍሎች ተገልጸዋል። ለምሳሌ ለአፄ ቴዎድሮስ ውድቀት ማነው ተጠያቂው? የሚለው ሐሳብ ሲነሳ ለብዙዎች የአፄ ዮሐንስ ስም ከፊት ይቀድማል። ይህ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ‘መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ’ እና ‘አዳፍኔ’ በሚለው መጽሐፎቻቸው አፄ ዮሐንስ የእንግሊዝን ጦር ሲቀበሉ፣ መንገድ መርተው ሲሸኙና ኋላም የተወላቸውን የጦር መሣርያ በመጥቀስ አፄ ዮሐንስን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ተስፋ ኪሮስ ደግሞ በመጽሐፉ የተለያዩ ጸሐፍትን ጠቅሶ በምዕራፍ አንድ ‘ታሪካዊ ዳራ’ በሚል ርዕስ ስር በጊዜው አገር ምድሩ እንዲሞት የሚመኘውና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ሆድና ጀርባ የሆነው አፄ ቴዎድሮስ እንዲወድቅላቸው ንጉሥ ምኒልክና ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ ባያሌው እንደሠሩ ይገልጻል (ገጽ 17 እስከ 50)። ሆኖም ጸሐፊው ለአፄ ቴዎድሮስ ውድቀት አፄ ዮሐንስን ተጠያቂ ላለማድረግ የሄዱበት ርቀት ውኃ አያነሳም።
በተለያዩ መጻሕፍት በተለይም ጸሐፊው ራሱ በተጠቀመባቸው ማጣቀሻዎች አፄ ምኒልክ፣ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ እንዲሁም አፄ ዮሐንስ በየፊናቸው የድርሻቸውን ተወጥተዋል። ታሪኩ እንዲህ በነበረበት ሁኔታ በፕሮፌሰር መስፍን አፄ ዮሐንስን ብቻ የውድቀቱ ሁሉ ተጠያቂ ወይም በተስፋ ኪሮስ አፄ ምኒልክና አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ብቻ ተጠያቂ ማድረጋቸው እየመረጡ ማንበብና ማጣቀስ እንደሚሉት ዓይነት ነው።
ሌላው በአፄ ዮሐንስ የሚነሳው ወቀሳ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ የወሰዱት ዕርምጃ ነው። በመጽሐፉ በምዕራፍ ሦስት ከገጽ 155 እስከ 172 በሚገባ ተዳሷል። ሆኖም ከላይ እንዳልኩት በተለየ ምዕራፍ እንጂ እንዲሁ በንዑስ ርዕስ ስር መሸጎጥ አልነበረበትም። በምዕራፍ አንድ ታሪካዊ ዳራ በሚል ርዕስ የቀረበው ሐተታ ግማሽ ታሪካዊ ዳራ፣ ግማሽ ስለአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ሰፊ ትንታኔ የሰጠበት ክፍል ነው (ከገጽ አንድ እስከ 50)። ምሉዕ ታሪካዊ ዳራ ትንታኔ አይደለም፣ ይበልጥ ከላይ እንደገለጽኩት በተለያዩ ምዕራፎች መካተት የሚገባቸው ሆነው አግኝታቸዋለሁ።
በመጽሐፉ ባይካተቱ ወይም በሁለት ሦስት አንቀጽ መታለፍ የሚገባቸው ጽሑፎች ተንዛዝተው የቀረቡበት ሌላው የታዘብኩት ነገር ነው። ለምሳሌ በምዕራፍ አራት ከተጠቀሰው ርዕስ ውጭ (ያለው ፋይዳ በአጭሩ ማለፍ እየተቻለ) በሆነ መልኩ ‘በንጉሥ ምኒልክና በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት መካከል የተደረገ ጦርነት’ የሚለው ንዑስ ርዕስ በተለጠጠ መልኩ ከገጽ 183 እስከ 192 ተተርኳል።
የሐሳብ ድግግሞሽ አልፎ አልፎ ይስተዋልበታል። ለምሳሌ አፄ ዮሐንስ በሥልጣን ዘመናቸው የሰላም ጊዜ ያሳለፉባቸው ስምንት ዓመታት በብዙ ቦታ በተደጋጋሚ በተለያዩ ጸሐፊዎች ተገልጸዋል። እነዚህ የሰላምና የኢኮኖሚ ዓመታት ግን መገለጫቸው ምን እንደሆነ አልተገለጸም። ከአፄ ሱስንዮስ ዘመን ጀምሮ በሃይማኖት ስም ደም አፋሳሽ ታሪክ ሌላው በምዕራፍ ሦስት በተደጋጋሚ የተገለጸ ርዕሰ ጉዳይ ነው፣ ይህም በትረካው ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንዳሳረፈ አምናለሁ።
በታሪክና ሥነ ጽሑፍ የጠራ ወሰን በሌለበት በዚህ የድኅረ ዘመናዊ ዘመን የታሪክ አጻጻፋችንና በሥነ ጽሑፍ አላግባብ ለወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ማስታገሻ ዕልፍ ሲልም ለእንካ ስሊያንታ ግብዓት ማድረግ በተለመደበት ጊዜ ‘አፄ ዮሐንስ ፬ኛ’ መጽሐፍ እንደዚህ ዓይነት ተፅዕኖ ያልጎላበት መጽሐፍ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የአፄ ዮሐንስ ቀለም
መጽሐፉ በአፄ ዮሐንስ ላይ የሚነሱ ዋና ዋና ጉዳዮችን ዳሷል። በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ተካሂደዋል ያላቸውን ስም ማጥፋቶች ፍትሐዊ ሊባል በሚችል መልኩ ለመከላከል ጥረት አድርጓል። በተለይም አፄ ዮሐንስ ከዘመነ መሳፍንት በባሰ መልኩ የተዳከመውን ማዕከላይ መንግሥት በማጠናከር የነበራቸውን አስተዋጽኦ በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል። የሃይማኖት ክፍፍልን በማጥራት በተለይም የቦሩ ሜዳ የሃይማኖት ክርክርን ከበቂ ታሪካዊ ዳራው ጋር የተገለጸበት ክፍል የአፄ ዮሐንስን ደማቅ ቀለም የሚያሳይ ነው። ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ የውጭ ወራሪዎችን ድል በመንሳት የአገራቸውን ዳር ድንበር ያስከበሩበትና የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል የወሰዱት ዕርምጃ የፖለቲካ ብስለታቸውን ያጎላዋል። ይህም ሌላው የአፄ ዮሐንስ ዓብይ አሻራ ነው።
ሌላው በመጽሐፉ የጉራዕ ድል የተተረከበት ክፍል፣ ባህሩ ዘውዴን ጠቅሶ ድሉን ከዓድዋ ድል ጋር ያነፃፀረበት መንገድም ድሉ በበቂ ያልተነገረለት፣ በኪነ ጥበብ ሥራዎች ቸል የተባለ የአገር አሻራ እንደሆነ ያሳያል። ባህሩ ዘውዴ ‘ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ’ በሚለው መጽሐፋቸው በጉራዕ ድል በብዛት ከትግራይ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃም እንዲሁም ከሸዋ የተውጣጣ ሠራዊት እንደተሳተፈና በድኅረ ጉራዕ ጦርነት የተገኘው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድል በመግለጽ ነው ድሉን ከዓድዋ ድል ጋር አብሮ መነሳት እንዳለበት ያወሱት (ገጽ 81 እስከ 90)።
የምንጭ/የዋቢ መጻሕፍት አጠቃቀም
አፄ ዮሐንስ ፬ኛ መጽሐፍ ከተለያዩ መጻሕፍት ስለአፄ ዮሐንስ መዋዕል የተዘገቡ/የተመዘገቡ መጽሐፎች ለማሰባሰብ የተደረገ ሙከራ ነው። በመጽሐፉ በተደጋጋሚ የእንግሊዘኛ ጽሑፎችንና ተዛማጅ ትርጉማቸውን በብዛት ተጠቅሷል። በወሳኝና መታለፍ በሌለባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ብቻ ዋናውን ጽሑፍ ከተዛማጅ ትርጉም ጋር ብቻ ማቅረብ በቂ ነበር። ለምሳሌ ከገጽ 223 እስከ 228 በስድስት ገጽ የተገለጸው ሐተታና ሌሎች ተደጋጋሚ የእንግሊዝኛና ተዛማጅ ትርጉሞች የመጽሐፉ ፍሰት ላይ እንቅፋት ፈጥረዋል።
ሌላው አንድን ሐሳብ ለማጎልበት ተከታታይነት ያላቸው በተለያዩ ጸሐፊዎች የተጻፉ ጽሑፎች አንባቢን ያሰለቻሉ። ጽሑፉ የሁሉንም ጸሐፊዎች ሐሳብ በሚጠቀልል መልኩ መጻፍና በግርጌ ማስታወሻ ላይ የሁሉንም ጸሐፊዎች መጽሐፍና የተወሰዱበት ገጽ መጥቀስ ለንባብ ምቹ ያደርገዋል።
በአፄ ዮሐንስ ፬ኛ መጽሐፍ እንደ ድክመት ያየሁት የትርጉም መጻሕፍትን መጠቀሙ አንዱ ነው። እንደ ታሪክ ተመራማሪ/ጸሐፊ ከትርጉም ይልቅ በተቻለ መጠን ዋናውን መጽሐፍ ማንበብ ተዓማኒነቱን ከፍ ያደርገዋል። እንዲሁም የትርጉም መጻሕፍት እንደማጣቀሻ ሲጻፉ በተርጓሚያቸው ሳይሆን በዋና ጸሐፊዎቹ መጠቀስ አለበት። በመጽሐፉ ይህ ሲሆን አላየሁም። ለምሳሌ ሙሉቀን ታሪኩ ‘አፄ ቴዎድሮስ (ትርጉም)’፣ ዓለማየሁ አበበ ‘የኢትዮጵያ ታሪክ (ትርጉም)’ እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።
ሠርግው ሀብለ ሥላሴ ‘Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270’ እንዳሉት፣ በይልማ ደሬሳ የተጻፈው ‘የኢትዮጵያ ታሪክ፣ በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን’ ዓይነት በበቂ ማጣቀሻ ያልተጻፉ የታሪክ መጻሕፍት እንደ ዋቢ መጠቀም ተዓማኒነቱን ያሳጣዋል ይላሉ፡፡ እንዲሁም በደብተራ ፍስሓ አብየዝጊ የተጻፈው ‘ታሪኽ ኢትዮጵያ’ ጸሐፊው ከነበሩበት ዘመን ውጭ ያለው ምስክርነት ወይም ታሪክ ምንጮችን ተጠቅመው የጻፉት ባለመሆኑ እንደ ማጣቀሻ መጠቀሙ አይመከርም፡፡
በመጽሐፉ በተለይም ከገጽ 185 በኋላ አጻጻፉና የዋቢ መጻሕፍት አጠቃቀሙ ላይ ጥድፊያ የበዛበትና አልፎ አልፎም ካለ በቂ ትንታኔ እንዳለ የተቀዱ (Copy and Paste) ናቸው። መጽሐፉ በዋቢ ማጣቀሻነት ሀብታምና ብዙ፣ በቀላሉ የማይገኙ መጻሕፍት ተጠቅሟል ለማለት አያስደፍርም።
ትኩረት የሚሹ
መጽሐፉ የአርትኦት ሥራውን ጥንቅቅ አድርጎ የጨረሰ ነው የሚባልለት መጽሐፍ አይደለም። የቃላት ግድፈቶች ይስተዋላሉ። በመጽሐፉ የካርታ፣ ፎቶ በተለይም ስለአፄ ዮሐንስ ከተጻፉ መጻሕፍት አለማካተቱ አንዱ ጉድለቱ ነው። በተለይም የአፄ ዮሐንስ የአገር ዳር ድንበር ለማስከበር የዘመቱባቸው፣ የአገር የውስጥ ጉዳዮችን መልክ ለማስያዝ የተደረጉ ዘመቻዎችን የሚያሳዩ ካርታዎች ቢካተቱ መጽሐፉን ምሉዕ ምሥል እንዲኖረን ያደርጋል።
ሌላው በአፄ ዮሐንስ ፬ኛ መጽሐፍ ለወሳኝ የመከራከርያ ጉዳዮች የሚያግዙ ደብዳቤዎችና ከዋናው ቅጂ ፎቶ ኮፒ ወይም ስካን የተደረጉ ጽሑፎች በአባሪ ላይ ቢካተቱ ተዓማኒነቱን ያጎሉት ነበር። በመጽሐፉ ምንም ዓይነት አባሪ አለመካተቱ ደግሞ ሌላው ክፍተት ይመስለኛል።
የዋቢ መጻሕፍት የአጻጻፍ ችግር ሌላው እንደ ክፍተት ያየሁት ነገር ነው። መጽሐፉ በአካዴሚ ሰዎችም ሊገመገም፣ እንደ ምንጭ ሊጠቀስ የሚችል በመሆኑ እንደ መጽሐፍ የተስተካከለና ምሉዕ መረጃ ሊያሳይ በሚችል መልኩ ሊቀርብ ይገባል። ለምሳሌ ‘ተክለ ፃድቅ መኩሪያ አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት’ ይህ አገላለጽ ሙሉ አይደለም። የታተመበት ዘመን፣ የታተመበት ማተሚያ ቤት አይገልጽም። ይህ አገላለጽ ሁሉም እንደ ዋቢ መጻሕፍት የተጠቀሱትን ያጠቃልላል።
የትርጉም ዋቢ መጻሕፍት ሲጻፉ ተርጓሚው ሁለተኛ አካል እንጂ ዋና ጸሐፊ ስላይደለ በደራሲዎቹ/የታሪክ ጸሐፊዎቹ ስም መጻፍ አለበት። በአፄ ዮሐንስ ፬ኛ መጽሐፍ የትርጉም ሥራዎች ኦርጅናሉን (ዋናውን) የመጽሐፉን ርዕስና የደራሲው/ጸሐፊውን ስም ሲጠቅስ አናይም። በዋቢ መጻሕፍት ዝርዝርም ቢሆን የተጻፉበት መንገድ ልክ አይደለም። ለምሳሌ፣ ‘ዓለማየሁ አበበ የኢትዮጵያ ታሪክ (ትርጉም)’ ይላል። በመሠረቱ መጽሐፉ ‘አንድርዜይ ባርትኒስኪና ዮዓና ማንቴል ኒየችኮ፣ 1971፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመርያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ኦስሊኔውም ቭሮክላቭ (ፖላንድኛ)፣ አካዴሚ ፌርላግ ቤርሊን (ጀርመንኛ)፣ (ትርጉም)።’ ተብሎ መገለጽ ነበረበት። ምዕራፎች ሲጻፉ በአዲስ ገጽ አለመጀመሩ፣ ምዕራፎችና በእያንዳንዱ ምዕራፎች የተዘረዘሩት ንዑስ ርዕሶች የተጻፉበት መንገድ ለማንበብ የማይጋብዝ ከመሆኑ ባሻገር ምዕራፎች እንደ ተራ ርዕስ ሊዘለሉ ይችላሉ።
በመጨረሻም
ሐሳብ መሠረት ያደረገ ሙግት በአገራችን አልተለመደም። ከዋናው ታሪክ ማን አድርሶን? ስለአስኳሉ ሳይሆን ስለቅርፊቱ ስንነታረክ መሽቶ ይነጋል። የእኔ ሰው ተነካብኝ ተብሎ የነኪውን ‘ሰው’ ከመዝለፍ በዘለለ ስለተፈጸመው ታሪክ ፋይዳ፣ መነሻ፣ ጉዳት ዘርዝሮ ለመተንተን እንግዳ ነን። በዚህም በታሪክና በሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ አፄዎቻችን፣ የጦር መሪዎችና የተለያየ አገራዊ አበርክቶ ያላቸው ጀግኖችን ለአካባቢው ሰዎች በመተው እየመረጡ ማግነንና እየመረጡ ማኮሰስ ላይ በርትተናል።
በአያት ታሪክ ልጅን መግደል፣ በማናውቀው ትናንት ዛሬን ማደብዘዝ ልምድ አድርገነዋል። በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የተጻፈው ‘የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የዓድዋ ድል’ በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 173 የልዑል ራስ አርአያ ሥላሴ ሚስት የነበሩት ንግሥት ዘውዲቱ፣ አፄ ምኒልክ መክዳታቸው እርግጥ ከሆነ ዘውዲቱን እንደ መያዣ እናቆያቸው ለሚለው የመኳንንቶቻቸው ምክር አፄ ዮሐንስ እንዲህ ነበር የመለሱት ‘በአባቷ በደል እርስዋን አልቀጣምና ምንም ቢሆን ይህን ምክራችሁን አልቀበልም’ አሏቸው። እስከ መቼ ዛሬአችንን ትናንቶች እየቀሙን እንኖራለን?
አፄ ዮሐንስ ፬ኛ መጽሐፍ ክፍቱን የተተወ መጽሐፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በመጽሐፉ የመተማን ጦርነት በሚተርክበት ክፍል የጸሐፊው ትንታኔ አለመኖሩና በዋይልድ ክሊመንትስ የተጻፈውንና ተዛማጅ ትርጉሙን በማቅረብ መጽሐፉን ይደመድማል። እንደ እኔ ‘ድኅረ መተማ’ የሚል ራሱን የቻለ ርዕስ ቢኖረውና በተሻለ ማጠቃለያ (እንደ መውጫ) እና ትንታኔ የመጽሐፉ የመጨረሻ ክፍል ቢሆን ጥሩ ይሆን ነበር የሚል እምነት አለኝ።
እንደ አፄ ዮሐንስ ዓይነቱን ባለ ደማቅ ቀለም የአገር መሪ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የተውትን አሻራ በሥነ ጽሑፍ፣ ቲያትር፣ ሙዚቃ፣ ታሪካዊ ልቦለድ ከፍ ማድረግ ለአገር ግንባታ የራሱ አስተዋጽኦ አለው እላለሁ። በዚህ አንፃር የተስፋ ኪሮስ ‘አፄ ዮሐንስ ፬ኛ’ የንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ቀለም ኢትዮጵያ ታሪክ ያስቃኘ መጽሐፍ ነው። ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ በሁለተኛ ዕትሙ ከላይ እንደ ድክመት የተነሱትን ሐሳቦች በማስተካከል ቢታተም መጽሐፉን ጥሩ ያደርገዋል እላለሁ።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡