በሔኖክ ያሬድ
‹‹ጋሼ ለማ፡-
ባላገርም ሥልጡን ከተሜም ነበር፡፡
ጋሼ ለማ፡-
ገበሬም ወታደርም ነበር፡፡
. . .
ጥበበኛም የልማት አርበኛም ነበር፡፡
አስተማሪ አስታራቂም ነበር፡፡
. . .
አፍቃሪ ተፈቃሪም ነበር፡፡
የቤተሰብም የሥነ ምግባራት አርአያም ነበር፡፡
ጋሼ ለማ፡-
ለጥበብ፣ ለልማት፣ ለሰላም፣ ለፍቅር
ለእኩልነት ለአንድነት እንደታገለ
አደራውን በትውልድ ላይ ጥሎ
እነሆ በክብር አረፈ፡፡››
ከስድስት አሠርታት በላይ በሥነ ሥዕሉ ማዕድ ገዝፈው የኖሩት ሠዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ (1921-2013) ሥርዓተ ቀብር ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ደሎ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲፈጸም፣ ወንድማቸው ሠዓሊና ደራሲ ገጣሚ አሰፋ ጉያ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ያስተጋቡት ድምፅ ነበር፡፡
በጥበብ ለጥበብ የኖሩት፣ ጥበበኛ በጥበብ እግር ይመላለሳል እንዲሉ፣ በእግረ ጥበብ የተመላለሱትና ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በ92 ዓመታቸው ያረፉት የአየር ኃይል ሻምበል ለማ ጉያ፣ ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመው በወታደራዊ አጀብና በአየር ኃይል ማርሽ ባንድና በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ባንድ ታጅቦ ነው፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸው ከመፈጸሙ በፊትም በቢሾፍቱ ስታዲየም የክብር አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡
‹‹የጥበበኛው ታሪክ ይቀጥላል፡፡ የአባቴን ታሪክና ገድል ለማስቀጠል ዝግጁ ነኝ፤›› በማለት ቤተሰባቸውን ወክላ የሐዘን መግለጫዋን በሽኝቱ ላይ ያሰማቸው ሠዓሊት ሰላማዊት ጉያ ናት፡፡
ከሥነ ጥበብ ትሩፋታቸው
ልሒቅ ሥነ ጥበበኛ ለማ ገጸ ታሪካቸው እንደሚያሳየው፣ በቆዳ ላይ መሣል የጀመሩት በኅብረተሰብአዊት ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዘመን ጀምሮ መሆኑንና በመጀመሪያ በፍየል ቆዳ ላይ የሣሉትም የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን ሲሆን ከኢትዮጵያ ነገሥታትና መሪዎች መካከል ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድረስ የነበሩትን ሠርተዋል። ሥዕላቱ በቢሾፍቱ ከተማ በገነቡት አፍሪካ አርት ጋለሪ/ ሙዚየማቸው ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የየብሔረሰቡን የአለባበስና የአኗኗር ዘይቤን የሚገልፁ በተለይም የኦሮሞን ሕዝብ ትውፊትን የሚያጎሉ ሥዕሎችን በመሣል ይታወቃሉ፡፡፡
በ65 ዓመታት የጥበብ ጉዞአቸው ያፈሩት የጥበብ ሥራ 10,000 እንደሚደርስ ይወሳል፡፡ ሥዕሎቻቸውን ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች በዓውደ ርዕይ አሳይተዋል፡፡
ስመጥር ካደረጓቸው ሥራዎቻቸው መካከል በግንባር ቀደምነት የምትጠቀሰው “ቋንጣ” የተሰኘችው ናት፡፡ የዚህችን ሥዕል አንድምታ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በሰጣቸው ጊዜ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡-
“በተለይ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ አድናቆትን የሰጠውና በሹማምንት ልዩ ትርጉምና አቃቂር በማውጣት ከየወቅቱ አዛዦች ጋር እንዲላተም ካስደረጉት የበኩር ሥራዎች ሳትጠቀስ የማታልፈው ቋንጣ የምትባለው ሥዕል ነች፡፡ ቋንጣ የአፍሪካን የሀብት ምዝበራ ወይም ሙስናን ፍንትው አድርጋ ታሳያለች፡፡
“በአንድ ቤት ጓዳ ውስጥ ቋንጣ በቀይ መልኩ ተዘልዝሎ ይታያል፡፡ ድመቶች ቋንጣውን መዥርጠው ለመብላት ይታገላሉ፡፡ ጠፍሩ አልጋ ላይ በድምሩ አራት ድመቶች ወጥተዋል፡፡ አንደኛው ግድግዳው በጥፍሩ ቧጥጦ ያወርዳል፡፡ አንዱ ቁመቱ አልደርስ ብሎታል፡፡ አንደኛው ደግሞ በእጁ የገባለትን እንደያዘ ሌላ ለማግኘት አንጋጧል፡፡ በእነርሱ ግፊያና ግርግር ጮጮ ሙሉ ወተት ተደፍቷል፡፡
“የወተቱ አወራረድ የዓባይ ፋፏቴን ተመስሎ ቀርቧል፡፡ የመጨረሻው ድመት የሸረሪት ድር የወረሰውን ድብኝት አፍጦ በሸረፋት ድር የተያዘውን ነፍሳት ለመያዝ ያስባል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ ግን ከአልጋው ሥር አይጥ እሸት በቆሎ ትቀረጥፋለች፡፡ ይህንን ሥዕል ስትመለከቱት የራሳችሁ ፍርድ ትሰጣላችሁ፡፡”
ቢቢሲ በአንድ ወቅት ስለ ቋንጣውና ስለድመቶቹ እንዲሁም ስለወተቱ ሠዓሊ ለማ ጉያ እንዲያብራሩለት ጠይቋቸው፣ ሥዕሉን ከሠሩት 42 ዓመታት ማስቆጠሩንና በዚህ ሥራቸውም አፍሪካና ችግሮቿን ያሳዩበት እንደሆነ እንደሚከተለው ገልጸውለት ነበር።
‹‹የአፍሪካ መሪዎችን በድመቶቹ መስለው የአገራቸውን ሀብት በሙስና ሲመዘብሩ፣ በአልጋው ሥር የሚታዩት የአኅጉሪቷ ጠላት አይጦች ደግሞ የአፍሪካን ሀብት ሲቀራመቱ ይታያሉ፡፡ እየፈሰሰ ያለው ወተትም ያለጥቅም ለዘመናት የሚፈሱት የአፍሪካ ወንዞች ምሳሌ ነው።››
ሥነ ጠቢቡ ለማ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የሃይማኖቶች መቻቻል፣ ኢሬቻን፣ የተፈጥሮ ሀብትና የሕዝቡን አኗኗር የሚያሳይ “እናት” ሌላኛዋ ዕውቅ ሥራቸው ስትሆን ከኢሬቻ ከክብረ በዓል ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች ባህላዊ ተግባራትን የሚሳየው “ኦዳ” ም ተጠቃሽ ነው፡፡