ሰላም! ሰላም! እንዴት ከረማችሁ? በዶናልድ ትራምፕ ንግግር የተበሳጫችሁ በሙሉ ንዴታችሁን ዋጥ አድርጉ፡፡ ‹‹ሙያ በልብ ነው›› እንዲሉ፣ የተከፋፈለ ልብን አንድ አድርጎ ለጋራ ጉዳይ መነሳትን የመሰለ ቁም ነገር እንደሌለ እናንተ ከእኔ በላይ ታውቃላችሁ፡፡ ከዛቻና ከፉከራው ቀነስ አድርጎ ቁም ነገሩ ላይ ማተኮር ነው የሚያዋጣውና በርታ እንበል፡፡ ሰሞኑን አንድ ቅጥቅጥ አሻሽጬ ኮሚሽኔን ልቀበል የሆነ ካፌ በረንዳ ላይ ተጎልቼ የባጡን የቆጡን አስባለሁ። ለካ አንዱ ከጎኔ ይነድፈኝ ይዟል። መቼም የእናንተ ነገር አይታወቅም። ዘመኑን አስባችሁ እባብ ወይ ጊንጥ የነደፈኝ ይመስላችኋል ብዬ እኮ ነው። ይኼ አስመስሎ መሣል ነገር አለ አይደል? እንደ ፎቶግራፍ? ንድፍ ስል እሱን ነው። ለነገሩ ዘንድሮ ሳይቀነስ ሳይጨመር የማይገለበጥ ነገር የለም። ‘ኮፒ ፔስት’ ይለዋል እንግሊዝኛው። በጥበብ ስም ‘ኮፒ’ መብዛቱ ገርሞን ሳናበቃ ልብ ‘ኮፒ’ ለማድረግ የሚጥርም እያየን ነው። ልብ አውልቁ እኮ በዛ እናንተ!
እናላችሁ ያለ ፈቃድ ያለ ኑዛዜ በልሙጥ ወረቀት መገልበጤ ሳይሆን ያናደደኝ በእስክሪብቶ መሣሌ ነው። ቆፍጠን ብዬ ‹‹እንዴት አንተ? እግዜር እኮ ሲፈጥረኝ እንድሳሳት ጭምር ነው። እንድሳሳት ብቻ ሳይሆን ተሳስቼ እንድታረም አድርጎ ነው። እንዴት አንተ ላታርም ላታርቅ በእስኪቢርቶ ትቸከችከኛለህ?›› እለዋለሁ፣ ‹‹ሥልጣን ስለሌለኝ እርሳስ ከየት አመጣለሁ?›› አይለኝ መሰላችሁ? እንዲያ ሲለኝ ላጲስ መዋጥ አማረኝ በቃ። የት አባቴ ልግባ? በጣም ነዶኝ ስለነበር፣ ‹‹እሺ እንዴት ሳታስፈቅድ ትሥለኛለህ?›› ብዬ ስደነፋ (ውሸት ምን ያደርጋል ሸጋ አድርጎ ሥሎኛል። ቀን አልወጣልኝ እያለ በዚያ ስይዘው በዚህ እየተበተብኝ ለምን እንደሆን እንጃ ፎቶና ሥዕል ይወጣልኛል፣ ኧረ እኔ ምን አውቄ?) ‹‹እዚህ አገር ለመጻፍና ለመናገር እንጂ ፈቃድ የሚያስፈልገው ለማየትና ለመስማት ሜዳው ነፃ ነው፤›› ሲለኝ ‘አሃ ይኼ ሰው ከጀርባው ሌላ ተልዕኮ ይኖረዋል’ ብዬ ብድግ አልኩ። በኋላ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ የገጠመኝን ስነግረው፣ ‹‹ደግሞ ብለው ብለው ፒካሶንም ማኖ አስነኩት?›› ብሎ እሱ ብሶብኝ ቁጭ። አሁን ፒካሶ ቢሰማ ምን ይላል? ሸማ ያለ ፈርጁ ተለበሰ ብሎ ያብዳል? ወይስ እሱም እንደ እኛ እንደ ዘመኑ ሰዎች ዋናው ቻፓ ነው ብሎ ምን ቸገረኝ ይላል? አንዱንም እንደማይል አውቄው አይደል እኔስ የምለፈልፍ!
እናላችሁ አንድ አዲስ አስፋልት መንገድ ተመረቀና ሥራ ጀመረ አሉ። ወዲያ ወደ ሰሜኑ በአንዱ ከተማ ነው። በኋላ ቢታይ ቢታይ ሰው በዜብራው አልሻገር ይላል። ‹‹ለምንድነው በዜብራ የማትሻገሩት?›› ሲባል መልሱ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ‹‹ያልቃል ብለን›› ነው አሉ ተባለ፡፡ ጉድ እኮ ነው። ታዲያ የማያልቅ ነገር አለ? ሲጨንቀውማ የትራፊክ ፖሊሱ በዜብራ የማይሻገር 200 ብር፣ ግራውን ይዞ የማይጓዘውን 300 ብር ቅጣት እንዲከፍል ወሰነ ተባለ። እኔ ይኼን አላውቅም። አንድ የሚሸጥ ቶርኖ አለ ተብዬ ለማየት ከከተማ ወጥቼ ርቄ ሄጃለሁ። አዲስ አበባ እንደ ለመድኩት እንዳሻኝ ስሻገር እንዳሻኝ ቀኜን ይዤ ስጓዝ የአካባቢው የትራፊክ ፖሊስ ቁም አለኝ። ‹‹ምንድነው የሚለው?›› ብዬ ዘወር ብል በአካባቢው ምንም ተሽከርካሪ የለም። አሁንም ስጓዝ ፊሽካ ነፍቶ፣ ‹‹አንተን እኮ ነው፤›› ብሎ ጨኸ። ጩኸቱ የእያሪኮን ቅጥር የሚያፈርስ ይመስል ነበረ!
‹‹እንዴት ነው እዚህ ደግሞ የተሽከርካሪ እጥረቱን በእግረኞች ዱካ ነው እንዴ የሚያጣጡት?›› ብዬ ቆምኩ። ‹‹ግራህን ይዘህ አትሄድም? ስንቴ ይነገራችሁ ግን እናንተ?›› ብሎ ተቆጣ። ‹‹የምን ግራ?›› አልኩኝ ራሴ ግራ ገብቶኝ። ፖሊሱ አተኩሮ ሲያየኝ ለአካባቢው እንግዳ እንደሆንኩ ገብቶት፣ ‹‹እዚህ እንደ አዲስ አበባ አይደለም። ስትጓዝ ግራህን ይዘህ ካልተጓዝክ ስትሻገር ዜብራ ላይ ካልተሻገርክ…›› ብሎ የነገርኳችሁን መቀጫ አብራራና ለቀቀኝ። በጣም ገረመኝ። ከዚህ በኋላ ነው ነዋሪው ዜብራው እንዳያልቅ እያለ አልሻገር ብሎ እንዳስቸገረ የሰማሁት። የትራፊክ ፖሊሱን ምሕረት ተቀብዬ በስተግራ በኩል ተሻግሬ ወደፊት ስጓዝ ከመሀል ከተማው ይልቅ ዳር ዳሩ እንዴት እየሠለጠነና ራሱን እየገራ እንደሚጓዝ አስተውል ጀመር። በኋላ አዲስ አበባ ተመልሼ ለባሻዬ ልጅ ሳወጋው፣ ‹‹እና የፌዴራሊዝም በጎ ገጽታ ነው እያልከኝ ነው?›› ብሎ ነገር ሊጀምረኝ ሞክሮ ነበር። ልክ እንደ ዶናልድ ትራምፕ ዕውቀት አጠር ወሬ በነበር ቀረ እንጂ!
ያው እንደነገርኳችሁ የሄድኩት ለሥራ ነበር። እናም አንዳንድ ነገሮችን አተኩሬ ማጤኔ አልቀረም። በተለይ ‘የካሽ ፍሎውን’ ነገር። ከዚህ በፊት ከምጠብቀው በላይ በሰው እጅ ላይ ያለው ገንዘብ ባንክ ገብቷል ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው ንብረትና የመሬት ዝውውርና ሽያጩ በባንክ አማካይነት በሚደረግ የገንዘብ ቅብብል ይቀላጠፋል። ‹‹ከዚህ በፊት ሰው ገንዘቡ ላይ ይተኛበት ነበር…›› አለኝ አንድ ነቃ ያለ ሊስትሮ ጫማዬን እየጠረገ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹በቃ በፊት ብሩ ላይ ተቀምጦ አራጣ ማበደር ነው። አራጣና አራጣ ብቻ ነው ጨዋታው የነበረው። ለምሳሌ ያ የማነው የጋሽ ማንትሴ ልጅ ብትል፣ እዚያ ታች ያለው ማንትሴ የሚባል ቤት ዓይተሃል? እነሱ ብትል ኧረ ተወኝ…›› ብሎ ዝም አለ። ሊስትሮው የነገረኝን ይዤ ተለቅ ያለ ሰው አገኘሁና ቀስ ብዬ ነገሩን ባነሳው፣ ‹‹በፊት አራጣው ነበር ችግሩ። አሁን ደግሞ አላስቀምጠን ያለው…›› ብሎ ግራ ቀኝ ተገላመጠና ‹‹አጉል አምልኮ ነው…›› አለኝ ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ። ጉድ ፈላ በሉ!
‹‹አምልኮ?›› ገርጥቼ ቀረሁ። የአላዲንና የፋኖሱ ዓይነት አስማት ነው? ወይስ ከዚያም እልፍ ይላል? እያልኩ በልቤ ማብራሪያ ስጠብቅ፣ ‹‹ሰው አሁን ብልጥ ሆኗል። እንደ ድሮው ፊት ለፊት መግደል መገዳደል እየተወ ነው። እስራቱም እየጠበቀ መጥቷላ። ስለዚህ ምን ተጀመረ አምልኮ። እከሌን በምናምን እንድፋው ይባላል… ማሴርና ሸር ማዳወር ነው…›› ሲለኝ የመጣሁበትን ትቼ በሸዋ በር በኩል አዱ ገነት መመለስ አማረኝ። አጠገቤ ተቀምጣ የምትሰለቸኝ ማንጠግቦሽ ከበርካታ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ሆኜ ላቅፋትና ጉያዋ ልሸጎጥ አማረኝ። እናስ ስለው ጎልማሳውን፣ ‹‹ምን እናስ አለው? ዋናው አለመቀደሙ ነው። ይልቅ አንተ ምን ልትሠራ መጥተህ ነው?›› ብሎ ወደ እኔ ዞረ። ማንን አምኜ ምን ልለው ነበር ድሮስ? የትራምፕ ድንቁርና አልበቃ ብሎ እዚህ ደግሞ የባሰ አለ፡፡ ኧረ ሰው ማመን ናፈቀን ጎበዝ!
በስንተኛው ቀን ያን የፈረደበትን ቶርኖ ለማሳየት ባለቤቱ እየመራ ወሰደን። ደንበኛዬን እንደሚገዛው ሳልጠራጠር ይልቅ ቶርኖው ስለሚጫንበት መንገድ እያየሁ እንጓዛለን። እንዳልኩት በራስ በጭራው ተገብቶ ማሽኑ ተፈትሾ እንዳበቃ ጥቂት ተከራክረው ገዥና ሻጭ በዋጋ ተስማሙልኝ። ‘ዲል’ ይላል አሉ ፈረንጅ! የሚደረገውን አደራርገን ለማግሥቱ ቀጠሮ ይዘን ተለያየን፡፡ እኔና ደንበኛዬ አንድ ሐራጅ የወጣ ጉደኛ ቤት አለ ተብለን እንዲያው ለማየት ባጃጅ መጠበቅ ጀመርን። አንዱ ደስ ያለኝ ነገር ታዲያ ምን መሰላችሁ? የታክሲ ሠልፍ ማየት እዚያ ይናፍቃችኋል። በየአቅጣጫው ባጃጅ ነው። ጭራሽ አንድ ባጃጅ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አውሎ ወደፈለጉበት መሄድ ይቻላል። ታዲያ አስተያየት አድርጋችሁ ሁለት ሦስት ብር ጨምራችሁ ትከፍላላችሁ እንጂ፣ ሰው እንዳልጭን ከልክለሃል ብሎ ባለባጃጁ የኮንትራት ሒሳብ አይጠይቅም። አያችሁ ምን ያህል ጨዋነት አሁንም እንዳለ፡፡ ወጣ ሲባል እኮ ቱባው ባህል እንዳለ ነው ያለው፡፡ ፈሪኃ ፈጣሪ ታክሎበት አትሉም ታዲያ!
አዲስ አበባ እንኳ ሚኒባሱን ብቻችንን ተቆጣጥረነው ቀርቶ ተቃቅፈን ተሳፍረንም ወያላው መልስ ሊያረሳሳን እንዴት ሲሽኮረመም እንደሚውል አስታውሱ። እኔ አስታውሼ ያስቆምኩት ባጃጅ ላይ ተሳፈርኩ። ወደ ነገርነው አካባቢ ወስዶ እንዳደረሰን ያንን የተባልነውን ቤት ፍለጋ አንዱን ልዩ ምልክት ነግረን ብንጠይቀው በኩራትና በደስታ ‹‹አላውቀውም!›› ብሎ ሳቀ። ኩራቱም ይሁን፣ ደስታውም ደስታ ነው። ሳቁን ምን አመጣው? እያልኩ ግራ ቀኝ እየቃበዝኩ ቤቱን ማሰስ ቀጠልኩ። ላካ ያ አላውቀውም ባዩ መንገዱን ትቶ ጥጉን ይዞ ቆሞ ስንደናበር እያየ ይዝናናላችኋል። ‹‹ይኼ የልብ ክፋት ዘር፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣… ሳይለይ በየአቅጣጫው እያደር አይሎ አገር ያለ ችግር ይለማል፣ ያድጋል ትላለህ?›› ብሎ ደንበኛዬ ከእኔ ቀድሞ ታዝቦት ኖሮ ጠየቀኝ። አሁን እስኪ መንገድ መሪነት ፀጋ እንጂ አንሶ መገኘት ነው እንዴ? አንድ ቀን እኮ ሁላችንም መንገድ ተመሪ መሆናችን አይቀርም፡፡ የግል ብሶት መሰለብኝ እንዴ? የገባው ይግባው!
በሉ እስኪ እንሰነባበት። አዛውንቱ ባሻዬ አደራ ስላሉኝ ብቻ ሳይሆን ወንዝ ተሻግሬ ቅቤና ማር ካልሸመትኩ ጉዞዬ ትርጉም ያጣብኛልና ሸጋ ቅቤና ማር ይዤ አዲስ አበባ ገባሁ። ባሻዬ የቅቤውን ለጋነት የማሩን ወለላነት አሽትተውና አጣጥመው ከመረቁኝ በኋላ፣ ‹‹እንዲያው ወጣ ሲባል አገሩ እንዴት ነው?›› ሲሉ ጨዋታ ጀመሩ። ‹‹አገሩስ ሰፊ ነበር እኛ እያጠበብነው አስቸገርን እንጂ…›› ብዬ ስለገበሬው ታታሪነት፣ የዋህነት፣ ጥጋብና ዕጦት ሳወጋቸው ቆየሁ። የአንበጣ መንጋ የደቀነውን ሥጋትም ነገርኳቸው፡፡ ስለከተማና ከተሜነት፣ ስለሥልጣኔና ትርጓሜው ባሻዬ ምን አሉ መሰላችሁ ቆይተው? ‹‹እኛ…›› አሉ ጋቢያቸውን ተጀቡነው እንደ ተቀመጡ። ባሻዬ አዲስ ርዕሰ ጉዳይ ይዘው ሲነሱ የእኔ ሥራ ማዳመጥ ነውና ጆሮዬን ሰጠሁዋቸው፡፡ ምናለበት ግን ብንደማመጥ!
‹‹…ይኼን ሁሉ ዘመን በታሪክ ስማችን ሲነሳ ይኼው የአዲስ አበባ ዕድሜ እንኳ መቶ ምናምን ዓመት ብቻ ነው። በርካታዎቹ ከተሞቻችን እኮ ስንትና ስንት የታሪክ ዳራ አላቸው መሰለህ። እነ ጎንደር እነ አክሱምን ካልክ ደግሞ ስንት መቶ ዓመታት ስንት ሺሕ ዓመታት ትቆጥራለህ… ግን…›› ብለው ባሻዬ፣ ‹‹የፓሪስን ሩብ ክፍለ ከተማ፣ የፕራግን ሲሶ ክፍለ ግዛት፣ የሮምን ሃምሳ ሜትር የኮብልስቶን ጎዳና ያህል ውበት፣ ሥልጣኔና ምቾት ያለው ከተማ የለንም። አይገርምህም? መቼም ዕድገት፣ ከተማና ከተሜነት ነው። ሕግና ሥርዓት ወጥሮ የያዘው የተደራጀ የአኗኗር ሥልት ማለት ነው ከተሜነት። እንዳለመታደል ሆኖ ይኼው አፍርሰን እየሠራን ነው…›› ሲሉ ቀበል አድርጌ፣ ‹‹ይኼንንስ ማን አየብን?›› አልኳቸው። አንገታቸውን በመስማማት እያወዛወዙ፣ ‹‹ያለን አማራጭማ እንዲያ ማድረግ ነው… ሌላ ምን አማራጭ አለን ብለህ ነው…›› እያሉ ሲስቁ አብሬያቸው መሳቅ ጀመርኩ፡፡ ዶናልድ ትራምፕን ፈጣሪ ከመንበራቸው እስኪነቅልልን እንሳቀው እንጂ፡፡ በሆነው ባልሆነው ነገር ከመበሳጨት በሆነው ነገር መደሰት የግድ ነው። ዓላማ አለንና ወደፊት ነው እንጂ ወደኋላ ብቻ ማየት የለብንም፡፡ አይመስላችሁም? መልካም ሰንበት!