Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊትምህርት ሚኒስቴር ማስክ ለመግዛት አንድ ቢሊዮን ብር ማውጣቱ ተነገረ

ትምህርት ሚኒስቴር ማስክ ለመግዛት አንድ ቢሊዮን ብር ማውጣቱ ተነገረ

ቀን:

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት ለማስቀጠል በሚደረገው ዝግጅት፣ ተማሪዎች ቫይረሱን እየተከላከሉ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የማስክ አቅርቦቱን ኃላፊነት የወሰደው ትምህርት ሚኒስቴር፣ በመላው አገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚሠራጩ ማስኮችን ለማስመረትና ለማሠራጨት አንድ ቢሊዮን ብር እንዳወጣ ታወቀ፡፡

ይኼንንና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት ከሪፖርተር ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)፣ ከጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት እንዲጀምሩ የተደረጉት የስምንተኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ማስክ እንዲደርሳቸው መደረጉን ተናግረዋል፡፡

‹‹አሁን ትምህርት ቤቶች ዳግም እንዲከፈቱ ባቀድነው መሠረት ማስክ የማዳረስ ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥት ግዴታ ነው፡፡ የሳኒታይዘርና የውኃ አቅርቦት ደግሞ የክልሎች ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ ማስክ እያቀረብን ነው፡፡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ስለሆነ የሚከፈቱት ቀስ በቀስ እየተመረተ ይዳረሳል፡፡ የስምንተኛና የ12ኛ ክፍል ትምህርት ይጀመር ሲባል፣ ለሁሉም ተማሪዎች ማስክ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ሁለት ሁለት ማስክ እንዲደርሳቸው ቢሆንም ዕቅዱ፣ አሁን ምርቱ በደንብ ስለሌለ አንድ አንድ ደርሷቸው እንጨምርላቸዋለን ብለናል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

- Advertisement -

ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዱ ትምህርት ቤት በወላጅ ኮሚቴና በአካባቢው የጤናና የትምህርት፣ እንዲሁም ሌሎች አመራሮች በተዋቀሩ ኮሚቴዎች አማካይነት በሚሰጥ ውሳኔ፣ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን ሲያሟሉና ይኼም በተለያዩ ኮሚቴዎች ሲረጋገጥ እንዲከፈቱ ነው አቅጣጫ የተቀመጠው ብለዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እስከ ዞንና ወረዳዎች የሚዘረጋ መዋቅር ያለው ኮሚቴ መዋቀሩን የጠቆሙት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴርም እስከ ወረዳ ካሉ የተለያዩ ኃላፊዎች ጋር በሳምንት ሁለት ጊዜ ስብሰባ ያደርጉ እንደነበር፣ አሁን ትምህርት ይጀመር ከተባለ በኋላ ዘወትር ሰኞ ስብሰባ እያደረጉ እንደሚገመግሙም አስረድተዋል፡፡

‹‹ባስቀመጥነው መንገድ እየተመራ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ውሳኔውንም ያልተማከለ ስላደረግነው በየአካባቢው ያለው ማኅበረሰብ እየገመገመ ነው የአካባቢውን ትምህርት ቤት የሚከፍተው፤›› ብለዋል፡፡

ለሁሉም ክልሎች ለማሠራጨት በታቀደው መሠረት ማስኮችን መግዛትና ማሠራጨት የተጀመረ ቢሆንም፣ በትግራይ ክልል ግን እስካሁን የማስክ ሥርጭት እንዳልተከናወነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹ለሁሉም ክልሎች የሚሆኑ ማስኮችን አዘጋጅተናል፡፡ የትግራይ ክልል ወረዳዎችና ዞኖችም ማስኮች መዘጋጀታቸውን አሳውቀን መጥተው እንዲወስዱ ነግረናቸዋል፤›› ያሉት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ እስካሁን ግን ከትግራይ ክልል መጥቶ ማስክ የወሰደ አንድም ወረዳና ዞን እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ለሁሉም ክልሎች ማስካቸውን እንዲወስዱ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን የተናገሩት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልልን በተመለከተ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር ግንኙነት ማድረግ ስለማይቻል ለወረዳዎችና ለዞኖች በስልክ ጥሪ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን በትግራይ ክልል የሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች በክልሉ አማካይነት ይላክልን በማለታቸው፣ እስካሁን ማስክ በትግራይ ክልል ማሠራጨት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

በየትኛውም ጊዜ መምጣትና ማስኮቹን መውሰድ እንደሚቻል የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በእርግጥ ይኼ የሚፈታበትን አማራጭ እየተወያየን ነው፡፡ በቀጥታ ለወረዳና ለዞን የሚደርስበትንና ማስኮቹን ማሠራጨት የምንችልበትን መንገድ ለማግኘት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ የጎርፍና የፀጥታ ችግር ባለባቸው የአፋር ክልልና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የትምህርት መርሐ ግብሩ ለሁኔታው በሚሆን ደረጃ ተስተካክሎ፣ ተማሪዎችን መቀበል እንዲጀመር ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በአፋር ክልል ዞን ሦስት በሚባለው አካባቢ በተከሰተው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ 81 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ የወደሙ መሆን፣ 61 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል የሚሉት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ እነዚህ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው ብሔራዊ ፈተናውንም ሆነ የትምህርት መርሐ ግብሩን እንደማይጎዱት አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ተማሪዎችን በአነስተኛ ቁጥር በአንድ ክፍል ውስጥ ለማስተማር በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ቀድሞ መምህራን የነበሩና በጡረታ የተገለሉ ወይም ሙያ የለወጡ ሁሉ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተገኝተው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በአካል ሄደው መመዝገብ የግድ እንደሚያስፈልግና ከመምህራኑ ጋር በመገናኘት የክፍለ ጊዜና የዕቅድ ምክክር መደረግ እንዳለበት በመታመኑ፣ ምዝገባው በድረ ገጽ እንዳይሆን መደረጉን ጌታሁን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ይሁንና መምህራኑ ወደ ትምህርት ቤት ለበጎ ፈቃድ ሲሄዱ ምንም ዓይነት ሰነድ መያዝ እንደማይጠበቅባቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹አስተምራለሁ ብሎ የሚሄድን ማንኛውንም ሰው እናምናለን፣ እንቀበላለን፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና በሆነ ጊዜ ሰነድ አቅርቡ ሊባል ይችላል ብለዋል፡፡

‹‹እኔም አስተምራለሁ›› በሚለው ንቅናቄ መሳተፍና ማስተማር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በአካል እንዲሄድና እንዲመዘገብ እንደሚፈለግ ገልጸው፣ ‹‹እኛ የምንጠብቀው በዩኒቨርሲቲም ሆነ በተለያየ ደረጃ አስተምሮ የሚያውቅ ሰው ይመጣል ብለን ነው፡፡ ጥሪ እያደረግን ያለነው በተለያየ መንገድ በማስተማር ሙያ ውስጥ ያለፉትን ነው፡፡ ሰነድ እንደ ቅድመ ሁኔታ አላስቀመጥንም፣ እናምናቸዋለን፤›› ብለዋል፡፡

ሰነድ ይዘው ቢቀርቡ ጥሩ ነው የሚሉት ሚኒስትሩ፣ አሁን ባያቀርቡም እንኳን ሊጠየቁ ይችላሉ ሲሉ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...