የስኳር ኢንዱስትሪው የሚመራበት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል
መንግሥት በስኳር ምርት ላይ የጣለውን ኤክሳይስ ታክስ ለማንሳት ማቀዱን የሪፖርተር ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ዕቅዱን ለመተግበርም የሕግ ረቂቅ መዘጋጀቱ ታውቋል።
መንግሥት ባለፈው ዓመት ባወጣው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ በስኳር ምርት ላይ ከፍተኛ የኤክሳይስ ታክስ መጣሉ የሚታወቅ ነው፡፡ የተጣለው የኤክሳይስ ታሪፍ የስኳር ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳና የአብዛኛውን ሸማች የመግዛት አቅም ያላገናዘበ በመሆኑ ሊነሳ ይገባል የሚል ምክረ ሐሳብ፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር ከቀረበ በኋላ ነው መንግሥት ማሻሻያ ለማድረግ ያቀደው፡፡
በመንግሥት በባለቤትነት የተያዙ የስኳር ፋብሪካዎችን በሽያጭ ለግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ የተያዘውን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ በተደረገው ጥናት ከተለዩት የዘርፉ ችግሮች አንዱ፣ በስኳር ምርት ላይ የተጣለው የኤክሳይስ ታክስ መሆኑን ምክረ ሐሳቡ ይጠቁማል።
ኤክሳይስ ታክስ በዋናነት በቅንጦት ሸቀጦችና የማኅበረሰቡን ጤና በሚጎዱ ሸቀጦች ላይ የሚጣል የግብር ዓይነት እንደሆነ፣ ግብሩ የሚጣልበት ዓላማም ሸማቹ ማኅበረሰብ ሸቀጦቹን እንዳይገዛ ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ያስረዳል። ለዚህም ሲባል የሚጣለው ታክስ በቀጥታ ወደ ሸማቹ የሚተላለፍ በመሆኑ፣ የሸቀጦች ዋጋን በማናር ማኅበረሰቡ ሸቀጦቹን ከመጠቀም እንዲቆጠብ ለማድረግ ጥቅም ላይ የሚውል የታክስ ዓይነት መሆኑን ያስገነዝባል።
በዚህም መሠረት አዲስ የተጣለው ኤክሳይስ ታክስ ታሪፍ በመሸጫ ዋጋ ላይ ተመሥርቶ የሚሰላ እንዲሆን መወሰኑን የሚጠቅሰው ምክረ ሐሳቡ፣ ስኳር ግን እንደ ሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በገበያውና በአቅርቦት ላይ ተመሥርቶ ዋጋው የሚወሰን ሳይሆን፣ በቀጥታ በመንግሥት በሚወሰን ዋጋ የሚሸጥ መሆኑን ያስረዳል።
በመሆኑም ስኳርን አስመልክቶ የተጣለው ኤክሳይስ ታክስ ወደ ተጠቃሚው የሚሻገርበት ምንም ዕድል እንደሌለ፣ ይልቁንም በአምራች ድርጅቶች ላይ ተጨማሪ የወጪ ጫና መፍጠሩን ያመለክታል። በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ አገሮች መካከል በአገር ውስጥ የስኳር ምርት ላይ ኤክሳይስ ታክስ የጣለችው ደቡብ አፍሪካ ብቻ መሆኗንና የታክስ ምጣኔውም ስድስት በመቶ እንደሆነ የሚገልጸው ምክረ ሐሳቡ፣ ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ወደ አገር ውስጥ በሚገባ ስኳር ላይ እንጂ በአገር ውስጥ በሚመረት ላይ ምንም ዓይነት የኤክሳይስ ታክስ እንዳላስቀመጡ ያስረዳል።
በኢትዮጵያ ስኳር በአመዛኙ ዝቅተኛ ገቢ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃ ሲሆን፣ በኢኮኖሚ እንዳደጉት አገሮች ከጤና አንፃር ታይቶ የስኳር የነፍስ ወከፍ ፍጆታን ለመቀነስ ተጨማሪ ታክስ መጣሉ በየትኛውም መሥፈርት ምክንያታዊ እንደማያደርገው፣ ከዚህም አልፎ የአገር ውስጥ አምራቾችን ተወዳዳሪነትን የሚጎዳና በተጀመረው የፕራይቬታይዜሽን ሒደት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ይጠቁማል።
በመሆኑም በአገር ውስጥ በሚመረት ስኳር ላይ የኤክሳይስ ታክስ መጠን ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ፣ ይህ ካልሆነ ግን የታክስ ምጣኔው ቢበዛ ከአምስት በመቶ ያልበለጠ እንዲሆን ጥናቱን የካሄደው ኮሚቴ በዚህ ላይ የተመሠረተ ምክረ ሐሳቡን ለገንዘብ ሚኒስቴር እንዳቀረበ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ምክረ ሐሳቡ የቀረበለት የገንዘብ ሚኒስቴርም የስኳር ኢንዱስትሪው የሚመራበትን የስኳር ኢንዱስትሪ አዋጅ እንዳረቀቀ ለማወቅ ተችሏል።
በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 30 ላይ የስኳር ኢንዱስትሪውን ከኤክሳይስ ታክስ ነፃ ስለማድረግ በሚል ድንጋጌ ሥር፣ ‹‹በቅንጦት ሸቀጦች ላይ የሚጣለው የኤክሳይስ ታክስ በስኳር ኢንዱስትሪው ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም፤›› ይላል። ይህ ረቂቅ አዋጅ ውይይት ተደርጎበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚፀድቅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በአሁኑ ወቅት በስኳር ምርት ላይ የተጣለው የኤክሳይስ ታክስ ምጣኔ 33 በመቶ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ የታክስ ምጣኔ በማኅበረሰቡ ላይም ሆነ በአምራቾች ላይ ጫና ከመፍጠሩ በተጨማሪ፣ ስለመንግሥት ስኳር ፋብሪካዎች ፕራይቬታይዜሽን ጉዳይ ለመስማት የመጡ የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ላይ ስለተጣለው ኤክሳይስ ታክስ ምጣኔ ሲነገራቸው ከፍተኛ ግርታ ሲፈጥርባቸው መስተዋሉን ምክረ ሐሳቡ አክሎ ገልጿል። የተረቀቀው የስኳር ኢንዱስትሪ አዋጅ ተወዳዳሪ የሆነ የስኳር ኢንዱስትሪ ለመገንባት፣ የስኳር ኢንዱስትሪ የምርት ሒደትና ገበያ ላይ ተገቢ የሆነ ውድድርና ተሳትፎ ለማሳካት ያለመ ነው ተብሏል።